መንገድ ላይ እየዞርን ይሄን ጥያቄ ብንጠይቅ አንዳንዶቹ ‹‹ወንድ ነው መጠየቅ ያለበት››፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ‹‹ሴት ናት መጠየቅ ያለባት›› እንደሚሉን የታወቀ ነው፡፡ ‹‹ሴት ናት መጠየቅ ያለባት›› የሚሉ ግን ብዙ አናገኝም፡፡ ምክንያቱ ያው ይታወቃል፤ ያልተለመደ ስለሆነ ወግና ባህላችንን ይጥሳል የሚል ነው፡፡ እኔ ስገምት ግን የብዙዎች መልስ የሚሆነው ‹‹ሁለቱም ቢጠይቁ ችግር የለውም፤ ዋናው ፍቅር ነው፤ ሴትም ወንድም መጠየቅ አለባቸው›› የሚል ነውብዙዎቻችንን የሚያስማማውም ይሄው ነው፡፡
ነገሩ ግን ወዲህ ነው፡፡
እኔ ሴቶች ናቸው መጠየቅ ያለባቸው ብዬ አቋም ይዣለሁ፡፡ ይሄንን ስል ግን ምክንያት ያልኳቸውን ነገሮች እንዲያጠናክርልኝ እንጂ ሁለቱም መጠየቅ አለባቸው፡፡ ሴቶች መጠየቅ አለባቸው ያልኩት ጠቅላላ እውነታ ሆኖ ሳይሆን ከማየውና ከምሰማው፤ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አነፃፅሬ ነው፡፡ ከአንድ ገጠመኝ ልጀምርላችሁ፡፡
ከአንድ ጓደኛዬ ጋር አንድ ባርና ሬስቶራንት ውስጥ ገባን:: ቀኑ የእረፍት ቀን ስለነበር እዚያው እየተጫወትን ቆየን፡፡ ይሄ ጓደኛዬ ያገኘውን ሴት ሁሉ መልከፍ ይወዳል፤ በዚህም በተደጋጋሚ እንጨቃጨቃለን፤ እኔ ደግሞ እንዲያ ባደረገ ቁጥር እበሳጫለሁ፤ እሳቀቃለሁ (በባህሪዬ ስለማልወድ እንጂ ወንጀል ነው እያልኩ አይደለም)፡፡ ቢሆንም ግን ያለንበት ቦታ ብዙም ስለማያስፈራና እንደ ነውር የሚታይበት ስላልሆነ እንደሌላው ቀን ‹‹እስኪ አርፈህ ተቀመጥ›› ሳልል እኔም አብሬ እየተቃለድኩ ነበር፡፡
በጽዳት ሥራ ላይ ያለችውን አንደኛዋን ልጅ እየጎተተ፣ እየተቃለደ፣ አገባሻለሁ እያለ ስንጫወት ቆየን፡፡ ስልኳንም ተቀበለ:: እንዲህ ስንጫወት ቆይተን ሄድን፡፡ እዚሁ ቤት ከአንዴም ሁለቴ ስንገባ እንዲህ እያለ ይቀላለዱ ነበር፡፡
ባለፈው እሁድ እዚያው ቤት ብቻዬን ገባሁ፡፡ ያቺ ልጅ ስታየኝ ሰላም ልትለኝ መጣች፡፡ ሰላም ተባብለን ‹‹‹‹ጓደኛህ የት ሄዶ ነው›› ብላኝ እኔም ቀልድ ጀመርኩ፡፡ ‹‹መቼ ነው የምትጋቡ? ለምን ቶሎ አትጋቡም?›› እያልኩ ስቀላልድ ጨዋታው ወደ ቁም ነገር መጣ:: ከሀሳቧ ስረዳ የልጁ አገባሻለሁ ማለት የምሩን ነው የመሰላት:: ‹‹እሱ ዝም አለ፤ እኔ መቸስ ሴት ነኝ፤ እኔ እንጋባ አልለው›› እያለች የውስጧን ነገረችኝ:: ልጁ እንደማያገባት ስለማውቅ ውስጤ እየተላወሰ ወደቀልድ ቀየርኩት፡፡ ከዚያው ቅጽበት ጀምሮ ስለወንዶች እንዲህ አይነት ባህሪ እያሰብኩ ነበር፡፡
ያቺ ልጅ በጽዳት ሥራ ላይ የተሰማራች ናት፤ ደመወዝዋ እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም፤ በጣም ተቸግራ እንደምትኖር ግልጽ ነው:: በዚህ ሕይወት ውስጥ ሆና ትዳር መያዝ፣ ልጅ ወልዶ መሳም ያምራታል፡፡ ስለዚህ አገባሻለሁ የሚል ወንድ ካገኘች መጓጓቷ አይቀርም፡፡
ህሊና ላለው ሰው እነዚህ ሴቶች ላይ መቀለድም ሆነ ማጭበርበር ምን ያህል እንደሚረብሽ አስቡት! አምናለሁ ‹‹አገባሻለሁ›› እያሉ መቀለድና መጫወት ምንም ችግር የለውም፤ ዳሩ ግን በሁኔታዎች ይወሰናል፡፡ ይቺ ልጅ በማህበራዊ ሕይወት ውስጥ የሚደረገውን ሁሉ ማድረግ ትፈልጋለች፤ ነገሩ የሚሳካ መስሏት ከእንዲህ አይነት ወንድ ጋር ግንኙነት ብትጀምር ከዚህ የከፋ የተበላሸ ሕይወት ሊያጋጥማት ይችላል ማለት ነው፡፡ በሽታ ላይ ትወድቃለች፤ ወይም ያልተፈለገ እርግዝና አርግዛ ለስነ ልቦና ጭንቀት ሁሉ ትዳረጋለች፡፡ በነገራችን ላይ እነዚህ በየመንገዱ ሕጻን ልጅ ይዘው ሲለምኑ የምናያቸው እናቶች ከእንዲህ አይነት ወንድ ጋር በፈጠሩት ግንኙነት የተከሰተ ነው፡፡
እንዲህ አይነት ወንዶች እንዲህ ባያጭበረብሩ ብሎ መምከር የተለመደና የተደጋገመ ነው፡፡ እኔ ግን የሚያናድደኝ ይሄን አመላቸውን መተው ባይችሉ እንኳን ከመሰሎቻቸው ጋር ቢያደርጉት፡፡ ለምሳሌ ያቺ ልጅ እንደነገርኳችሁ ናት፡፡ አንድ ቦዘኔ እና ሰካራም ወንድ፤ እሷን ከማጭበርበር ለእሱስ ቦዘኔዎች አይሻሉትም? ጨርቃቸውን ጥለው ለእብደት ትንሽ የቀራቸው፣ በየጎዳናው የሚባልጉ፣ በየስካር ቤቱ ቀልባቸው እስኪጠፋ የሚጨፍሩ አሉ፤ ለምን ከእነርሱ ጋር አይቦዝንም?
ሌላ አጋጣሚ
ሰሞኑን በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ ሲዘዋወር የነበረ አንድ ፎቶ አይታችሁታል፡፡ ሴቷ ተንበርክካ ለወንዱ ‹‹ታገባኛለህ ወይ›› ብላ ቀለበት ስታስርለት፡፡ ይሄን ድርጊት ተከትሎ ክርክሮች ነበሩ፡ ፡ አንዳንዶች(ሴቶችን ጨምሮ) ‹‹ወግና ባህላችንን አጠፋች፣ ይቺ ሴት አሰዳቢ!››የሚሉ፤ አንዳንዶችም ‹‹ደግ አደረገች! ዋናው ፍቅር ነው፤ ሴት የማትጠይቅበት ምን ምክንያት አለ?›› የሚሉ ነበሩ፡፡
እኔ ግን እዚህ ላይ ያልገባኝ ነገር፤ እነዚህ በሴቷ ሲፈርዱ የነበሩ ሰዎች ‹‹ሴት ናት ማግባት የምትፈልግ›› ሲሉ የነበሩ ናቸው፡ ፡ ወንዶች አጭበርባሪዎች ናቸው፤ ትዳር መያዝ አይፈልጉም፤ ሴቶች ናቸው ትዳር መያዝ የሚፈልጉ ሲባል ነበር፡፡ ታዲያ ሴቶች ከሆኑ ትዳር ፈላጊ ሴቷ ‹‹ታገባኛለህ ወይ›› ብትል ምን ችግር አለው? እንዲያውም አግባብ የሆነው ይሄኛው ነው አይደል? በዚህ በኩል ያለው የባህልና ወግ መጣስ ምኑም አይታየኝም፡፡ እንዲያውም ወግና ማዕረጉ በአደባባይ ‹‹ታገባኛለህ ወይ›› ማለቷ ነው፡፡ ቆይ ግን ስንት ሴቶች ናቸው ካላገባኸኝ ብለው ከጓደኛቸው ጋር የተለያዩ? በጓደኝነት ውስጥ ሆነው ሴቷ አይደለች እንዴ ቶሎ ካልተጋባን የምትል? ታዲያ ቀለበቱን እሷ ማሰሯ ምኑ ይደንቃል?
ከላይ የጠቀስኳቸው ሁለቱም አጋጣሚዎች ሴቶች እንዲጠይቁ የሚያስገድዱ ናቸው፡፡ ሴቶች ናቸው ትዳር የሚፈልጉ ከተባለ፤ ስለዚህ እነርሱ ቢጠይቁ ምን ችግር አለው? ሲጀመር ሴቶች ናቸው ትዳር የሚፈልጉ የሚለውም ስህተት ነው:: እንዲህ እንድንል ያደረገን ግን ሴቶች ትዳርን በሚገባ መምራት ስለሚችሉ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ጠጥቶ በመስከር፣ ሌላ ቦታ እየሄደ በመወስለት የሚታወቅ ወንድ ነው:: ሴቶች ቤታቸውን በሚገባ ስለሚይዙ እነርሱ ብቻ ትዳርን የሚፈልጉ አስመሰለው፡፡
መጀመሪያ ላይ የነገርኳችሁ አጋጣሚ ግን ከዚህም በላይ እንዲያውም ሴቶች እንዲጠይቁ ያስገድዳል፡፡ የነገርኳችሁ በጣም ቀላል አጋጣሚ ነው፤ አጋጣሚውን ግን እንደምሳሌ እንጠቀመውና ከዚህ የከፋ ወንድ ቢያጋጥማትስ? እንዲህ አይነቱን ወንድ በይፋ መጠየቅ የለባትም? ‹‹እኔ ሴት ነኝ፤ እንዴት እጠይቀዋለሁ!›› ብላ ብትተወው ማነው ተጎጂው?
ይሄ አጉል ልማድ እየጎዳ ያለው ሴቶችን ነው፡፡ እሱ እንደፈለገው እየጠየቀ ያማርጣል፤ እሷ መጠየቅ ስለሌለባት ያገኘችውን ታገባለች፤ ከዚያም ወዳልሆነ ሕይወት ውስጥ ትገባለች፤ ታዲያ ይሄ ነው ወግና ባህል ማለት?
እንዲያውም በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ሴቶች ናቸው መጠየቅ ያለባቸው:: በትክክል ለትዳር የሚሆንን ወንድ መርጠው መጠየቅ አለባቸው:: አለበለዚያ ማንም አተላ ገልባጭ እያታለለ ጎዳና ላይ ሊጥላቸው አይገባም!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 8/2011
ዋለልኝ አየለ