ቅድመ -ታሪክ
ልጅነቱን በገፋበት መንደር ትምህርት ቤት ገብቶ ፊደል መቁጠር ችሏል።ከተማን ጠንቅቆ ቢያውቀውም ለእሱ ግን የገጠር ህይወት አዲሱ አይደለም። በትምህርቱ እምብዛም ያለመግፋቱ ህይወቱን የሚመራበት አማራጭን እንዲፈልግ ግድ ብሎታል።ለዚህ ዓላማውም የትውልድ ስፍራውን ሜታ ሮቢን ትቶ ወደ እንጪኒ ከተማ ተጓዘ ።
ለድሪባ እንጪኒ ምቹ ሆነለት።ኑሮን በፈለገው መንገድ ለመምራት ምርጫ ያደረገው የንግድ ሥራም እንጀራው ይሆን ዘንድ ዕድሉን ሰጠው። እንዳሰበው ሆኖ ከአቅራቢያው ከሚገኝ ገጠር እህል እያስጫነ በትርፍ መነገድ ያዘ። አቅሙ ሲጎለብትም ጥሩ ነጋዴ ወጣው። ውሎ አድሮ ኪሱ በገንዘብ ተሞላ። ይሄኔ ነገን በተሻለ የሚያልመው ልቡ አርቆ ማሰብ ጀመረ።
ነጋዴው ድሪባ ሁሌም ስለ አዲስ አበባ ሲወራ ጆሮው ይሰላል።ይህ ቦታ ለእርሱ እንጀራውን ለማሳደግ አላማውንም ለመከወን መልካም እንደሚሆን ያምናል።ወደዚህ ስፍራ ቢመጣ ይበልጥ አትርፎ ዕቅዱን ያሳካል። ከትላንቱ ዛሬን ከበረታም የተሻለ ሸጦ የበለጠ ይቆጥራል። ይህን ዕቅድ ደጋግሞ ያሰበው ነጋዴ የልቡን ለማድረስ ውሎ አላደረም። አዲስ አበባ ገብቶ ከመሰሎቹ ሲግባባም ጊዜ አልወሰደም ።
ድሪባ መሳለሚያ አካባቢ የጀመረው የእህል ንግድ ቀስ በቀስ ደራለት። ቀድሞውኑ በሚያውቀው ልምድ ገበያውን ለመያዝ መጣሩም ስኬትን አስጨበጠው ።በአጭር ጊዜ ታዋቂ የእህል ነጋዴ ሆኖ በርካታ ደንበኞችን አፈራ።እንዳሰበው ነገሮች ሲሳኩም ገንዘብ በመያዝ ጥሪት መቋጠር ጀመረ።
ነጋዴው ድሪባ ራሱን ለመለወጥ የእህል ንግዱ ብቻ አልበቃውም።አሁንም ይበልጥ መስራትና የተሻለ ዛሬን መፍጠር እንዳለበት ይሰማዋል።ለዚህ ሀሳቡ ምላሽ በሆነለት የኮንስትራክሽን ሥራ ለመግባት ደግሞ ደጋግሞ አስቧል። በሀሳቡ ገፍቶ ለመወሰንም ጊዜ አልፈጀም። ያለውን ገንዘብና አቅም ተጠቅሞ ሥራውን በኮንትራት ማሰራት ጀመረ።
እህሉን በሚሸጥበት በረንዳ ገበያው ሲደራለት ግንባታው ባለበት ስፍራ ደግሞ ሥራው ይቀጥላል።ድሪባ በሁለቱም ወገን እረፍት የለሽ ትጋቱን ገፋበት ። ውሎው የልፋቱን ያህል አልነፈገውም። በቂ የሚባል ገቢ አገኘበት። እንዲህ መሆኑ የኑሮውን መንገድ አቃናው። ከራሱ ተርፎም ለሌሎች ጭምር የስራ ዕድል ፈጠረ ።
አሁን ድሪባ የተሻለ አቅም ይዟል።ከእህል ንግዱ ጎን የጀመረው የኮንትራት ግንባታ በእጅጉ እያዋጣው ነው።አዲስ አበባን እንዳሰባት በማግኘቱ የልቡ ደርሷል።በኑሮው የተለወጠው ነጋዴ ገንዘብ ከመያዝ በዘለለ በተሻለ ቤት ይኖራል። የራሱን መንቀሳቀሻ መኪና መያዙ ደግሞ የዕለት ሥራውን ፈጥኖ ለማሳካት፣ በህይወቱም አንድ ለውጥ ለማከል አግዞታል።
ገንዘብ ሲይዝና አቅሙ ሲጎለብት ድሪባ ከትላንት ይልቅ ዛሬን ዘመነበት።የተሻለ ለብሶ አምሮ መታየትንም ወደደ። እያደር ግን ከገንዘቡ መምጣት ጋር የደህንነቱ ጉዳይ ያሳስበው ጀመር።ይሄኔ የሚቀርባቸውን ሰዎች አማከረ ።አማካሪዎቹ ሀሳቡን ተረድተው በአንድ ጉዳይ አስማሙት።ለራሱ መጠበቂያ የሚሆን ሽጉጥ ቢገዛ እንደሚበጀው ነግረው አሳመኑት።
ድሪባ የመካሪዎቹን ሀሳብ ተቀበለ።ራሱን ለመጠበቂያ ሲል የገዛውን ሽጉጥም በእጁ አስገባ።ከዚህ በኋላ በደህንነቱ ላይ ስጋት ያልተሰማው ነጋዴ ሽጉጡን በወገቡ እንደያዘ መዘዋወርን ለመደ ። በሚንቀሳቀስባቸው ስፍራዎች ሁሉ መጠበቂያውን ሸጉጦ ውሎ ማምሸትን አዘወተረ ።
አንዳንዴ ድሪባ ራቅ ብሎ መዝናናትን ይመርጣል። ከስራ መልስ የአልኮል ብርጭቆ ይዞ ራሱን የሚደብቅባቸው የመጠጥ ግሮሰሪዎችም ብዙ ናቸው።በአንዳንድ ቦታዎች ያሉ ደንበኞቹ ደግሞ የእሱን መድረስ በጉጉት ይናፍቃሉ። ሁሌም መምጣቱን እየናፈቁ በተለየ ቅርበት ይቀበሉታል።
አንዳንድ ሴቶች ደግሞ ግብዣው ስለሚያስደስታቸው ከእሱ ጋር ማምሸትና ማውጋትን ይመርጣሉ። ከመጠጡ እየተጎነጩ ከጨዋታው ቢጋሩት ይወዳሉ።በነዚህ ሥፍራዎች ሁሌም በየምሽቱ እንዲህ አይነቱ እውነት ይዘወተራል። በሙዚቃ እየተዋዛ በመጠጥ ሞቅታ የሚቀጥለው ጨዋታ ስካርና ጭፈራን አስከትሎ በጠብና ውዝግብ ይቋጫል።
ድሪባ ብዙውን ጊዜ ጥግ ይዞ መጠጡን ይጎነጫል።ይሄኔ ከጎኑ አረፍ ብላ ግብዣውን የምትጋራ አስተናጋጅ ብቅ ትላለች።ምሽቱ ገፍቶ ወደመጣበት ሲመለስም ነገውን እየናፈቁ በጉጉት የሚሸኙት አይታጡም።አንዳንዴ ደግሞ ከባንኮኒው ተደግፎ ከረጅሙ ወንበር ተንጠልጥሎ ያመሻል።በዚህ ጊዜም ከእሱ ዙሪያ ታዳሚዎች አይታጡም።
ነጋዴው ሁሌም መኪናውን ይዞ ጎራ በሚልባቸው ስፍራዎች ከታዳሚው እየተጫወተ ፣ከአስተናጋጆች እየተቃለደ ማምሸቱን ልምድ አድርጓል።አንዳንዴ ከጨዋታ ብዛት ምሽቱ ገፍቶ ጊዜው ሊገሰግስ ይችላል።እንዲህ በሆነ ጊዜ ድሪባ ስጋት አይገባውም።ሁሌም ቢሆን አፍጥኖ በሚያገባው መኪና ይተማመናል። ከጎኑ የሚሽጠው ማካሮቭ ሽጉጥም ከስጋት ሁሉ እንደሚጠብቀው ያምናል።
መጋቢት 5 ቀን 2004 ዓ.ም ምሽት
ድሪባ በዚህ ቀን እንደተለመደው በሥራ ሲወጠር ቆይቷል።ማምሻውን ግን ድካሙን ለማርገብና የልማዱን ለማድረስ ወደ አንድ መዝናኛ አምርቷል።በስፍራው ሲደርስ ከሆቴሉ መጠጥ ቤት በርከት ያሉ ሰዎች ነበሩ።ጥቂት ቆይቶ ግን ከነበሩት መሀል አብዛኞቹ ሄደው ጥቂቶች ብቻ ቀሩ። የእሱን መድረስ ያስተዋሉ አስተናጋጆች ቦታ መያዙን እንዳዩ የፍላጎቱን ጠየቁት።
ነጋዴው እንግዳ ጎርደን ጂን በቶኒክ እንዲመጣለት አዞ ከአንድ ጥግ ቁጭ አለ ።የእሱን ቦታ መያዝ ያየችው የሆቴሉ አስተናጋጅም ወንበሯን ስባ ከአጠገቡ ተቀመጠች። ድሪባ ያዘዘው እንደመጣለት ለእሷም የምርጫዋን ጠይቆ ጋበዛት።ጥቂት ቆይተውም ጨዋታቸውን ቀጠሉ።
የሆቴል ቤቱ ድባብ በሙዚቃ ጩኸት ደምቋል። የሲጋራውና የመጠጡ ሽታም አካባቢውን ማናወጥ ጀምሯል። ሰዓቱ እየገፋ ጊዜው እየነጎደ ነው። ያም ሆኖ ግን አሁንም ወደ ሆቴሉ የሚገቡ በርክተዋል።ድሪባና አስተናጋጇ ባሉበት ጥግ ሆነው ጨዋታቸውን ቀጥለዋል። ከመጠጡ እየተጎነጩም መደጋገሙን ይዘዋል።
ጥቂት ቆይቶ ሁለት ሰዎች ተከታትለው ወደ ሆቴሉ ገቡ። ሁለቱም ፊታቸው ላይ ሞቅታ ይነበባል። በስፍራው ገና መድረሳቸው ቢሆንም ከሁኔታቸው ሌላ ቦታ ሲጠጡ መቆየታቸው ያስታውቃል። ወደውስጥ እንደዘለቁ በአይናቸው አመቺ ስፍራ ፈልገው ተቀመጡ። እንደተቀመጡም የሚፈልጉትን መጠጥ አዘው መጎንጨት ጀመሩ።
የሁለቱን ሰዎች መድረስ ያስተዋለችው አስተናጋጅ ወንበር መያዛቸውን አረጋግጣ ከድሪባ አጠገብ ተነሳች። ሰላምታ ሰጥታቸውም ወዲያውኑ ወደነበረችበት ተመለሰች። እንዲህ ማድረጓን ያየው ናትናኤል የተባለው ወጣት በሁኔታዋ መናደዱን በገጽታው ገለጸላት። ከሄደችበት እንድትመለስና አጠገባቸው እንድትቀመጥም ትዕዛዙን ሰጣት።
አስተናጋጇ የናትናኤልንሀሳብ አልተቀ በለችም። ፊቷን እንዳዞረች ከድሪባ ጋር ጨዋታዋን ቀጠለች። ይህን ያየው የናትናኤል ጓደኛ ዮናስ ድምጹን ከፍ አድርጎ ወደእነሱ እንድትመለስ ተናገራት። አስተናጋጇ የሚለውን አልሰማቸውም። ፊቷን ሳትመልስ በጨዋታዋ ገፋችበት። ይሄኔ ሁለቱም ጓደኛሞች ንዴት ያዛቸው። ዮናስ ከተቀመጠበት ተነስቶ እሷ ወዳለችበት አመራ። እጇን በእጁ ይዞም ቦርሳዋን ነጠቃት።
አስተናጋጇ በመግባባት እየሳቀች ቦርሳዋን ተቀብላ ወደ ድሪባ ተመለሰች። ዳግመኛ መናደድ የጀመረው ዮናስም ካለበት ሆኖ ጥርሱን መንከስና እጁን ማወራጨት ያዘ። እሱ የአስተናጋጇ ሁኔታ አብሯት ባለው ሰው ምክንያት መሆኑን ገምቷል። ይህን ሲያውቅም የውስጡን ስሜት መቆጣጠር ተሳነው። ጥቂት ቆይቶ ጓደኛው ወደ መጸዳጃ ቤት ለመሄድ ከወንበሩ ተነሳ ።ዮናስም የእሱን እግር ጠብቆ ወደ ድሪባ ወንበር ተጠጋ።
ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ በሁለቱ ወገን እንደዋዛ የተጀመረው ጨዋታ አቅጣጫውን ስቶ ነበር። ድሪባ የተቀላቀለበት ወግ ለሁለቱ ባልንጀሮች የሚዋጥ አልሆነም። አንዳቸው ሲናገሩ ሌላቸው የሚያክሉት አስተያየትም ከእሱ ጋር በአንድ አላዘለቃቸውም። ጨዋታቸው ጠብ እያጫረና ነገር እየጎተተ ቆይቷል። ይህን ስሜት አምቆ የቆየው ዮናስ ድሪባ አጠገብ ሲደርስ የቀድሞውን ጭቅጭቅና አለመግባባት እያሰበ ነበር።
አሁን ዮናስና ድሪባ ፊት ፊት ተፋጠዋል። በስካር ከናወዙ አንደበቶቻቸው መልካም ንግግር እየወጡ አይደለም። ዮናስ አይኑን እንዳፈጠጠ የእሱን ማንነት ያውቅ እንደሆን ጠየቀው። ከኪሱ ገብቶም መታወቂያውን አውጥቶ አሳየው። ጥያቄውን ሰምቶ መታወቂያውን ያየው ድሪባ በሁኔታው ብሽቀት ያዘው። የእሱ ማንነት ለማንም ምንም ያለመሆኑን ለማስረዳት ሲሞክርም ንዴቱ ቀደመው።
ሁለቱ ሰዎች ተፋጠው ለግብግብ እንደተጋጠሙ ወደ መጸዳጃ ያመራው ናትናኤል ከነበረበት ተመለሰ።ሁኔታቸውን ሲመለከትም ለጓደኛው ለማገዝ የሸሚዙን እጅጌ ጠቀለለ ። ድሪባ ከጓደኛው ጠብ መግጠሙ የእሱን መሄድ ተከትሎ መሆኑን አስቧል። ይህ አጋጣሚም በእጅጉ አናዶታል። አለመግባባቱ ቀጥሎ ጭቅጭቁ ሲያይል ደግሞ ከሁሉም ዘንድ የሚወረወሩ ቃላቶች እሳት የሚጭሩ ሆኑ።
የምሽቱ አየር በጠብና ግርግር እንደጋለ ሁለቱን የሚገላግሉ ሰዎች መሀል ለመግባት ሞከሩ። ሙከራው ግን በቀላሉ የሚሳካ አልሆነም። ከድብድቡ ይልቅ የሚሰነዘሩና ድንገት አንጀት የሚገቡ ክፉ ቃላቶች ለጠቡ የእሳት ላይ ቤንዚን መሆናቸውን ቀጠሉ።አለመግባባቱ ጠንክሮ ግርግሩ በጠብ ሲታጀብ ድንገት የደረሱት የሆቴሉ ባለቤት ድሪባን ይዘው ሊያግባቡ ሞከሩ። እሱም ቃላቸውን ሰምቶ ቤቱን ትቶ ሊወጣ መንገድ ጀመረ ።
ሽኩቻ የቆየበት የመጠጥ ቤት ሳሎን የድሪባን መውጣት ተከትሎ ዝምታ የወረሰው መሰለ።ድሪባ በሆነው ሁሉ ንዴት ቢይዘውም ቦታውን ጥሎ ወደ መኪናው ማምራት ጀምሯል።ቁልፉን ከበሩ ሰክቶ ለመግባት ሲሞክር ግን ሁለቱ ባልንጀሮች ከኋላው ደርሰው ትከሻውን ያዙት።እነሱን ለማስለቀቅ ሲታገልም አንድ ሞቅ ያለ ጥፊ ፊቱ ላይ አረፈበት። ጥፊው ከዮናስ መዳፍ የተሰነዘረ ነበር።
አሁን ሁለቱ ጓደኛሞችና ብቸኛውን ድሪባ መደባደብ ጀምረዋል።ሁኔታቸውን ያየው የሆቴሉ ዘበኛ መሀላቸው ገብቶ ሊገላግል ሞከረ። ግልግሉ በእሱ አቅም ብቻ የሚሆን አልነበረም። ሌሎችም ታክለውበት ለጊዜው ለመላቀቅ ሞከሩ።በሆነው ሁሉ ብሽቀት የያዘው ድሪባ የሁለቱ አብሮ እሱን መደብደብ በእጅጉ ተሰምቶታል። እልህና ብሽቀት እየተናነቀውም ከገላጋዮቹ እጆች ለማምለጥ እየሞከረ ነው።
የሆቴሉ ባለቤት በድጋሚ ደርሰው ሁለቱን ወጣቶች ወደ ኋላ መለሱ። በዚህ መሀልም ዮናስ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ድሪባን ለመምታት ተንደረደረ።ተመልሶ ወደ መኪናው ያመራው ድሪባ በእጁ የሆነ ነገር ሸፍኖ በፍጥነት ሰዎቹ ወደሚገኙበት ሳሎን አመራ። ይሄኔ ድንገት በእጁ ላይ ያለውን ማካሮቭ ሽጉጥ የተመለከተው ዮናስ ፉከራውን አቆመ። በድንጋጤም ላብ አጠመቀው። እግሮቹ እየተንቀጠቀጡና ልቡ እየመታ ባገኘው አቅጣጫ አሳብሮ ተፈተለከ።
የተከሰተውን ያላወቀው ናትኤል ፊት ለፊት ባየው ድሪባ ላይ ተከመረበት።እጆቹን የኋሊት ይዞም ከመሬት ላይ ጣለው። መውደቁን እንዳወቀ አሸናፊነት ተሰማው። ወዲያው ጉሮሮውን አንቆ ትንፋሽ አሳጣው። እንደምንም ትግሉን ሊቋቋም የሞከረው ድሪባ ገላጋዮች ከመግባታቸው በፊት የተቀባበለውን ሽጉጥ አመቻችቶ አነጣጠረ። ሙከራው ዒላማውን አልሳተም።ሁለት ጥይቶች እላዩ ላይ ባለው ሰው አካል ላይ መመሰጋቸውን ተመለከተ ።
ድሪባ በጥይት የተመታው ናትናኤልን ከላዩ ላይ አሽቀንጥሮ ከሆቴሉ ግቢ በሩጫ አመለጠ። የተኩሱን ድምጽ ሰምተው በድንጋጤ የተሰበሰቡ ሰዎች በደም ተነክሮ የወደቀውን ወጣት አስከሬን አስተዋሉ። ፈጥነውም ለፖሊስ በመደወል የሆነውን ሁሉ ተናገሩ።
የፖሊስ ክትትል
መረጃውን ሰምቶ በስፍራው የደረሰው ፖሊስ የአደጋውን ስፍራ በጥንቃቄ መረመረ። የሟችን አስከሬን አንስቶም ማስረጃዎችን ከሚገባቸው አካላት ሰበሰበ። ከወንጀል ድርጊቱ በኋላ ከአካባቢው ስለተሰወረው ድሪባና ከሟች ጋር በመሆን ጠቡን ያስነሳውን ዮናስን ለመያዝ የሚያስችለውን መረጃ ለይቶ አሰሳውን ጀመረ።
ውድቅት ሌሊት 8፡00 ሰዓት
ወንጀሉ በተፈጸመ ምሽት የተረበሸው አካባቢ አሁንም አልተረጋጋም። በማይተዋወቁ ሰዎች መሀል እንደዋዛ በተጀመረ ያለመግባባት ህይወት መጥፋቱ ብዙዎችንአስደንግጧል። የባንኮኒው ደንበኞች ጨዋታና ፍጻሜው እያነጋገረ ነው። የሟችን አስከሬን ከሆቴሉ ከተነሳ በኋላ ተጠርጣሪውን ለመያዝ አሰሳው ጀመረ። ድሪባ ከአካባቢው ርቆ ላለመሄዱ በቅርብ የቆመችው መኪና አመላካች ሆናለች። ይህን ያወቀው ፖሊስም ከአካባቢው ሳይርቅ ደፈጣውን ቀጠለ። ኮሽታውን እያደመጠና ኮቴና ድምጾችን እየለየም ከጨለማው ጋር ተፋጠጠ።
ምሽቱ እየገፋ፣ጭርታው ሲቀጥል ከአንድ ሰዋራማ ጥግ የሆነ አካል ሲንቀሳቀስ ታየ።ይሄኔ በድብቅ ያደፈጡ የፖሊስ አባላት አይኖች በንቃት አፍጥጠው ማንነቱን ለመለየት ፈጠኑ።ስለድሪባ የተነገራቸውና በእውን እያዩት ያለው እውነት ተመሳሳይ ሆነ። ፖሊሶቹ በተጠርጣሪው ድሪባ እጆች ላይ ካቴና አጥልቀው በቁጥጥር ስር ለማዋል ጊዜ አልፈጀባቸውም።
ፖሊስ በተጠርጣሪው ድሪባ ላይ የጀመረውን ምርመራ ቀጥሏል።የፖሊስ መዝገብ ቁጥር 280/04 በመርማሪ ሳጂን ግሩም ታረቀኝ መሪነት የሚጠናከረውን መረጃ የቴክኒክ ማስረጃና የምስክሮችን ቃል ሰብስቦ አጠናቋል ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 8/2011
መልካምስራ አፈወርቅ