ትዝ ይለኛል የመጀመሪያው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በ1999 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሲከበር መሪ ቃሉ “ሕገ-መንግስታዊ ቃል ኪዳን የአብሮነታችን መገለጫ ነው” የሚል ነበር። ከዚያ በኋላ አምስተኛውና በድጋሚ በአዲስ አበባ የተከበረው በዓል መሪ ቃል “ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘን የአገራችንን ህዳሴ ወደማይቀለበስበት ደረጃ ላይ እናደርሳለን” ይል ነበር፡፡ እነሆ ዛሬ ለ13ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ልናከብር ዋዜማ ላይ የምንገኘው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል “በብዝሃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል የሚከበር ነው፡፡ህዳር 29 የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህላቸውን፣ ማንነታቸውን በፍፁም ነፃነት ለመግለፅ የበቁበት፣ የልማት ተቋዳሽ የሆኑበት፣ ተሳትፏቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ዕውን ያደረጉበትን ህገ-መንግሥታችን የፀደቀበት ነው፡፡ ይህ ቀን ለኢትዮጵያ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ገፀ-ብዙ ትሩፋት አስገኝቷል ማለት ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በህገ-መንግሥቱ ውስጥ የተቀመጡ መብቶቻቸውን ተጠቅመው አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ያስቀመጡትን ራዕይ ተግባራዊ ለማድረግ በጋራ ተረባርበዋል።በእርስ በርስ ጦርነትና ረሃብ ትታወቅ የነበረች አገር ባለሁለት አሃዝ ዕድገት በማስመዝገብ ከአፍሪካ አልፋ በዓለም በዕድገት ጎዳና እየተራመደች መሆኑን ማሳወቅ የቻለችውም ህገ-መንግሥቱ ለዜጎች ባጎናፀፈው ሙሉ መብትና በተገኘው አንፃራዊ ሰላም ነው።
ባለፉት ጊዜያት መንግሥት የከተማ ነዋሪዎችን ህይወት ለመለወጥ እንዲቻል የተለያዩ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን ነድፎ ተንቀሳቅሷል። በዚህም በርካታ የከተማ ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሆኑበትን የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን በማስፋፋት ዜጎች ሥራ እንዲፈጠርላቸው በመደረጉ የነዋሪዎች ህይወት በመጠኑም ቢሆን መለወጥ ችሏል።
በዜጎች መካከል ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ለማድረግ በከፍተኛ ድጎማ የመኖሪያ ቤቶችን በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች በመገንባት በእጣ ማከፋፈል ተችሏል። ይህም የከተማ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች የቤት ባለቤት ሆነው ታይቷል።
በትምህርትና በጤናው ዘርፍ መንግሥት እያከናወናቸው የሚገኙት ተግባራት አንጸባራቂ ድሎች የተሞሉ ናቸው። በጥቂት ዓመታት ብዙ የመንግሥትና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተከፍተዋል። የአገራችን የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ብቻ ከ45 በላይ ሲደርስ፤ የግል ዩኒቨርሲቲዎችም ብዙ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ አርሶ አደርና አርብቶ አደሮች ከተመፅዋችነት ተላቅቀው በራሳቸው ጥረት አካባቢያቸውን አልምተው መጠቀም እንደሚችሉ በተግባር ሰርተው አሳይተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ዕድል ተዘግቶ በተፋጠነ ዕድገት እንዲተካ ያደረገው ዋነኛ ለውጥ በአርሶ አደሩና በገጠር የጀመረው የልማት ርብርብ መሆኑ አይካድም፡፡
በዲፕሎማሲው መስክም ከጎረቤት አገራት ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ በሰላም አብሮ የመኖር ፖሊሲን በማራመድ ሰላማቸውን ላጡ አገራት ሰላማቸው እንዲጠበቅና በአሸባሪዎች የሚደርስባቸውን ጥቃት በመመከት ሰላማቸው እንዲረጋገጥ የሕይወት መስዋዕትነት እስከመክፈል የደረሰ ድጋፍ ተደርጓል፡፡በዚህም የአገሪቱ ገፅታ በመልካም ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡
እነዚህ ከላይ በጥቂቱ የተዘረዘሩ በጎ ተግባራት ይበል የሚያሰኙ ቢሆንም እንኳ በአገሪቱ ውስጥ ለረጅም ዓመታት ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ስር የሰደደው የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የሌብነትና የማጭበርበር ተግባራት ተጀምሮ ለነበረው ሁለንተናዊ ልማት ስኬታማነት እንቅፋት ሆነው ለችግር ዳርገውናል፡፡
ዛሬ በርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል አጥተው ይንገላታሉ፣ በመኖሪያ ቤት እጦት በመንገድ ዳር በላስቲክ መጠለያ ለብርድ፣ለዝናብና ለፀሀይ ተጋልጠው ይገኛሉ፡፡የትምህርቱ ዘርፍ የላቀ ውጤት የተመዘገበበት ቢሆንም፤ በትምህርት ጥራት ረገድ በበቂ ሁኔታ ባለመሰራቱ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የሚወጡት ባለሙያዎች ብቃት አጠያያቂ ሆኗል፤ ዲግሪ ይዘው ሥራ የማግኘት ዕድሉም እንደሰማይ የራቀ ሆኖባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የልማት መሰረት ግብርና ቢሆንም ለእርሻ ሜካናይዜሽን እገዛ ትኩረት ባለመስጠት፣ በዘርና በማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት፣ በግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ ማነስ፣ በመድሃኒት አቅርቦት ጉድለት፣በገበያ እጦት፣በመንገድ ችግር በመሳሰሉት መድረስ የሚገባን ደረጃ ላይ ሳንደርስ ቀርተናል፡፡ ለዕድገታችን የኋልዮሽ ጉዞ ዋናው ምክንያት ደግሞ የገንዘብ እጥረት መሆኑ አይካድም፡፡
በእኔ ዕምነት አገሪቱ የገንዘብ ዕጥረት አጋጥሟት ያለመችውን ልማት ሳታሳካ የቀረችበት ዋናው ምክንያት በመንግሥት የኃላፊነት ቦታዎች ተመድበው የነበሩ የሥራ መሪዎች አገርና ሕዝብን በቅንነት ከማገልገል ይልቅ የራሳቸውንና የዘመዶቻቸውን ኑሮ የተደላደለ ለማድረግ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንዲባክን ወይም እንዲዘረፍ አስተዋፅዎ በማድረጋቸው ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በየቀኑ በከተማም ሆነ በክልል በመኪና እየተጫነ ለማሸሽ ሲሞከር የሚያዘው የውጭ አገርና የአገር ውስጥ ገንዘብ ለልማት ውሎ ቢሆን ኖሮ የቱን ያህል ችግሮቻችንን ያቃልል እንደነበር መገንዘብ አይከብድም፡፡ ይህ ግለኝነት የበርካታ ዜጎቻችንን ሕይወት መለወጥ ሲችል በድህነት አዘቅት ውስጥ እንዲቆዩ አሉታዊ ተፅዕኖውን አሳድሯል፡፡
ነገ የምናከብረው በዓል ከላይ በተጠቀሰው ዓይነት በስኬትና በውድቀት ውስጥ ሆነን የምናከብረው ሲሆን፤ ያለፈውን ክፉና ጎጂ ተግባር ለህግና ለህሊና ፍርድ ሰጥተን ስናበቃ ዳግም እንዳይመለስ ከፍትህ አካላት ፍትሀዊ ውሳኔን እንጠብቃለን፡፡ መልካም ሥራዎቹን ደግሞ እንደ በጎ ልምድ ወስደንና መነሻ አድርገን በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሠረተውን የህዝቦች አንድነት ይበልጥ በማጠናከር ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እሴቶቻቸውንና ባህላቸውን እንዲለዋወጡ በማድረግ በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነት የምናጠናክርበት ሊሆን ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በጋራ የሚያከብሩት ዓመታዊ በዓል የሕዝቦችን አብሮ የመኖር እሴት እያጎለበተና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብን እያሰረፀ ዛሬ ላይ ደርሷል ብንልም፤ በአሁኑ ወቅት ይህንን የአብሮነት እሴቶቻችንን የሚሸረሽሩ እኩይ ተግባራት እየተከሰቱ በየክልሉ ለእርስ በርስ ግጭቶች መነሻ ምክንያት የማይሆኑ ጥቃቅን ምክንያቶች እየተስተዋሉ ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያውያን ብረት አንስተው ጨቋኝ ሥርዓትን የተፋለሙት መሰረታዊ ማንነታቸውን የሚያሳጣና ሰብዓዊ ክብራቸውን የሚጋፋ አስከፊ ሥርዓት ስላጋጠማቸው የህይወት መስዋዕትነት ከፍለው ሥርዓቱን ላይመለስ አስወግደውታል።
ይህ የተባበረ ክንድ አንድነቱን አጠንክሮ ለልማት በመነሳት ባከናወነው ተግባር ዛሬ አገሪቱ የደረሰችበት የልማት ደረጃ ላይ ማረፍ ብትችልም ለሕዝብ ጥቅም ከመቆም ይልቅ የራሳቸው ጥቅም ብቻ ዓይናቸውን የጋረዳቸው፣ የወገኖቻቸው ረሃብና ስቃይ የማይታወሳቸው፣ የተገኙበትን ድሃ ህዝብ የዘነጉ አካላት የህግ ክትትል ሲደረግባቸው በአገሪቱ መረጋጋት እንዳይኖር የእርስ በርስ ግጭት ለማስነሳት የሚያደርጉት ሙከራ ለልማት እንቅፋት ስለሚሆን በአብሮነት ትስስር ሕዝብ ሊመክተው ይገባል።
በብዙዎች መስዋዕትነት የተገኘውን ሰላም ለማደፍረስና ለሕዝቦቿ መበጣበጥን የሚመኙ የሰላም ጠንቆች እነርሱ ልጆቻቸውን በሰላም አገር እያስተማሩ፣ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የሚያሰራጩትን አገርን የማበጣበጥ ተግባር በነቃ የሕዝብ ተሳትፎ ተቀባይነት ማሳጣት ተገቢ ነው፡፡
ዜጎች አገሪቱን አሁን የደረሰችበት ደረጃ ለማድረስ በአካልም በገንዘብም በከፈሉት መስዋዕትነት በዓለም አቀፍ ደረጃ በበጎ መጠራታችን አስከፊ የነበረው ገፅታችን መለወጡን የምናይበት በመሆኑ ልባችን ደስታን ተጎናፅፎ፣ በቀጣይ ከዚህ በበለጠ ከፍ የምንልበትን ተግባር የምናከናውንበት እንጂ ባገኘነው ድል ተኩራርተን እጆቻችንን አጣጥፈን የምንቀመጥበት መሆን የለበትም፡፡
በተለይም ካለፉት ስምንት ወራት ጀምሮ አገሪቱ የተያያዘችው አዲስ የለውጥ ጎዳና ተዘፍቀን ከነበርንበት አረንቋ አውጥቶ ፣መልካም አስተዳደርን አስፍኖ፣ ልማታችንን አፋጥኖ፣ ሰብዓዊ መብታችንን አስከብሮ፣ ዕድገታችንን ከቆመበት የሚያስቀጥል በመሆኑ ለአገሩ መልካምን የሚያስብ ሁሉ ሊደግፈው ይገባል፡፡
መጪው ጊዜ የአገራችን ስም በበለጠ በመልካምነትና በዕድገት የሚጠራበት እንዲሆን ዛሬ የምናከናውነው በጎ ተግባር መሰረት ስለሚሆን ለነገ የላቀ ዕድገታችን እያንዳንዷን የዛሬ ተግባራችንን በመልካም ጥረታችን ማለምለም ይኖርብናል፡፡
መቼውንም ቢሆን ማንኛውም ተግባር ሲከናወን ሁሉም ጉዞ አልጋ በአልጋ እንደማይሆን በመረዳት፤ሕገ መንግሥታዊ ችግሮች አሉ ብለን የምናምን ቢሆን እንኳ በጊዜው እንደሚፈታ ተገንዝበን እስካሁን የተገኘውን ድል ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ሰላምን መምረጥ ቸል ሊባል አይገባውም፡፡
ይህ በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በኢፌዴሪ ህገመንሥስት በተጎናፀፉት መብት በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነታቸውን በማጠናከር ዓለምን ያስደመመ ዕድገትን እንዳመጡ ሁሉ ዛሬም ኢትዮጵያዊ አንድነታቸውን ለዓለም በማሳየት የአገሪቱን ታላቅነት የሚያረጋግጡበትን ሰላማቸውን ሊጠብቁት ይገባል፡፡
አያሌው ንጉሴ