ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል አቅርቦት፣ የጋራጅና የፓርኪንግ ማበረታቻዎች ሊሰጣቸው ነው

አዲስ አበባ፡- መንግሥት ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል አቅርቦት፣ የጋራጅና የፓርኪንግ ማበረታቻዎችን ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ በርኦ ሀሰን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በተመለከተ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት ማብራሪያ፤ በሀገሪቱ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ለማስፋፋት መንግሥት የተለያዩ ማበረታቻዎችን እያደረገ ይገኛል።

ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል አቅርቦት፣ የጋራጅና የፓርኪንግ ማበረታቻዎችን ማድረግ በተመለከተ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ያሳያል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በኢትዮጵያም ማበረታቻዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ሰነዶችን በማዘጋጀት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እንዲስፋፉ መንግሥት ከቀረጥ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ማድረጉን ገልጸው፤ ሙሉ በሙሉ ከውጭ ሀገር ተገጣጥመው ለሚገቡ 15 በመቶ፣ በከፊል ተገጣጥመው ለሚገቡ አምስት በመቶ እና ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ የሚገጣጠሙ ከሆነ ከቀረጥ ነፃ የማድረግ ሥራ መሠራቱን አስታውቀዋል።

የቀረጥ ማበረታቻው በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ላይ ከሚጣለው ታክስ ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ በመሆኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በሀገሪቱ ለማስፋፋት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው ብለዋል። እንደ አቶ በርኦ ገለጻ፤ መንግሥት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማስፋፋት ባደረገው የቀረጥ ማበረታቻ ከውጭ የገቡና በሀገር ውስጥ የተገጣጠሙ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ከ100 ሺህ በላይ ደርሷል ብለዋል።

መንግሥት ያደረገው የቀረጥ ማበረታቻ የባለሀብቱን ተነሳሽነትና የሀገሪቷን የታዳሽ ኃይል አቅርቦት ለማሳደግ እንዲሁም የአየር ብክለትን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ እንደሚረዳም ተናግረዋል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት ለአካባቢ እና ለማኅበረሰብ ጤናማ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችሉ ትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ውስጥ አረንጓዴ ትራንስፖርት ተግባራዊ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሀገሪቱ ለነዳጅ ግዥ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ መቀነስ መቻላቸው እና ለአየርና የድምፅ ብክለት መንስኤ ባለመሆናቸው ተመራጭ ያደርጋቸዋል ብለዋል። ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የጥገና እና የቻርጅ መሙያ ማዕከላት እጥረትን ለመቅረፍ እስካሁን ድረስ በአዲስ አበባ 60 የቻርጅ መሙያ ማዕከል መገጠማቸውን ገልጸው፤ በ10 ዓመት በአዲስ አበባ አንድ ሺህ 176 በክልል ከተሞች ደግሞ አንድ ሺህ 50 የቻርጅ መሙያ ማዕከላትን ለመገንባት ታቅዷል ብለዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ውስጥ 148 ሺህ የቤት አውቶሞቢሎች እና 48 ሺህ 555 አውቶቡሶችን ወደ ሀገር ለማስገባት አቅዶ እንደነበር አስታውሰው፤ እቅዱ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት እየተሳካ በመሆኑ እና መንግሥት ለጉዳዩ በሰጠው ትኩረት 439 ሺህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማስገባት እና ሁለት ሺህ 335 የኃይል መሙያ ማዕከል ለመገንባት እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You