ለመኖር – መልካም እጆችን ፍለጋ

እሷና ልጅነት…

ልጅነቷን ስታስብ ብዙ ጉዳዮች ውል ይሏታል። እንደ ልጅ የእናት ፍቅር አላየችም። እንደእኩዮቿ እናቷን ‹‹እማዬ›› ብላ አልጠራችም። ገና ጨቅላ ሳለች ወላጆቿ ባይስማሙ እናት ልጆቻቸውን ትተው ከቤት ጠፉ ። የዛኔ እሷና ታናሽ ወንድሟ በዕድሜ ሕጻናት ነበሩ። አባወራው ከሚስታቸው መጥፋት በኋላ ሁለቱን ልጆች ተንከባክበው ያዙ። እናት ልጆቹን ጥለው ቢሄዱም ከአባት ንጹሕ ፍቅርን አላጡም።

ከእናት በላይ…

ውሎ አድሮ አባት ሌላ ሚስት አገቡ። ለምለምና ታናሽ ወንድሟ ከአዲሷ እናታቸው ጋር ሕይወትን ቀጠሉ። እንጀራ እናት እንደ ተለምዶ ስሟ አልሆነችም። ስለእነሱ ዋጋ የምትከፍል፣ ልዩ ፍቅር የምትሰጥ መልካም ሴት ናት። ሁሌም ለልጆቹ ምቾት አብዝታ ትጨነቃለች። ስለነሱ መኖር የእሷን ጥቅም ትተዋለች። ሁለቱ በወግ ሳያድጉ ሌሎች ልጆች እንዲጨመሩ አትሻም። የሚገባቸውን አግኝተው፣ የልባቸው እንዲሞላ ሁሌም የእሷ ፍላጎት የተገታ ነው።

ለምለም ዛሬ ላይ ሆና ይህን እውነት ስታስብ አፏን ሞልታ ‹‹እንጀራ እናቴ›› ልትል ይቸግራታል። እሷ ያልወለደቻቸው መሆኑን ያወቀችውም ስምንተኛ ክፍል እንደገባች ነበር። እውነቱን እስክትሰማ በእንጀራ እናቷ ዘንድ አንዳች ክፍተት አላየችም። ፍቅር መግባ፣ ብዙ ዋጋ ከፍላ አሳድጋቸዋለች። ስለእሷ ታላቅ ክብር አላትና ወላጅ እናቷን ከዚህች ድንቅ ሴት አታወዳድርም።

ለምለም በቀለ በእንጀራ እናቷና በወላጅ አባቷ የፍቅር እጆች ላይ አደገች። በትምህርቷ ጎበዝ ከሚባሉት ጎራ የምትሰለፍ ናት። አንዳንዴ ስለቤተሰቧ ስታስብ በድህነት ያሳደጓት አባቷ ውለታ ይከብዳታል። እሷ ሁሌም ኑሯቸው ቢሻሻል ሕይወታቸው ቢለወጥ ትወዳለች። ይህን ለማሳካት ገና ተማሪ ነች። የጎደለውን ሞልታ ያጡትን ለመስጠት ደግሞ ግዜው ይረዝምባታል።

ለምለም አሁን አስረኛ ክፍል ደርሳለች። ከዚህ በኋላ በትምህርቷ ከበረታች ተስፋ አታጣም። ሥራ ይዛ ቤተሰቦቿን ታግዛለች፣ ለእሷም ለወንድሟም ትተርፋለች። ይህን ሀሳቧን ለማሳካት ውጥኗ እንዳቀደችው አልቀጠለም። በወቅቱ በምትሰማው የዓረብ ሀገር ሕይወት ውስጧ ተማረከ። ይህኔ ለምታስበው ዓላማ አቋራጩ መንገድ እሱ ብቻ መሆኑ ገባት። ልቧ ሸፈተ፣ እግሯ ተነሳሳ። አንድ ቀን ተወልዳ ካደገችበት ጅማ በድንገት ተነስታ ጠፋች።

የለምለም መዳረሻ ሻሸመኔ በኋላም አዲስ አበባ ሆነ። ቀድሞ በእንግድነት የተቀበሏት አመጣጧ ለዓረብ ሀገር መሆኑን ሲያውቁ እንድትማር ገፋፏት። አዲስ አበባ ስትደርስ ግን ይህን ሀሳብ የተቃወማት አልነበረም። ከባዕድ ዘመድ ቤት እየሠራች እንድትኖር ዕድሉን አገኘች።

በዚህ ቤት በቆየችባቸው ጊዜያት እንዳሰበችው ዕቅዷ አልፈጠነም። እንዲያም ሆኖ አልከሰረችም። ጥሩ የሕይወት ልምድ ቀስማለች፣ የቤት ሙያን ተምራለች። የትዳር አጋሯን አግኝታለች። ያለፈችበት መንገድ ሻካራ ቢሆንም የዚህ ቤት ኑሮዋ ስለነገ ቆርጣ እንዳታስብ ምክንያቷ ነበር። ከሦስት ዓመት በኋላ ወደዓረብ ሀገር ለመሄድ ተሳካላት።

አዲስ አበባ ካለችበት ቤት እያገለገለች ብትቆይም። የፓስፖርት ወጪዋ የተሸፈነው ከድሀ አባቷ ኪስ ሆነ። ለምለም የፍላጎቷ ሲሞላ ጓዟን ሸክፋ ተነሳች፣ ዓላማዋን አልረሳችም። ነገዋን እያለመች ወደ ዓረብ ሀገር አመራች።

በሀገረ ቤሩት…

ለምለም ቤሩት ላይ እግሯ እንደረገጠ ፈጥና ወደሥራ ገባች። አሠሪዎቿ መልካም የሚባሉ ናቸው። ስለግዴታዋ ሲነግሯት መብቷን እያከበሩ ነው። ሙሽሮቹ ባልና ሚስቶች በሰብዓዊነት የሚያምኑ የሰው ክብርን የማይጋፉ መሆናቸውን አውቃለች። ይህ እውነት ሕይወት ሳይከብዳት ኑሮዋን እንድትወደው አድርጓታል። ጥንዶቹ ባሕሏን ያከብራሉ። የሀገሯን ምግብ አብስላ እንድትመገብ ይሁንታቸውን ሰጥተዋል።

ስደተኛዋ ወጣት የሰው አገር ሕይወቷ በነፃነት ተዋዝቷል። ከምታሳድገው ሕጻን ጋር በእኩል እያወሩ ቋንቋውን ለምዳለች። የምታገኘው ክፍያ ብዙ የሚባል አይደለም። እንዲያም ሆኖ ‹‹አነሰኝ›› አትልም፡ ስለነገ ታስባለችና የእጇን እየቆጠበች ነው።

አሁን ለምለም ሀገርቤት ተመልሳለች። የያዘችው ገንዘብ እዚህ ግባ አይባልም። የሠራችበት የላቧ ፍሬ ነውና ከበረከቱ ለወላጆቿ የውሀ ቧንቧ አስገብታ የተቀረውን ለቤት አጥር አውላለች። ባሕር ቆርጣ የሄደችበት እንጀራ እንደሌሎች ብር አላሳፈሳትም። በሠላም መመለሷ ግን ለእሷ ከትርፍ በላይ ነው።

ለምለም ተመልሳ አዲስ አበባ ስትገባ ሰባራ ሳንቲም ይሉት ከእጇ አልነበረም። በወቅቱ ከእሷ የሚጠብቁ እጇን ቢያዩም ምንም ማድረግ አልቻለችም። ቤሩት ከመሄዷ በፊት ይቀርባት የነበረው የቤቱ ወጣት ዛሬም ከእሷ አልራቀም። ስለነገ ተስፋ ይሰጣታልና በፍቅር ዘልቀዋል። ይህ ግንኙነት ግን በእናቱ ዘንድ የተወደደ አይመስልም።

ጓደኛዋን ያገኘችው ሦስት ዓመት ከኖረችበት፣ ብዙ ሙያና የኑሮ ልምድ ከቀሰመችነት ቤተሰብ መሐል ነው። የእሱ ኑሮ ከአሳዳጊ አባቱ ዘንድ ነው። እሷ ቀድሞ የኖረችው በወላጅ እናቱ ቤት ነውና ይህ ቅርበት ለመገናኘታቸው ምክንያት ሆኗል ። ሁለቱ ይግባቡ እንጂ ፍቅራቸው ዕንቅፋት አላጣውም። በዚህ መሐል እርግዝና መከሰቱ ደግሞ ሁኔታዎችን አክብዶ ለችግር ዳርጓታል። ለምለም አሁንም በባሏ እናት ቤት ትኖራለች። የአሁኑ ኑሮዋ ግን የቀድሞው አይነት አልሆነም፡ የትናንቷን ታዛዥ አገልጋይ ዛሬ እንደ ልጅ ሚስት መቀበሉ የከፋ ሆኗል።

ቤተሰቦቹ እሷን ሳይሆን በሚወለደው ልጅ ብቻ ፍላጎት አላቸው። ከወለደች በኋላ ዓረብ እንድትሄድና ከእነሱ ሕይወት እንድትወጣ ይሻሉ። የጥንዶቹ ሕይወት ፈተና እየገጠመው ነው። እነሱን ለመለየት የሚመስሉ ክፉ ወሬዎች መመላለስ ጀምረዋል። እርግዝናዋ የከበዳት ለምለም ባልተመቸ ሁኔታ ሕይወትን መቀጠል አዳጋች ሆኖባታል።

ለምለም ሠላማዊ ዕንቅልፍ አታውቅም፣ ጤና የላትም። እንደ ነፍሰጡር ያማራትን የምታገኝ አይደለችም። በተለያየ ቤት የሚኖሩት ጥንዶች በእሱ መማር ምክንያት ወደጋብቻ አልገቡም። ድንገቴው እርግዝና ደግሞ ለትዳር ዕቅድ አላበቃቸውም። እሷ በእሱ እናት ቤት፣ እሱ ደግሞ በአሳዳጊ አባቱ ቤት እየኖሩ ነው።

ከቀናት በአንዱ ከምትኖርበት የባሏ እናት ቤት በአስቸኳይ እንድትወጣ ተነገራት። ይህ እውነት ለነፍሰጡሯ ለምለም እጅግ አስደንጋጭና ፈታኝ ነበር። ዕለቱን ዝናብ ሲጥል ውሏል። ሐኪም ቤት ውላ ቤት የገባችው ሴት እረፍትን ሽታለች። በድንገት ‹‹ውጭልን›› መባሏ ይባስ ቀኑን አጨልሞ ዙሪያው ገደል አደረገባት።

አሁን ሁኔታዎች መልካም አልሆኑም። ቀጣዩን ግዜ ጅማ ወዳለው የእናቷ ልጅ መሄድ ነበረባት። ይህን ለማድረግ ግን በእጇ ምንም የለም። ለትራንስፖርት ከሰዎች ያገኘችውን ጥቂት ገንዘብ ይዛ ከቤት ወጣች። ባለቤቷ ርቃ ትሄዳለች ብሎ አላመነም። ትመለሳለች ሲል በዝምታ አስተዋላት ።

ነፍሰጡሯ እንግዳ

ለምለም ጅማ ስትገባ ወንድሟ ተቀበላት። ከጊዜያት በኋላ ሴት ልጅ ወልዳ ታቀፈች። አንድ ወር እንደሞላት ባለቤቷ አዲስ አበባ እንድትመለስ ሁኔታዎችን አመቻቸ። ተመልሳ ወደነበረችበት የገባችው ለምለም ልጇን እያሳደገች ሕይወትን ቀጠለች። ባሏ እናቱ ቤት ያስቀምጣት እንጂ ኑሮው ከአሳዳጊዎቹ ዘንድ አልተነጠለም። የልጅ ልጅ የሳቀበት ቤት ለጥቂት ግዜ ሠላሙ ተመለሰ። የለምለም በድንገት መታመም ግን ሁኔታዎችን ሊለውጥ አስገደደ። እናት ሕመሟ ከበድ በማለቱ ልጇን እንዳታጠባ በሐኪም ተከለከለች። አባት በየቀኑ እነሱን መንከባከቡ በቤተሰቦቹ ፊት ጥሩ ትርጉም አላመጣም። አማትና ምራት በየሰበቡ ይሻከሩ፣ ቅያሜን ይፈጥሩ ያዙ።

ውሎ አድሮ የሁለቱ ሴቶች ፍቅር ቀዘቀዘ። ከዓመታት በፊት ለምለም የአዲስ አበባን ሕይወት የጀመረችው፣ የሴት ልጅን ሙያ የተማረችው ከእሷው ዘንድ ነበር። ዛሬ ‹‹አማቷ›› ናት ብትባልም ትናንት እንደ እናት የምታያት መከታዋ ነበረች። አሁን ግን ይህ ታሪክ ተሽሯል። ለምለም ከቤት ወጥታ ባሏ ወደሚኖርበት ቤተሰቦች ቤት ተቀላቅላለች ።

አዲስ ሕይወት…

አሁን ለምለም፣ ልጇና አባወራው በአንድ መኖር ይዘዋል። የገቡበት ቤት ለእሱ ከልጅነቱ የኖረበት ነው። በቤቱ እንደ አባት ያሳደጉትን ጨምሮ እህት የሆኑት ሌሎች ቤተሰቦች ይኖራሉ። ባል ልጅና ሚስቱን ይዞ ሲገባ የሁሉም ስሜት መልካም ይመስል ነበር። በአንድ ጣራ ስር የተጀመረው ሕይወት ማግስቱን ከአንድ ማዕድ ያስቆርስ ያዘ። በዚህ ቤት የግል ይሉት ኑሮ የለም። ለምለም በጉልበቷ እየሠራች ትልቁን አባትና መላውን ቤተሰብ ትመግባለች። ይህ አይነቱ ሕይወት ልጇን ይዛ ለተቀላቀለችው እንግዳ ምቹ አልሆነም።

ለመኖር ሲባል የተጀመረው መንገድ ቢቆረቁርም እንደ ነገሩ ቀጥሏል። ሁሌም እጀ መልካሟ ለምለም ሙያና ጉልበቷን አትሰስትም። የሚቀርብላትን ለቤተሰቡ እያደረሰች ልጇን ታሳድጋለች። ጊዜያትን ያስቆጠረው ሕይወት በኩርፊያ መቀያየምና ጸብ እንደተዋዛ ነው። አሁንም ምርጫ የለሿ ሴት በፈተና መሐል መመላለስ ይዛለች። ላለመናገር በዝምታ የምታልፋቸው ጉዳዮች በውስጧ ቅያሜን ማኖር ጀምረዋል።

ለእሷ ለባሏና ቤተሰቦቹ ያልተመቸው አኗኗር ጊዜያትን እየቆጠረ ነው። ለምለም ወጥታ እንዳትሠራ የልጇ ጉዳይ ሰበብ ሆኗል። በሕመም ምክንያት መማርና መሥራት ያቆመው ባለቤቷ እያገዛት አይደለም። ወጥቶ እንዲሠራ ብትፈልግም ቤተሰቦቹ አልፈቀዱም። ልጇን ስትል አቅሟን የሰጠችው ለምለም ያለአንዳች ምርጫ በቤት ውስጥ ታጥራለች። በየቀኑ ጥገኝነት የሚያስከፍላት ዋጋ በርክቷል። እንጀራ በወጥ ብቻ የምትበላው ሕጻን ለቤተሰቡ ደስታን ፈጥራለች። እንደ ልጅነቷ ግን ብዙ ጎድሏታል። ለምለም ይህን ብታውቅም እውነቱን ከመቀበል ውጭ ምርጫ የላትም።

ውሎ አድሮ ሁኔታዎች በነበሩበት አልቀጠሉም። ለምለም መሥራት እየቻለች ፍላጎቷ አልሞላም። የጥገኝነት ሕይወትም መሯታል። ይህ እውነት ዓረብ አገር እንድትሄድ ከውሳኔ አደረሳት። ያሰበችው አልቀረም። የጀመረችው የጉዞ ሂደት ተጠናቆ ለመንገድ ተዘጋጀች። ወደባሕሬን ስታቃና ልጇ ሁለት ዓመት አልሞላትም ነበር።

ኑሮ በባሕሬን..

ለምለም ባሕሬን ደርሳ ሥራ ጀመረች። ካገር ስትወጣ የተነገራትና ሲከፈላት ያገኘችው ደሞዝ ግን ልዩነት ነበረው። ገንዘቡ ለምን አነሰ ስትል የሚመለከታቸውን ሁሉ ጠየቀች። በቂ ምላሽ ሳታገኝ ወራት ተቆጠሩ። የገባችበት ቤት ብዙ ቤተሰብ አለው። ከጠዋት እስከማታ ሲደክሙ መዋል የግድ ነው። የዚህ ቤት ኑሮ ከፊተኛው ሕይወት ይለያል። እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በካሜራ ይቀረፃል። ለምለም የምታርፍበት፣ የምትበላበት ግዜ ሁሉ በአሠሪዎቿ የእጅ ስልክ መረጃው ይደርሳል። ለእሷ ሕይወት ከባድ ሆኗል። ክፍያው መጨመር፣ መስተካከል አልቻለም። እስካሁን የሁለት ወር ደሞዟን ለደላሎች ከፍላለች። የ ሁለት ወር ደግሞ ለባለቤቷ ልካለች።

ከቀናት በአንዱ ለለምለም የልጇ መታመም መልዕክት ደረሳት። ክው ብላ ደነገጠች። መሥራት፣ መዋል ማደር አልቻለችም። ፈጥና አሠሪዎቿን እንዲያሰናብቷት ጠየቀች። ኮንትራቷ ለሁለት ዓመት መሆኑን አስታውሰው ‹‹እምቢኝ››አሏት። ምርጫ አልነበራትም። ኢሚግሬሽን ሄዳ እጇን ሰጠች። ከአስራ አምስት ቀናት እስር በኋላ ያሰበችው ተሳካ።

ኑሮን እንደ ትናንት…

ሀገርቤት ስትገባ የአራት ወር ቆይታዋ ብዙ ነገር ቀይሯል። ሕጻኗ ትኩረት በማጣቷ ታማለች። በናፍቆት ተሳቃለች። አጋጣሚ ሆኖ የላከችው አምስት ሺህ የማይሞላ ገንዘብ ከባንክ እንዳለ ነው። ለጉዳይ ካዋለችው ሌላ ከፊሉን ለባሏ ኮሌጅ ምዝገባ አንስታ እሷ ሕይወትን በትናንቱ መንገድ ተመለሰችበት። ባለቤቷ በሕመም ምክንያት ያቋረጠውን ትምህርት ይመዝገብ እንጂ አልቀጠለውም። ይህን ስታውቅ ሠርቶ ይገባ ዘንድ ጠየቀች። እምቢ አላለም። ከአንድ ጓደኛው ጋር በእኩል የሚታሰብ የጫት ቤት ሥራ ጀመረ። ኑሮ በመጠኑ የተሻለ መሰለ። ለምለም ግን ዳግም ዓረብ ሀገር ለመሄድ ትሯሯጥ ያዘች።

ሁሉም ጉዳይ እንደታሰበው አልሆነም። የኮሮና መምጣት ከጉዟዋ መለሳት። ይህን ተከትሎ ሁለተኛው ልጅ ተረገዘ። ዛሬም ከጥገኝነት ያልወጣው ሕይወት ሠላም የለውም። ነፍሰጡር መሆኗ ቤተሰቡን አላስደሰተም። ይህ ችግር ሳይቀረፍ የባለቤቷ አጋር እሱን ከዕዳ ጥሎ ገንዘባቸውን ይዞ መጥፋቱ ተሰማ። ባለዕዳው ያለበትን እንዲከፍል ሲወሰን ችግሩ ለአሳዳጊው አባት ተረፈ።

ሥራ መጥፋቱ፣ ዕዳ መከተሉ ቀዳዳውን አሰፋ። ለምለም ለመውለድ ሆስፒታል ስትገባ ከባሏ በቀር ማንም ጎኗ አልነበረም። በእጅጉ ተከፋች። የአራስነት ቆይታዋ መልካም አልነበረም። ይህ እውነት ቅያሜን አስከትሎ በቀጣዩ ሕይወት ፈተናውን አጠላ። አሁን አንድ ሕጻን ታክሎ የቤተሰቡ ቁጥር ጨምሯል። ከትናንቱ በላቀ የኑሮው ትግል ቀጥሏል ። ለምለም እንደቀድሞው ለቤቱ ኃላፊነትን ወስዳ ትሠራለች፣ ትደክማለች።

ሌላው ፈተና…

ለምለም በአካባቢው ‹‹ሴፍቴኔት››ተጠቃሚ ነች። ባለቤቷም ወጥቶ የሚገባበት ሥራ ጀምሯል። ገቢው በመጠኑም ቢሆን ጎዶሎ እየሞላ፣ ችግር እየተፈታ ነው። ይህ መንገድ ግን ብዙ አላራመደም። በድንገት የጀመረው የነርቭ ሕመም ሌላ ፈተና አስከተለ። ቀድሞ መነሻ የነበረው እክል ከሚውልበት ሥራ ጋር አልተስማማም። ለዓይኖቹ ጤና ጭምር ዕንቅፋት ሆነ። ይህን ተከትሎ ሥራውን እንዲያቆም በሐኪም ታዘዘ።

አሁን አንድ የሚሠራ ኃይል ተቀንሷል። ይህ እውነት ጫናውን በለምለም ትከሻ ሊያርፍ ግድ ብሏል። ባለቤቷ ጥቂት ሲያገግም ሥራ ጀመረ። እሷም ሙያዊ ሥልጠናዎች እየወሰደች አቅሟን በዕውቀት አሳደገች። ኑሮ በቤቱ እንደትናንቱ ቀጥሏል። ባል አሁንም በጤናው እየተፈተነ ነው። ሥራ ፈቶ ቤት ከዋለ ቀናት ቆጥሯል። ለምለም ዝም አላለችም። ባገኘችው አጋጣሚ ችግሯን እያዋየች ሥራ ትጠይቃለች። አንድ ቀን መልካም ጆሮዎች አዳመጧት። በዳግማዊ ሚኒሊክ ትምህርት ቤት ሕጻናት ማቆያ ለእሷ የሚሆን ሥራ ተገኘ።

ይህ አጋጣሚ ለልጆቿና በሕመም ቤት ለዋለው ባሏ አንድ እርምጃ መፍትሔ ሆነ። ሥራ መጀመሯ ሲታወቅ ከቤተሰቡ መነጠል እንዳለባት ተነገራት። ብታዝንም በላቧ ወዝ ጎዶሎዋን መሙላት፣ ቤቷን መምራት ያዘች። ሕይወት በእጅጉ ፈተናት። ሥራ ማግኘቷ ሌላ ችግር አስከተለ።

በትልቁ ሳሎን መሮጥ የለመዱ ልጆች ወሰን ተበጀላቸው። በራሳቸው ጎጆ ውለው አደሩ። በአንድ ማዕድ መቁረሱ ቀርቶ የብቻ ዓለም ተጀመረ። የትናንቱ አብሮነት ተረሳ። መገለል ይሉት ነገሰ። ቤተሰቡ በአንድ ሲሆን የእሷ ብቸኝነት ጎልቶ ታየ። ምርጫ አልነበራትም። የመጣውን ሁሉ በጸጋ ተቀበለች።

ዛሬ ኑሮ ተወዷል። በእሷ ገቢ ብቻ የቆመው ጎጆ እየተንገዳገደ ነው። ስለኑሮዋ ዘወትር ብትደክምም ሕጻናትን አሳድጎ ራሷን የሚያስችል፣ ባሏን የሚያሳድር አቅም ከእሷ የለም። ያሳለፈችውን መከራና ችግር በ‹‹ነበር›› አልፋዋለች። ዛሬ የቆመችበት ሕይወት ግን ነገን ማስከተሉ ከስጋት ጥሏታል። የዓይን ጉዳይ ችግር የሆነበት ባሏ አሁን እየሠራ አይደለም። ምሽት ላይ አካባቢን ጠብቆ ከሚያገኘው ገቢ ጥቂት ይደጉማታል።

እሷ ግን ዛሬ የሚሰሟትን ጆሮዎች፣ የሚያይዋትን ዓይኖች፣ የሚያነሷትን መልካም እጆች ትሻለች። ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ ኑሮዋ አላቆ ልጆቿን ከጓዳ የሚያወጣላት፣ ከብቸኝነት የሚገላግላትን ወገን ትጣራለች። ብርቱዋ ወጣት ለምለም በቀለ።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You