ኢትዮጵያውያን ለድል የሚጠበቁበት የሻንጋይ ዳይመንድ ሊግ

የ2024 የዳይመንድ ሊግ ውድድር ከአንድ ሳምንት በፊት በቻይና ዚመን ተጀምሮ ዛሬ ሁለተኛው መዳረሻ ከተማ ላይ ደርሷል። ከዳመንድ ሊጉ መዳረሻዎች መካከል አንዷ የሆነችው ቻይና ሁለተኛውን የዳይመንድ ሊግ ውድድር ዛሬ በንግድ ከተማዋ ሻንጋይ ታስተናግዳለች። በተለያዩ ርቀቶች እንዲሁም በሜዳ ተግባራት በሚደረጉት ውድድሮች ላይ ከመላው ዓለም የተውጣጡ 25 የሚሆኑ የኦሊምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮኖች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተረጋግጧል። ከእነዚህ መካከልም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተጠቃሽ ናቸው።

የፓሪሱ ኦሊምፒክ ጥቂት ወራት ብቻ የቀሩት መሆኑን ተከትሎ ውድድሩ አትሌቶች ሀገራቸውን ለመወከል የሚያስችል ብቃታቸውን ከሚያሳዩባቸውና ዝግጅቶቻቸውንም ከሚለኩባቸው መድረኮች መካከል አንዱ የዳይመንድ ሊግ ውድድር ነው። በመሆኑም የዛሬው ውድድር በጠንካራ ፉክክር የታጀበ እንደሚሆን ይጠበቃል። ኢትዮጵያውያኑ የዓለምና የኦሊምፒክ ሻምፒዮኖች ዛሬ በሻንጋይ የሚካፈሉባቸው ፉክክሮችም ከወዲሁ አጓጊ ሆነዋል።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለድል ከሚጠበቁበት ፉክክር ቀዳሚው የ5ሺ ሜትር ውድድር ሲሆን በሁለቱም ፆታ የአሸናፊነት ቅድመ ግምትም አግኝተዋል። ኢትዮጵያውያን ውጤታማ ከሆኑባቸው ርቀቶች መካከል አንዱ በሆነው የ5ሺ ሜትር ሴቶች የቀድሞዋ የዓለም ክብረወሰን ባለቤት ለተሰንበት ግደይ በዛሬው ውድድር ተሳታፊ መሆናቸውም በስፖርቱ ቤተሰብ ዘንድ ፉክክሩ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል። በውድድር ዓመቱ በብዙ የውድድር መድረኮች ያልታየችው ኮከብ ከበርካታ የሃገሯ ልጆች ጋር በመሆን ዛሬ ሻንጋይ ላይ ለአሸናፊነት ትሮጣለች።

በ10ሺ ሜትር ይበልጥ የምትታወቀው ለተሰንበት በ5ሺ ሜትርም በርካታ ስኬቶችን ያጣጣመች ሲሆን፤ እአአ በ2020 ቫሌንሲያ ላይ 14:06.62 በሆነ ሰዓት የዓለም ክብረወሰንን ከእጇ ማስገባቷ አይዘነጋም። ይህ ሰዓት አሁን ላይ በሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ የተሻሻለ ቢሆንም በዚህ ውድድር ከሚካፈሉት መካከል ግን ቀዳሚው ነው። ከዚህ ፈጣን ሰዓት እንዲሁም ከአትሌቷ ድንቅ አቋም የተነሳም ለተወዳዳሪዎቿ ፈታኝ እንደምትሆን ይጠበቃል።

ከለተሰንበት በተጨማሪ በውድድሩ ከሚሳተፉ አትሌቶች መካከል በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚገኙ ሲሆን፤ ለአሸናፊነት የሚደረገው ፉክክር ተጠባቂ ነው። ልምድ ያላቸውና አዳዲስ አትሌቶች በተካተቱበት ውድድር መቅደስ አለምሸት፣ አስማረች አንለይ፣ ውብርስት አስቻል፣ አሳየች አይቸው፣ አያል ዳኛቸው እና የኔዋ ንብረት ይገኙበታል። በአንጻሩ ለኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው ከሚገመቱት ኬንያውያን አትሌቶች መካከል ፌይዝ ቼሮቲችና ማርጋሬት አኪዶር ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ አትሌቶቹ የሚታወቁትና ውጤታማም የሆኑት በሌሎች ርቀቶች እንደመሆኑ የአሸናፊነት ግምቱ ወደ ኢትዮጵያውያኑ ያደላ ሊሆን ችሏል።

በዚህ ርቀት የወንዶች ውድድርም በተመሳሳይ የበላይነቱ በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሊያዝ እንደሚችል ነው የሚጠበቀው። ምክንያቱ ደግሞ የኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር ሻምፒዮናው አትሌት ሰለሞን ባረጋ በዳይመንድ ሊጉ ዛሬ እንደሚሮጥ በመታወቁ ነው። እአአ በ2018 የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ ሊሆን የቻለው ግን በ5ሺ ሜትር ባሳየው ብቃት መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ ባለፈ በርቀቱ ያለው 12:43.02 የሆነ ፈጣን ሰዓት በውድድሩ ላይ ከሚካፈሉት ሁሉ ቀዳሚው ያደርገዋል። ወጣቱ አትሌት የተያዘውን የውድድር ዓመት በዓለም የቤት ውስጥ የዙር ውድድር የጀመረ ሲሆን፤ አትሌቱ ካለበት አቋም አንጻርም በዛሬው ውድድር ለተፎካካሪዎቹ በቀላሉ እጅ እንደማይሰጥ ይጠበቃል።

በኢትዮጵያውያን በኩል በዛሬው ውድድር ከሚካፈሉት መካከል አንዱ አትሌት ኩማ ግርማ ነው። ይህ አትሌት ከሳምንት በፊት በዚመን ዳይመንድ ሊግ 5ሺ ሜትር በመሮጥ አስደናቂ አቋሙን ያስመሰከረው የ3ሺ ሜትር መሰናክል የክብረወሰን ባለቤቱ አትሌት ለሜቻ ታናሽ ወንድም መሆኑም ትኩረት ስቧል። አትሌቱ በቅርቡ ጋና ላይ በተካሄደው የአፍሪካ ጨዋታዎች ላይ በዚህ ርቀት ሃገሩን ወክሎ 4ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው። ንብረቴ ክንዴ፣ ቢንያም መሐሪ እና ንብረት መላክ ደግሞ ቀላል ግምት የማይሰጣቸው የውድድሩ ጠንካራ ተፎካካሪ ኢትዮጵያውያን ወጣት አትሌቶች ናቸው።

በቶኪዮ ኦሊምፒክ በዚሁ ርቀት 4ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ኒኮላስ ኮፕኮሪር፣ በዳይመንድ ሊግ ልምድ ያለው ሳሙኤል ማሳይ እንዲሁም ቤንሰን ኪፕላጋት የመሳሰሉ ኬንያውያን አትሌቶች ጠንካራውን የአሸናፊነት ፉክክር እንደሚያደርጉ ይገመታል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You