ምክር ቤቱ 21 ነጥብ 74 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አፀደቀ

አዲስ አበባ፡የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 21 ነጥብ 74 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አጸደቀ፡፡

ምክር ቤቱ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤን ትናንት ሲያካሂድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2016 በጀት ዓመት ተጨማሪ በጀት መግለጫን ያቀረቡት የአስተዳደሩ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን እንደገለጹት፤ የከተማ አስተዳደሩን የወጪ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት፣ የገቢ አፈጻጸሙ በማደጉ፣ በ2015 በጀት ዓመት ጥቅም ላይ ያልዋለ ሀብት በመኖሩ እንዲሁም ከተለያዩ የገቢ ምንጮች የተገኘና የሚገኝ መሆኑ በመረጋገጡ የሀብት ምደባ ተደርጓል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ የገቢና ወጪ ልዩነት ያለ በመሆኑ ለወጪ ፍላጎቱ ምላሽ ለመስጠት የሀብት ምደባና ክፍፍል ስልትን ሲከተል መቆየቱን ገልጸው፤ በተደረገው የሀብት ምደባም የወጪ በጀት 21 ነጥብ 74 ቢሊዮን በተጨማሪ በጀትነት እንዲፀድቅ መቅረቡን አስታውቀዋል፡፡

ለመደበኛ ወጪ 909 ነጥብ 25 ሚሊዮን ብር ለካፒታል ሥራዎች ደግሞ 20 ነጥብ 83 ቢሊዮን ብር ተመድቧል ያሉት ኃላፊው፤ የካፒታል በጀቱ ለተጀመሩ የግንባታ ሥራዎች፣ ለመንገድ፣ ለካሳ ክፍያ፣ ለአረንጓዴ ልማትና አካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ማጠናቀቂያ እንዲሁም ለጤና ተቋማት የውስጥ ግብዓት ማሟያ የሚውል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የመደበኛ በጀቱ ደግሞ የሠራተኛ ጥቅማጥቅም ማሻሻያ በመደረጉ፣ እንዲሁም ለመምህራንና ለፖሊስ ቅጥር የሚውል ነው ብለዋል፡፡

በጠቅላላ ከተመደበው በጀት ውስጥ ለማእከል ሴክተር መስሪያ ቤቶች 19 ነጥብ 76 ቢሊዮን ለክፍለ ከተሞችም አንድ ነጥብ 97 ቢሊዮን ብር መሆኑን ገልጸዋል፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተሻሻለው የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ መሠረት የከተማ አስተዳደሩ ያቀረበውን ተጨማሪ በጀት ምክር ቤቱ ተቀብሎ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ ለሚያከናውናቸው ልዩ ልዩ ተግባራት 140 ነጥብ 29 ቢሊዮን ብር በጀት ማፅደቁን አስታውሰው፤ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከቀጥታ ታክስ፣ ቀጥተኛ ካልሆኑ ታክስ አገልግሎቶች፣ ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢና ከሌሎች አማራጮች 108 ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታውሰዋል፡፡

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You