ስኬት በብዙ መንገድ ይገለፃል። ሁሉም እንደየሙያውና እንዳለበት ሁኔታም ነው ለስኬት ያለውን አመለካከት የሚገለፀው። አንድ ሁሉንም ሊያስማማ የሚችለው ነጥብ ግን ስኬት በየትኛውም የሙያ ዘርፍም ይሁን በየትኛውም ሁኔታና፣ ቦታ፣ ጊዜና ሰአት በፊት ከነበሩበት አነስተኛ፣ ዝቅተኛ፣ የማይጠቅም ወይም የማይረባ ሕይወት መውጣትና ወደተሻለ ቦታ መምጣት ነው። ሕይወትን በእውን መኖር ነው።
አንዳንድ ሰዎች በተለያዩ ሱሶች ተጠምደው በስተመጨራሻ ከሱስ ሕይወታቸው የመውጣት ፍላጎት ቢኖራቸውም ከዚህ መጥፎ ልማድ ለመላቀቅ ሲቸገሩ ይስተዋላል። ሱሳቸውን ለመተው ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም ተስፋ ቆርጠው እዛው የሱስ ሕይወት ውስጥ ተመልሰው ሲገቡ ይታያሉ። ነገር ግን ከዚህ የሱስ ሕይወት ድንገት መንጭቀው ወጥተው ወደ ጤናማ ሕይወት የሚመለሱ ሠዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ሱስን አሸንፈው ወደጤናማ ሕይወት በመመለሳቸው ብቻ ስኬታማ ብለን ልንወስዳቸው እንችላለን።
ደረጃው ይለያይ እንጂ ሁሉም ሰው ራሱን የሚያስተዳድርበት ገቢ አለው። አንዳንዱ ብዙ ሰርቶ ገቢውን በእጥፍ ያሳድጋል። ሌላው ደግሞ እንደአቅሙ ተፍጨርጭሮ በመጠኑም ቢሆን ገቢውን የሚያሳድግ አለ። እዚህ ጋር በእጥፍ ገቢውን ያሳደገውም፤ በገቢው ላይ መጠነኛ ጭማሪ እንዲኖር የለፋውም በየራሳቸው ስኬታማ ናቸው። ምክንያቱም ሁለቱም ገቢያቸውን ለማሳደግ ሠርተዋል፤ ልዩነት ቢኖረውም ገቢያቸውን አሳድገዋል።
እነዚህን እንደምሳሌ አነሳን እንጂ በየትኛውም የሥራ መስክ በሕይወቱ ስኬታማ መሆን የማይፈልግ ሰው የለም። ሁሉም ስኬታማ መሆን ይፈልጋል። የሰው ልጅ በሕይወቱ አውቆም ሆነ ሳያውቀው መሆን የሚፈልገው ነገር ቢኖር ስኬማ መሆን ነው። ነገር ግን እውነተኛ ስኬት ምን እንደሆነ በጥልቀት የሚያውቁ ሰዎች በቁጥር እጅግ በጣም ትንሽ በመሆናቸው ሁሉም ሰው ስኬታማ ነው ማለት አይቻልም። ምንም እንኳን ሁላችንም ስኬታማ መሆን ብንፈልግም እውነተኛ ስኬታማ ሰዎች ቁጥራችን ጥቂት ነው። ታዲያ ለምድን ነው ሁላችንም ስኬታማ መሆን ያልቻልነው? ይህ ስለስኬት ስናወራ መሠረታዊ ከሆኑ ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ ነው።
ገና ከመነሻው የስኬት ትርጉሙ ካልገባን አላፊው አግዳሚው ሁሉ ይወስደናል። ወዳላሰብንበት አቅጣጫ እንሄዳለን። ስለዚህ ስኬት ምን እንደሆነ ገና ጉዞ ሳንጀምር ማወቅ ይጠበቅብናል። በስኬታማና ስኬታማ ባልሆኑ ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት ማጤን ይኖርብናል። ዛሬ ላይ ስኬት የሚለው ቃል በየቦታው የሚወራ ሆኗል። ከዚህ አንፃር ሰዎች በስኬት ዙሪያ ግራ ተጋብተዋል ማለት ይቻላል።
ስለስኬት ትርጓሚ በተለያዩ ምሁራን የተለያየ ትርጓሜ ቢሰጥም ኧርን ናይቲንጌል የተሰኘው ምሁር ስለስኬት ያስቀመጠው ትርጓሜ ሁሉንም የሚያስማማ ይመስላል። ምሁሩ ስኬት ማለት የሕይወታችንን ዋነኛና ልንሆነው የምንችለውን የመጨረሻውን ትልቁን መልክ ቀስ በቀስ መሬት ላይ እውን የማድረግ ሂደት ነው ይላል። በአንድ ግለሰብ ምናብ ውስጥ ያለ አንድ መልክ አለ። ሊሆነው የሚፈልገው የሆነ ሰው አለ። አሁን ግን አልሆነውም። ምድር ላይ ያ ሰው የለም። በዛ ሰውዬ ምናብ ውስጥ ነው ያ ሰው ያለው። ያንን ልንገነባ የምንፈልገውን ትልቁን ሕይወት ቀስ በቀስ መሬት ላይ ስጋ የማልበስ ወይም እውን የማድረግ ሂደት ነው እንግዲህ ስኬት ማለት።
አንድ ሰው የሕይወት አማካሪ ወይም ሳይካትሪስት ጋር ሄዶ ‹‹ራሴን ለማጥፋት በተደጋጋሚ ሙከራ እያደረኩ ነው፤ በጣም ድብርት ይሰማኛልና፤ ዶክተር ምን እንዳደርግ ትመክረኛለህ? ይለዋል›› ያው ዶክተሩም ሙያው ስለሆነ ሰውዬውን በተለያየ ርእስ ካናገረውና ብዙ ምልክታ ካደረገ በኋላ ‹‹ምንም የሆንከው ነገር የለም እኮ ። ግን ድብርት ሲሰማኝ ድብርቴ እንዲጠፋልኝ እኔ የማደርገውን ነገር ልምከርህና አንተም ብትሞክረው ደስ ይለኛል›› አለው።
ይህች ዓለም የምትሸልመው ውጤትን እንጂ ጥረትን አይደለም። ወዳጄ! ለምትወደው ነገር ጥግ ድረስ እየጣርክ ከሆነ ስኬታማ ነህ። ማንም ቆሞ እንዲያጨበጭብልህ አትጠብቅ። ውድቀትህን ማንም ሳይነግርህ ይሰማህ የለ? በቃ! ጥፋት ስታጠፋ፣ በሕይወትህ ስህተት ስትሠራ ምን ነካኝ? ብለህ ራስህን ትጠይቅ የለ? ስኬት ለራስህ ብቻ የሚሰማህ ልዩ ስሜት ነው። በብዙ ሰዎች መወደድና መከበር ስኬት ቢሆን ኖሮማ ኤልቪስ ፕሪስሊ፣ ማይለስ ሞርኖ፣ ማይክል ጃክሰን፣ ዊትኒ ሂዩስተን በሚሊዮኖች እየጠወደዱ፣ ሚሊዮኖች እነሱን መሆን እየተመኙ የአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚ አይሆኑም ነበር። ወይ ደግሞ ራሳቸውን አያጠፉም ነበር።
ስኬታማ እንደሆኑ ብንመሰክርላቸውም እነርሱ ግን ስኬታማ እንደሆኑ ላያምኑ ይችላሉ። ምክንያቱም ስኬት በውስጥ የሚሰማ ልዩ ስሜት ነዋ። ስኬታማ እንደሆንሽ እንዲሰማሽ ማንም ምንም ማድረግ አይችልም። ስኬታማነት እንዲሰማሽም በብዙዎች ዘንድ መከበርና መወደድም አይጠበቅብሽም። እንዴ! የምትሠሪውን ሥራ ሁሉም ላያውቀው ይችለል እኮ። ጎበዝ አካውንታንት፣ ጎበዝ መምህር፣ ጎበዝ ዶክተር፣ ጎበዝ ፋርማሲስት፣ ጎበዝ ጋዜጠኛ፣ ጎበዝ የሥነ ልቦና ባለሙያ ከሆንሽ ስኬታማ ነሽ። አንተም እንደዛው።
ብዙዎች ያንቺን ስኬት መመስከር አይጠበ ቅባቸውም። ይህች ዓለም የምትሸልመው ውጤትን እንጂ ጥረትን አይደለም። ወዳጄ! እንደነገርኩህ ለምተወደው ነገር ጥግ ድረስ እየጣርክ ከሆነ ስኬታማ ነህ። አንቺም እንደዛው። ማንም ቆሞ እንዲያጨበጭብልህ አትጠብቅ። ውድቀትህን ማንም ሳይነግርህ ይሰማህ የለ። ጥፋት ስታጠፋና በሕይወትህ ውስጥ ስህተት ስትሠራ ምን ነካኝ ብለህ ራስህን ትጠይቅ የለ። በቃ! ስኬትህንም ማንም እስኪነግርህ አትጠብቅ።
አሁን ራሱ ይህን ሃሳብ ተቀብለኸው ስኬትን በተለየ መንገድ እንድታየው ከሆንክ እኔ ራሴ ሃሳቡን ላንተ በማድረሴ ስኬታማነት ይሰማኛል። ምክንያቱም ስኬት ውስጣዊ ስሜት ነዋ! በእድሜዬ ምን ሰብስቢያለው ብቻ ሳይሆን ምን አይነት ሰው ሆኛለው ብለህ ራስህን ጠይቅ። የምታገኘው መልስ ስኬት የሚባለውን ስሜት ይፈጥርልሃል ወይም ደግሞ ስኬትን አድነህ እንድታገኝ ይረዳሃል። ስኬት ባሰባሰብከው ሀብት፣ ባጠራቀምከው ጥሪት ብቻ አይለካም። በሆንከውም ነገር ነው የሚወሰነው።
ታላቁ የዓለማችን ፈላስፋ ፓላቱ በአንድ ወቅት ‹‹ታላቁ ድል ራስን መቆጣጠር ነው›› ብሏል። ‹‹እርሷ ስትናገር ዓለም ያደምጣታል›› የምትባለው ማርጋሪት ታቸር ወይም ‹‹the iron lady›› በዓለማችን ላይ በጊዜው በጣም ተፅኖ ፈጣሪ ከሚባሉ ሰዎች ውስጥ ግምባር ቀደሟ ነበረች። የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር እዛ የስኬት ደረጃ ላይ ብትወጣም በአእምሮዋ የተረጋጋች ባለመሆኗ ብቻ ማንም ነኝ የሚል ስሜት እየተሰማት ነው ከዚህ ዓለም በሞት ተለየችው።
ስኬታማ እንደሆንክ ሰዎች ቢመሰክሩልህም ዋናው ጥያቄ አንተስ በውስጥህ ምን ይሰማሃል የሚለው ነው። አሁንም ደግሜ ልንገርህ! ስኬት ማለት ለራስህ የሚሰማህ ስሜት ነው። ለብዙዎች ምሳሌ ልትሆን ትችላለህ። ቤተሰብ፣ ዘመድና ሀገር ሊኮራብህ ይችላል። ውስጥህ ግን ያ ስሜት ከሌለ ስኬት እጅህ ላይ የለም። ‹‹man bfrom mars women frome venus›› ወይም ወንዶች ከማርስ ሴቶች ከቬነስ የተባለው መፅሃፍ ብዙ ቤተሰቦችን ከመበተን አድኗል። ብዙ ትዳሮችንና የፍቅር ግንኙነቶችንም ከመፍረስ ታድጓል።
የመፅሃፉ ደራሴ ዶክተር ጆን ግሬይ ግን የራሱን ትዳር ከማፍረስ አላዳነውም። ይህ ሰው የተለየ ሁኔታ ወይም ከአቅም በላይ የሆነ አጋጣሚ ገጥሞትም ሊሆን ይላል ትዳሩን ያፈረሰው። ልንፈርድበትም አይደለም። ነገር ግን እኛ የምናደንቀው በሚሊዮኖች ኮፒ የሸጠውን ዘ ቤስት ሴለር ከሚባሉ ደራሲዎች ውስጥ የሚመደበው ይህ ሴኬታማ ደራሲ እንኳን በውስጡ ለራሱ ስኬታማነት ላይሰማው ይችላል። ምክንያቱም ስኬት ስሜት ነው። ለራስህ ብቻ የሚሰማህ ስሜት።
ስኬት በርግጥም ስሜት እንደሆነ ለማወቅ ከፈለክ በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ ‹‹ሰምበቴ›› በሚል ርእስ የለቀቁትን ቪዲዮ ማየት በቂ ነው። በዚህ ቪዲዮ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ብለዋል። ‹‹በጣም የማስታውሳት አንድ ሰምበቴ የምትባል ለማኝ ነበረች። ሰዎች ገንዘብ ሲያዋጡ አንድ ብር ሰጠችን። ቀኑን ሙሉ ከለመነችው ገንዘብ ሰብስባ አንድ ብር ሰጠችን። አጋሮ ላይ ሆስፒታል፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህት ቤትና ወጣት ማእከል ሠራን። ሰምበቴ ስትጠየቅ ግን ሠራሁ ትላለች››
ሰምበቴ አንድ ብር አዋጥታ እኔም ነው የገነባሁት ብላ የሚል ስሜት ከሰጣት ስኬታማ ነች። ምክንያቱም ስኬት ለራስህ ብቻ የሚሰማህ ስሜት ስለሆነ። ከራሱ ጋር የሚጣላ በፍፁም ያልተረጋጋ ሰው የስኬት ጫፍ ቢወጣ እንኳን ያንን ስኬት ማጣጣም አይችልም። ለምን? ካልከኝ ስኬት ከውጪ የሚሰጥህ ሳይሆን በውስጥ የሚሰማህ ስሜት ነው።
ከላይ እንደመንደርደሪያ ያነሳሁትን ምሳሌ ልድገመውና በሌላ አቅጣጫ ስኬትን ላሳይህ። አንድ ሰው የሕይወት አማካሪ ወይም ሳይካትሪስት ጋር ሄዶ ራሴን ለማጥፋት ብዙ ጊዜ እየሞከርኩ ነው። በጣም ድብርት ይሰማኛል። ዶክተር ምን እንዳደርግ ትመክረኛለህ? ይለዋል። ዶክተሩም ሙያው ስለሆነ በተለያየ ርእስ ካናገረውና ብዙ ምልከታዎችን ካደረገ በኋላ ምንም የሆንከው ነገር እኮ የለም! ግን እኔ ድብርት ሲሰማኝ ድብርቴ እንዲጠፋልኝ የማደርገውን ነገር ልምክርህና አንተም ብትሞክረው ደስ ይለኛል አለው። ከዛ ዶክተሩ ምን አለው? ወደ አደባባዩ በሚወስደው መንገድ ላይ ሰርከስ የሚሠሩ ሰዎች አሉ። ለምን በቀን ሁለት ጊዜ እዛ አትሄድም። በርግጠኝነት ትዝናናለህ። ሰርከሱን ከሚሠሩት ሰዎች መካከል በአስቂኝ ማስክ ፊቱን ሸፍኖ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሳቅህን መቆጣጠር እስኪያቅትህ ድረስ የሚያስቅህ አርቲስት አለ።
ያንን የሰርከስ ባለሙያ ወይም አርቲስት እያየህ ድብርትህ አራግፈህ የደስታህ ጫፍ ላይ እንደምትወጣ አትጠራጠር ይለዋል። ሰውዬው ግን መለሰ ‹‹የኔ ችግር የተለየ ነው ዶክተር ያ አርቲስት እኔ ነኝ›› አለው። ታዲያ ይህ ሰው ለብዙ ሰዎች መሳቅና መዝናናት ምክንያት ሆኖ ከባድ ድብርት ቢሰማው አትፍረድበት። ምክንያቱም ያገኘው ስኬት ለሌሎች ነው እንጂ ለእርሱ አልተሰማውም። ለዛ ነው ስኬትን በሰበሰብከው ነገር ሳይሆን በሆንከው ነገር ለካው የሚባለው። ምክንያቱም ደግሜ እንደነገርኩህ ስኬት ስሜት ነው። ከውጭ የሚሰጥህ ሳይሆን ለራስህ ከውስጥህ የሚሰማህ ስሜት ነው።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም