የኮሪደር ልማቱ ቱሩፋቶች

አዲስን አበባን እንደ ስሟ አዲስና ውብ ማድረግን፣ የአፍሪካ መዲናን ከአፍሪካ ትላልቅ ከተሞች ተርታ ማሰለፍን ባቀደው፣ ከተማዋ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የገነባቻቸውንና እየገነባች የምትገኛቸውን ትላልቅ መሠረተ ልማቶች ማገናኘትን ባለመው የኮሪደር ልማት በርካታ ተግባሮች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በዚህ ከአንድ ወር በፊት ለተጀመረ ግዙፍ የመሠረተ ልማት ግንባታ በሚያስፈልጉ ስፍራዎች ላይ የሚገኙ በርካታ ሕንጻዎች እንዲፈርሱ፣ መሠረተ ልማቶች እንዲነሱ፣ ወዘተ ተደርጓል። አንዳንድ ሕንጻዎች ደግሞ ከምድር ወለላቸው የተወሰነውን ለእግረኛ መንገድ እንዲለቁ እየተደረገ ይገኛል። ሕንጻዎቹ የኮርደር ልማቱ ለሚካሄድባቸው አካባቢዎች በወጣው ስታንዳርድ መሠረት እድሳት እንዲያደርጉም እየተደረጉ ናቸው። ሰፋፊና ዘመናዊ የተሽከርካሪና የእግረኛ መንገዶች የብስከሌት መንገዶችና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ግንባታ እየተጣደፈ ነው፤ ለ24 ሰዓት፣ ለሰባት ቀናት እየተካሄደ የሚገኘው ይህ ልማት እኔ በምሠራበት መሥሪያ ቤት አካባቢ ከአራት ኪሎ ወደ ፒያሳ በሚወሰደው መንገድ ልማት ብቻ ልማቱ ምን እንደሚመስልና አሁን የደረሰበትን ከፍተኛ ደረጃ መመዘን ይቻላል።

የፒያሳ አራት ኪሎ ቀበና መገናኛ ኮሪደር የፒያሳ አራት ኪሎውን ከፍል በየቀኑ እመለከታለሁ፤ በከፍተኛ ርብርብ ብዙ ሥራዎች እየተካሄዱበት ይገኛል።በእዚህ መንገድ ከመንገድ ግንባታው አስቀድሞና ጎን ለጎን በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል። ለኮሪደር ልማት ግንባታው ሲባል ከተማ አስተዳደሩ ጨክኖ የገባባቸው ሥራዎች ብዙና ትላልቅም ናቸው። ለሥራው ያስፈልጋሉ በተባሉ ስፍራዎች የነበሩ እስከ አራት ፎቅ የሚደርሱ ወለሎች ያላቸው ሕንጻዎች ጭምር እንዲፈርሱ ተደርጓል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሳይንስ ፋኩልቲ አንድ ሕንጻ ሙሉ ለሙሉ ፈርሷል፣ ሌላም ሕንጻ የተወሰነው አካሉ ፈርሷል፤ እዚያው ድል ሐውልት ፊት ለፊት ከብልጽግና ጽሕፈት ቤት ጎን የነበሩ ሁለት ሕንጻዎችም ፈርሰዋል። ጆሊ ባር ከእናት ሕንጻዋ ተቆርጣ ተሰናብታለች። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሳይንስ ካምፓስ እንዲሁም ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሰፊ መሬት ተወስዷል። ከእዚህ ኮሪደር አጠገብና ትንሽ ፈንጠር ብሎም ያሉ ሌሎች የተለያዩ ሕንጻዎች እንዲፈርሱ ተደርጓል። አራዳ ክፍለ ከተማ አካባቢም እንዲሁ ጥቂት የማይባሉ የተለያዩ አገልግሎቶች ይሰጥባቸው የነበሩ ቤቶች ፈርሰዋል።

የኮርደር ልማቱ በሚያልፋባቸው ጎዳናዎች አቅራቢያዎች የሚገኙ በርካታ ሕንጻዎች ቢፈርሱም፣ በከተማዋ እስከ ቅርብ ጊዜ ይደረግ እንደነበረው የፀዳው ቦታ ክፍቱን አልተቀመጠም። የተለያዩ ግንባታዎች ተጀምረዋል፤ መጀመር ብቻ አይደለም፤ /በኛ ሀገር መጀመር ችግር የለውም፤ አጠናክሮ መቀጠልና መጨረስ እንጂ፣ እነዚህ ግንባታዎች ግን እየተጣደፉ ናቸው። ለፒያሳ አራት ኪሎ ማንም ሊገምተው በማይችል መልኩ ሰፊ የተሽከርካሪ፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች እየተገነቡ ናቸው። ከመንገዶቹ ግንባታ ጋር የተለያዩ የስልክ፣ የውሃና፣ የአሌክትሪክ፣ የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች ተያይዘው ተዘርግተዋል፤ እየዘረጉም ናቸው።

በግንባታዎቹ ለመሠረተ ልማት በሚል ዶማና አካፋ ተይዞ ምልልስ የማይደረግባቸው ሥራዎች ናቸው። የታክሲና የአውቶብስ ማቆሚያ ተርሚናሎች፣ መፀዳጃ ቤቶች፣ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ የውሃ ፋውንቴኖች ጎዳናዎቹን ውበት የሚያላብሱ የመንገድ መብራቶችና የመሳሰሉት ግንባታዎች እንደሚካሄዱ ይጠበቃል፤ ለእነዚህ ሥራዎች የሚያስፈልጉት መሠረተ ልማቶች እየተዘረጉ ናቸው። አንዳንዶቹም ግንባታዎች ተጀምረዋል። በርካታ የግንባታ ማሸነሪዎችና የሰው ኃይል ተሠማርተውበት በሚገኘው በዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት፣ ግንባታው ማታ በታየበት ሁኔታ ጧት አይገኝም፤ ብዙ ርቀት ሄዶ ነው ጧት ላይ የሚገኘው። ማታ አካባቢውን የተመለከተ ጧት አዲስ ነገር ይመለከታል። በተለይ በሳምንቱ መጨረሻና በበዓላት ወቅት ከሥራ አካባቢ የራቁ ሰዎች ወደ ሥራ ሲመለሱ በተመለከቱት ለውጥ በእጅጉ ሲደመሙ መመልከትና መስማት ተለምዷል።

ግንባታዎቹ ከመሠረተ ልማት ግንባታ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የቅንጅት ጉድለት የማይነሳባቸው፣ ለበርካታ ዓመታት እፎይታን የሚሰጡ ናቸው፤ የኤሌክትሪክና የስልክ ገመዶች እንዲሁም ምሰሶዎች በመንገዶች ላይ የሚያሳድሩትን የገጽታ መበላሽት የሚያስቀርም ተደርጎ እየተካሄደ ነው። የኮሪደር ልማቱ አንድ ዘመናዊ መንገድ የሚያስፈልጉት መሠረተ ልማቶች በሙሉ እንዲሟሉለት የሚደረግበትና ውብ አካባቢ የሚፈጠርበት፣ የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ የሚያሳልጥ፣ ውበቷን የሚጨምር ይሆናል። ልማቱ ቀጣዩ የከተማዋ ገጽታ ምን መመስል እንዳለበትም ገና ከአሁኑ ማመላከት እያስቻለ ነው፤ በዋና ዋና መንገዶች የሚካሄዱ ግንባታዎች ከዚህ በኋላ ከአስር ሜትር ርቀት በኋላ መካሄድ እንዳለባቸው የተመላከተ ሲሆን፣ በሌሎች መንገዶችም እንዲሁ እንደ መንገዶቹ ሁኔታ የተወሰኑ ሜትሮችን ገባ ብሎ ብቻ ግንባታ እንደሚካሄድ የከተማ አስተዳደሩ ሕግ አውጥቷል።

ይህ ሁኔታ በትላልቅ አደባባዮችና ጎዳናዎች አፍንጫ ስር ግዙፉ ግንባታ የሚካሄድበትን ሁኔታ ማስቀረትና በዚህም መንገዶችን ማስፋት ሲያስፈልግ በቂ ቦታ እንዲኖር የሚያስችል ሁኔታን የሚፈጥር እንደመሆኑ፣ በቀጣይ በወሰን ማስከበር ወቅት የሚያጋጥምን ችግር በሚገባ እንደሚፈታ ይታመናል። ጎዳናዎችና አደባባዮች ለቀቅ ያሉና ዘና ተብሎ እንቅስቃሴ የሚደረግባቸው እንዲሆኑ ያደርጋል። በኮሪደር ልማቱ የሚገነቡት የመንገድ መሠረተ ልማቶች ሰፋፊና ዘመናዊ መንገድ የሚያስፈልገው መሠረተ ልማት የሚሟላላቸው መሆናቸውም ከተማዋን በትራፊክ እንቅስቅሴ የተሳለጠች፣ በምሽት ዘና ተብሎ የሚኬድባት፣ ለቱሪስትና እንግዳም ምቹ እንድትሆን ያስችላሉ።

የተንጣለሉ የተሽከርካሪና እግረኛ መንገዶች የሚኖሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ ለሞተር አልባ ተሽከርካሪዎች /ሳይክል/ እንቅስቅሴም ትኩረት የሰጠ እንደመሆኑ የትራንስፖርት አማራጭ እንዲኖር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ይህ ሁሉ ሲሠራ ግን ብዙ መስዋዕትነት እየተከፈለ ነው፤ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖርባቸው የነበሩ የሚታወቁ የከተማዋ መንደሮች ነዋሪዎች በመልሶ ልማቱ እንዲነሱ ተደርጓል፤ መንግሥት ይህን ሲያደርግ ለልማቱ ተነሺዎች መኖሪያ ቤቶችን በማቅረብ ነው፤ የቀበሌ ቤት ይኖር እንደ ፍላጎቱ ተስተናግዷል፤ የጋራ መኖሪያ ቤት ከፈለገ የጋራ መኖሪያ ቤት፣ የቀበሌ ቤት ከፈለገም እንዲሁ የቀበሌ ቤት ተሰጥቶታል፤ የግል ይዞታ ላላቸው ቦታና ካሣ ሰጥቷል።

በዚህ በኩል ቅሬታ ያለው ካለ አቤት እንዲልም በከተማ አስተዳደር፣ በክፍለ ከተማ ደረጃ ኮሚቴ አንዲቋቋም ተደርጓል። በዚህም መሠረት ቅሬታ ያላቸው ያንን እያደረጉ ናቸው። ለእዚህ ሁሉ ነዋሪ ቤት ማቅረብ፣ ለእዚህ ሁሉ ነዋሪ በውድ ዋጋ ሊሸጥ የሚችል ቦታ መስጠትና ካሣ መክፈል፣ በርካታ የመኖሪያ ቤት ፈላጊዎች ባሉባት ከተማ መኖሪያ ቤቶችን አፍርሶ ያሉትን ውስን መኖሪያ ቤቶች ለተነሺዎች መስጠት ውስጥ መግባት በአጠቃላይ ሀገሪቱ ካላት ውስን ሀብት አኳያ ሲታይ ልማቱን ለማካሄድ ሲባል ምን ያህል መጨከን ውስጥ እንደተገባ መረዳት ይቻላል። በዚህ ላይ ልማቱን ለማካሄድ ደግሞ ከፍተኛ ሀብት ይፈልጋል።

ይህ ሁሉ መንግሥት የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር ትልቅ ዋጋ እየከፈለ መሆኑን ያመለክታል። መንግሥት ይህን ሁሉ አርጎም ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቋል። ልማቱ ያስተጓጎላቸው ነገሮች እንዳሉ አምኗል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ /ዶክተር/ ‹‹የኮሪደር ልማቱን ለማከናወን ሲባል የማኅበረሰቡን አጥር፣ ቤት፣ የመሥሪያ ቦታ እያፈረስን ያለነው ከተማዋን በገባነው ቃል መሠረት ለማስዋብና በኢትዮጵያ ልክ የሆነች ከተማ ለመፍጠር መሆኑን ተገንዝባችሁ የተጎዳችሁ ካላችሁ በይቅርታ መንፈስ ትብብር እንድታደርጉልን እጠይቃለሁ ሲሉ ከገለጹት በግልጽ መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ያልተገነባ ሀገርና ከተማ ተደጋጋሚ መፍረስ ይገጥመዋል፤ የፌዴራል መንግሥትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ተባብረን ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አሁን ያፈረስናቸውን ስፍራዎች ጠግነን አዲስ አበባን በገባነው ቃል መሠረት ውብ ለማድረግ ቀን ከሌት እንሠራለን ባሉት መሠረትም ሥራዎች ቀን ከሌት መሠረታቸውን ቀጥለዋል። በአራት ኪሎ አካባቢ አንዳንድ መንገዶች ለትራፊክ ክፍት እየተደረጉ ናቸው።

ከቱሪስት ሆቴል ወደ ማርያም ማዞሪያና ራስ መኮንን አፍንጮ በር እንዲሁም ከአፍንጮ በር በራስ መኮንን አርጎ ወደ ዳኑ ሆስፒታል ለተሽከርካሪዎች ክፍት ተደርገዋል። ይህም መንግሥት ለሕዝቡ በገባው ቃል መሠረት ግንባታውን እያፈጠነ መሆኑን ያመለክታል። በሌሎች ኮሪደሮችም እንዲሁ ተመሳሳይ ተግባር እየተከናወነ ስለመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ ከሚሰጣቸው መግለጫዎች እንገነዘባለን። በእነዚህ የኮሪደሩ አካባቢዎችም በአራት ኪሎ አካባቢ ያለው አይነት የግንባታ ፍጥነት የሚስተዋል ከሆነ በእርግጥም በተባለው ጊዜ ሥራው ሊያጠናቅቅ ይችላል። በኮሪደር ልማቱ የሚሸፈኑ አካባቢዎች በርካታ ናቸው። ከፒያሳ አራት ኪሎ መገናኛ ፣ ከመገናኛ ሲኤምሲ ኮኔክሽን ማዕከል፣ ከሜክሲኮ ሣር ቤት፣ ቄራ ፣ ጎተራ፣ ወሎ ሰፈር ቦሌ፣ ከቦሌ መገናኛ የኮሪደር ከልማቱ የሚካሄድባቸው መስመሮች ናቸው።

የኮሪደር ልማቱ በፒያሳ አራት ኪሎ እንደሚታየው አይነት ሰፊ ከሆነ ደግሞ በልማቱ የሚከናወኑ ተግባሮች እጅግ በርካታ ናቸው ማለት ነው። ሁሉም ሥራዎች ደግሞ የተጀመሩት አንዴ ነው። ይሁንና ከከተማ አስተዳደሩ የሚሰጡ መግለጫዎች እንደሚያመለክቱት፤ ሥራው እጅግ ሰፊ ቢሆንም በጥሩ ሁኔታ እየተፈጸመ ነው፤ ከፍ ብዬ እንዳነሳሁት ከፒያሳ አራት ኪሎ ያለው የኮሪደር ልማቱ አካል ግንባታ ያለው የአፈጻጸም ፍጥነት በሌሎች አካባቢዎችም በተመሳሳይ እየፈጸመ ከሆነ ልማቱን በተባለው ጊዜ ለማድረስ ብዙም የሚቸግር አይሆንም። መንግሥት የኮሪደር ልማቱን ስድስት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ርብርብ እንደሚያደርግ ባስቀመጣው አቅጣጫ መሠረት እየሠራ ነው። መንገዶቹን በሦስት ወር ውስጥ የማጠናቀቅ እቅድ እንዳለም ከከተማ አስተዳደሩ የወጣ መረጃ ይጠቁማል። ክረምቱ ከመግባቱ በፊት የመንገድ ሥራው ሊጠናቀቅ ይችላል ማለት ነው። ይህም ከግንባታው ጋር በተያያዘ በክረምት ወቅት በትራፊክ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እንደማይፈጠር ያመላክታል።

የኮሪደር ልማቱ ሥራዎች በርካታ ናቸው፤ እንደ አንድ ፕሮጀክት የሚቆጠሩ ናቸው ብዬ አልወስድም። የከተማ አስተዳደሩ እስከ አሁን በርካታ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ገንብቶ ወደ ሥራ አስገብቷል። ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች ነበሩ፤ ይሁንና እነሱንም በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በመሥራት ለልማቱ ያለውን ቁርጠኝነት በተጨባጭ አስመስክሯል። የዚህ ኮሪደር ልማት ሥራዎች ግን ለእኔ የበለጠ ግዙፍ ሆነውብኛል። በእርግጥ የዓድዋ ሙዚየም ሰፋፊ ሥራዎች የተሠሩበት የዓድዋ ሙዚየም በጣም ግዙፍ ፕሮጀክት እንደነበር እወስዳለሁ።

እስከ አሁን በተመጣበት ሁኔታ ሲታይ ከዚህ ፕሮጀክት ውጪ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የተካተቱበት ግዙፍ ፕሮጀክት አላስተዋልኩም፤ ከሚፈጸሙበት የጊዜ ሰሌዳ፣ ከብዛታቸው አኳያ ስመለከታቸው ደግሞ ትላልቅ ሥራዎች የተካተቱባቸውም ናቸው። ሥራዎች በእቅዱ መሠረት እየተፈጸሙ ያለበት የቱንም አይነት ግዙፍ ፕሮጀክት ለመፈጸም የሚያስችል አቅም መገኘቱን ያመለክታል። ለእዚህ ግን ከዝግጅት ሥራዎች አንስቶ ሊጠቀሱ የሚገባቸው በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ ቢችሉም፣ ዋናው ተጠቃሹ ምክንያት ብዬ የምወስደው ክትትልና ቁጥጥር ነው። በተለያዩ ፕሮጀክቶቻቸው ላይ እንዳረጋገጡት የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባና ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ፕሮጀክት የት እንደደረሰ በየጊዜው እየገመገሙ ይገኛሉ። ይህ ክትትልና ቁጥጥራቸው ሪፖርት ከማዳመጥ በዘለለ፣ በፕሮጀክት ሳይት ላይ በመገኘት በየጊዜው የሚፈጸም እንደመሆኑ ለውጤታማነቱ ከፍተኛውን አስተዋፅዖ አበርክቷል።

የክትትልና ቁጥጥር ሥራው ባለፉት የከተማ አስተዳደሩም ሆነ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቶች ላይ በሚገባ የታየና ውጤታማነቱም በተለያዩ ወገኖች ጭምር የተመሰከረለት እንደመሆኑ ይህ ፕሮጀክትም ውጤታማ እንዲሆን እንደሚያደርግ ከእስከ አሁኑ አፈጻጸም መረዳት ይቻላል። በዚህ ግዙፍ ፕሮጀክትም የመንግሥት ግዙፍ የግንባታ ፕሮጀክቶች ለኮንስትራክሽን ዘርፉም ጥሩ ትምህርት ቤት መሆን እንደሚችሉ አሁንም ማሳየት እየተቻለ ነው። በፕሮጀክት መጓተት የምትታወቅ ሀገር ላይ ነው ይህን አፈጻጸም ማሳየትም የተቻለው። ይህ ስኬት ለታመሙና በቀጣይም ሊታመሙ ለሚችሉ ፕሮጀክቶቻችን ሕክምና ወሳኝ ነውና ፕሮጀክት በባለቤትነት በመምራት የሚታወቁ የክልል መንግሥታት፣ ሌሎች የፕሮጀክት ባለቤቶች፣ የግንባታ ተቋራጮችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ከዚህ ትምህርት ቤት ገብተው ሊማሩ ይገባል እላለሁ።

ዘካርያስ

አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You