በክልሉ በሌማት ትሩፋት የተገኘው ምርት ሌሎች ክልሎችንም ተጠቃሚ እያደረገ ነው

አዲስ አበባ፡- በሲዳማ ክልል ከሌማት ትሩፋት የሚገኘው ምርት ሌሎች ክልሎችንም ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን የክልሉ እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ገለጸ።

የክልሉ እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተክሌ ጆንባ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በክልሉ ከሌማት ትሩፋት ሥራዎች የተገኘው ውጤት እጅግ አበረታች ነው።ከሌማት ትሩፋቱ የተገኘው ምርት ከክልሉ አልፎ ሌሎች ክልሎችንም ተጠቃሚ እያደረገ ነው።

አሁን ላይ የሌማት ትሩፋት ውጤት የሆነው የእንቁላል ምርት ከሲዳማ ክልል ወደ ባህርዳር፣አዲስ አበባ፣ጂግጂጋ እና አፋር በየሦስት ቀኑ 120ሺ እንቁላል እንደሚላክ የተናገሩት አቶ ተክሌ፤ በክልሉም የሌማት ትሩፋት ከመጀመሩ በፊት 14 ብር ሲሸጥ የነበረው የአንድ እንቁላል ዋጋ ወደ 7 እና 8 ብር መውረዱንም ተናግረዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 127ሺ የእንስሳት ዝርያዎችን ማሻሻል የተቻለ ሲሆን፤ በወተት ልማት 384 ሺ ቶን ወተት ተመርቷል።ስድስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዶሮ፣16ሺ 468 ቶን እንቁላል ፣ ከአንድ ሺ አምስት መቶ 39 ቶን የማር ምርት ፣ዘጠኝ መቶ አራት ኪሎ ግራም የሀር ክር፣ ሁለት ሺ ስምንት መቶ ሰባት ቶን የአሳ ምርት እንዲሁም 41 ሺ ሦስት መቶ ዘጠኝ ቶን የስጋ ምርት በዘጠኝ ወራት በሌማት ትሩፋት ማምረት ተችሏል።

በሌማት ትሩፋት ትልቅ የሥራ እድል መፈጠሩን የሚናገሩት ኃላፊው፤ ለ21 ሺ 737 ወጣቶች እና ሴቶች አዲስ የሥራ እድል መፈጠሩን አመልክተዋል። ወጣቶቹ የወተት ላም በማርባት፣ መኖ በማልማትና በመሸጥ፣ወተት በመሸጥ፣ በዶሮ እርባታ እና በማር ምርት ተደራጅተው እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እየጠቀሙ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

የሌማት ትሩፋት በዶሮ፣በወተት ፣በማር፣በአሳ እና በስጋ ልማት በተሠራው ሥራ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት በማገዝ የራሱን ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በቅርቡ ለሚከበረው የትንሳኤ በዓል በሀዋሳ ከተማ የዶሮ እና እንቁላል መሸጫ ጊዜያዊ የመሸጫ ቦታዎች በማዘጋጀት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን በመጥቀስ፤ በበዓሉ ምክንያት ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ እንደማይኖር ተናግረዋል።

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You