የሞርካ- ግርጫ- ጨንቻ መንገድ በቀጣይ ዓመት ለትራፊክ ክፍት ይሆናል

አዲስ አበባ:- የሞርካ- ግርጫ- ጨንቻ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ስድስት ኪሎ ሜትር የወሰን ማስከበር ሥራ በተያዘው ዓመት የሚጠናቀቅ ከሆነ መንገዱ በቀጣይ ዓመት ለትራፊክ ክፍት እንደሚሆን የፕሮጀክቱ ተጠሪ ኢንጂነር አስቻለው ባልቻ ገለጹ። የመንገዱ ግንባታ 72 በመቶ ደርሷል።

የፕሮጀክቱ ተጠሪ ኢንጂነር አስቻለው ባልቻ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የሞርካ- ግርጫ- ጨንቻ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ስድስት ኪሎ ሜትር የወሰን ማስከበር ሥራ በተያዘው ዓመት የሚጠናቀቅ ከሆነ መንገዱ በቀጣይ ዓመት ለትራፊክ ክፍት ይሆናል።

የሞርካ- ግርጫ- ጨንቻ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት 72 በመቶ ደርሷል ያሉት ኢንጂነር አስቻለው፤ ፕሮጀክቱ ሞርካ፣ ዋጫ፣ ወይዛ፣ ሁሉ ቆዴ፣ ዛዳ፣ ዶኮ፣ ጨንቻ ከተሞችን ያገናኛል ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት የፕሮጀክቱን ግማሽ ክፍል ቀሪውን ደግሞ በ2017 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ያሉት ኢንጂነር አስቻለው፤ 72 ነጥብ ስድስት ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ይህ መንገድ 39 ነጥብ አራት ኪሎ ሜትር የሚሆን የአስፋልት ንጣፍ ሥራው መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው የሥራ ተቋራጭ ቤጂንግ አርባን ኮንስትራክሽን ግሩፕ መሆኑን የገለጹት ኢንጂነር አስቻለው፤ መንገዱን ለመገንባት የሚያስፈልገውን አንድ ነጥብ 967 ቢሊዮን ብር በኢትዮጵያ መንግሥት እየተሸፈነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የማማከሩን ሥራ ደግሞ ኮር ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ ኃላ/የተ/የግ/ማ እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

መንገዱ በከፍተኛ ወሰን ማስከበር ችግር እንዲሁም በፕሮጀክቱ ክፍል ከኪ.ሜ 39 እስከ 45 ከፍተኛ መሬት መንሸራተት ችግር ምክንያት ተጓትቶ ቆይቷል ሲሉም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የፕሮጀክቱ ኢንጂነር እያሱ ገብሬ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት እየተሠራ የሚገኘው አስፓልት ኮንክሪት ግንባታ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም ሁለት የድልድይ ሥራዎችን በማጠናቀቅ 39 ነጥብ አራት ኪሎ ሜትር የአስፋልት ንጣፍ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ቀድሞ ለመጓጓዝ ይወስድ የነበረውን የጉዞ ጊዜ በሁለት ሰዓት ተኩል ይቀንሳል ያሉት ኢንጂነር እያሱ፤ መንገዱ ሲጠናቀቅ የሚኖረው ፋይዳ ከተማን ከከተማ ማገናኘት፣ ለከተማ እድገት፣ ታካሚን በተሻለ ፍጥነት ጤና ተቋም ለማድረስ እና አምራች ምርቱን ለገበያ ማቅረብ እንዲችል ያደርጋል ብለዋል።

የመንገዱ ስፋት በወረዳ ከተማዎች 21 ነጥብ አምስት ሜትር፣ በቀበሌ ከተማዎቸ 12 ሜትር፣ በገጠር ስምንት ሜትር ስፋት አለው ሲሉም ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የተጀመረው 2012ዓ.ም ሲሆን፤ ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ የመንገድ ግንባታው መዘግየቱን ገልጸው፤ በውሉ መሠረት የፕሮጀክቱን ግማሽ ክፍል በ2016 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ለማስረከብ እንዲሁም ቀሪውን በ2017 ዓ.ም ለማስረከብ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You