የከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ልክ እንደሌሎቹ የጤና እክሎች ተጋላጭንት የሚያሰፉ ነገሮች ናቸው የሚባል ቢሆንም በትክክል በምን ሊከሰት እንደሚችል በጥናት የተረጋገጠ መረጃ የለም። ይሁን እንጂ በቤተሰብ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ችግር ካለ፣ በተወሰነ መልኩ በዘር የሚሄድ ነገር ካለ ወይም ደግሞ እናት የተለያዩ በሽታዎች ለምሳሌ የስኳርና የደም ግፊት ታማሚ ከነበረች የከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ በእርግዝና ወቅት ሊከሰት እንደሚችል የዘርፉ ጤና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በየሶስት ደቂቃ ከከንፈርና ከላንቃ መሰንጠቅ ጋር አንድ ህፃን እንደሚወለድ መረጃዎች ያሳያሉ። በእንፃሩ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአምስት ደቂቃ አንድ የከንፈርና ላንቃ ቀዶ ህክምና እንደሚሠራ መረጃዎቹ ይጠቁማሉ። ይህም ከከንፈርና ላንቃ ጤና ችግር ስፋት አንፃር እየተደረገ ያለው የቀዶ ህክምና እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን ያሳያል። የላንቃ መሰንጠቅ ያለባቸው 60 ከመቶ የሚጠጉ ህፃናት ደግሞ ህክምና ሳያገኙ እንደሚሞቱ ጥናቶች ያመለክታሉ።
በኢትዮጵያም ቢሆን በቂ ልየታዎች ባለመደረጋቸው ነው እንጂ ከከንፈርና ላንቃ ጤና ችግር ጋር የሚወለዱ ህፃናት ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል። የከንፈርና የላንቃ ቀዶ ህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ በወላጆች በኩል ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆንና አገልግሎቱ በአብዛኛው በረድዔት ድርጅቶች የሚሰጥና ውስን መሆን ደግሞ የታሰበውን ህፃናት ቁጥር ያህል በቀዶ ህክምና ተደራሽ ማድረግ አልተቻለም። እንዲያም ሆኖ ግን በተለይ ‹‹ስማይል ትሬን›› የተሰኘው ዓለም አቀፍ በጎ አድራጎት ድርጅት በከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ቀዶ ህክምና ተደራሽ በመሆን የብዙ ኢትዮጵያውያን ህፃናትን ፈገግታ መልሷል።
ዶክተር ቤቴል ሙልጌታ ስማይል ትሬን በተሰኘው ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት የምስራቅ አፍሪካ ፕሮግራም ማናጀር ሆነው ያገለግላሉ። እርሳቸው እንደሚሉት ድርጅቱ የከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ቀዶ ህክምናዎችን ይሠራል። ከዘጠና በላይ በሚሆኑ ሀገራትም ይንቀሳቀሳል። ከተመሠረተበት ከሃያ አምስት ዓመት ጀምሮ እስካሁን ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ቀዶ ህክምናዎችን ሠርቷል። በኢትዮጵያ ደግሞ 38 ሺ ያህል ቀዶ ህክምናዎችን አድርጓል።
ድርጅቱ በዚህ የቀዶ ህክምና የሚታየውን የባለሙያዎች አቅም ማነስ ለማሳደግ ይሠራል። ለዚህም በተለያዩ ሆስፒታሎች ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎች አጭርና ረጅም ሥልጠናዎችን ይሰጣል፤ እርዳታም ያደርጋል። የከንፈርና የላንቃ ቀዶ ህክምና አገልግሎቱም በኢትዮጵያውን ሀኪሞች፣ የሰመመን ባለሙያዎችና ነርሶች ይሰጣል። የባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ ታሳቢ በማድረግ ከተለያዩ ሆስፒታሎች ለተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች /team cleft/ ወይም በከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ላይ በቡድን ሆነው ውጤታማ ቀዶ ህክምና ማድረግ የሚያስችላቸውን ሥልጠና ‹‹ላይፍ ቦክስ›› ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር በቅርቡ ሰጥቷል።
ይህ ሥልጠና ቀዶ ሀኪሞችን፣ የሰመመን ባለሙያዎችንና ነርሶችን ያሳተፈ ሲሆን ሠልጣኞች የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ቀዶ ህክምናን እንዴት በቡድን መሥራት፣ የቡድን መንፈስ ማምጣትና በቀዶ ህክምናው ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደሚችሉ ግንዛቤ የጨበጡበት ነው።
ስማይል ትሬን ከ90 በመቶ በላይ የላንቃና የከንፈር መሰንጠቅ ቀዶ ህክምና የሚያደርገው ለህፃናቶች ሲሆን ህፃናት የራሳቸው የሆነ የሰውነት አወቃቀር ያላቸው በመሆኑ የህፃናቱን የቀዶ ህክምናና የሰመመን ህክምና የራሱ ጥንቃቄ አለው። ለዛም ነው ቀዶ ህክምናው ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲሰጥ የኢትዮጵያውያን የጤና ባለሙያዎችን አቅም በየጊዜው ለማሳደግ ሥልጠና የሚሰጠው።
እንደ ዶክተር ቤቴል ገለፃ በከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ምክንያት በህፃናት ላይ ተደራራቢ ችግሮች ይፈጠራሉ። ከነዚህ ውስጥ አንዱ የአመጋገብ ችግር ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ በተለይ የላንቃ መሰንጠቅ ያለባቸው 60 ከመቶ የሚጠጉ ህፃናት ህክምና ሳያገኙ ይሞታሉ። ከዚህ ችግር አንፃር ህፃናቱ የተሟላ የከንፈርና የላንቃ ህክምና ያስፈልጋቸዋል። የሥነ ምግብ አገልግሎትም እንዲሁ ለህፃናቱ ያስፈልጋል።
ህፃናቱ ላንቃቸው ክፍት ሆኖ ሲዘጋ ወይም በቀዶ ህክምና ወደነበረበት ሲመለስ ንግግራቸው ስለሚቀየር የንግግር ህክምናም ያስፈልጋቸዋል። ላንቃቸው ክፍተት ስለነበረው የጥርሳቸው አቀማመጥ ትክክል አይሆንም። ስለዚህ የጥርስ ህክምናም ይሰጣቸዋል። እንዲሁም ከእንዲህ አይነት መሰል አፈጣጠር ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮች በማህረሰቡ ዘንድ መገለልና መድሎኦም ጭምር ስለሚያስከትሉ የማህበራዊና የሥነ ልቦና ህክምናም ጭምር ይፈልጋሉ። ስለዚህ ቀዶ ህክምናው ብቻ በቂ አይደለም ማለት ነው።
ከዚህ አንፃር ስማይል ትሬን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሥነ ምግብ ህክምና በሁለት ሆስፒታሎች እንዲሰጥ አድርጓል። በዚህ ዓመት ደግሞ በተጨማሪ አምስት ሆስፒታሎች ውስጥ ህክምናው እንዲሰጥ ያደርጋል። የንግግር ክህሎት ደግሞ ሁለት ሆስፒታሎች ላይ እየተሰጠ ይገኛል። የጥርስ አቀማመጥ ህክምናም በአንድ ሆስፒታል ላይ ይሰጣል። የሥነ ልቦና ህክምናም በተመሳሳይ በአንድ ሆስፒታል ላይ እየተሰጠ ይገኛል።
ዶክተር ቤቴል እንደሚያስረዱት በኢትዮጵያ ከላንቃና ከንፈር መሰንጠቅ ጋር የተያያዘ ችግር ያለባቸው ህፃናት ቁጥር ከፍተኛ ነው ተብሎ ይገመታል። ካለው ከፍተኛ ቁጥር አንፃር ግን በሚፈለገው ልክ የቀዶ ህክምና አገልግሎቱን ለማግኘት ህፃናት ወደ ጤና ተቋማት አይመጡም። እናቶችም በዚህ ችግር ምክንያት ከፍተኛ ጫና ውስጥ ይገባሉ።
የከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ በህክምና የሚስተካከል አይመስላቸውም። ጡት ማጥባት አይችሉም። ልጃቸውን መመገብ ይቸገራሉ። ልጃቸው ትንታ ያጋጥመዋል። የሚፈለገውን መጠን ያህል ጡት አይጠባም። ከዚህ አንፃር የህፃኑ ክብደት ይቀንሳል። በዚህና ተያያዥ ምክንያቶች የበርካታ ህፃናት ሕይወት ይቀጠፋል።
ስለዚህ ከመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ብሎም ከሚዲያዎች ጋር መሰራት ያለበት ዋነኛ ጉዳይ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ያለባቸው ህፃናትን አስቀድሞ በመለየት ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ህክምናው እንዳለና የት እንደሚሰጥ ለወላጆች መረጃ መስጠት ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ከተቻለ ህፃናት ሳይጎዱና የሰውነታቸው ክብደት ሳይቀንስ በትክክለኛው ሰአት ቀዶ ህክምና አገልግሎቱን አግኝተው ጤናማ ሆነው ማደግ ይችላሉ።
በሌላ በኩል በዓለም አቀፍ ደረጃ በየሶስት ደቂቃ ከከንፈርና ከላንቃ መሰንጠቅ ጋር ይወለዳል። በእንፃሩ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአምስት ደቂቃ አንድ የከንፈርና ላንቃ ቀዶ ህክምና ይሠራል። ከችግሩ ስፋት አንፃር ብዙ ቀዶ ህክምናዎችን መሥራት ይጠበቃል። ቀዶ ህክምናውን ያላገኙና አገልግሎቱን የሚጠባበቁትን ህፃናትንም መለየት ያስፈልጋል።
በአለርት ሆስፒታል የፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ሃኪም ዶክተር ይገረሙ ከበደ በከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ቀዶ ህክምና ዙሪያ ለቀዶ ሃኪሞች፣ ለነርሶችና ለሰመመን ባለሙያዎች በዓመት ሁለት ጊዜ ሥልጠና ይሰጣል። ማንኛውም የቀዶ ህክምና ከአደጋ ነፃ አይደለም። ስለዚህ የዚህ /team cleft/ ሥልጠና ዋና ሃሳብ የከንፈርና የላንቃ ታካሚዎችን ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ቀዶ ህክምና አድርጎ ከህክምና ተቋም እንዲወጣ ማድረግ ነው። ይህም እያንዳንዱን የቀዶ ህክምና ሂደቶችን መጠበቅን ያካትታል።
አንድ ቀዶ ህክምና የሚያደርግ ታካሚ ከቀዶ ህክምና በፊት፣ በቀዶ ህክምና ወቅትና ከቀዶ ህክምና በኋላ ምን አይነት ጥንቃቄ እንደሚደረግለትም ነው የዚህ ሥልጠና ዋነኛ ፅንሰ ሃሳብ። በዚህ የቀዶ ህክምና ወቅት ምን አይነት ችግሮች ሊገጥሙ እንደሚችሉና እንዴት ከነዚህ ችግሮች መውጣት እንደሚቻል ሠልጣኞች ግንዛቤ ወስደዋል። በቡድን ሥራ የቀዶ ሀኪሞች፣ ነርሶችና የሰመመን ባለሙያዎች የከንፈርና ላንቃ ቀዶ ህክምናውን አፅንኦት ሰጥተው እንዲሠሩ የሚያስችል ሥልጠና ነው።
የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ በተፈጥሮ በእርግዝና ወቅት የሚከሰትና አብሮ የሚወለድ ችግር ነው። በፅንስ አድገት ወቅት የላንቃ ወይም የከንፈር ክፍል በጊዜው መግጠም እያለበት ሳይገጥም ሲቀር ክፍተት ይፈጠርና የከንፈር ወይም የላንቃ መሰንጠቅ ተፈጥሮ ከዚህ ጋር ህፃኑ አብሮ ይወለዳል።
የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ዓለም አቀፋዊ ቢሆንም በአፍሪካ ይበልጥ ጎልቶ ይታያል። በኢትዮጵያም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህፃናት ከከንፈርና ከላንቃ መሰንጠቅ ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዳሉባቸው ይነገራል። ችግሩ በደምብ ታውቆ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ቀዶ ህክምና አገልግሎት መሰጠት የተጀመረውም ካለፉት አስራ አምስትና ሃያ ዓመታት ወዲህ ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ይህን የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ቀዶ ህክምና አገልግሎት በአብዛኛው የሚሰጡት የፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ሀኪሞች ናቸው። ቀደም ሲልም እንዲህ አይነቱ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ቀዶ ህክምና ይሠራል ተብሎ አይገመትም። ስለዚህ እንደማንኛውም ህመም አብዛኛው ወላጅ ዝም ብሎ ነበር ልጁን ወደ ሆስፒታል ለማሳከም ይዞ የሚሄደው። በጊዜው የቀዶ ህክምና ሥልጠናው በተሻለ ሁኔታ ስለማይሰጥ አንዳንድ ጊዜ ከእውቀት ጉድለትም ቢሆን ዝም ብለው የላንቃና የከንፈር መሰንጠቁን ለማያያዝ የሚሞክሩ አሉ።
አሁን ግን ከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ቀዶ ህክምና በፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና ካሪኩለም ውስጥ የተካተተ ነው። ቀዶ ሀኪሞችም ይህን ሥልጠና ሲያጠናቅቁ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ቀዶ ህክምና አቅም ይገነባሉ። ባለፉት ሃያ ዓመታትም በርካታ ኢትዮያውያን ሀኪሞች በዚህ የከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ቀዶ ህክምና ሠልጠነዋል። ይህም የቀዶ ህክምና አገልግሎቱን በብዙ ቦታዎች ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል።
እንደ ዶክተር ይገረሙ ማብራሪያ በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡ ከከንፈርና ከላንቃ መሰንጠቅ ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር እየጠረዳ መጥቷል። በፊት ግን ከዚህ ችግር ጋር በተያያዘ ህፃናት ሲወለዱ እንደፈጣሪ ቁጣ ቆጥረው ልጃቸውን እስከመግደል ወይም ደግሞ እስከመደበቅ የሚደርሱ ነበሩ። በዚህም ምክንያት በታማሚው ላይ የሚደርስ መድሎኦና መገለል አለ። የሥነ ልቦና ጫናም ይኖራል።
በህክምናው በኩል ከሚታዩ ችግሮች መካከል ደግሞ አንዱ ህክምናው በአብዛኛው አዲስ አበባ የሚሰጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በገጠር አካባቢዎች የሚገኙና የዚህ ችግር ሰለባ ለሆኑት ተደራሽ አለመሆን ነው። በዚህ የተነሳ በወላጅም ሆነ በታካሚው በኩል የተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ጫናዎች ይኖራሉ። ወላጆችም ካለባቸው ችግር የተነሳ ወደከተማ መጥተው ልጆቻቸውን የማሳከም እቅድ የላቸውም።
ከዚህ አንፃር ስማይል ትሬን የተሰኘው ድርጅት ለነዚህ በገጠር አካባቢ ላሉና ለህክምናው ተደራሽ ላልሆኑ የህብተሰብ ክፍሎች የትራንስፖርት፣ የምግብና የህክምና ወጪ ችሎ በአዲስ አበባ ህክምናውን እንዲገኙ ያደርጋል። በዚህም በተወሰነ መልኩ ለነዚህ ዜጎች የህክምናው በር ተከፍቷል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም