ከ100 ሺህ ሔክታር በላይ አሲዳማ መሬትን በማከም ምርታማነትን የማሳደግ ንቅናቄ ተጀመረ

አዲስ አበባ፡- ከ100 ሺሕ ሔክታር በላይ አሲዳማ መሬትን በማከም ምርታማነትን የማሳደግ ንቅናቄ በመላ ሀገሪቱ ተጀምሯል።

የ2016/17 ምርት ዘመን አሲዳማ መሬትን ለማከም የሚረዳ የግብርና ኖራ አቅርቦትና ስርጭት ሀገራዊ ማስጀመሪያ የንቅናቄ መርሐ ግብር ትናንት ተካሂዷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በመርሐ ግብሩ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ የሀገር ሕልውና የብዙ ጉዳዮች ድምር ውጤት ቢሆንም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ደግሞ የብዙ ችግሮች መፍትሔ ነው ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኑሮ ውድነት መቀነስ አጀንዳ ሲነሳ ምርትና ምርታማነት ላይ ትኩረት ማድረግን እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፤ አጠቃላይ የአገር ኢኮኖሚና እድገት የሚመጣው ምርትና ምርታማነትን ማረጋገጥ ሲቻል ነው ብለዋል።

ምርትና ምርታማነት ሀገራዊ የሕልውና ጉዳይ መሆኑን አብራርተው፤ ምርታማነት ሲረጋገጥ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሱ በርካታ ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል አስታውቀዋል።

ምርታማነት ጉዳይ ሀገራዊ አጀንዳ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከድህነት አዙሪት ውስጥ በመውጣት ራሳችንን እንቻል ሲባል ምርትና ምርታማነትን በማረጋገጥ ጭምር ነው ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የአፈርን ጤናማነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።

እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የአፈር ጤናማነት ካልተረጋገጠ ምርት ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ፤ እንደ ኖራ ባሉ የተለያዩ አማራጮች አሲዳማ አፈርን መከላከል ይገባል። ኖራ ርካሽና በቅርበት መገኘት የሚችል የግብርና ግብዓት በመሆኑ፤ ምርትን ለመጨመር የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ ኖራን ለአሲዳማ መሬት ማከሚያነት በመጠቀም ምርታማነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

ይህን እውን ማድረግ የሚቻለው በመደማመጥ መንፈስ በመሥራት፤ የተሟላ ዕቅድ በማዘጋጀትና ሥራን በዲሲፕሊን በመፈጸም ሙያተኛና አርሶ አደሩ ጋር መድረሱን በማረጋገጥ ነው ብለዋል።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ባለፉት ዓመታት በምርምር ተቋማት በግብርና ኤክስቴንሽን ሠርቶ ማሳያ እንዲሁም በተለያዩ ፕሮጀክቶች ሲከናወኑ በነበሩ ሥራዎች አሲዳማ አፈርን በግብርና ኖራ በማከም የሰብል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደተቻለ አስታውቀዋል። የማስጀመሪያ የንቅናቄ መርሐግብር በግብርና ኖራ 100 ሺህ ሄክታር መሬት ለማከም ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል።

የግብርና ኖራ የተጨመረባቸው ማሳዎች ከፍተኛ የምርት ጭማሪ ማሳየታቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ለአብነትም ስንዴ 71 በመቶ፣ ገብስ መቶ በመቶ፣ በቆሎ 28 በመቶ፣ እንዲሁም ባቄላ 88 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ አሲዳማ አፈርን ለማከም የሚያስችል ከፍተኛ የኖራ ክምችት እንዳለ በማዕድን ሚኒስቴር በኩል መረጋገጡን ጠቁመዋል። የኖራን አቅርቦት ከማሻሻል አንጻር ክልሎች ካላቸው ውስን አቅም ጎን ለጎን የሲሚንቶ ፋብሪካዎች አምርተው ማቅረብ እንዲችሉ መግባባት ላይ እንደተደረሰም ጠቅሰዋል።

የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመላክተው፤ እየታረሰ ካለው የመሬት ሽፋን 43 በመቶ በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ ነው። ከዚህ ውስጥ 28 በመቶ በጠንካራ አሲዳማነት የተጠቃ ሲሆን፣ ይህም በአጠቃላይ ከሚታረሰው መሬት ሦስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር ይሸፍናል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን መጋቢት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You