አዲስ አበባ፣ ወቅታዊነትን መሰረት በማድረግ በሀገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ችግሮችን በመፍታት አንድነትን ለማጠናከር መንግሥትና ህዝብ የየራሳቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው የጨፌ ኦሮሚያ ጽህፈት ቤት ባዘጋጀው 13ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ውይይት ተሳታፊዎች አስታወቁ፡፡
ጽህፈት ቤቱ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ የክልሉ የተለያዩ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች፣ አመራሮች፣ አባገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር ትናንት በኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ባካሄደው ውይይት ላይ የተሳተፉ እንደገለጹት፤ በተለያዩ ሀገሪቷ አካባቢዎች የተፈጠሩት መፈናቀሎች፣ ግድያና ሁከት ዘላቂ መፍትሄ አግኝቶ ህዝቡ ወደ ቀደመ ሰላማዊ ኑሮው እንዲመለስና የቆየ ኢትዮጵያዊ አንድነቱ እንዲጠናከር መንግሥትና ህዝብ የየራሳቸውን ኃላፊነት በመወጣት መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
የኦሮሚያ የሥነ ምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን ቡድን መሪ አቶ ጋሩማ ነፈባሳ በሰጡት አስተያየት የቋንቋና የባህል ልዩነት ካልሆነ የኢትዮጵያ ህዝቦች በደም የተሳሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ወቅታዊነትን ተከትሎ የተፈጠረው ችግር ለዘመናት አንድ የሆነን ህዝብ ለከፋ ችግር መዳረግና አንድነቱ እንዲሸረሸር ማድረግ እንዳልነበረበት ገልጸዋል፡፡ችግሩ ቀጥሎ የከፋ ሁኔታ ላይ ሳይደርስ የፌዴራል፣ የክልሉ መንግሥትና ህዝቡ የጋራ መፍትሔ መፈለግ እንዳለባቸው፤ በተለይም መንግሥት ተከታታይነት ያለው ውይይት ከህዝቡ ጋር በማድረግ ችግሩን መፍታት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ውይይቱ ወቅታዊና አስፈላጊ እንደሆነ የገለጹት የሀገር ሽማግሌ አቶ ቶለሳ ኪሼ ተፈቃቅረውና ተከባብረው በኖሩ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች መካከል መፈጠር ያልነበረበት ችግር ተፈጥሮ ማየታቸው እንዳሳዘናቸውና የችግሩ መንስኤም ተለይቶ ህዝብ ወደቀድሞ ሰላሙ እንዲመለስ መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ ሁሉም የየድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ፤ በተለይ ኦሮሞ የተበደለንና በዳይን በማስማማት ቂምና ጥላቻ እንዲወገድ ጥሩ የግጭት መፍቻ ሥርዓት እንዳለውና ወገኑን አቅፎ በመኖር የሚታወቅ በመሆኑ መፍትሔ መስጠት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
የጨፌ ኦሮሚያ አፈጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት፤ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው ውይይት ብዝኃነትን የበለጠ የሚያጠናክሩና አንድነትን የሚያደምቁ ሥራዎችን ለመሥራት ሁሉም የየራሱን ድርሻ እንዲወጣ ለማስቻል ሲሆን፣ ጥላቻና ቅራኔን በማስቀረት በህዝቦች አንድነት ላይ ክልሉ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከተለያዩ የመንግሥት አመራሮችና የሃይማኖት አባቶችን ያሳተፈ ቡድን በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ከህዝብ ጋር ውይይት መካሄዱንና የተጀመረው ሥራም እንደሚጠ ናከር ገልጸዋል፡፡
የጨፌ ኦሮሚያ የመንግሥት ኮሙኒኬሽንና የመረጃ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ደምሴ በሀገሪቱ ልዩ ልዩ አካባቢዎች ያጋጠሙ ችግሮችና ችግሮችን ለመፍታት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ለተሳታፊዎቹ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፣ በተለይም የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የህዝቡን ባህላዊ እሴት ሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባ፣ በመንግሥት የሚፈታውንም በመለየትና በመቻቻል ችግሮችን መፍታት እንደሚያስ ፈልግ፣ ሰላም ያላትን ዋጋ በምሳሌ በማጣቀስ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ለምለም መንግሥቱ