ኢትዮጵያ ብዙ ታሪካዊ፤ ባህላዊና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስቦች አሏት። ይሁን እንጂ፤ የሆቴል፤ የመንገድ፤ የመብራትና መሰል ለቱሪስት አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶች አለመሟላታቸው የቱሪዝምን ፍሰት መጠንና ገቢውን ጠፍረው ይዘውታል። ይህች ምድር የአክሱም ሃውልቶች፤ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፤ የፋሲል ግንብ፤ የጀጎል ግንብ፤ የኮንሶ ባህላዊ እርከን ስራ፤ የሰው ልጆች መነሻ ሆና የምትቆጠረው ሉሲ የተገኘችበት የታችኛው የአዋሽ ሸለቆ፤ የሰሜን ተራሮች ፓርክ፤ የሶፍ ኦመር ዋሻና ሌሎችም በተባበሩት መንግስታት የባህል፤ የትምህርትና የሳይንስ ማዕከል በዓለም ቅርስነት ያስመዘገበች አገር ናት። እነዚህ ሁሉ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብቶች ናቸው፡፡
አቶ ስንታየሁ ወርቁ በሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የምግብና መጠጥ መስተንግዶ አገልግሎት ትምህርት ክፍል ኃላፊ ናቸው።በኢንስቲትዩቱ ለአራት ዓመታት አስተምረዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሆቴል ማኔጅመንት፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በህዝብ አስተዳደር ይዘዋል።በኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው እያደገ ያለና ብዙ የስራ ዕድል እየፈጠረ ቢሆንም፤ ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር ገና ብዙ ይቀረዋል።ይህን በጅምር ያለ ኢንዱስትሪ የግሉ ሴክተርም ሆነ መንግስት ተባብረው ማሳደግ ይኖርባቸዋል።ምክንያቱም የቱሪዝም ገቢ ባደገ ቁጥር ህብረተሰቡም ሆነ መንግስት ተጠቃሚ ይሆናሉ።ሰፊ የስራ ዕድልም መፍጠር ይቻላል ይላሉ፡፡
በተለይ ይላሉ አቶ ስንታየሁ፤ የሆቴሉ መስክ የመስተንግዶ ጥራትና ቅልጥፍና ውስንነት ይታይበታል።በኢትዮጵያ የሆቴል ተቋማት ገና አላደጉም።በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ታጭቀው ነው የሚገኙት፤ ሆቴሎቹ በቂ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ስለሌላቸው ደንበኞች ሲቸገሩ ይታያሉ።እነዚህን ሆቴሎች አገልግሎታቸውን በጥራትና በቅልጥፍና በማቅረብ ደንበኞቻቸውን ማርካት ቢችሉ ለቱሪስት ፍሰት መጨመር ከፍተኛ ድርሻ ይኖራቸዋል የሚል እምነት አላቸው፡፡
ሌላው፤ በሆቴል ዘርፍ ያሉ ሰራተኞች የአቅምና የትምህርት ችግር ጎልቶ ይታይባቸዋል።ስለዚህ የሙያተኞችን አቅም በመገንባትና በሆቴሎች በቂ ቦታ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ መንግስት ዘርፉን ሊደግፈው ይገባል የሚል ሀሳብ አላቸው።ምክንያታቸውም የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ሲያስገኝ በመንግስት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው የወጪ ንግድ ከሁለት ነጠብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ያልዘለለ ገቢ እንደሚገኝበት ያወሳሉ፡፡
በተለይ መንግስት ለሆቴልና ቱሪዝም የትምህርት ተቋማት የሚያስፈልጉትን ቁሳቁሶች በማሟላትና ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት እንዲሰጡ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ስራ መስራት አለበት። የመምህራኑንም አቅም ማጎልበትና በውጭ አገር የተሻሉ ተሞክሮዎችን ቀስመው የሚመጡበትን አሰራር ማመቻቸት አለበት።ለምሳሌ፤ እነ ኬንያ፤ ታንዛኒያና ደቡብ አፍሪካ በቱሪዝም መስክ አንቱታን የተጎናጸፉ ተጠቃሽ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዳላቸው ይናገራሉ። ለዚህም ነው በቱሪዝም ፍሰት ረገድ ከአፍሪካ ቀዳሚውን ቦታ ሊይዙ የቻሉት ባይ ናቸው፡፡
ስለዚህ አሉ አቶ ስንታየሁ፤ በኢትዮጵያ በቱሪዝምና በመስተንግዶ ዘርፍ ትምህርት የሚሰጡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን አቅም ማጎልበት ቱሪስቶች ሲመጡ በሆቴሎች ውስጥ ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች እንዲኖሩ ያደርጋል።ቱሪስቶችም በሆቴሎችና በቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች በሚሰጡ አገልግሎቶች እርካታ እንዲያገኙ ያስችላል።የቆይታቸውንም ጊዜ እንዲያራዝሙ ይገፋፋል።ይህ ደግሞ አገሪቱ ከቱሪዝም የምታገኘውን ገቢ ያሳድግል።የቱሪዝምንም ፍሰት ይጨምራል፤ የስራ ዕድልንም ያሳድጋል ሲሉ ያብራራሉ።
የኢትዮጵያ ቱሪዝምና ሆቴል ስራ ኢንስቲትዩት በአሁኑ ጊዜ አጫጭር ስልጠናዎችን ጨምሮ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ እያስተማረ ነው የሚሉት የኢንስቲትዩቱ ኃላፊ፤ ለተግባራዊ ትምህርት መስጫ የሚሆኑ ቁሳቁሶች አሉት።ነገር ግን ኢንስቲትዩቱ እንደ አርአያ የሚቆጠር ዘመናዊ ሆቴል ሊኖረው ይገባል።ምክንያቱም ዛሬ በዓለም ላይ ሆቴሎች በጣም ዘመናዊ እየሆኑ ነው።
በእነዚህ ሆቴሎች የተጠቀመ ሰው ወደ ኢትዮጵያ ታሪካዊና የተፈጥሮ ስፍራዎችን ለመጎብኘት ሲመጣ የውጭ ሆቴሎች ከሚሰጡት አገልግሎት ተመጣጣኝ አገልግሎት ማግኘት ይፈልጋል።ስለዚህ፤ በሆቴሎች ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስልጠና ያገኘ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ያስፈልጋል።ለእነዚህ ተቋማት ለየት ያለ ድጋፍ አድርጎ በኢንዱስትሪው የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት ይቻላል ይላሉ፡፡
እንደ አቶ ስንታየሁ ገለጻ፤ ኢንስቲትዩቱ ባለው አቅም ተማሪዎቹ ከሌሎች አቻ ተቋማት የተሻለ እውቀትና ክህሎት ይዘው እንዲወጡ ያደርጋል። ከሆቴሎች ጋር በመተባበርም ሄደው የተግባር ስልጠና የሚያገኙበትን ሁኔታ ያመቻቻል።በኢንስቲትዩቱ ውስጥም በቂ የተግባር ስልጠና የሚያገኙበት በመሆኑ በቂ እውቀትና ክህሎት ጨብጠው ይወጣሉ።በቋንቋ ረገድም እግሊዘኛ፤ ፈረንሳይኛ፤ ጀርመንኛና በቅርቡ ደግሞ የቻይና ቋንቋ ያስተምራል። ሆኖም፤ ከኢንስቲትዩቱ የሚወጡ ተማሪዎች በጣም ውስን በመሆናቸው ለአገሪቱ ቀርቶ ለአዲስ አበባ ሆቴሎችና አስጎብኝ ድርጅቶች በቂ የሆነ የሰው ኃይል ማቅረብ አልተቻለም ፡፡
ወደፊት የሆቴል ኢንዱስትሪው በኢትዮጵያ እጅግ ጥሩ ተስፋ አለው የሚል እምነት አለው የሚሉት አቶ ስንታየሁ፤ ምክንያቱም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ከተሞች ሆቴሎች እየተስፋፉ መጥተዋል። በፖለቲካው ረገድም ለውጥ በመምጣቱ አኩርፈው የነበሩ የዲያስፖራ ማህበረሰብ ይበልጥ የሚሳተፉበት ኢንዱስትሪ ይሆናል። ስለዚህ የሆቴል ግንባታ ከአሁኑ በላይ የሚስፋፋበት ይሆናል የሚል ተስፋ አላቸው።
የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገራት ቱሪስቶችን ፍሰት ለማሳደግ የተሻለ አገልግሎት መስጠት ያስፈልጋል።በተለይ፤ በሆቴል ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች በሙያው የሰለጠነ፤ የታነጸና ስነ ምግባር ያለው የሰው ኃይል ቀጥረው ማሰራት ይጠበቅባቸዋል ይላሉ።ጥቅሙም ጥራትና ፈጣን አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የቱሪስቱን የቆይታ ጊዜ ማራዘም ያስችላል።ገቢንም ያሳድጋል ሲሉ በክህሎትና በዕውቀት የተሻለ ባለሙያ የሚያስገኘውን ጥቅም ያብራራሉ፡፡
አብዛኛዎቹ ከሆቴልና ቱሪዝም ኮሌጆች ተመርቀው የሚወጡት ተማሪዎች የተግባር የሙያ ብቃታቸው ውስን እንደሆነ የሚገልጹት በቢሾፍቱ ከተማ የፔራሚድ ሪዞርት ባለቤት አቶ ዳንኤል በዳኔ፤ ይህን ችግር ለመፍታትም ሆቴሎች በራሳቸው የማሰልጠኛ ማዕከል በማቋቋም በሆቴል መስተንግዶ፤ በምግብ ዝግጅት፤ በቤት አያያዝና አጠባበቅ የአጭር ጊዜ ስልጠና ሰጥተው እንደሚቀጥሩ ይናገራሉ።
ይህም የሆቴሎችን ትርፋማነትና የደንበኞችን እርካታ እንዲጨምር አድርጓል ነው ያሉን፤ ከ200 በላይ ሰራተኞች ያሉት ፔራሚድ ሪዞርት በአሁኑ ጊዜ በ260 ሚሊዮን ብር ወጪ የማስፋፊያ ስራ እየሰራ ይገኛል።አዲሱ ሆቴል 80 የመኝታ ክፍሎች፤ የእንግዳ መቀበያ ቤት አለው።የልጆች ማቆያ ቤትና መጻሕፍት ቤትም እንዳለው አቶ ዳንኤል ነግረውናል።ይህም በዘርፉ ከፍተኛ ገቢ እንደሚገኝበት ማሳያ ነው፡፡
ቢሾፍቱ የቱሪዝም መዳረሻ ከተማ ናት። እርግጥ ነው እንደ ቢሾፍቱ ባሉ ከተሞች የሆቴል ግንባታ እየተስፋፋ ይገኛል።በከተማዋ ባሉ የተፈጥሮ ሀይቆችና ለአዲስ አበባ ከተማ ቅርብ ከመሆኗ አኳያ ትልቅ የመዝናኛ ከተማ መሆን ስትችል የሆቴል ዘርፉ ብዙ ትኩረት ሳይሰጠው በመቆየቱ ገና ጅምር ላይ ነው።በአሁኑ ጊዜ በከተማዋ የቱሪስት ፍሰቱ እየጨመረ በመምጣቱና ገቢውም እያደገ በመሄዱ ትልቅ ተስፋ እየታየ መጥቷል።
በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኙ ሁሉም ሪዞርቶች የማስፋፊያ ግንባታ እያካሄዱ እንደሚገኙ አቶ ዳንኤል ገልጸውልናል።እኛም ተመልክተናል።በተለይ ቅዳሜና እሁድ በርካታ ቱሪስቶች ወደ ከተማዋ እየመጡ ናቸው።አዲስ አበባ ከተማም ሆነ ሌሎች ከተሞች የተሻሉ የሆቴል ባለሙያዎችን የደመወዝ ጭማሪ በማድረግ ከአንዱ ሆቴል ወደ ሌላው የመውሰድ አዝማሚያ ይታያል።ይህ ችግር በቢሾፍቱም ይታይ ነበር።አሁን ግን የቢሾፍቱ ሆቴሎች ማህበር በመቋቋሙ ችግሩ ተፍትቷል። በሌላ በኩል፤ ከባድ የስነ ምግባር ችግር የታየበትና ከአንድ ሆቴል የተባረረ ሰራተኛ በሌሎች ሆቴሎች እንዳይቀጠር መረጃ እንደሚለዋወጡ ሁሉ አቶ ዳንኤል ነግረውናል።
ወይዘሮ ጸሀይ እሸቱ፤ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ስልጠና አግኝተው በኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት በመስተንግዶና የምግብ ዝግጅት ቡድን መሪ ሆነው ይሰራሉ።የሆቴልና የቱሪዝም ዘርፍ በኢትዮጵያ እድገት እያሳየ መምጣቱን፤ ለባለሙያዎችም ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠሩን ይመሰክራሉ።በቀጣይም ዘርፉን ለማሳደግ ጥራት ያለውና በተግባር የታገዘ ትምህርት ለሆቴሎች ጥራት ማደግና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት መሰረት በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል የሚል መልዕክት አላቸው፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ5/2011
ጌትነት ምህረቴ