የመንገድ መዘጋት ለታክሲዎች ያመቻል!

ሰሞኑን በብዙ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የመንገድ ማስፋፊያ ሥራዎች እየተሠሩ ስለሆነ መንገዶች ተቆፋፍረዋል። በዚህም ምክንያት የትራንስፖርት መጉላላት ተፈጥሯል። በእንዲህ አይነት አጋጣሚዎች የእኛ ሕዝብ ሕገ ወጥ ሥራ ለመሥራት ሰበብ ይፈልጋል። ‹‹የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል›› እንዲሉ፤ በየሰበብ አስባቡ ዋጋ የሚጨምሩት ባለታክሲዎች ከሰሞኑ ምንም አይነት አግባብነት የሌለው የዋጋ ጭማሪ እያስደረጉ ነው።

አንድ የሥራ ባልደረባዬ የነገረኝን ገጠመኝ እንደ ማሳያ ላድርግ። ከላምበረት መነኻሪያ ወደ አራት ኪሎ ለመምጣት ታክሲ ሲያጣ በአውቶብስ ተራ ታክሲ ገባ። ከላምበረት አውቶብስ ተራ የተለመደው የታክሲ ሒሳብ 25 ብር ነው። ረዳቱ 30 ብር ነው የምትከፍሉት አለ። ለምን? ሲባል አራት ኪሎ መንገድ እየተቆፋፈረ ስለሆነ አለ። ‹‹እና ቢቆፋፈር ርቀቱ ጨምሯል? ወይስ ዳገት ተጨምሮበታል?›› ተብሎ ሲጠየቅ በምኒሊክ ሆስፒታል እንደሚሄድ ተናገረ። ይሄ መስመር ማለት ግን ወደ አውቶብስ ተራ ለመሄድ ብዙ ጊዜ የሚጠቀሙት (እንዲያውም እንደ አቋራጭ የሚጠቀሙት) መንገድ ነው። ግን ማሳበቢያ ይፈለጋል። በዚያው እየተገነባ ባለው መንገድ ላይ እየሄዱ ልክ እንደተለየ ነገር ያዩታል። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ደንብ አስከባሪዎች ምንም አይሏቸውም። ባለታክሲዎችም ሕግ አያከብሩም።

ልብ ብላችሁ ከሆነ፤ ተራ አስከባሪውን ለማናደድ ብለው ወዳላሰቡበት መስመር ይሄዳሉ። ለምሳሌ ከመገናኛ አራት ኪሎ ለመሄድ ያሰበው ታክሲ፤ ተራ አስከባሪውን ያናደደ መስሎት ‹‹አልሄድም›› ይላል፤ ወይም ወደሌላ ቦታ ይጠራል። ሰው ረጅም ሰልፍ ተሰልፎ እያዩ በድብቅ መጫን ያስደስታቸዋል። ከሰልፉ ላይ ቢጭኑ ምን ችግር አለው? ለእነርሱስ ቶሎ ለመሙላት በሥርዓት የተሰለፈው ሰው አይሻልም? ይሄ ብዙ ቀን የታዘብኩት ነው። ለምሳሌ ከአራት ኪሎ ወደ መገናኛ ለመሄድ ሥላሴ ጋ ረጅም ሰልፍ ካለ ሰልፉ ጋ አይጭኑም። ሰልፉን አልፈው ሄደው ይጭናሉ። ከሰልፉ ላይ አንዴ ከመሙላትና አንድ አንድ ሰው ከማንጠባጠብ የቱ ይሻል ነበር?

አንዳንዶቹ ደግሞ ቅርብ ቦታ ይጠራሉ። ለምሳሌ ከአራት ኪሎ መገናኛ መሄድ እየቻሉ ‹‹ቀበና›› እያሉ ይጠራሉ። ቀበና ካስገቡ በኋላ ግን የመገናኛ ሒሳብ ተቀብለው ይሄዳሉ፤ ወይም ከቀበና እንደ አዲስ የመገናኛ ይቀበላሉ። የዚህ ታክሲ አሠራር ጥቅም ሊገባኝ አልቻለም። ምናልባት ሰልፍ ሳይዙ የቆሙ ሰዎችን ለመጥቀም ይሆን? እንደ እኔ ተስፋ ቆርጠው በእግር ለመሄድ ላሰቡት ተብሎ ይሆን? የታክሲ ተራ አስከባሪውስ ይሄን ምስጢር ያውቅ ይሆን? በዚህ ሁሉ ውስጥ ባለታክሲው የሚጠቀመው ነገር ሊገባኝ አልቻለም፤ እንዲያውም የሚባክን ጊዜ ነው ያለው። ቀበና እያለ አንድ አንድ ሰው በማንጠባጠብ ያን ሁሉ ደቂቃ ከማባከን ከሰልፉ ላይ ቢጭን ቶሎ ይሄድ ነበር። ምናልባት ቀበና ከሆነ ለተራ አስከባሪው የምትከፈለዋን 10 (መጠኑን እርግጠኛ አይደለሁም) ብር ለማስቀረት ይሆን? ምክንያቱ እሱ ሳይሆን አይቀርም!

በነገራችን ላይ እነዚህ ነገሮች የሚሆኑት በባለታክሲዎች ጥፋት ብቻ አይደለም፤ በራሳቸው በተራ አስከባሪዎችም ጭምር ነው። የተራ አስከባሪዎች የመከልከል ሥልጣን እስከምን ድረስ እንደሆነ ባላውቅም ባለታክሲዎች እንዲህ አይነት ሥራ መሥራታቸውን ግን በሚገባ ያውቁታል።

እንዲያውም በተራ አስከባሪዎች አስተባባሪነት የሚፈጸም ጥፋት ሁሉ አለ። ለምሳሌ፤ ከመገናኛ ወደ ላምበረት እና 02 የሚጭኑ ታክሲዎች የተለመደው ቦታ ይታወቃል። ዳሩ ግን ይህ የሚሆነው መንገደኛ በሚበዛበት የሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ላይ ብቻ ነው። ከረፋድ 4፡00 አካባቢ በኋላ ታክሲዎች የሚጭኑት ከተለመደው ፌርማታ ውጭ ነው። ይህ ማለት ትራንስፖርት ባለሥልጣን ከፈቀደው ቦታ ውጭ የታክሲ መጫኛ ሲሆን ደንብ አስከባሪ የተባሉት ዝም ይላሉ ማለት ነው። መንገደኛውም ብዙ ርቀት በእግር ለመሄድ ይገደዳል ማለት ነው። ደንብ አለማስከበራቸው ሳያንስ ይባስ ብሎ ‹‹እዚህ መጫን አይቻልም፤ ክልክል ነው›› እያሉ ያልተፈቀደ ቦታ ድረስ ርቀው እንዲሄዱም ያደርጋሉ፤ ይህ የሚስተዋለው ብዙ ጊዜ ከመደበኛ የሥራ መግቢያና መውጫ ውጭ ባለው ነው። ጠዋት ሲጫንበት የነበረ ቦታ ከረፋድ በኋላ የሚከለከልበት ምክንያት ምንድነው? ባለታክሲዎችስ ተሻግረው ስለጫኑ የሚያገኙት ጥቅም ምን ይሆን? ሒሳቡ ተመሳሳይ ነው። ምናልባት የሚያገናኛቸው ጥቅም ይኖር ይሆን?

ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ችግር የሆነው ሰበብ እየፈለጉ ዋጋ መጨመር እና ለዋጋ ጭማሪ ሲሉ መደበኛውን መስመር ትተው ውስጥ ለውስጥ ረጅም ጊዜ የሚያባክኑት። የሥራ ቦታዬ አራት ኪሎ ስለሆነ ምሳሌዎቼ ከአራት ኪሎ ይበዛሉ። ለምሳሌ ከአራት ኪሎ መገናኛ ለመሄድ መንገድ ተዘጋግቷል በሚል ሰበብ ‹‹በ…. ነው የምንሄድ›› ብለው ይናገራሉ። መንገደኛውም አማራጭ ስለሌለው ከታሪፍ ውጭ የተባለውን ከፍሎ ይገባል። ችግሩ ግን ገንዘቡ ብቻ አይደለም። መንደር ለመንደር ሲሽሎከለክ በዋናው መንገድ ቢሄድ ከሚወስደው ሰዓት በላይ ይወስዳል። መንገደኛውም ‹‹በዚያው ይሻል›› ነበር እያለ ከመጉላላት ውጭ አማራጭ የለውም። እንደዚያ መንደር ለመንደር ሲያንከራትት ቆይቶ ዋናው መስመር ሲገባ፤ ከተገነጠለበት ቦታ ብዙም ራቅ ያላለ ይሆናል። ሲሄድ የቆየው ተጨማሪ ኪሎ ሜትሮች ነበር ማለት ነው። በዚህ ሁሉ ውስጥ የብዙዎች ውድ ጊዜ ሲባክን ቆይቷል ማለት ነው።

ይህ አካሄድ ሕገ ወጥ ነው። ምናልባትም የትራፊክ ፖሊስ ለመሸሽም ሊሆን ይችላል። ዋናው ምክንያት ግን ተጨማሪ ለማስከፈል ነው።

እንዲህ በትንሽ ትልቁ ሰበብ የሚፈልጉ ባለታክሲዎች አሁን ደግሞ ሠርግና ምላሽ ሆኖላቸዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ እየተሠራ ያለው የመንገድ ማስፋፋት ሥራ ያን ያህል ጉዞ አስተጓጎለ የሚባል አልነበረም። ዳሩ ግን ሰበብ የሚፈልጉት ባለታክሲዎች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ መጉላላቱን አጣደፉት። ሲፈልጉ በተከለከለ መንገድ ላይ ይሄዳሉ። ሲፈልጉ ደግሞ ያልተከለከለውን መንገድ እንደተከለከለ አድርገው ተጨማሪ ለማስከፈል በሚያመች ሁኔታ ያደርጉታል። በጣም ባስ ሲል ደግሞ ያንኑ መንገድ (መደበኛውን ማለት ነው) አጠገቡ የሆነች ነገር እየተቆፈረች ስለሆነ ብቻ ያለምንም ይሉኝታ ተጨማሪ እናስከፍላለን ይላሉ። ለምን ሲባሉ ያቺን እየተሠራች ያለች ነገር ይጠቅሳሉ። ነገርየው እኮ ከታክሲው ጉዞ ጋር ምንም የማይገናኝ፣ ከተለመደው መዘጋጋት ውጭ ምንም ተጨማሪ ችግር ያልፈጠረ ሊሆን ይችላል።

ስለዚህ ግንባታው ሲሠራ የባለታክሲዎች ነገርም ቁጥጥር ይደረግበት!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You