በዚህ ዘመን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ከሚያሳልጡ መሳሪያዎች መካከል የኢንተርኔት አገልግሎት ቀዳሚውን ስፍራ እየያዘ ይገኛል። የኢኮኖሚ እንቅስቃሴያቸውን በቴክኖሎጂ ያላስደገፉ ሀገራት ከጊዜው ጋር የመራመድ እድላቸውም ጠባብ ነው። በኢትዮጵያም አብዛኛው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከኢንተርኔት ጋር ያለው ቁርኝት ከቀን ወደቀን እየጨመረ ይገኛል።
በከተሞች የእለት ከእለት እንቅስቃሴ አካል እየሆነ ከመጣው የኤ ቲ ኤም የባንክ አገልግሎት ጀምሮ ግብር ለመክፈል፤ ገንዘብ ለማዘዋወር፤ የትራንስፖርት ትኬት መቁረጥን በርካታ የንግድ እንቅስቃሴዎችም ከምርት ማስተዋወቅ እስከ አገልግሎት መስጠት ወደ ኢንተርኔት መጠቀም እየገቡ ናቸው።
አንዳንድ ድርጅቶችም ለራሳቸው የሚያዘጋጇቸውና ኢንተርኔትን የሚጠቀሙ መተግበሪያዎችም ሌላው የኑሮ ማቅለያ፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማሳለጫ ማድረግ ውስጥ ገብተዋል። ዜጎች ቴክኖሎጂ በመጠቀም የእለት ከእለት እንቅስቃሴያቸውን እንዲያቀላጥፉ የሚያስችሉ መተግበሪያዎችን እንዲያስፋፉ፤ በኢትዮ ቴሌኮም በኩልም የኔትወርክ ማስተካከያ እንዲሁም ተደራሽነትና ጥራትን ማስጠበቅ እንደሚገባ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የኢንተርናሽናል አይሲቲ ኮሚሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጋሻው ሽባባው እንደሚያብራሩት፤ የትኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጊዜ ይውሰድ እንጂ ወደ ቴክኖሎጂ መጠቀም መምጣቱ አይቀርም። የኢንተርኔት አገልግሎትን እየተጠቀሙ ኢኮኖሚን በማንቀሳቀሱ በኩል በኢትዮጵያ የተጀመሩ ስራዎች ቢኖሩም፣ እንደ ሀገር ብዙ የሚቀር አለ።
በስፋት ከምናያቸው የባንክና የድርጅቶች የገንዘብ ዝውውር ባለፈ በግለሰብና በተቋም ደረጃ ሊሰሩ የሚችሉ በርካታ ስራዎች እንዳለ አቶ ጋሻው ጠቅሰው፣ እንደ ሀገር እየተሰሩ ያሉና በርካታ ፋይዳ ያላቸው መተግበሪያዎች ከኔትወርክ ችግር ጋር በተያያዘ ተገቢውን አገልግሎት ሲሰጡ አይታይም ይላሉ።
እንደ አቶ ጋሻው ገለጻ፤ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እከሌ ይሄን ፈጠረ፤ ይሄ ድርጅት ይህን የኢንተርኔት አገልግሎት አስጀመረ ሲባል መስማት የተለመደ ቢሆንም በተነገረውና በተባለው ልክ ብዙ ጊዜ አገልግሎት ሲሰጥ ግን አይታይም።
በዚህ ዘመን የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር ለማገናኘት ካለ ኢንተርኔት አይታሰብም። በርካታ ሀገራት ጥሬ ገንዘብ ማንቀሳቀስን እየቀነሱ መጥተዋል፤ ይሄ ተግባር እዚህም የተጀመረ ቢሆንም ዛሬም ድረስ በተገቢው መንገድ እየተጠቀምንበት ነው ለማለት ግን አያስደፍርም ሲሉ ያብራራሉ።
ይሄንን በጣም ማስፋፋት ከተቻለ የውጪ ምንዛሬንም ከጥቁር ገበያ ለመከላከል ይረዳል። በአሁኑ ወቅት ያለውን የጥሬ ገንዘብ ህትመትና ዝውውርም ከመቀነሱ ባሻገር የተገልጋዩን ደህንነት የተጠበቀ እንዲሆን ይጠቅማል ይላሉ።
አቶ ጋሻው እንዳብራሩት፤ በኢትዮጵያ ያልተተገበሩ ነገር ግን ለአስርት ዓመታት ቀሪው ዓለም እየተገለገለባቸው ያሉ መተግበሪያዎች አሉ። እነዚህን በመቅዳትና ከሀገራዊ ሁኔታ ጋር በማቀራረብ መስራትም ይጠበቃል። እነዚህን በስልኮቻችንና በላብቶፖቻችን በመጠቀም ልናገኛቸው የምንችላቸውን አገልግሎቶች ለመጠቀም ግን በሀገሪቱ ያለው የኢንተርኔት አገልግሎት ምቹ ነው ለማለት አያስደፍርም።
በመሆኑም ዋይፋይ እንደሌሎች ሀገራት በየትኛውም ቦታ በቀላሉ ማግኘት እንዲቻል ኔትወርኮችን ማስፋፋት ይጠበቃል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቱን የሚያቀርብበት ዋጋውም መቀነስ ይጠበቅበታል። አሁን ካለው አምስት ስድስት እጥፍ ዋጋ በመቀነስ ከህዝቡ አንድ አምስተኛውን ማስጠቀም ቢቻል ከብዛት አሁን ከሚያገኘው የተሻለ ገቢ ተቋሙም ማግኘት የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠርም ይቻላል።
እንደ ሀገር ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቱን የተሻለ እንዳያደርግ ሌላ ደርጅት አለመኖሩና ተወዳዳሪ ማጣቱ አንዱ ችግር ነው የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፣ በሌሎች ሀገራት አገልግሎቱን ከሚያቀርቡ ተቋማት ጋር የሚደረጉ ስምምነቶች እንዳሉም ይጠቅሳሉ። እነዚህ ስምምነቶች በርካታዎቹ በሀያ አራት ሰዓት ውስጥ ቢበዛ ከአንድ ደቂቃ በላይ መቆራረጥ እንደሌለበት የሚያስገድዱ መሆናቸውን አቶ ጋሻው ይገልጻሉ።
ከዚህ በላይ ከሆነ የደረሰውንም ኪሳራ እያንዳንዱ ተቋም የሚጠይቅበት የህግ አግባብ እንደሚኖር፣ ይህንን ግን በሁለት ምክንያቶች በኢትዮጵያ ማድረግ እንዳልተቻለም ይጠቁማሉ። አንደኛ አገልግሎቱ ቢቋረጥ ተጠያቂ ለማድረግ የተቀመጠ የህግ አግባብ የለም፤ ሁለተኛ አንድ ድርጅት ወይንም ግለሰብ አገልግሎቱ ካልተስማማው ለመቀየር አማራጭ የለውም፤ በመሆኑም በችግር ለመቆየት ይገደዳል ሲሉ ያብራራሉ።
ይህን የሚያስከትለው የተፎካካሪ አለመኖር መሆኑን ጠቅሰው፣ ኤርትራ አራት የሚደርሱ የኢንተርኔት አገልግሎት የሚያቀርቡ ተቋማት በአብነት ይጠቅሳሉ። በመሆኑም ቴሌ አቅሙ እንኳን ከሌለው አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ በግል የመንግስት አጋርነት ለማስፋፋት መንቀሳቀስ አለበት። ባለሀብትንም በየደረጃው ማሳተፍ ይጠበቅበታል ሲሉ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአፕልኬሽን ዴቨሎፕመንት ቡድን መሪ አቶ ጌታቸው ኩመራ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው የተሰራውንና አገልግሎት እየሰጠ ያለውን የመታወቂያ መተግበሪያ ዋቢ በማድረግ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ተገልጋዩን ከወጪ፣ ከጊዜ ብክነትና ከጉልበት ብክነት መታደግ መቻሉን ይጠቅሳሉ። ይሁንና የኔት ወርክ መቆራረጥ የታሰበውን ያህል እንዲጓዝ እንዳላስቻለው ይጠቁማሉ።
ቡድን መሪው እንደሚያብራሩት፤ አዲሱ አገልግሎት እስከ ተጀመረበት ጊዜ ድረስ ተማሪዎች ለምዝገባ፣ ውጤት ለማየት፤ መረጃ ለመለዋወጥ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ በአካል መገኘት ግድ ይላቸው ነበር። ይሄ ደግሞ በተለይ ራቅ ካለ አካባቢ የሚመጡትን ለከፍተኛ ወጪና እንግልት ሲዳርግ የቆየ ጉዳይ ነው።
አዲሱ መተግበሪያ የተማሪዎችን እንግልት ለመቀነስ ከገቡበት ጊዜ አንስቶ ተመርቀው እስከሚወጡ ድረስ በሁሉም ቦታ መቆጣጠር የሚያስችል መታወቂያ ላይ የሚገጠም ሶፍትዌር ነው። ተማሪዎች ይህንን ሶፍት ዌር በመጠቀም ውጤታቸውን ማየት፤ በአካል ሳይገኙ ምዝገባ ማድረግ መምህራን የሚሰጧቸውን ዶክመንቶች በቀጥታ( ኦን ላይን) ማግኘት የሚያስችላቸው ሲሆን፣ ከዩኒቨርሲቲው ግቢ ውጪም በኔት ወርክ እንዲሁም ኢንተርኔት ማግኘት የማይችሉት በአጭር የፅሁፍ መልእክት እንዲገለገሉ የሚያስችል ነው።
የተሰራው ስማርት ዲጂታል መታወቂያ ተማሪው መታወቂያውን ከኪሱ ሳያወጣ በካፌም ሆነ ቤተ መፅሀፍት ሲገባ ለመለየት ያስችላል። የተባረረ ተማሪ፤ ካፌ ተመጋቢ ያልሆነ፤ መፅሀፍ የተዋሰ ባጠቃለይ የተማሪው መረጃ መተግበሪያውን በማየት ማረጋገጥ ይቻላል።
በመምህራኑም በኩል ከሀገር ውጪም ሆነው አስተማማኝ በሆነ መንገድ ዶክመንት ለመላክና ለመቀበል እንዲሁም ውጤት ለማስገባት የሚያስችላቸው ቢሆንም፣ የኔት ወርክ ችግር እነዚህን ሁሉ አገልግሎቶች ለማዳረስ አላስቻለም ሲሉ ያብራራሉ። የኢንተርኔት አቅርቦት በበርካታ ቦታዎች መገኘቱ ጥሩ መሆኑን ጠቅሰው፣ መቆራረጥና መዘግየት ግን አሁንም ያልተቀረፉ ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
እንደ ጌታቸው ማብራሪያ፤ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አርባ ሺህ የሚደርስ ተማሪ አለው ይህንን ሊቆጣጠር የሚችል ሶፍት ዌር ከውጪ ለማስመጣት የሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተሞክሮ እንደሚያሳየው ሰባ ሚሊየን ብር ድረስ ውጪን ይጠይቃል።
መተግበሪያውን የዩኒቨርሲቲው ሰራተኛ በመደበኛ ስራው እንደሰራው ጠቅሰው፣ ለሰርቨር ብቻ አንድ ሚሊየን ብር የማይሞላ መውጣቱን ተናግረዋል። መተግበሪያውን በዚህ መልኩ እውን ማድረግ ቢቻልም የዝግጅቱን ያህል አገልግሎት እየሰጠ አይደለም ይላሉ።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽህፈት ቤት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሪት ጨረራ አክሊሉ በበኩላቸው ተቋሙ አስፈላጊውን ሁሉ እያደረገ አገልግሎቱን በማዘመን ኢኮኖሚውን ለመደገፍ እየሰራ እንደሆነ ይናገራሉ። ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ኢትዮ ቴሌኮም ከሁሉም ተቋማት ጋር መገናኘቱ የግድ መሆኑን ጠቅሰው፣ የአይሲቲ ዘርፉ ብዙ ያልተሰራበት ብዙ ሊሰራ የሚገባውና ለኢኮኖሚውም ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ በቅርበት በትብብርና በአጋርነት እየሰራና አስፈላጊም ሲሆን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ይላሉ።
እንደ ኃላፊዋ ማብራሪያ፤ ተቋሙ ኔትወርክ በማስፋፋት በኩል በርካታ ችግሮች ነበሩበት፤ ህንፃዎች ጣራ ላይ ለመጠቀም አስቸጋሪ ስለነበር በዚህ ኔትወርክ ተደራሽነት እና በጥራት ላይ ውስንነት ነበር። በፋይበር መቆራረጥ ላይ ያለውም ችግር የመቋረጥ ብቻ ሳይሆን የጥራትም የመዘግየትም ችግር ያጋጥማል ።
የኤሌክትሪክ አቅርቦትም አንዱ ማነቆ ነው። ኮር ሳይት የሚባሉትና ለብዙ ሳይቶች መሰረት ከሆኑት ጋር ደግሞ ኤሌክትሪክ ሲጠፋ ችግሩ ሰፊ ይሆናል፤ እነዚህን ሁሉ በጀነሬተር ማድረግ ደግሞ ያስቸግራል።
‹‹ በአሁኑ ወቅት በሞባይል አገልግሎት ረገድ በሀገሪቱ 80 ሚለየን ተጠቃሚ ማስገልገል የሚችል አቅም ቢኖርም አገልግሎቱን እየተጠቀመ ያለው ግን 43 ሚሊየን ብቻ ነው። ኢንተርኔት የምንቀበለው ከጅቡቲ ከኬንያ ነው፤ ይህንን አቅም ለማሳደግ ከሁለቱ ሀገራት ጋር የተጀመሩ ስራዎች አሉ።››ሲሉ ያብራራሉ።
አንዳንድ ጊዜ ድርጅቶች የጠየቁት የኢንተርኔት መጠንና የሚሰጡት አገልግሎት ሳይመጣጠን ሲቀር እንዲሁም ከሙያተኛ አቅም ጋርም በተያያዘ ችግር ሊኖር እንደሚችል ጠቅሰው፣ ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት ፈላጊው ባቀረበው ጥያቄ መሰረት በማቅረብና ችግርም ሲኖር በፍጥነት ተከታትሎ እያስተካከለ እንደሚገኝ ይገልጻሉ። የአንዳንድ ተቋማትን ችግር ለማቃለል የተቋሙ ኃላፊነት ባይሆንም ድጋፍና ስልጠና እንደሚሰጥም ነው የተናገሩት። አንዳንድ ጊዜ ህብረተሰቡ ግንዛቤ ስለሌለው በተለይ ባንኮች አካባቢ በሀይል መቆራረጥ አገልግሎት ሳያገኝ ሲቀር የኔትወርክ ችግር አድርጎ እንደሚወስድም ይገልጻሉ።
የዋጋ ተመንንም በተመለከተ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንዷ ዝቅተኛ የኢንተርኔት አገልግሎት የምታቀርብ ሀገር ናት የሚሉት ወይዘሪት ጨረር፣ ተቋሙ ከአርባ እስከ ሃምሳ በመቶ የሚደርስ የታሪፍ ማሻሻያ ካደረገ ዓመት እንደማይሞላውም ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ለተቋሙ የሚደርሰው ግብረ መልስ የሚያሳየው የዋጋ ችግር መኖሩን ሳይሆን ጥራት ላይ እንዲሰራ ነው ያሉት ኃላፊዋ፣ ጥራት ላይ መስራቱ ደግሞ የራሱን የተቋሙን ገቢ የሚያሳድግ እንደመሆኑ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል። ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም ዋጋውን ተመጣጣኝ በማድረግ ተደራሽነትና ጥራቱን ለማስተካከል አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ማስተካከያ መደረግ ካለበት የሚታይ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህም ከታሪፉ ቅናሽ በኋላ ሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊየን የኢንተርኔት ተጠቃሚ ማግኘት የቻለ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በአጠቃለይ ሃያ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን የኢንተርኔት ተጠቃሚ አገልግሎቱን እያገኘ መሆኑን አብራርተዋል። ተወዳዳሪ በሌለበት ሁኔታ ይሄ የተደረገው የህዝቡን አጠቃላይ አቅም ከግምት በማስገባት መሆኑን ጠቅሰው፣ የግሉ ዘርፍ እንዲሳተፍም በመንግሥት በኩል የተጀመሩ ስራዎችም እንዳሉም ተናግረዋል።
የዋጋ ማሻሻያ የሚደረገው የተቋሙን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የሀገሪቱን ሁኔታ ከግምት ባስገባ መልኩ መሆኑን ኃላፊዋ ጠቅሰው፣ ተቋሙ ሌሎች ተቋማት በኢኮኖሚው መስክ ያላቸውን እንቅስቃሴ ከማሳለጥ ባለፈ ለመንግሥት ትልቅ ገቢ የሚፈጥር መሆኑንም ይገልጻሉ።
እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፤ ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ከሰበሰበው ገቢ ዲቪደንድ አራት ነጥብ አምስት ቢሊየን ብር፣ በግብር ደግሞ ሰባት ነጥብ ስድስት ዘጠኝ ቢሊየን ብር ገቢ አድርጓል። ይሄ ገንዘብ ደግሞ በተዘዋዋሪ መንግሥት የሚሰራቸውን ትልልቅ ፕሮጀክቶች በመደገፍ ህዝቡን ተጠቃሚ ያደርጋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ