ዶክተር አደፍርስ ወርቁ ይባላሉ። የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪና በኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት የአየር ንብረት ሳይንስ ምርምር ዳይሬክተር ናቸው። በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ወይም በቀላሉ የማይጋለጥ አረንጓዴ ኢኮኖሚን መገንባት፤ ከዚሁም ጋር ተያይዞ በትራንስፖርቱ፣ በኢነርጂው፣ በግብርናው በተለይም በደን ልማት ዘርፉ በኩል እራሱን፤ የአየር ንብረቱን ከማጣጣምም ሆነ ከሌሎች ጋር አስተሳስሮ መሄድን በተመለከተ እንዲያብራሩልን ጠይቀናቸዋል። የሰጡን አስተያየትና ማብራሪያ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ዶክተር አደፍርስ ወርቁ እንደሚናገሩት፤ የአየር ንብረት ሳይንስ ምርምር አላማ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ወይም በቀላሉ የማይጋለጥ አረንጓዴ ኢኮኖሚን መገንባት ሲሆን ይህም በአገሪቱ የልማት ፖሊሲ ውስጥ ያለና በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ይሳካል ተብሎ እየተሰራበት ያለ ተግባር ነው። በትራንስፖርቱ፣ በኢነርጂው፣ በግብርናው በተለይም በደን ልማት ዘርፉ በኩል እራሱን፤ የአየር ንብረቱን ከማጣጣምም ሆነ ከሌሎች ጋር አስተሳስሮ መሄድ ላይ በሚገባ መስራትና እነዚህኑ ወደ አረንጓዴው ኢኮኖሚ ማምጣትን ያካተቱ ተግባራትን ማከናወን ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ይህን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግብ ለማሳካት በቅድሚያ አንድ ሀገር በራሱ “የአየር ንብረት ለውጥ” በሚለው መሰረተ-ሀሳብ እና በሳይንሱ ላይ በቂ እውቀት ሲኖር ነው። ይህም የአገሪቱን የአየር ንብረት ትላንት ምን ይመስል ነበር፤ ዛሬስ ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው፤ ነገስ ምንድነው የሚሆነው? የሚለውን በሚገባ ማወቅ ላይ የተመሰረተ ነው።
የዝናቡ፣ በልጉ፣ ክረምቱ ሁኔታ እንዴት ነው የሚሆነው? ጎርፉ፣ ሙቀቱ፣ አየሩ ወዘተ ሁሉ ምን ይመስላል፤ ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው ? የሚለውን ሁሉ በበቂ ጥናት ላይ በመመስረት ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን የአንድን አካባቢ የአየር ሁኔታ ማወቅና የወደፊቱን መተንበይ እንደሚቻል ዶክተር አደፍርስ ይናገራሉ።
እንደ እሳቸው ገለፃ፤ የሚመሩት ዳይሬክቶሬት በእነዚህ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በስፋት በማጥናት ለፖሊሲ አውጪዎችና ለሚመለከታቸው አካላት መረጃ ይሰጣል። ይህ አሰራርም አደጋን ሙሉ ለሙሉ ባያስቀር እንኳን ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት በእጅጉ ለመቀነስ ይረዳል።
በይበልጥ የምርምር ስራዎቻቸው የሚያተ ኩሩት ምን አይነት የአየር ንብረት እንዳለ በመለየት የአርሶ አደሩን ተጋላጭነት መቀነስ ላይ ሲሆን አንድ አካባቢ ላይ አርሶ አደሩ ምን አይነት ሰብል ቢዘራ፣ ምን አይነት አትክልት ቢያላምድና ቢተክል በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንደሚሆን፤ ምን ምን ተግባራትን ቢያከናውን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከሚመጣ አደጋ ሊድን እንደሚችል ሁሉ መረጃ የሚሰጥ ተቋም ነው።
ለምሳሌ አሁን ያሉ የእፅዋት ዝርያዎች ወደፊት ሊጠፉ ይችላሉ። ወይም አሁን ባሉበት ሁኔታ ወደፊት ላይኖሩ ይችላሉ። ቡናን ብንወስድ አሁን በሚበቅልበት አግሮ-ኢኮሎጂ የዛሬ 50 እና 60 አመት ላይበቅል ይችላል። ስለዚህ ይህንንና የመሳሰሉትን ሁኔታዎች ችግር ከማድረሳቸው በፊት ከወዲሁ በማጥናት መፍትሄ ማፈላለጉ የኢንስቲትዩቱ፤ በተለይም እሳቸው የሚመሩት ዳይሬክቶሬት ሀላፊነት ነው።
ገበሬው የሚኖርበትን ስነ-ምህዳር በመጠበቅና ተጋላጭ እንዳይሆን ማድረግ ላይ እየሰራ የሚገኘው ይህ ዘርፍ፣ ከትራንስፖርቱ፣ ከኢንዱስትሪው፣ ከሌሎችም የሚወጡ ሙቀት አማቂ በካይ ጋዞችን መቀነስ ላይ በአግባቡ እንዲሰሩ ለሚመለከታቸው አካላት መረጃዎችን ይሰጣል። በተለይ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂን እውን ከማድረግ አኳያ የምርምር ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው።
እንደ ተመራማሪው ገለፃ፤ ይሄ አገር ደን የሚመነጠርበት፣ ውሃ የሚበከልበት አገር ነው። ጠንካራ የምርምር ተቋማት ያስፈልጉታል። ከዚህ አኳያ የምርምር ስራዎች በዚች አገር ላይ ለውጥ አምጥተዋል ማለት የሚቻልበት ደረጃ ላይ ገና አልተደረሰም። እስከ ዛሬም ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶት የተሰራበት አይደለም። በተለይ በደን ሀብት በኩል ለምስራቅ አፍሪካ አገራት መትረፍ ሲቻል አልሆነም። ገና በቅርቡ “የአካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲቲዩት” ተቋቁሞ ወደ ስራ የገባው። አሁን ከቀድሞው ትንሽ ይሻላል፤ መንግስትም ትኩረት ሰጥቶታል። በጀት ከመንግስት ብቻ ሳይሆን ከሌላም እየተገኘ ነው።
“ደን፣ ውሃ፣ ሀይልና የመሳሰሉት አካባቢ ከፍተኛ ችግር አለ። የችግሩ ምንጭም በከፍተኛ ደረጃ የደን መራቆት እና እሱ ያስከተለው የውሃ እጥረት ነው። ጥልቅ ጉድጓዶች በደለል በመሞላታቸው ምክንያትም ሲዘንብ ውሃው እንዳለ ወደ ውጪ አገር መሄዱ፣ የዝናብ መቆራረጥ መኖር ዋና ዋናዎቹ ተግዳሮቶች ናቸው››ሲሉ ዶክተር አደፍርስ ይናገራሉ።
እሳቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያ የተለያየ ስነ-ምህዳር ያላት አገር ነች። በቆሎ፣ ስንዴ እና የመሳሰሉትን ማምረት ያስችላል። ለእንስሳት እርባታ፣ ለመስኖ ልማት ምቹ ሁኔታ ያለባትም አገር ነች። ሌላው ቀርቶ አንድ እርሻ መሬት ላይ ያለው ብዝሀ-ህይወት ቀላል አይደለም፤ ለምግብና ለእንስሳት መኖ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡
አገሪቱ ለተለያዩ ጠቀሜታዎች ሊውሉ የሚችሉ የተለያዩ የእፅዋት ዝርያዎች እንደ ልብ አሏት የሚሉት ዶክተር አደፍርስ፤ ይህ እራሱ የተለያየ ስነ-ምህዳር የመኖሩ ውጤት ነው። ሌሎች አገራትን ካየን ወይ ስንዴ ወይ በቆሎ ብቻ ሲያመርቱ ይታያል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ስነ-ምህዳራቸውም ሆነ የአፈራቸው አይነት ስለማይፈቅድላቸው መሆኑን ያስረዳሉ። በርካታ አገራት አቀማመጣቸው ዝቅ ያለ ስፍራ ላይ ነው።
ሱዳን፣ ኬኒያና መካከለኛው ምስራቅ ብንወስድ ዝቅ ያለ ስፍራ ላይ ናቸው። ዝቅ ያለ ስፍራ ደግሞ ሞቃታማ ነው። በመሆኑም የፈለጉትን ማምረት አይችሉም። ኢትዮጵያ ግን ከፍታ/ተራራማ ስፍራ ላይ በመሆንዋ ከፍተኛ ጠቀሜታ አግኝታለች። በደን ሸፍን ቢሆን ኖሮ ከቱሪዝም ተጠቃሚ መሆን ይቻል እንደነበር ያመለክታሉ፡፡
‹‹የኛ አገር ስነ-ምህዳር በጣም ጥሩና ከተሰራበት ቶሎ መልስ የሚሰጥ ነው›› የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ የዘርፉ ችግር ተቀናጅቶ፣ ተናቦ የመስራት ችግር መሆኑን ይጠቅሳሉ። ባለድርሻ አካላቱ ካላቸው ብዛት አንፃር ተናበውና ተቀናጅተው ሰርተው ቢሆን ኖሮ ከፍተኛ ደረጃ ይደረስ ነበር። በየመስሪያቤቱ የተሰጠህን ገንዘብ የት አደረከው ተብሎ ነው ኦዲት የሚደረገው እንጂ የሰራሀው ስራ የታል፤ ምን ደረሰ፤ ምን ፋይዳን አስገኘ? የሚለው ኦዲት አይደረግም፡፡
ገንዘቡን ችግኝ ተከልኩበት ማለት ብቻውን አያዋጣም፤ የተተከለው ችግኝ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰና ለኢኮኖሚው፣ ለአየር ንብረት ጥበቃው ያደረገው አስተዋፅኦ ሁሉ መፈተሽ ይገባል፡፡ በዚህ በኩል ድክመት አለብን። ያም ነው ባለ ድርሻ አካላቱ ተቀናጅቶ በመስራት ብክነትን፣ ድግግሞሽን፣ በተቃራኒ አቅጣጫ መሄድን፣ አለመናበብን እንዲያስወግዱ አስገዳጅ ሁኔታ ያልሆነባቸው። በሌላው አለም ገንዘቡ ምን ላይ እንደዋለ ብቻ ሳይሆን የተሰራው ስራም የት እንደደረሰ ስለሚፈተሽ ተቀናጅቶ የመስራቱ ነገር የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም።
ዶክተር አደፍርስ እንደሚሉት፤ ደን የሚተካ የተፈጥሮ ሀብት ነው። እንደ ነዳጅ አላቂ አይደለም። ዋነኛ ችግር አለመጠበቅና አለመተካት ነው። እየተጠቀምን መተካት እንችላለን፤ ለመጠቀም ብቻም ሲባል የሚለማ ዛፍም አለ፤ እሱንም ማድረግ ይቻል ነበር። ለከሰል ብቻ ዛፍ ማልማት ይቻላል፤ ይህም በአማራ ክልል፤ አዊ ዞን አካባቢ በተግባር እየታየ ነው።
በብዝሀ-ህይወት፤ ብዛት ካላቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ ከአለም 25ኛ፤ ከአፍሪካ 5ኛ ነች። በጣም ብዙ ብዝሀ ህይወት ቢኖርም ምን አይነት የተፈጥሮ ሀብት እና ያለንን የብዝሀ ህይወት አቅም ገና ተፈልጎ አልተደረሰበትም፡፡ ጉልበትና የውሀ ሀብት እያለ ወደ ኢኮኖሚ መቀየር ግን አልተቻለም። ለዚህ የሚሆኑ ተቋማት አልተገነቡም። ‹‹ይሄ የኔ፤ ይሄ ያንተ እየተባባልን ነው ያለነው። የጋራ ነገር ለማየት ሳንችል ቆይተናል።››
የሚሉት ዶክተር አደፍርስ፤ በተለይ ተበትኖ የነበረው ህዝብ አሁን ሀገሬ እያለ ስለሆነ፤ ጥሩ የሆነ፣ የለውጥ አመራር ወደ ሀላፊነት ስለመጣ፤ አገሪቱ ገና ያልተነካ የተፈጥሮ ሀብት ስላላት፤ ዜጎች ከምን ይደርስብኝ ይሆን ጭንቀት የወጡና ተረጋግተው መስራት የቻሉ በመሆኑ በአካባቢና አየር ለውጥ ስራዎቻችን ላይ ከፍተኛ ለውጥ ይመጣል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ዶክተር አደፍርስ ያመለክታሉ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2011
ግርማ መንግሥቴ