በኩራዝ አስታሚ ድርጅት የታተመ መጽሐፍ ነው። የልጅነት ትውስታ መመለስ ከሚችሉ መጽሐፍትም አንዱ ነው። በደራሲ ኒኮላይ ጎጎል ተፅፎ በመስፍን አለማየው የተተረጎመው “ካፖርቱ” የተሰኘው ድንቅ መጽሐፍ። መጽሐፉ ከታተመ ረዘም ያለ ጊዜ ሲሆነው፤ በታሪክ አወቃቀሩ፣ በስነ ፅሑፍ ይዘቱና ቋንቋ አጠቃቀሙ ዘመን ተሻጋሪ ነው።
የደራሲ ጎጎልን ስራ ደግሞ ደራሲ መስፍን አለማየው ከፍ ባለ የቋንቋ ይዘት በወላጅ ደራሲው የስሜት ከፍታ ወደ አማርኛ መልሶታል። ታዲያ ባሳለፍነው ሳምንት የቡክ ፎር ኦል ድረ ገጽ መስራች የመጽሐፍት አስተውሎት እና ሀያሲው አቶ ቴድሮስ ሸዋንግዛው በምልሰት ወደአለፈው ዘመን በመመለስ ይህንኑ መጽሐፍ ለውይይት አቅርቦት ነበር። እኔም ምንም ጊዜው ቢረዝም ይህንን ጣፋጭ ዘመን ተሻጋሪ የስነ ፅሑፍ ውጤት ማሳለፍ አልፈለኩምና እንድትቀምሱ እንካችሁ እላለሁ።
መጽሐፉ ታሪኩን የሚጀምረው በአንድ የመንግስት መስሪያ ቤት በፀሐፊነት ተቀጥሮ የሚሰራ አካኪይ አካኪዬቪች ባሽማሽኪን የሚባል ሰው አቋም ገጽታ እና ስራ ሁኔታ በማተት ነው። አካኪይ አካኪዬቪች ባሽማሽኪን ቁመቱ አጭር፣ ፊቱ ፈንጣጣ የበላው፣ አይኑም ዘወትር የቦዘና የፈዘዘ፣ ቀይ ፀጉሩ ገባ ገባ ማለት የጀመረ ነበር። የስራ መደቡ መጠሪያ ተራ ፀሃፊነቱን የሚያጎላ “አማካሪ” የሚል ማዕረግ ያለው ነው።
በመስሪያ ቤቱ ለረዥም ጊዜ ስለቆየ፣ እዚህ ቦታ ከተቀመጠ ስንት ዓመት እንደሞላው ወይም ይህንን የስራ ድርሻ ማን እንደሰጠው የሚያውቅ የለም። ስራ አስኪያጆችና ሌሎች ሹማምንት ተቀያይረዋል ፤ አካኪይ አካኪዬቪች ግን ዘወትር በአንድ ቦታ፣ በአንድ የስራ መደብ ተቀምጦ ያንኑ አሰልቺ የሆነውን ሰነድ የማገልበጥ ስራውን ያከናውናል። ከስራ ባልደረቦቹ መሐል አንድም እንኳን የሚያከብረው የለም። የበላዮቹ በንቀት ይመለከቱታል። እኩዮቹ ደግሞ መሳቂያና መዘባበቻ አድርገውታል።
አካኪይ አካኪዬቪች ለግሉ ደስታም ሆነ ለአለባበሱ ሳይጨነቅ፣ ስራውን ብቻ በትጋት ያከናውናል። በዚህ ዓለም ላይ ከልቡ የሚጨነቅለት ነገር ስራው ብቻ ነው። አረንጓዴ የነበረው ካፖርቱ አሁን አርጅቶ የዛገ ብረት መስሏል። ከቤቱ ወደ ስራ በሚመላለስበት ወቅት አካባቢውን ፍፁም ስለማያስተውል፣ ህፃናት የወረወሩበት ገለባ፣ ልጣጭ ወይም ሌላ ቆሻሻ ካፖርቱ ውስጥ እንደተሰገሰገበት እንኳን አይገነዘብም። ቤት እንደደረሰ ፣ የጎመን ሾርባ ወይም ትንሽ ስጋ ይቀማምስና ከቢሮ ይዞት የመጣውን ሰነድ መገልበጡን ይቀጥላል። ሲጨርስ፣ አልጋው ውስጥ ገብቶ ይተኛል። በዓመት በሚወረወርለት 400 ሩብል ተደስቶ ይኖራል ፤ በቃ ይኸው ነው የአካኪይ አካኪዬቪች ህይወት!
በዓመት 400 ሩብል ብቻ የሚከፈላቸው ተራ ፀሀፊዎችም ቢሆኑ እንኳን ፣ እራሳቸውን ከከባዱ የክረምት የሰሜኑ ብርድ መጠበቅ አለባቸው። አካኪይ አካኪዬቪች የነበረው አንድ ካፖርት በጣም አርጅቶ ነበር። ስለዚህ ልብስ ሰፊው ፔትሮቪች ጋር ሊወስደው ወሰነ። ፔትሮቪች ግን ካፖርቱ በጣም ስላረጀ ሊጠገን እንደማይችል ቁርጥ አድርጎ ነገረው። በ150 ሩብል አዲስ ካፖርት ሊሰፋለት እንደሚችል ፣ አሮጌውን ካፖርት ግን ጭራሽ ንክች እንደማያደርግ ጨምሮ አስረዳው።
ከልብስ ሰፊው ቤት ሲወጣ፣ ፀሐፊውን ጥልቅ ሐዘን ውጦት ነበር። ለአዲስ ካፖርት ማሰፊያ የሚሆን ምንም ገንዘብ አልነበረውም። በሚቀጥለው እሁድ ወደ ፔትሮቪች ዘንድ ተመልሶ ሄዶ። አሮጌ ካፖርቱን ይጠግንለት ዘንድ በመለማመጥ ለመነው። የፔትሮቪች መልስ ግን ቁርጥ ያለ ነበር። አካኪይ በመጨረሻ መራሩን እውቀት መቀበል እንዳለበት ተገነዘበ። አዲስ ካፖርት ማስፋት እንዳለበት ወሰነ። ነገር ግን ካፖርቱን ፔትሮቪች በ80 ሩብል ብቻ እንደሚሰፋለት ገምቷል።
ግማሹን ገንዘብ አሁኑኑ በጥሬው መክፈል ይችላል። ለዘመናት አንድ አንድ ኮፔክ እየቆጠበ ያጠራቀመው ገንዘብ አለ። ለሚቀጥለው ዓመት ሻይ መጠጣትና ማታ ማታ ደግሞ ሻማ ማብራት ቢተው እንዲሁም ጫማው ቶሎ አልቆ ወጪ እንዳያስወጣው ቢጠነቀቅ ያንኑ ያህል መቆጠብ ይችላል። ይህንኑ ቁጠባውን ያንኑ ቀን አንዳንድ ወጪ የሚያስወጡ ነገሮችን በመተው ጀመረ።
የሚቀጥለው ዓመት ለአካኪይ አካኪዬቪች ታላቅ የምስራች ይዞ መጣ። በተለመደው 40 ሩብል ፈንታ 60 ሩብል የበአል ጉርሻ ከመሥሪያ ቤቱ ተሰጠው። 40 ሩብሉ ቀድሞውኑ እቅድ ተይዞለታል። ስለዚህ የቀረውን 20 ሩብል እና ከቆጠበው ገንዘብ ላይ ጨምሮ፣ ከልብስ ሰፊው ጋር ጥሩ ጨርቅ ገዙ፤ የገዙት ጨርቅ ለስላሳ ግን ጠንካራ፣ ለገበር የሚሆን ደግሞ ጥጥ፣ ለኮሌታው ደግሞ የድመት ቆዳ በርካሽ አገኙ። ከትንሽ ጭቅጭቅ በኋላ ለፔትሮቪች የእጅ ድካሙ 12 ሩብል እንዲከፈለው ተስማሙ።
በመጨረሻ ካፖርቱ ተሰፍቶ አለቀ። በአንድ ጠዋት ፔትሮቪች ካፖርቱን ከደንበኛው ቤት ተገኝቶ አስረከበ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ክረምቱ ገብቶ፣ ቅዝቃዜውም በርትቶ ነበር። አካኪይ አካኪዬቪች በድል አድራጊነት ካፖርቱን ለብሶ ስራ ሄደ። አዲስ ካፖርት የማሰፋቱ ዜና በመስሪያ ቤቱ እንሰተሰማ፣ ድፍን ሰራተኛው ካፖርቱን ለማየት ከመተላለፊያው ክፍል ተሰበሰበ። አንዳንዶቹም ለማስመረቂያ ድግስ ቢጤ መዘጋጀት እንዳለበት አሳሰቡ። አካኪይ አካኪዬቪች ሲያመነታ፣ የአቃቤ ፀሐፊው ምክትል፣ በምትኩ ሁሉም እርሱ ቤት ማታ መጥተው ሻይ እንዲጠጡ በመጋበዙ ከሀፍረት ገላገለው።
አካኪይ በካፖርቱ ተጀቡኖ፣ አመሻሽ ላይ ከቤቱ ወጣና ወደ ግብዣው ቤት መሄድ ጀመረ። እኩለ ሌሊት እንዳለፈ ጋባዡን አመስግኖ ወደ ቤት ለመመለስ ተዘጋጀ። ጎዳናው ጭር ብሏል። ድንገት ከጨለማው ውስጥ ሁለት ወጠምሻዎች ብቅ አሉና ካፖርቱን ቀምተው ተሰወሩ። ወዲያውም በቅርቡ ወደነበረው ዘበኛ ሄዶ ስርቆቱን አሳወቀ። ዘበኛው ግን ሃምሳ አለቃው ቢሮ ሄዶ ቢያመለክት እንደሚሻል ነገረው። አካኪይ በጭንቀት እንደተደቆሰ ቤቱ ደረሰ።
ቤት ያከራዩት አሮጊት ፖሊስ ጋር እንዳይሄድ መከሩት፤ ይልቁንም ለተቆጣጣሪው እንዲያመለክት አሳሰቡት። በሚቀጥለው ቀን የስራ ባልደረቦቹ ገንዘብ አሰባሰቡለት። ነገር ግን የተሰባሰበው ገንዘብ ጥቂት ከመሆኑ የተነሳ፣ በምትኩ ምክር ሊለግሱት ወሰኑ። በምንም አይነት ሁኔታ ወደ ፖሊሱ የሃምሳ አለቃ እንዳይሄድ ሀሳብ አቀረቡለት። በዚያ ፋንታ የፖሊሶቹን ስራ
ሊያፋጥን ወደሚችለው “ትልቁ ሰው” ዘንድ እንዲሄድ መከሩት። አካኪይ በመጨረሻ “ትልቁ ሰው” ዘንድ ቀጠሮ አስያዘ። ነገር ግን “ ትልቁ ሰው” የባለጉዳዩን የስራ መደብ ትንሽነት ሲረዳ ተቆጥቶ አካኪይን አባረረው። አካኪይ ከ “ትልቁ ሰው” ቢሮ ወጥቶ ጎዳናውን ሲቀላቀል ከባድ ውርጭ ተቀበለው፤ ቤት ሲደርስም ጉሮሮውን ስላመመው አልጋው ውስጥ ገብቶ ጥቅልል ብሎ ተኛ።
ለጥቂት ቀናት ስለ ካፖርቱ መጥፋትና ስለ አንድ “ትልቅ ሰው” ከቃዠ በኋላ ሞተ። ይህንን ተከትሎም ጥቂት ቀናት ከተጠበቀ በኋላ አካኪይ ይሰራው የነበረውን ስራ የሚሰራ ሌላ ሠራተኛ ተቀጠረ። ብዙም ሳይቆይ በካሊንኪን ድልድይ አካባቢ አንድ የሞተ የመንግሥት ሠራተኛ የጠፋበትን ካፖርት ሲፈልግ እንደታየ አሉባልታ ተሰማ።
አካኪይ አካኪዬቪች ከመንገደኞች ላይ ካፖርታቸውን መንጠቁ ሲሰማ፣ ፖሊሶች ይህንን የሞተ ሰው ይዘው እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጣቸው። በአንድ ምሽት “ ትልቁ ሰው” ከወዳጆቹ ጋር ሲጠጣና ሲዝናና ካመሸ በኋላ ከሚስቱ ሌላ ካስቀመጣት ውሽማ ጋር ለመዳራት ወደሷው ለመሄድ ወሰነ። ጋሪው ላይ ተደላድሎ ተቀምጦ እንዳለ፣ ድንገት አንዳች ነገር አንገቱን በኃይል ጭምድድ አርጎ ሲይዘው ታወቀው። ዞር ሲል ግርጣቱ ከሚያስፈራው አካኪይ አካኪዬቪች ጋር አይን ለአይን ተገጣጠመ።
ከፍርሀቱ ብዛት የለበሰውን ካፖርት አውልቆ ወረወረው ፤ ጋሪ ነጂውንም “አዙርና በቀጥታ ወደ ቤት ውሰደኝ” አለው። የአካኪይ አካኪዬቪች የሙት መንፈስ የ”ትልቁን ሰው” ካፖርት ሳይወደው አልቀረም። ምክንያቱም ከዚያ በኋላ መንገደኞችን አዋክቦ ወይም ካፖርታቸውን ነጥቆ አያውቅምና። ለማንኛውም ይህ ከመጽሐፉ ለቅምሻ የተወሰደ ቁንጽል ታሪክ ነው። መፅሐፉን በሙላት ታነቡት ዘንድ ግብዣዬ ነው። መልካም ንባብ!
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2011
አብርሃም ተወልደ