ልጆች! እንዴት ናችሁ? ትምህርት ጥሩ ነው? ዛሬም ስለትምህርት እያነሳን እንማማራለን። ልጆች የሂሳብ ችሎታችሁን ለማሳደግ ከመደበኛ ትምህርትና ጥናት ውጭ ምን ታደርጋላችሁ? እንወዳደራለን ካላችሁ ጎበዞች ናችሁ። በተለምዶ ሂሳብ ይከብዳል ሲባል እንሰማለን ነገር ግን ካነበባችሁ ቀላል ነው። በየጊዜው ማንበብና ችሎታችሁን የሚያሳድግላችሁን ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ ማለት የለባችሁም።
የሂሳብ ችሎታቸውን ለማጠናከር ከመደበኛ ትምህርታቸውና ጥናታቸው ውጭ በ ‹‹ማትስ ፕላስ ማይንድ›› ለሁለተኛ ዙር ሂሳብ የሚወዳደሩ ተማሪዎች ሰሞኑን ፈተና ሲወስዱ አግኝቼ አነጋግሬያቸዋለሁ። ፈተናው በየዙሩ ሃያ የሂሳብ ጥያቄዎች ያሉት ሲሆን ውድድሩ ስድስት ዙሮች አሉት። ውድድሩ የሚያበቃው (የሚጠናቀቀው) ለአሸናፊዎች ሽልማት በመስጠት መሆኑን ከአዘጋጆቹ ተነግሮኛል። የሚወዳደሩ ተማሪ ዎች ደግሞ የሂሳብ ችሎታቸውን ማሳደግ የሚፈልጉና ከተለያየ ትምህርት ቤት የተውጣጡ ናቸው።
በሉተራን ትምህርት ቤት የአራተኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ዳግማዊ አዲስ በማትስ ፕላስ ማይንድ የሂሳብ ትምህርት ተወዳዳሪ ነበር። አንደኛና ሁለተኛ ዙሮችን ጥሩ ውጤት በማምጣት አልፏል። አሁን ለሶስተኛ ዙር ተፈትኗል። ይሄንንም በከፍተኛ ውጤት ወደ አራተኛው ዙር እንደሚያልፍ ነው በልበ ሙሉነት የነገረኝ።
ይህን ፈተና ለመወዳደር ዋናው ፍላጎት ብቻ ስለሆነ ሁሉም ተማሪ ቢወዳደር ደስ ይለኛል ይላል። ዳግም እንደሚለው ‹‹ማትስ ፕላስ ማይንድ›› መወዳደር ከጀመረ ወዲህ የሂሳብ ችሎታው በጣም ጨምሯል። እስከመጨረሻው ዙር መቀጠል የሚፈልጉ ተማሪዎች በሙሉ በደንብ ማጥናት አለባቸው። መፅሐፍ ላይ ያሉ ምሳሌዎችን ማየትና ማጥናት ይኖርባቸዋል የሚለው ዳግም አባቱና የአባቱ ጓደኛ እንደሚያስጠኑት ይናገራል። እሱም ያልገባውን ይጠይቃል ፤ ሲያስረዱት ይከታተላል። ጥሩ ውጤት ለማምጣት በደንብ ያጠናል።
ባሩክ ዳኒኤል የሀርመኒ ሂልስ አካዳሚ ተማሪ ነው። ሁለቱን ዙሮች ጥሩ ውጤት አምጥቷል። አንደኛውን ዙር ከሃያ አስራ ስምንት ፤ ሁለተኛውን ዙር ደግሞ አስራ ዘጠኝ በማምጣት ነው ለሶስተኛው ዙር ፈተና የታጨው። አሁን ፈተናው ጠንከር ያለ መሆኑን ይናገራል፤ ያም ሆኖ ግን እንደሚያልፍ እርግጠኛ ነው።
በተለይ በ‹‹ማትስ ፕላስ ማይንድ›› የሂሳብ ትምህርት መወዳደር ከጀመረ ጀምሮ የሂሳብ ችሎታው ስለጨመረለት ሁሉንም ውድድሮች አልፎ አንደኛ እንደሚወጣ ነግሮኛል። ልጆች በፕሮግራም ማጥናት አለባቸው። ለጨዋታና ለሌሎች ነገሮችም ፕሮግራም ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ነው የተናገረው። ውድድሩን በአንደኝነት ለማሸነፍና የሽልማቱ ባለቤት ለመሆን በማሰብ ብዙ መፅፍቶችን እንደሚያነብ ይናገራል። ይህም የሂሳብ እውቀቱን ከፍ እንዳደረገለት አጫውቶኛል። ባሩክ ጥናቱን ሲያጠና አባቱና እናቱ እገዛ ስለሚያደርጉለት ደስተኛ መሆኑንና ለማሸነፍም ጉጉት እንዳደረበት ነግሮኛል።
ተማሪ አርሴማ በለጠ የቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተማሪ ናት። አርሴማም ሦስተኛ ውን ዙር ተፈትና ስትወጣ ነው ያገኘኋት። ፈተናው በጣም ቀላል ነበር። ያለፉትንም ሁለት ዙሮች ሳልቸገር ነበር ያለፍኩት ስትል አጫውታኛለች። የመጀመሪያውን ዙር አስራ ሰባት ከሃያ በማምጣት ማለፍ ችላለች። ሁለተኛውን ዙር ደግሞ አስራ ዘጠኝ አምጥታለች። የሦስተኛውን ዙሩ ፈተና እንደምትደፍን ግምቷን ነግራኛለች።
አርሴማ አንደኛ ለመውጣት ስለምትፈ ልግ በፕሮግራማ ታጠናለች። ጥሩ ውጤት እንድታመጣ ያደረጋት ደግሞ በትምህርት ቤት መምህራን ከማድመጥ በተጨማሪ ማስታዎሻዋን በጥናት ሰዓትዋ ትከልሳለች። ከአክስቷ ጋር በመሆን ታጠናለች። ተማሪዎች እንዳይወድቁ በእቅድ ማጥናትና እንደ ማትስ ፕላስ ማይንድ ያሉ የሂሳብ ውድድሮች ላይ ቢሳተፉ መልካም ነው ስትል ትመክራለች።
ልጆች ሌላዋ ያነጋገርኳት እጅግ በጣም ጎበዝ የሆነች ተማሪ ናት። ተማሪ ሄመን ቴዎድሮስ ትባላለች።በናዝሬት ትምህርት ቤት የአራተኛ ክፍል ተማሪ ናት። ሄመን አምና በነበረው ማትስ ፕላስ ማይንድ አገር አቀፍ ውድድር ላይ ሁለተኛ በመውጣት የሰባት ሺ ብርና የብር ሜዳልያ ተሸላሚ እንደነበረች ነግራኛለች። አሁን በተዘጋጀው ውድድርም አንደኛ በመውጣት ሽልማቱን ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ናት።
ሄመን አምና በነበረው ውድድር ላይ ስድስተኛ ዙር ለመድረስ እንዳልተቸገረች አጫውታኛለች። ለዚህ ደግሞ በፍጥነት መስራትና አለመሳሳት ነው እንጅ ፈተናው አይከብድም ትላለች። በተለይ ደግሞ“ ’ማትስ ፕላስ ማይንድ’ ውድድር ደስ ስለሚለኝ እንዳልወድቅ ስል በቤት ውስጥም ከፈተናው በፊት ቀድሜ እለማመዳለሁ። አምና በነበረው ውድድር ከአንድ ስህተት በስተቀር ሁሉንም ፈተናዎች መድፈን ችያለሁ“ ብላኛለች።
ሄመን ጥናቷን የምታጠናው በራሷ ተነሳሽነት ነው። ረጅም ሰአት ታነባለች። ሂሳብ ካላጠናች እንቅልፏ እንደማይመጣላት ትናገራለች። ተማሪዎች ሁሌም ለጠቅላላ እውቀት የሚሆኑ መጽሀፍት ማንበብ እንደሚያስፈልግ ትመክራለች። ልጆች ሁሌም ለማንበብ መሰልቸትና መዘናጋት የለባቸውም። በየቀኑ የሚያነቡ ከሆነ እውቀታቸው ስለሚዳብር ከፍተኛና የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚችሉ ተናግራለች። በዘንድሮው ዓመትም በተወዳደረችባቸው ዙሮች አርባና አርባ አምስት ከሃምሳ በድምሩ ከመቶ ዘጠና አምስት አምጥታለች። በዚህ ወድድርም አንደኛ ለመውጣት በቂ ዝግጅት እያደረገች ነው።
ያኤል ዳኒኤል የሀርመኒ ሂልስ አካዳሚ የአራተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን የሶስተኛ ዙር ተፈታኝ ናት። ፈተናው ቀላል በመሆኑ ከሃያ ከአስራ ሰባት በላይ እንደምታመጣ ገምታለች። አንደኛ ወጥታ አሸናፊ ለመሆን በዝግጅት ላይ ናት። በቤት ውስጥ አባትዋ፣ እናትዋና ወንድሟ በማስጠናት ያግዟታል። ተማሪዎች ጥሩ የንባብ ስልቶችን ተጠቅመው ማጥናት ከቻሉ ጥሩ ሂሳብ ችሎታ ይኖራቸዋል። እንዲሁም ፈተና ሲደርስ ለመከለስ ቀድመው መዘጋጀት መቻል አለባቸው። ተማሪ ያኤል ከትምህርት ቤት እንደተመለሰች የቤት ስራዋን ሰርታ ስታጠናቅቅ ደግሞ የትምህርት አይነቶችን ሳትመርጥ በፕሮግራም ታነባለች።
”የማትስ ፕላስ ማይንድ“ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ከበደ አጥናፉ እንደሚሉት፤ ማትስ ፕላስ ማይንድ የተማሪዎችን የሂሳብ ችሎታ በውድድር መልክ እንዲያሳድግላቸው ተብሎ የተዘጋጀ ነው። ብዙዎች በአጭር ጊዜ ልዩ የሂሳብ ችሎታ እንዲኖራቸው አድርጓል። በተለይ ደግሞ ”ሂሳብ ይከብዳል“ የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት ይቀርፋል። ተማሪዎች ብቃት እንዲኖራቸው ማድረግ የ‹‹ማትስ ፕላስ ማይንድ›› ዋና አላማ ነው።
ልጆች! ይህ ውድድር በመላው ኢትዮጵያ የሚደረግ ነው። በውድድሩም ጥሩ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች የተለያዩ ሽልማቶች ይበረከትላቸዋል። ይህም ተማሪዎች የሂሳብ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩና የማንበብ ፍላጎታቸው እንዲጨምር ያበረታታል። በዚህ ዓመትም ወደ ሰላሳ ሺ ተማሪዎች ይወዳደራሉ። ወድድሩም በመጀመሪያ በየት ምህርት ቤቱ የሚደረግ ሲሆን ከሰባ ፐርሰንት በላይ ያመጡ ተማሪዎችን በመመልመል በከተማ ደረጃ እንዲወዳደሩ ይደረጋል። ከዛ በከተማ ደረጃ የተዘጋጀውን የሂሳብ ፈተና ያሸነፉ ተማሪ ተሸላሚ ይሆናል።
የማትስ ፕላስ ማይንድን ፈተና የሚፈተኑ ተማሪዎች ብዙ እየተጠቀሙ ነው። ተማሪዎች ፈተናውን ላለመውደቅ ሲሉ ያጠናሉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ ጎበዝና ያለማንም አነሳሽነት እንዲያነቡ ያስችላቸዋል ሲል ተናግሯል። እንዲሁም የንባብ ችሎታቸውም ይዳብራል። በፕሮግራም እንዲያነቡና ለሌሎች ትምህርቶችን ለማጥ ናትም ተነሳሽነት እንዲኖራቸው ያደርጋል። የማትስ ፕላስ ማይንድ ፈተናን የሚፈተኑ ተማሪዎች ሙሉ ለሙሉ የትምህርት አቀባ በል ችሎታቸው ይዳብራል ሲሉ አቶ ከበደ ይናገራሉ ።
ልጆች! እናንተስ የሂሳብ ችሎታችሁን ለማሳደግ ስትሉ ከትምህርታችሁ ውጪ እንዲህ ትጥራላችሁ? የምትጥሩ ተማሪዎች ቀጥሉበት። ጥረት የማታደርጉ ግን ዛሬውኑ መጀመር ይኖርባችኋል። ተሞክሯቸውን ያካፈሉን ተማሪዎች በራሳ ቸው ተነሳሽነት የሂሳብ ችሎታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረላቸው ነው። ልክ ተሞክሯውን እንዳካፈሉን ተማሪዎች የምትጥሩ ከሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ መደመ ርን፣ ማባዛትን፣ማካፈልንና መቀነስን ትችላላችሁ። እንዲሁም የማንበብ ልምድ ያዳብራል። እሺ! መልካም ቀን።
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2011
ሞገስ ፀጋዬ