ተቋሙ በግማሽ ዓመቱ 23 ነጥብ 46 ቢሊዮን ብር ገቢ አገኘ

አዲስ አበባ፡- በ2016 በጀት ግማሽ ዓመት 23 ነጥብ 46 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አስታወቀ፡፡

የተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ደምሰው በንቲ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በመርከብ አገልግሎት፣ በጭነት አስተላላፊነት፣ በወደብና ተርሚናል አገልግሎት እንዲሁም በኮርፖሬት አገልግሎት ዘርፍ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት 17 ነጥብ 23 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ፤ 23 ነጥብ 46 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ጠቁመው፤ ከታክስ በፊት ሦስት ነጥብ 26 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አብራርተዋል፡፡ በግማሽ ዓመቱ የድርጅቱን መርከቦችና የኪራይ መርከቦችን በመጠቀም አንድ ሚሊዮን 886 ሺ 399 ቶን ዕቃ ለማጓጓዝ ታቅዶ ሁለት ሚሊዮን 214 ሺ 156 ቶን የተለያዩ ዕቃዎችን ማጓጓዝ እንደተቻለ አስረድተዋል።

የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት የገቢና ወጪ ኮንቴይነር ፍሰት 197 ሺ 699 ኮንቴይነር ለማጓግዝ ታቅዶ 204 ሺ 358 ኮንቴነር ማስተናገድ ተችሏል ብለዋል፡፡ በግማሽ ዓመቱ ቀደም ባሉት ዓመታት ተጀምረው መጓተት የታየባቸው ፕሮጀክቶችን በመግምገም አፈጻጸማቸውን ለማሻሻል የክትትል ሥራ መሠራቱን አመላክተው፤ በግንባታ ሂደት ላይ የነበሩ 14 የካፒታል ፕሮጀክቶች በማጠናቀቅ ርክክብ መድረጉን አቶ ደምሰው አስታውቀዋል።

አቶ ደምሰው እንዳመላከቱት፤ በዚህም መጓተት በታየባቸው 10 ፕሮጀክቶች በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ከነበሩበት 52 ነጥብ ስምንት በመቶ አፈጻጸም ወደ 73 ነጥብ ሁለት በመቶ ማምጣት መቻሉን ገልጸዋል፡፡ በቃሊቲና ሞጆ ወደብና ተርሚናል ቅርንጫፎች እንዲሁም በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች እየተከናወኑ የሚገኙ የፕሮጀክት ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውንም አቶ ደምሰው ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ ድርጅቱ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ከመደገፍና አትራፊነቱን ጠብቆ ከመቀጠል በተጨማሪ ወጪ ንግድን ለማበረታታት መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በማኑፋክቸሪንግና በወጪ ንግድ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ድጋፎችን እያቀረበ መሆኑን አስረድተዋል።

በሚሰጡ ድጋፎች መሠረት በወጪ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ለምርት ግብዓትነት ለሚያስገቧቸው ጥሬ ዕቃዎች፣ ከየብስ ትራንስፖርት የትርፍ ህዳግ እንዲሁም ከባሕር ትራንስፖርት የትርፍ ህዳግ የዋጋ ቅናሽ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ የአፈር ማዳበሪያ፣ የቁም እንስሳት፣ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን የተለያዩ የወጪና ገቢ ምርቶችን በባሕር ከማጓጓዝ በተጨማሪ በሀገር ውስጥ መርከበኞችን በማሰልጠን ላይ የሚገኝ ተቋም ነው።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን የካቲት 20 / 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You