በአገር ተቆርቋሪነታቸው እና በነጋዴነታቸው ነው የሚታወቁት። ጨዋታ አዋቂነታቸው ደግሞ ሌላኛው የባህሪያቸው ተወዳጅ ክፍል ነው። ከአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስከአሁኑ የዶክተር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤት ድረስ ያለውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ማህበራዊ ሕይወት ጉዞ ያጨቀ ዕውቀትን ይዘዋል። የሽምግልና ክልል በደረሰው ዕድሜያቸው ደግሞ ከሱቅ ባለቤትነት እስከ አዲስ አበባ ከተማ ታክሲ ሾፌርነት እንዲሁም እርሻ ኢንቨስትመንትን የቀመሰ ሕይወትን አሳልፈዋል።
አቶ ሽባባው ፈንታ ይባላሉ። የታዋቂዋ እንስት አቀንቃኝ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) እና የባለሀብቷ ፍሬሕይወት ሽባባው እንዲሁም የሌሎች ስመጥሮች ወላጅ አባት ናቸው። አቶ ሽባባው ውልደት እና እድገታቸው በቀድሞው አጠራሩ አገው ምድር መተከል ውስጥ ግምጃ ቤት ማርያም በተባለ አካባቢ ነው።
አባታቸው የመንግሥት ሠራተኛ ነበሩ። እናም ስለዘመናዊ ሥራዎች ያላቸው ግንዛቤ ከፍተኛ በመሆኑ አቶ ሽባባው ወደ ንግድ እንዲሰማሩ ጥረት አድርገዋል። አባት ጥቂት ከብቶችን ሸጠው በተገኘው ገንዘብ ለልጃቸው ሸቀጣሸቀጥ መደብር ከፈቱበት።
በወቅቱ የተደሰቱት አቶ ሽባባው በ20 ዓመታቸው በመደብሯ ተቀምጠው ለኅብረተሰቡ ለዕለት ፍጆታ የሚውሉ ምግብ እና የተለያዩ ምርቶችን ማቅረብ ተያያዙት። በሚያገኙት አነስተኛ ትርፍ ከከተማ ምርት ገዝተው በመንደራቸው ትንሽ ሱቅ ያቀርባሉ እንዲህ እንዲህ እያሉ ለአራት ዓመታት ቢሰሩም ትርፉ ግን ሊያዋጣቸው አልቻለም።
የሥራ ዘርፍ መቀየር ስለፈለጉም ወደ አዲስ አበባ ሄደው አዲስ ሥ ራ ለመሞከር ልባቸው ተነሳሳ። በ1955 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ያገኙትን ሥ ራ ለማከናወን ነው፤ በአንድ ሰው አማካኝነትም አምስት ኪሎ ቅድስተማርያም ቤተክርስቲያን አካባቢ የሚገኝ ጋራዥ ውስጥ ሥ ራ ተገኘላቸው። በዚያ ሲሰሩም ከመኪና ጥገና ባለፈ ለማሽከርከር ፍላጎት ስነበራቸው ሹፌርነት ሙያ ለመልመድ ምቹ አጋጣሚ በመሆኑ የጋራዥ ሥ ራውን ወደውታል።
በጋራዥ ቆይታቸው ከዕለት ጉርሳቸው በቀር ክፍያ ባይሰጣቸውም ጥሩ ሙያ ግን መቅሰም ችለው እንደነበር ያስታውሳሉ። በሥራቸው ላይ ደግሞ ከአንድ ጣሊያናዊ ጋር ጥሩ መግባባት ፈጥረዋል። ጣሊያናዊውም አቶ ሽባባውን ቮልስ ቫገን መኪና እንዲሾፍሩ ያለማምዳቸው ነበር። በኋላም ጥሩ መሾፈር በመቻላቸው መንጃ ፈቃድ አውጥተው የጋራዥ ሥራውን ለቀቁ።
ወዲያውም «ሚሊቼንቶ» የተባለች በወቅቱ ለታክሲ አገልግሎት የምትውል ተሽከርካሪ ላይ መስራት ጀመሩ። በየቀኑ መርካቶ እና ፒያሳ እየተመላለሱ ተሳፋሪዎችን በማገልገል መስራታቸውን ቀጥለዋል። ለአራት ዓመታት በታክሲ ሥ ራ እንደቆዩ ግን የእራሳቸውን መኪና ገዝተው በመዲናዋ እየተዘዋወሩ መስራት ምርጫቸው አደረጉ። አንድ ላንድሮቨር መኪና በስድስት ሺ ብር ገዝተውም የተለያዩ ዕ ቃዎችን እያጓጓዙ ሰርተዋል።
የላንድሮቨሯ ገቢ ከፍ ሲል ደግሞ እሷኑ ሸጠው «መርቸዲስ» የተሰኘውን 50 ኩንታል የሚጭን ከባድ መኪና ይገዛሉ። እናም ሦስተኛ መንጃ ፈቃድ አውጥተው የከባድ መኪና ሥራን ማቀላጠፉን ተካኑበት። በወቅቱ በከባድ መኪና ሹፌርነታቸው ከደቡብ እስከ ሰሜን፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ እህል እና የተለያዩ ምርቶችን ያመላልሱ እንደነበር ያስታውሳሉ።
በዚህ ወቅት ግን ከትራንስፖርት ሥራው በተጨማሪ በተወለዱበት አካባቢ ያለውን የቤተሰብ እርሻ ለማዘመን የተለያዩ መሣሪያዎችን ወደ መንደራቸው ይወስዱ ነበር። በተለይ ለእርሻቸው የሚሆን ዘመናዊ ትራክተር በመግዛት ለመተከል እና አካባቢው አርሶ አደር መሣሪያውን ማ ስ ተ ዋ ወ ቃ ቸ ው ን አይዘነጉትም። ቦሎቄ፣ በቆሎ እንዲሁም አኩሪ አተር የመሳሰሉትንም ያመርታሉ። በጎን ደግሞ የተወሰኑ ከብቶችን በማርባት ለገበያ ያቀርባሉ።
በ ታ ታ ሪ ነ ታ ቸ ው የተለያዩ ሥ ራዎችን እያከናወኑ ሳለ ግን ያልጠበቁት ነገር ተከሰተ። የአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት ወርዶ በደርግ ተተካ። ቤተሰባቸው ላይም ከፍተኛ እንግልት ከመድረሱ ባለፈ አቶ ሽባባው አድሃሪ ናቸው ተብለው እንዲገደሉ በሚል ይሳደዱ እንደነበር ያስታውሳሉ። የአካባቢያቸው ኅብረተሰብ ግን ለምን ይገደላሉ እርሳቸው ዘመናዊ የግብርና ሥራን ባስተዋወቁ የሚል ሃሳብ በማንሳቱ ንብረታቸው ተወርሶ እርሳቸውን ተዋቸው።
በወቅቱ አስር ሺ ብር የነበረው ትራክተራቸውን እና የተለያዩ ንብረቶች ሲወረሱ የተወሰኑ ከብቶቻቸውን ቤተሰባቸው ጋር አኑረው የተሽከርካሪ ሥ ራቸውን ቀጠሉ። ይሁንና ወደ ቀያቸው በየጊዜው መመላለሱን እና ለአዳዲስ ሥራ የሚሆን እቅድ ይዘው ማሰላሰሉን አላቋረጡም ነበር። እናም መተከል ላይ በናፍታ የሚሰራ የዘይት መጭመቂያ ቤት አቋቋሙ። የዘይት ንግዱ ጥሩ ቢሆንም በወቅቱ ከ500 ሺ ብር በላይ ማንኛውም ሰው እንዳይኖረው የሚል ሕግ ስለነበር ተበድረውም ቢሆን ማስፋፊያ ለማከናወን አላሰቡም።
በ1977 ዓ.ም ደግሞ ጣሊያኖች የጣና በለስ ግድብን ሊገነቡ ወደመተከል ብቅ ስለማለታቸው ያያሉ። በወቅቱም አንድ ወዳጃቸው ጠጋ ይሉና «ፈረንጆች ወደ አካባቢው ሲመጡ የሆቴል አገልግሎት ይፈልጋሉ እናም ለምን ዘርፉን አትቀላቀልም» ብለው ሹክ ይሏቸዋል።
በሃሳቡ የተስማሙት የንግድ ሰው ጣና በለስ የተሰኘውን ሆቴል መተከል ላይ ገንብተው ጣሊያኖቹን እያስተናገዱ ነዋሪውንም የሆቴል ሥራ እያለማመዱ ገቢ መሰብሰብ ቀጠሉ። ብልሁ ሰው ታድያ በዚህ ብቻ አላበቁም ጣና በለስ እና መተከል ላይ ደግሞ ሁለት ነዳጅ ማደያዎችን ከፍተው ሥራቸውን አጠናከሩ። ክንደ ብርቱው የንግድ ሰው የተለያዩ ሥራዎችን እየከወኑ ሀ ብት ለማፍራት ቢሞክሩም አሁንም ግን ሌላ ፈተና ገጠማቸው።
ጊዜው 1983 ዓ.ም ነበር፤ ኢህአዴግ በደርግ መንግሥት የተተካበት። እናም በሽግግሩ ወቅት ሥርዓት አልበኞች በፈጠሩት ግርግር የሆቴላቸው እና የነዳጅ ማደያቸው ንብረቶች በሙሉ ተዘረፉ። እናም ሁሉም ንግድ በአንድ ጊዜ ቆመ። «ለሕዝብ ተቆርቋሪ የሆኑ ሃሳቦች ስለማነሳ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ዓይን አልወደድም ነበር» የሚሉት አቶ ሽባባው፤ በወቅቱ እስከሞት ግድያ የደረሰ አደጋ ሊያደርሱባቸው የሚፈልጉ ሰዎች እንደነበሩ ያስታውሳሉ።
ንብረታቸው ሲዘረፍ ግን ዝም ብለው ያልተቀመጡት ጠንካራ ሰው ወደ ባህር ዳር በማቅናት በመተከል የጀመሩትን የሆቴል ንግድ ማስቀጠል ፈልገዋል። ጣና ሐይቅ ዳር በተገነባችው ከተማ ላይ ፍቃድ ጠይቀው ድብ አንበሳ የተሰኘ ሆቴል ማስገንባቱን ተያያዙት። የጥንት የኢትዮጵያን ታሪክ እና ባህል በሚያንጸባርቅ መልኩ በጥራት የተሰራ ባለ ሁለት ፎቅ ሕንፃ አስገንብተው በ1986 ዓ.ም ሆቴሉ ተከፈተ።
በጎን ደግሞ ባህር ዳር ላይ ቦታ ገዝተው ከመተከል ይዘዋቸው የመጡትን አምስት ላሞች ማርባት ጀመሩ። አምስቱ አስር እየሆኑ እነሱም እየተዋለዱ በርካታ ከብቶችችን ማርባት ችለዋል። ይሁንና በአንድ ወቅት አስር ላሞቻቸው በመርዝ የተገደሉበትን አስከፊ ጊዜ አይረሱትም። በወቅቱ የተለያየ ምክንያት ቢሰጣቸውም እርሳቸውን ለመጉዳት ሆን ብሎ ያደረገ ሰው በመኖሩ ለጊዜው አበሳጭቷቸው ነበር።
በሆቴል ንግዱ ደግሞ ጥቂት ዓ መታትን እንደሰሩ የባድመ ጦርነት በመጀመሩ ሌላ ፈተና ይዞባቸው ብቅ አለ። የየትኛውም ፓርቲ አባል ባይሆኑም በተለያዩ መድረኮች እና ከሰዎች ጋር በሚኖራቸው ቆይታ በሚያነሷቸው የሕዝብ ጥያቄዎች ምክንያት ይፈረጁ እንደነበር ያስታውሳሉ። በወቅቱ የሆቴል ንግዳቸው የተቀዛቀዘበት እና ገቢያቸውም ያሽቆለቆለበት ነበር።
አቶ ሽባባው እንደሚናገሩት፤ በፖለቲካው ምክንያት በርካታ የአማራ ክልል ባለሥልጣናት ሳይቀር እርሳቸው ሆቴል እንዳያርፉ ጫና ይደርስባቸዋል። እርሳቸው ጋር የተገለገለ ደንበኛ በግምገማ ወቅት ትችት ይደርስበት ነበር። ይህ ሁሉ የተከሰተው ደግሞ ለምን በማለታቸው ነው።
በርካታ ጫና ቢደርስባቸውም ቅሉ ከሥራቸው ውልፍት አላሉም። ከጦርነቱ አራት ዓመታት በኋላ ዳግም ያንሰራራውን የሆቴል ገቢያቸውን እያሻሻሉ ለዚህች ቀን ደርሰዋል።
አሁን ላይ አቶ ሽባባው በሥራቸው 83 ሠራተኞችን ቀጥረዋል። ባህላዊ መጠጥ እና ምግቦቻቸውም ሆነ በምቹ አልጋዎች ለአገር ውስጥ ብሎም የውጭ አገር ደንበኞችን እያስተናገዱ ይገኛል።
የዶክተር አብይ መንግሥት እና ጊዜው ለሥራ ምቹ በመሆኑ የተሻለ ሥራ እንደሚያከናውኑም ተስፋ አድርገዋል። በሌላ በኩል ባህር ዳር ላይ የቀጠለው የከብት እርባታ አንድ መቶ የሚደርሱ ከብቶችን ይዟል። ባለቤታቸውም የከብት እርባታውን እየተቆጣጠሩት ይገኛል።
የመተከሉ ሰው አቶ ሽባባው የአሁን እቅዳቸው ዘመናዊ የወተት ማቀነባበሪያ መክፈት ነው። በቀን አምስት ሺ ሊትር ወተር አቀነባብሮ የሚያሽግ ፋብሪካ ለመገንባት ዝግጅት ላይ ናቸው። ለፋብሪካውም 30 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ጥናት አድርገዋል።
«ከአስር በላይ ልጆች አሉኝ» የሚሉት ጠንካራው የንግድ ሰው ከሥራቸው በተጓዳኝ፣ የተሻለ ትውልድ ለመፍጠር ልጆቻቸውን በጠንካራ የሥራ መንፈስ እንዳሳደጉ እና የተወሰኑትም ነፍስ እስኪያውቁ በምግባር እየኮተኮቱ ያደጉ መሆኑን ይናገራሉ። ከብዙ በጥቂቱ ታዋቂዋ ልጃቸው ጂጂ፣ ብርሃኔ፣ ዘውዱ እና ፍሬሕይወት ይሰኛሉ።
የልጃቸው ጂጂ ጤንነት እየተመለሰ በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን እና በቅርቡ ወደ አሜሪካ ለመሄድ ማሰባቸውን ይገልጻሉ። ሌላኛዋ ልጃቸው ወይዘሮ ፍሬሕይወት ደግሞ በኢትዮጵያ የንግድ ሥራ ለመከወን በማሰባቸው የሃሳብ ድጋፍ እያደረጉላቸው ይገኛል። እራሳቸው፣ አባትም ሁኔታዎች ሲመቻቹ ሰፋፊ እርሻ ዘርፍ ላይ የመሰማራት ትልቅ ፍላጎት አላቸው።
አቶ እሽባባው እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለዜጋው የሚተርፍ በቂ የተፈጥሮ ሀብት አለ። ጎጃም ውስጥ ብቻ የሚገኘው ተፈጥሮ መላ ኢትዮጵያን ሊመግብ ይችላል። በመሆኑም ወጣቱ በግብርና እና ከብት ማድለብ ሥራዎች ላይ ቢሰማራ ውጤታማ መሆን ይቻላል። ለዚህ ደግሞ ቁልፉ ገንዘብ ነው፡፡ በመሆኑም የመንግሥት አካላት በቂ የመስሪያ ገንዘብ ብድር ካመቻቹ ወጣቱ የመለወጥ አቅም አለው።
ወጣቶች በበኩላቸው ለውጡን ደግፎ ከመንግሥት ጎን በመቆም ወደሥራ መሰማራት ይኖርባቸዋል። እናም ወጣቱ አረንጓዴውን መሬት ወደገንዘብ በመቀየር እርሻ እና ወተት ሀብት ላይ ቢሰማራ የተሻለ ገቢ ይኖረዋል፤ የሚል እምነትና ምክር አዘል መልዕክትም ነው አቶ ሽባባው ያስተላለፉት።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 1/2011
ጌትነት ተስፋማርያም