ኮሚሽኑ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ሥራዎችን ለመሥራት ተዘጋጅቷል

አዲስ አበባ፡- ግጭት ባለባቸው አካባቢዎችም ሥራዎችን ለመሥራት የተሟላ ዝግጅት እንዳለው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ ሥራውን በአግባቡ እንዳያከናውን አንዳንድ ቦታዎች ላይ የጸጥታ ችግሮች ተግዳሮት ሆነዋል። ሆኖም የጸጥታ ችግሮች ባሉባቸው አካባቢዎችም ከመንግሥት፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ከሲቪክ ማኅበራት ጋር በመተባበር፤ በተለይ መከላከያ ሠራዊቱና ፖሊስ ሽፋን በመስጠታቸው ሥራዎች በመሠራት ላይ ናቸው።

በቅድመ ዝግጅቱ ወቅት በአማራ ክልል ባሉ አካባቢዎች በመቅረብ ስለ ኮሚሽኑ እቅድ ከሕዝቡ ጋር ውይይት ማድረግ ተችሎ ነበር ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የተሳታፊ ልየታ ለማድረግ በታሰበበት ወቅት ግጭት ተፈጥሮ እንደነበረና፤ ኮሚሽኑ ተስፋ ሳይቆርጥ ከክልሉ አመራሮች፣ ከሲቪክ ማኅበራት፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎችና ከምሁራን ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ገልጸዋል። በሌሎች አካባቢዎች የተጀመሩትን ሥራዎች ግጭቱ ባለባቸው አካባቢዎችም ጎን ለጎን ለማስኬድ በኮሚሽኑ በኩል የተሟላ ዝግጁነት መኖሩን አስታውቀዋል።

«ለእኛ እንቅፋት ሆነው የቆዩት ግጭቶች ናቸው። ግጭቶቹ በንግግርና በምክክር እንደሚፈቱና ወደ ብሔራዊ አንድነት እንደምንመለስ ተስፋ ይደረጋል። ወደፊት ቀስ በቀስ በንግግር እየተፈቱ ሲሄዱ ችግሮችም ሲቃለሉ ሀገራዊ ምክክሩም ግቡን ይመታል» ብለዋል።

በትግራይ ክልልም ምሁራንን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ጠቅሰው፤ በሁሉም በኩል ምክክር ለማካሄድ አዎንታዊ ፍላጎትና አመለካከት እንዳለ ተናግረዋል። ችግሮችን ለመፍታት እየተነጋገሩ ነገሮች ሲስተካከሉ ኮሚሽኑ ወደ ምክክር እንደሚገባ ተስፋ ተሰጥቷል ብለዋል።

ኮሚሽነሩ አክለው እንደገለጹት፤ እስካሁን በቅድመ ዝግጅትና በዝግጅት ምዕራፍ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። በዝግጅት ምዕራፉ በዋናነት የኢትዮጵያን አውድ ጠንቅቆ ማወቅ ነበር። በዚህም በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች በአካል በመገኘት ከአመራሮች ጋር የመተዋወቅ፣ የአሠራር ሥርዓቶችን የማሳወቅና ከኮሚሽኑ ጋር የሚያገናኛቸውን አካላትን የመፍጠር፤ በተመሳሳይ 48 ከሚደርሱ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ውል መፈራረም ተችሏል። ዩኒቨርሲቲዎች ትንሿ ኢትዮጵያ ተብለው ስለሚታሰቡ በትብብር እየተሠራ ነው።

«በአሁን ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ እስከ 80ሺህ የሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን አነጋግረናል። የሚያበረታቱ ግብዓቶችና ቅድመ አጀንዳዎች ተገኝተዋል። ከአማራና ትግራይ ክልል ውጪ ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በክልሎች የእስካሁኑን ሥራዎች በሚገባ አጠናቅቀናል» ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ፤ የተሳታፊ ልየታን በሚመለከት በሲዳማ ክልል፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሐረሪ እና በሱማሌ ክልሎች እየተጠናቀቀ ነው።

የእስካሁኑ ሥራ ከ90 በመቶ በላይ ክልሎች ላይ ተጠናቅቋል። በኦሮሚያ ክልልም ቢሆን በስፋት እየተሠራ ይገኛል። በቅርቡ ይጠናቀቃል። የሕዝቡ ተነሳሽነት ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ሰላማዊ የሆነ ሀገር ለመገንባት፤ በዘላቂነት ዕድገትና ልማት ለማምጣት፤ ግጭትና ጦርነትን ለማስቆም እያንዳንዱ ሰው ዝግጁ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸው፤ ሕዝቡ ችግሮች ሲፈጠሩ ለችግሮች መፍትሔው መዋጋት ሳይሆን መመካከር ነው ብሎ እንደሚያምንም አብራርተዋል።

አዲሱ ገረመው

 

አዲስ ዘመን  የካቲት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You