በእኔ እምነት ኢትዮጵያዊ አራዳ ገመና የለውም። ብዙ ነገሮቻችን ላይ ችግር የፈጠረው ገመና ይመስለኛል። በነገራችን ላይ በገመና እና በአይነኬነት (Taboo) መካከል ልዩነት አለ። አይነኬነት (ታቡ) የሚባሉት ማህበረሰቡ ተስማምቶ የማይላቸው፣ በአደባባይ የማይነገሩ ነገሮች ናቸው። «ታቡ» የሌለው ማህበረሰብ የለም፤ ሁሉም «ታቡ» አለው። ልዩነቱ እኛ ጋ «ታቡ» ያልናቸው ሌላው ጋ በአደባባይ የሚነገሩ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ሌሎች ጋ «ታቡ» የሆኑት ደግሞ እኛ ጋ በአደባባይ ሊነገሩ ይችላሉ። ገመና ግን ይሄ አይደለም።
«ገመና» የሚለው ቃል አረባቡ ራሱ የተለየ ነው። ለዚሁ ብዬ አንድ መዝገበ ቃላት ላይ አይቼ ነበር። የከሳቴብርሃን ተሰማ መዝገበ ቃል ላይ «ገመነ» ከሚለው ቃል የመጣ ነው ይላል። ገመነ የሚለው ቃል በዕለት ከዕለት ተግባሩ ወይም ሥራው ተናደደ፣ ተቃጠለ፣ ተበሳጨ ማለት ነው።
እንግዲህ ይሄ ወደ ስም ሲረባ ገመና ሲሆን ብስጭቱ ንደቱ መሆን ነበረበት። ይሄን ገመና የሚለውን የሚፈታው የዕለት ከዕለት ብስጭቱን ሸፈነ የሚል ይጨመርበታል። ኃጢአቱን ነውሩን ሸፈነ ማለት ነው። ግን ሸፈነ ሳይሆን ጠረገ የሚል ትርጉም ቢሰጠው ኖሮ ሕይወታችን ይለወጥ ነበር። ምክንያቱም ሁሉም ሰው ነውሩን ለማጽዳት ይተጋ ነበር። ገመና የሚለውን ግን ለመሸፈን ነው የምንጠቀምበት።
ገመና ከቤተሰብ ይጀምራል፤ ወይም ከግለሰብ ይጀምራል። አንድ ሰው ፍቅረኛውን አውልቆ አውልቆ ጣላት። በማግስቱ ጓደኛዋ «ምነው ምን ሆነሽ ነው፤ እንደዚህ ያደረገሽን ሰው ፖሊስ ጋ ሄደሽ መናገር አለብሽ» አለቻት። «አስቤ ነበር ግን ምን ይደረግ የራሴው ሆኖብኝ ነው፤ እጮኛዬ ነው» አለች። «ውይ! እሱንማ ምን ታደርጊያለሻ፤ ገመናሽን!» አለቻት በዚያው ቀረ።
በእኛ ማህበረሰብ ውስጥ ገመና ከግለሰብ ጀምሮ የግፍና የነውር መቋጠሪያ ቀረጢት ሆኖ ያገለግላል። ይሄ ከፍ እያለ በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በድርጅት ደረጃ ይደርሳል። ድሮ ገመና ጓዳ ውስጥ ነበር የሚደበቀው። አሁን መንግሥትም ገመና አለው። ድርጅትም ገመና አለው።
አንድ የሐረር ልጅ ዳይሬክተር ሆኖ የሚሰራበት ትምህርት ቤት ውስጥ አንድ ሌላ ሰው ዳይሬክተር መሆን ይፈልጋል። ያ ዳይሬክተር መሆን የሚፈልገው ሰው ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የዳይሬክተሩን ስም ያጠፋል። ከሚያስተምረው ትምህርት ላይ 10 ደቂቃ እየዘገየ፣ 10 ደቂቃ ቀድሞ እየወጣ፤ ከ40 ደቂቃ ውስጥ 20ውን ደቂቃ ያባክነዋል።
ዳይሬክተሩ ይናደድና ስብሰባ ይጠራል። «ሰዓት እየሰረቃችሁ ነው፤ በአግባቡ ስሩ» ሲል መጀመሪያ እጁን ያወጣው ያ 20 ደቂቃ የሚቀጣው መምህር ነው። «ይሄ እኮ የአስተዳደርን ሥራ አለማወቅህ ነው፤ አንተ አሁን ብታውቅ በአንድ ደብዳቤ የሚያልቅ እኮ ነው።
ማስጠንቀቂያ ትጽፋለህ፤ ሁለተኛ ሦስተኛ እያልክ ማስጠንቀቂያ ከጻፍክ በኋላ ማባረር ነው። ይሄን የተማሪዎች ውድ ሰዓት ማባከን!» እያለ ተናገረ። ይሄን ሲናገር የትምህርት ቤቱ ባለቤት አለ (የግል ትምህርት ቤት ነው)።
እንዳለጌታ ከበደ እንዳለው ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያዊ አራዳ ነበር፤ በዚያ ላይ የሐረር ልጅ ነው። «እንዲህ ያደረከው እኮ አንተ ነህ!» ብሎ ነገረው። ይሄ በትክክል የሆነ ገጠመኝ ነው የነገርኳችሁ፤ «በቃ አንተ ነህ! አደርገዋለሁ!» ብሎ ቢለመን ቢለመን እምቢ አለ። በዚሁ ምክንያት ስብሰባው ተበተነ።
እንዲህ የሚያደርግ ሰው ነው የሚያስፈልገን። እንዲህ ገመናን የሚያጋ ልጥ። ስብሰባ እኮ የፖለቲካ ገመና መሸፈኛ ነው። አንዳንድ መስሪያ ቤት ትልልቅ ነውር ይሰራና «ተገማግመናል» ይባላል። ተሸፈነ ማለት ነው፤ ሌላ የነውር ምዕራፍ ይጀመራል።
ገመና ያሳደጋቸው ሁለት ነገሮች አሉ። አንዱ ማስመሰል ሲሆን ሌላው ስም አለመጥራት ነው። በጣም የሚገርመኝ ነገር ስም አለመጥራት ነው። አንዱ የማናድግበት ነገር ስም አለመጥራት ነው። ለምሳሌ ይሄ መድረክ እንዲሳካ ድጋፍ ያደረጉ አካላት እነ እገሌ እነ እገሌ እየተባለ ይመሰገናሉ። ይሄ መድረክ እንዳይካሄድ ያደረጉ አካላት ቢኖሩ ግን ስማቸው አይጠራም።
አንድ ጊዜ ፕሮፌሰር መስፍን በአንድ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ላይ ቃለመጠይቅ ሊደረጉ ሲጠየቁ «እኔ ስም እጠራለሁ፤ የጠራሁትን ስም መቁረጥ፣ መለወጥ አይቻልም! እገሌ እያልኩ ነው የምናገር» አሉ። ጋዜጠኛው ተስማምቶ ቃለመጠይቅ ተደረገ፤ ስም እየጠሩ የተደረገው ቃለመጠይቅ ተላለፈ። የሰማው ሁሉ በጣም ነበር የደነገጠው።
የማናድግበት ምክንያት ይሄ ነው። ስም አለመጥራት ግልብ እንድንሆን ያደርጋል። ግልብነት ስል አንድ ነገር ትዝ አለኝ። አንድ ዕለት በአንድ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ላይ ጋዜጠኛው «ይሄ ትውልድ የሥነ ምግባር ዝቅጠትን ተቀዳጅቷል» ሲል ሰማሁት። መቀዳጀት ለጥሩ ነገር ነው። ገመናውን አወጣሁበት ይቅርታ!
ስም አለመጥራት የእውነትና የእውቀ ታችንን ሽንቁር የምንወትፍበት ነው። ጋዜጠኛው ይመጣና «አሁን እየተከሰተ ባለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሚቀጥለው ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ አዝመራው ሊጎዳ እንደሚችል አንዳንድ የኦሞ አካባቢ የሚኖሩ ገበሬዎች ተናገሩ» ይላል።
አሁን የኦሞ ገበሬ ስለሚቀጥለው ዓመት አዝመራ ምን የሚያውቀው ነገር አለው? ለምን እገሌ ተናገረ አይባልም? አሁን አሁን «ቶክ ሾው» ላይ አይታችሁ ከሆነ «አንተን እኮ እንዲህ እንዲህ ብለው የሚያሙህ አሉ፤ በዚህ ላይ ምን ትላለህ» ይባላል። ይሄ «እኔ አይደለሁም፤ ስም አልጠራሁም» ለማለት መሸሻ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ልማድ ከእውቀት ያሸሻል። ጥንቅቅ ያለ እውቀት ነው መሆን ያለበት።
እድር እንኳን ዕቃዎች ቀስ በቀስ እየጠፉ ሲሄዱ ስብሰባ ይጠራል። ዕቃውን ወስዶ ያስቀረው ሰውዬ ቀድሞ ያወጣና «ይሄ ነውር ነው፤ ገመናችን ነው፣ የወሰደ ሰው ይመልስ» ይላል። ዕቃውን የወሰደው ሰው እኮ ስሙ መዝገብ ላይ አለ፤ ለምን ስሙ ተጠርቶ አይጠየቅም? የእድሩ ዳኛ ለምን ያንን ስም እንደማይጠራ አይገባኝም። መጨረሻ ላይ በሉ የወሰዳችሁ ሰዎች በወር ውስጥ እንድትመልሱ ተብሎ ስም ሳይጠራ ይለያያሉ። ይሄ እስከ አገር ድረስ ሄዷል።
የኢህአዴግን ስብሰባ ብታዩ «በለውጡ የተገኙ ነገሮች ተስፋ የሚሰጡ ናቸው» ይባላል፤ ለዚህ አሁን ምን ስብሰባ ያስፈልጋል? «መፈናቀሉ በቁጥጥር ሥር መዋል አለበት» አሁን ይሄ ምን ስብሰባ ያስፈልገዋል? መግለጫው ሁሉ ስብሰባ የማያስፈልገው ነው። የደበቁት ገመና አለ። ያንን መሸፈኛ ነው ስብሰባው።
ብዙ ነገር እየበዛ እየበዛ እየበዛ ሲሄድ ያንን መሸፈኛ ነው። እንዲህ ዓይነት ነገር የእውቀት ክፍተት ያመጣል። ሚዲያዎችን ብታዩ ፕሮግራሙን የሚሸፍንለት ነገር ነው የሚፈልግ። የግለሰብ ስም እንደማንጠራው ሁሉ የወል ስም ለመፈብረክ ደግሞ እኮ የሚቀድመን የለም።
ትዝ ይለኛል ሰኔ 22 ቀን 1983 ዓ.ም የኢትዮጵያን የሽግግር መንግሥት ቻርተር ለማጽደቅ ስብሰባ ነበር። ቻርተሩ ላይ «ይሄንን ቻርተር ተግባራዊ አድርጎ፣ ዴሞክራሲ አስፍኖ ቋሚ የሆነ መንግሥት ለማምጣት አንዳንድ ፀረ ቻርተር ኃይሎች የሚያደርጉትን ተቃውሞ መቋቋም ያስፈልጋል» ይላል።
ቻርተሩ ገና ሳይወጣ «ፀረ ቻርተር»ይሄ እንግዲህ ምን ማለት ነው። መንግሥት እዚያ ውስጥ የሚከታቸው ሰዎች አሉት ማለት ነው። መሆን ያለበት ቻርተሩ ከወጣ በኋላ የሚቃወሙት ከተፈጠሩ ነው ይህን ማለት። ሳይቃወሙ ቃሉን ማዘጋጀት የግፍ እና የአምባገነንነት ጅማሮ ነው። እነ እገሌን እዚህ ነው የማስገባቸው ብሎ የታሰበበት ነው።
ገመና መኖሩ ከምን አጎደለን ካልን፤ ከእውነታ አራቀን። ነገሮችን ሸፋፍነን ማስመጥ ሆነ። «እውነታን ስንሸፋፍን ያልሆነውን መምሰል ያምረናል»። ገመና በደብቅን ቁጥር ማስመሰል የዕለት ከዕለት ኑሯችን ይሆናል። ገመና መደበቅ ስንጀምር የማህበረሰቡን ፍላጎት ነው እየገደልን ያለነው።
ገመና አሁን በመንግሥት ደረጃ ሆኗል። የግብርና ሚኒስትር የነበረ ሰው ያጠፋው ጥፋት ተደብቆ እንደገና ሌላ ሚኒስትር ይደረጋል። እኛ እኮ እንኳን የራሳችንን የፈጣሪን ገመና እንኳን የምንሸፍን ነን። የአካል ጉዳት ያለበትን ሰው እንኳን ቤት ውስጥ እንደብቃለን።
አዲስ ዘመነረ ቅዳሜ ሰኔ1/2011