ቅድመ -ታሪክ
ቀኑን በተለየ ውሎ ያሳለፉት ባልቴት ምሽት ላይ የደከማቸው ይመስላል። ነገ ታላቁ የሁዳዴ ጾም የሚያዝበት ቀን ነው። ወይዘሮዋም ቀጣዩን የሁለት ወራት የጾም ቆይታ ለመጀመር ከጎረቤቶቻቸው ጋር የወጉን ሲያደርጉ አርፍደዋል። ከአንዱ ቤት ቡና፣ ከሌላው ቤት ቁርስና ምሳ ሲሉ የዋሉት ሴት ምሽት ላይ ጥቂት አረፍ ብለው ወደ መኝታቸው አምርተዋል።
ሴትዬዋ በዚህ ግቢ ብቸኛ ነዋሪ ናቸው። ገለል ብሎ የተሰራው መኖሪያቸው እምብዛም ከሌሎች ጋር የሚያገናኝ አይደለም። እሳቸው ደረቅ እንጀራ ሸጠው ስለሚያድሩ ሁሌም በደንበኞቻቸው ይጎበኛሉ። የሰፈሩ ወንደላጤዎች፣ ብቸኛ የሚባሉ ሴቶችና ሌሎችም የእሳቸውን እንጀራ ይመርጡታል። በመልካም ትህትና ተቀብለው በንጹህ አጥፈው የሚሸጡት እንጀራ ገበያ ስቦላቸዋል።
አሁን ምሽቱ ገፍቷል። ገና በጊዜ ደምቃ የወጣችው ጨረቃ በዳመና መሸፈን ጀምራለች። ጭርታ በዋጠው የገርጂው ካዛንቺስ መንደር የሚሰማው የውሾች ድምጽ ብቻ ሆኗል። ገና በጊዜ በራቸውን ዘግተው ጋደም ያሉት ወይዘሮ ዕንቅልፍና ድካም እያናወዛቸው ነው። ድንገት ግን በጆሯቸው ሽው ያለው የጣር ድምጽ ከነበሩበት አስፈንጥሮ አስነሳቸው።
በራቸውን ከፍተው እንደወጡ ጆሯቸውን ይዘው አዳመጡ። እየቆየ የሚሰማው ድምጽ ቀድሞ የሰሙት አይነት ነበር። ቀስ እያሉ ወደ ድምጹ አቅጣጫ ተራመዱ። የጨለማው ብርታት እንዳሰቡት አላሳያቸውም። በርቀት የወደቀ ነገር ያዩ መሰላቸው። ለመጠጋትም ለመራቅም ሲወላውሉ «እማማ፣ እማማ» የሚል ደካማ ድምጽ ተሰማቸው። ክው ብለው ደነገጡ።
ወይዘሮዋ ልባቸው እየመታ ወደሰውዬው ተጠጉ። ከአጥራቸው ጥግ የወደቀውን ሰው ጠጋ ብለው አስተዋሉት። ማንነቱ አልጠፋቸውም። በየቀኑ እንጀራ የሚገዛቸው ወንደላጤ ወጣት ነው። እሱ መሆኑን ሲያውቁ ከወደቀበት ሊያነሱት የአቅማቸውን ታገሉ። ገና እጃቸውን ሲያሳርፉበት ስቃዩ ገባቸው። ወጣቱ ክፉኛ በመጎዳቱ መነሳት አልቻለም።
በአካባቢው የቅርብ ጎረቤት የለም። የወጣቱ ጉዳት ከባድ መሆንም ጉዳዩን አላቀለለም። ጥቂት ቆይቶ ግን ከአጥሩ ውጪ የሰዎች ድምጽ ተሰማ። ይህን ያወቁት ወይዘሮ ሰዎቹን ለእርዳታ ጠሯቸው። እነሱም የሆነውን ሁሉ አውቀው መምጣታቸው ነበር። ወጣቱን ከወደቀበት ሲያነሱት ክፉኛ እየደማ ነበር። የስቃዩ ብርታትም ትንፋሹን ማድከም ጀምሯል።
ወደግቢው የገቡት ሰዎች በአካባቢው የተሰማውን የተኩስ ድምጽ ተከትሎ የደረሱ ናቸው። ወጣቱ በተተኮሰበት ጥይት መመታቱና መቁሰሉን አውቀዋል። ሰዎቹ ፈጥነው ወደ ፖሊስ ስልክ ደወሉ። በመጣው አምቡላንስም ቁስለኛውን ጭነው ወደ ሆስፒታል ፈጠኑ። ከፍተኛ ጣርና ጩኸት የሚያሰማው ወጣት ስቃዩን መቋቋም እየተሳነው ነው። ትንፋሹ መቀዝቀዝ አካሉ መድከም ይዟል።
ፖሊስና ለእርዳታ የመጡት ሰዎች የተጎዳውን ሰው ወደ ህክምና አድርሰዋል። ተጎጂው በጣር መሀልም ቢሆን ስለተፈጸ መበት ድርጊት ቃሉን እንዲሰጥ በማገዛቸው ተደስተዋል። ይህን አድርገው ዞር ከማለታቸው ግን የተጎጂው ህይወት ስለማለፉ መረጃ ደረሳቸው። ይህኔ ሁሉም በሁኔታው አዝነው አንገታቸውን ደፉ።
በወቅቱ የነበረው የፖሊስ ስሜትና አቅጣጫ ግን ከሌሎች የተለየ ሆነ። በተጨማሪ መረጃዎች ለድርጊቱ ተጠያቂ የሚያደርገውን አካል ለማግኘት እንቅስቃሴውን የጀመረው በፍጥነት ነበር።
የካቲት 3 ቀን 2003 ዓ.ም ምሽት
የዘንድሮውን ቅበላ በተለየ ሁኔታ ማሳለፍ የፈለጉት ጓደኛሞች ከረፋዱ ጀምሮ ተገናኝተዋል። ሳምንቱን ሙሉ በስራ በማሳለፋቸው የዛሬውን የዕረፍት ቀን በተለየ ሊያከብሩት አስበዋል።ሁሉም የስራ ውሏቸው ተመሳሳይ ነው። ካገራቸው እንጀራን ፍለጋ ሲወጡ ዓላማቸው ሰርተው ማግኘትና ራስን መለወጥ ነው። አብዛኞቹ የቀን ሰራተኞች ናቸው። ገሚሶቹ በግንበኝነት ገሚሶቹ ደግሞ በአናጺነት ሙያ ሲደክሙ ይውላሉ።
በአገር ልጅነትና በተለየ ቅርበት የተወዳጁት ባልንጀሮች ሁሌም ባይሆን አልፎ አልፎ እየተገናኙ መዝናናትን ለምደዋል። ተከራይተው በሚኖሩበት ሰፈር ብዙዎች ያውቋቸዋል።ጥቂቶቹ ትዳር መስርተው ልጆች አፍርተዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ እራሳቸው እያበሰሉ የሚመገቡ ናቸው። እንዲህ እንደ አሁኑ እረፍት በሆነ ጊዜም መንደራቸው መሀል ከሚገኝ አንድ ኮረፌ ቤት ያዘወትራሉ። እየተገባበዙና እየተጨዋወቱም ቀኑን ያጋምሳሉ።
የዛንዕለታም የሆነው ይኸው ነበር። ታደሰና ሁለት ጓደኞቹ ቅበላን ምክንያት አድርገው ተገናኝተዋል። የአቅማቸውን ሲቃመሱ ውለውም ወደ ኮረፌ ቤቱ አምርተዋል። ሰአቱ ለአይን ያዝ ቢያደርግም ከተቀዳላቸው ጠላ እየተጎነጩ መጫወታቸው አልቀረም። በየመሀሉ ለሽንት ወጣ እያሉ ይመለሳሉ። የጀመሩትን እየጨለጡም ሌላ ብርጭቆ ያስሞላሉ።
ሰአቱ ሁለት ሰአት ከሰላሳ ላይ እያመላከተ ነው። የጊዜው መምሸት ጓደኛሞቹን ከነበሩበት አስነስቶ ወደ ቤት ሊያጣድፋቸው ግድ ብሏል። ሁሉም ሂሳባቸውን ዘግተው አብረዋቸው ያመሹትን ተሰናብተው ወጡ። ጥቂት ተራምደውም ሶስቱ ጓደኛሞች ወደ አንድ ጥግ አመሩ። ጎን ለጎን ሆነው ጨዋታቸውን ቀጠሉ። የጠጡትን ሊያቃልሉ ለሽንት መቆማቸው ነበር።
ያሉበት ስፍራ ገለል ያለ አጥር ስር ነው። ጨለማው ደግሞ «አይን ቢወጉ አይታይም» ይሉት አይነት ሆኗል። ጥቂት ቆይቶ አንድ ጎልማሳ ወደ እነሱ ሲቀርብ ታዬ። ከአጥሩ ጥግ የቆሙት ሰዎችን ማወቅ የፈለገ ይመስላል። እየተጠጋ ማንነታቸውን ጠየቀ። አልመለሱለትም። አፍታ ቆይቶ ጥያቄውን ደጋገመ። አሁንም ዝምታ ተቀበለው። ሰውዬው ከቤቱ አጥር ስር የቆሙት ሰዎች ሁኔታ አላማረውም። ከመኖሪያው ጥግ ለሽንት መቆማቸው አብሽቆታል።
ጎልማሳው ወደሰዎቹ በቅርበት ተጠጋ። እየተጠጋ ማንነታቸውን ደጋግሞ ጠየቀ። ሶስቱ ጓደኛሞች ምላሽ ሳይሰጡት ዝም አሉ። ይህን ሲያውቅ ንዴትና ድንጋጤ ወረረው። የተናቀ የተተወ መስሎ ተሰማው። ምላሽ ባያገኝም ጥያቄውን አላቆመም። አሁንም ዝም መባሉ አናዶታል። የእነሱ ወደእሱ መቅረብም አስግቶታል። ጓደኛሞቹ ፊታቸውን ካዞሩበት መመለሳቸውን እንዳስተዋለ የመጨረሻውን ጥያቄ ሰነዘረ። አሁንም መልስ የለሹ ዝምታ ተቀበለው።
ሰውዬው ሁኔታው እያሰጋው ነው። በራሱ መኖሪያ አጥር ስር በአሳቻ ሰአት የመጡት ሰዎች ወዳጆቹ እንደማይሆኑ ጠርጥሯል። ለጥያቄው ዝምታ መምረጣቸውም ያለምክንያት እንዳልሆነ ገምቷል። በዚህ ሰአት ቤቱ አቅራቢያ የሚገኝ ጠላት እንጂ ሌላ አይሆንም። እናም ቅድሚያ ራሱን ማዳንና አጥቂዎቹን መመከት ይኖርበታል።
ጓደኛሞቹ ጉዳያቸውን ጨርሰው ከመራቃቸው በፊት ሰውዬው ፊት ለፊት ሮጦ ተጋፈጣቸው። አሁን ስለማንንታቸው መጠየቅ አላሻውም። ማድረግ ያለበትን ሁሉ ወስኗል። በእጁ የያዘው ማካሮቭ ሽጉጥ ጥይቶችን እንደቃመ ያውቃል። ሽጉጡን የገዛው ከእንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ራሱን ለመጠበቅ ነው። እናም አጥሩ ስር በቆሙ አጥቂዎች መቀደም የለበትም።
ሽጉጡን አቀባብሎ ወደ ሰማይ ተኮሰ። ሁኔታው ያስደነገጣቸው ወጣቶች በድንጋጤ በረገጉ። ሰውዬው ጊዜ አልፈጀም። በፍጥነት ወደጓደኛሞቹ አነጣጠረ። ጥይቶቹ ዒላማቸውን አልሳቱም። የመጀመሪያዎቹ ጥይቶች በቅርብ ባገኙት ታደሰ አካል ላይ አረፉ። ተኳሹ እጁን አልመለሰም። እንደገና አነጣጠረ። አሁንም ሌላውን ጓደኛውን አላጣውም። ሁለቱ ባልንጀሮች ፊትና ኋላ ሆነው ወደቁ። ባለ ግዳዩ ጎልማሳ ይህን እንዳወቀ ራሱን አረጋጋ። አሁን ጠላቶቹን ቀድሞ ጥሏል። የሚያስፈራና የሚያሰጋው የለም።
ሰውዬው ማኮሮቭ ሽጉጡን እንደያዘ አካባቢውን ላይና ታች ቃኘ። ከመሳሪያው ተኩስ በኋላ ውስጡ አልተረጋጋም። ፍርሀትና ድንጋጤ ያብረከርከው ይዟል። ድንገት አይኖቹን መለስ ሲያደርግ በአካባቢው ከሚገኝ ባለሱቅ ጋር ተጋጠመ። ባለሱቁ ሰዎቹን ተኩሶ እንደመታ አይቷል። ይህን እንዲያውቅበት ግን አልፈለገም። ሰውዬው ሽጉጡን በእጁ እንደያዘ በመቆየቱ እሱንም እንዳይገድለው ሰግቷል።
ታደሰ ከባልቴቷ አጥር ግቢ እንደምንም ተስቦ ከደረሰ በኋላ በእሳቸውና በሌሎች እርዳታ ሆስፒታል ቢደርስም መትረፍ አለመቻሉ ብዘዎችን አሰዛኗል። ሁለቱ ጥይቶች በግራ ደረቱ በኩል በመግባታቸው ጉዳቱ የከፋ ነበር። ፖሊስ ሆስፒታል አልጋ እንዳረፈ ቃሉን ሊቀበለው ሞክሯል። ወጣቱ በሞትና ህይወት መካከል ሆኖ እንደምንም ለመናገር ችሏል።
የዛንዕለት ምሽት እሱና ጓደኞቹ ወደ አጥሩ የተጠጉት ለሽንት እንጂ ለሌላ ጉዳይ አልነበረም። ሰውዬው በሽጉጥ ጥቃት ከማድረሱ በፊት ደጋግሞ ቢጠይቃቸውም ጉዳዩን ነገሬ ሳይሉ አልፈውታል። ታደሰ ስለ ጎልማሳው አጥቂ ማንነት ፈጽሞ አያውቅም። ከላይ የለበሰው ቀይ ሹራብ ስለመሆኑ ግን ትውስ ብሎታል። ፖሊስ ሌሎች ጥያቄዎችን ለመጨመር ባይቻለውም ከሟች ያገኛቸው መረጃዎች ጠቃሚ ነበሩ።
የታደሰ የቅርብ ጓደኛ በተተኮሰበት ጥይት ተመቶ ቆስሏል። ጉዳቱ ቀላል ባይሆንም ለሞት የሚያበቃው አልነበረም። እሱም ቢሆን ለፖሊስ የሰጠው ቃል ከሟች ጓደኛው የተለየ አልነበረም። በጥይት ጥቃት ካደረሰባቸው ሰው ጋር ትውውቅም ሆነ ጠብ የላቸውም። ከዚህ ቀድሞም ቢሆን በአይን አይተውት አያውቁም።
ከድርጊቱ በኋላ ሰውዬው ከአካባቢው መሰወሩ ተሰምቷል። ስለማንነቱ ለማወቅ ለፖሊስ ብዙ ውጣውረድ ባይኖረውም እጁን ያለመስጠቱና ከስፍራው መሰወሩ ግን ዕንቅልፍ የሚነሳው ሆኗል። ፖሊስ የዛንዕለት ምሽት በደረሰው መረጃ ከሰውዬው መኖሪያ ደርሷል። ዙሪያ ገባውን ከቦም እጁን በሰላም እንዲሰጥ ጠቋል። ሰውዬው ግን አስቀድሞ ባዘጋጀው የጓሮ በር አምልጦ ከአካባቢው ተሰውሯል።
ፖሊስ ከወንጀሉ መፈጸም ማግስት የተጠርጣሪውን መኖሪያ ለመፈተሽ ባደረገው ጥረት የሽጉጡን መሰል ጥይቶች አግኝቷል። ከአካባቢው ሰዎችም ስለማንነነቱና ስለቤተሰቦቹ ሁኔታ ጠይቆ ተረድቷል። በወቅቱ ግለሰቡን ለመያዝ አልተቻለም። ተጠርጣሪው ሰፈር መንደሩን ርቆ ከአካባቢው መሰወሩ ተረጋግጧል።
አቶ መኮንን ደበበ በአካባቢው ከሚታወቁ ነባር ነዋሪዎች መሀል አንዱ ነው። ውልደትና እድገቱ ገጠር ቀመስ በመሆኑ ሲያርስና ከብቶችን ሲያረባ ቆይቷል። ያለበት አካባቢ ከተማ መሆን ሲጀምርና አካባቢው ሲለወጥ ደግሞ ህይወቱን እንደ ወቅቱ አመሳስሎ መኖር ጀመረ። በሚኖርበት ግቢ የቆርቆሮ ቤቶችን ገንብቶ እያከራየና ከብቶችን እያረባ ህይወቱን ማቅናት ያዘ።
አስተዳደጉ ከእርሻ ህይወት የራቀ ባለመሆኑ ቤቱ ሁሌም ጎድሎ አያውቅም። ትዳር መስርቶ ዘጠኝ ልጆችን የሚያሳድገው ይዞት ከቆየው ሀብትና ጥሪቱ በመሆኑ እስከዛሬ ጓዳው እንደሞላ ቆይቷል። ወላጆቹ እሱ ከሚኖርበት አካባቢ የቀረቡ በመሆናቸው ቤተሰቡ የሰፋና በቁጥር የበረከተ ነው። ጊዜ ሲለወጥና ሀብት ሲጨምር ጎልማሳው አባወራ ራሱንና ቤተሰቦቹን መጠበቅ እንዳለበት ሲሰማው ቆይቷል።
መኮንን እራሱን ለመጠበቂያ ሲል የገዛው የማካሮቭ ሽጉጥ ከጎኑ ተለይቶት አያውቅም። ከቤቱ በራቀና በተራመደ ቁጥር ለሚገጥመው ችግር ሁሉ የዋስትና ያህል ይቆጥረዋል። ሽጉጡን ይዞ ሲዘዋወር ማንም እንደማይደፍረው ይሰማዋል። ከእሱ ጠብና አጉል ንግግር የሚሹ ሁሉ የጎኑ መሳሪያ ማስታገሻ የሆነ ያህል አብሮት ሲዞር ቆይቷል።
የቅበላው ፍጻሜ
ዕለቱ ለመጪው የሁለት ወራት የጾም ጊዜ ቅበላ የሚደረግበት ነው። ይህን ቀን ምክንያት አድርገው እንደየቤታቸው የሚዘጋጁ አንዳን ዶችም የአቅማቸውን ሲያደርጉና ሲገባበዙ ውለዋል። መኮንንም ይህን ቀን በተለየ ሁኔታ ለማሳለፍ ያሰበ ይመስላል። እንደአባወራነቱ ለቤቱ የሚገባውን አድርጎ ወደ ቤተሰቦቹ መኖሪያ የሄደው ገና በጠዋቱ ነበር። አዛውንት እናት አባቱን አስደስቶ ጾም ማስያዝና የሚገባውን ምርቃት መቀበል ለእሱ የተለመደ ነው።
ቀኑን በተለየ ደስታ ያሳለፈው መኮንን አመሻሽ ላይ ሁሉን ተሰናብቶ ወደመጣበት መመለስ ጀምሯል። ምሽት ሁለት ሰአት ከሰላሳ አካባቢ ወደ ሰፈሩ እንደተቃረበ የቤቱን አቅጣጫ ይዞ ተጓዘ። በሩ አጠገብ ከመድረሱ ግን ሶስቱን ሰዎች በርቀት አያቸው። ሁሉም ፊታቸውን ወደሱ ቤት መግቢያ በር አዙረዋል። ሁኔታቸው አላማረውም።
መኮንን ቀረብ ብሎ ማንነታቸውን ሊያጣራ ፈለገ። እነሱ ግን ሊነግሩት አልፈቀ ዱም። ሁኔታቸው በእጅጉ አናደደው። እንዲህ አይነቶቹን እምቢተኞች በምን ማስታገስ እንዳለበት ከራሱ መከረ። ምክሩ «ልክ ነህ» ሲል ለውስጡ አቀበለው። ሰዎቹ ምንአልባትም ሌቦች አልያም ሊጎዱት የሚሹ ጠላቶች ይሆናሉ። ይህ ሁሉ ሀሳብ ለመኮንን ትክክል ነበር።
አከታትሎ የተኮሰው ጥይት ሁለቱን መቶ እንደጣላቸው አረጋግጧል። ከዚህ በኋላ ግን አልተረጋጋም። በፍጥነት ከቤቱ ገብቶ መምለጫውን አመቻቸ። ቤተሰቦቹን አስጠንቅቆና ከእነሱ መክሮም በጓሮ በር ሮጦ አመለጠ። ጥቂት ቀናት ቆይቶ በጥይት ከመታቸው መሀል አንደኛው ስለመሞቱ ሰማ።
ፀፀት ያሰደደው ሽሽት
መኮንን የአንዱን ወጣት መሞት ከሰማ በኋላ በሀሳብና በጸጸት መብከንከን ይዟል። በሰራው ድንገተኛ ወንጀል ቤተሰቡን ተለይቶ የገነባውን ትዳር ማፍረሱ እያስቆጨው ነው። ያም ሆኖ ግን ራሱን ለህግ አሳልፎ መስጠትን አልፈለገም። በእጁ የሚገኘውን መሳሪያ እንደያዘ ከእህቱ ቤት ለወራት ተደበቀ። አልፎ አልፎ ሹልክ እያለ መኖሪያው ይመጣና ልጆቹን አይቶ ይመለሳል። እግረ መንገዱንም ስለሱ የሚወራውን እያጣራ ራሱን ይጠብቃል። ይጠነቀቃል።
አንድ ቀን አቶ መኮንን የቅርብ ጓደኛና አብሮ አደጉ ከሆነው ዘውዱ ቤት በማለዳ ገሰሰ። ዘውዱና መኮንን አበልጆች ናቸው። ዘውዱ ጓደኛውን ሲያየው ደነገጠ። ስለሱ ሰምቶ ስለነበር በጨዋታ መሀል እጁን ለህግ እንዲሰጥና ራሱን ነጻ እንዲያወጣ ሊመክረው ሞከረ። መኮንን ያልጠበቀው ሀሳብ በመሆኑ ድንገቴው ምክር አልተመቸውም። ጥቂት ቆይቶ ግን ከእህቱ እንደሚማከር ነገረው።
መኮንን ጓደኛውን አንድ እቃ በአደራ እንዲያስቀምጥለት ጠየቀው። የአደራ ዕቃው የሰው ህይወት ያጠፋበት ማካሮቭ ሽጉጥ ነበር። ዘውዱ ሽጉጡን እንደተቀበለ አስራ ሁለት መሰል ጥይቶቹን ቆጥሮ አስረከበው። በቅርቡም ተመልሶ እንደሚመጣ ነግሮት ተሰናበተው። ይህ ከሆነ ወራት ተቆጠሩ። መኮንን እንደ ቃሉ ሳይሆን ቀርቶ ድምጹን አጠፋ። ጓደኛውም መሳሪያውን ይዞ ደጁን ሲያይ መዋል ልማዱ ሆነ።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ የወንጀል ድርጊቱ በማን እንደተፈጸመ መረጃ ከደረሰው ወዲህ ተጠር ጣሪውን ለመያዝ ክትትሉን ቀጥሏል። መኮንን ይገኝባቸዋል በተባሉ ስፍራዎች ሁሉ የሲቪል ክትትል አባላቱን አሰማርቷል። የፖሊስ መዝገብ ቁጥር 391/2003 በየዕለቱ የሚገኙ ማስረጃዎችን እየመዘገበ ነው።
ከዕለታት በአንዱ ቀን ፖሊስ ተጠርጣሪ መኮንን እግር በእግር ተከታትሎ በቁጥጥር ስር አዋለው። መኮንን በህግ ጥላ ስር ከዋለ በኋላ ስለፈጸመው ድርጊት ሁሉ አምኖ ቃሉን ሰጠ። በጥርጣሬ መንፈስ ተነሳስቶ የማያውቀውን ሰው ህይወት ማጥፋቱና አካል ማጉደሉም በእጅጉ እንደሚጸጽተው ተናገረ።
ፖሊስ ጥያቄውን ቀጠለ። ወንጀሉን የፈጸመበት ጦር መሳሪያ የት እንደሚገኝ ጠየቀው። መኮንን ያደረገውን አልደበቀም። ከመሰል አስራ ሁለት ጥይቶቹ ጋር ለአበልጁ ለአቶ ዘውዱ እንደሰጠው ተናገረ። ጊዜ ያልፈጀው ፖሊስ ዘውዱ ይገኝበታል ከተባለ ስፍራ ሄዶ በቀጥጥር ስር አዋለው። ግለሰቡንም በወንጀል ተባባሪነት ተጠያቂ ሊያደርገው ክስ መሰረተበት።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ1/2011
መልካምስራ አፈወርቅ