
የሰው ልጅ በህይወቱ ድጋፍን የሚሻ ደካማ ፍጥረት ነው። ማንም ይሁን ማን የሚደገፍበትን ትከሻ መመኘቱ ከሰውነት መለኪያ መስፈርት ውስጥ ይመደባል። በተለይም ሰውን ደግፎ ለማቆምና ለማበርታት እንደ አባት ምቹ ትከሻ ያለው የለም። አባትነት በእምነት የተገነባ በጠንካራ የፍቅር ሰንሰለት የተሰናሰለ ድንቅ ቁርኝት ነው።
‹‹አባት›› የሚለው ቃል ብዙ ጊዜ የአንድ ነገር ምንጭ ወይም ጀማሪ የሚል ትርጓሜን ይይዛል፡፡ ‹‹አባት›› ማለት ተፈጥሮውን ‹‹ለልጆቹ›› የሚያስተላልፍ ማለት ነው፡፡ ‹‹አባት›› ማለት በልጆቹ ላይ ስልጣን ያለው ማለት ነው፡፡ ምድራዊ ልጆች ሰውነታቸውንና ነፍሳቸው ከወላጆቻቸው ይወስዳሉ፡፡ አባትነት በሰው ሰውኛ ሲገለፅም ልዩ ምስጢር አለው።
አባትነት እምነት፤ እናትነት እውነት በሚል ብሂልም አባት መሆኑን በእምነት አምኖ ተቀብሎ ለልጆቹ ጥላ ሆኖ ከመከራ ከልሎ ሲያሳርፍ፤ ማደጋቸውን በጉጉት እየተመለከተ ነጋቸውን በአይነ ህሊናው ሲቃኝ፤ በእርጅናው ደግሞ በፀሎት የልጆቹን ቀና መንገድ ሲመኝ የሚኖር ታላቅ ገፀ በረከት ነው አባትነት።
ታዲያ ይህን የአባትነት ሚስጢር ያፈረሰ ትስስሩን ባልተገባ መንገድ የበጠሰ አባት ሲገኝ የጎደለውን የአባትነት እምነት ሲታይ የኑሮ ሚዛኑ ተዛባ አያሰኝ ይሆን እላለሁ። አባት ጠባቂ መደገፊያ ማምለጫ መሆን ሲገባው እራሱ የመከራ ቋት ሆኖ ሲገኝ ማን ይወቀሳል። ለዛሬ ተናጋሪ ዶሴ አምዳችን የ8 ዓመት የእንጀራ ልጁን አስገድዶ የደፈረው ግለሰብ ልናካፍላችሁ ወደድን።
ይህን የወንጀል ታሪክ ኅብረተሰቡን በሚያስተምር መልኩ ይቀርብ ዘንድ የፈቀዱልንን የአዲስ አበባ ፖሊስ መዝገብ ቤት ሰራተኞች እያመሰገንን ታሪኩን በዚህ መልኩ አቅርበነዋል። መልካም ንባብ።
እናትና ልጅ
ገና በአፍላው የወጣትነት ዘመኗ ነበር ከተወለደችባት ቀዬ የወጣችው። ያኔ ከድህነት ለማመለጥ አቅዳ ነበር ወደ አዲስ አበባ የመጣችው። ከድህነት አመልጥበታለሁ ያለችበት ስራ የልጅነት ልጇን እስኪያሳቅፋት ድረስ ያገኘቻትን ገንዘብ እየቆጠበች ሕይወቷ ለማሻሻል ትታር ነበር።
በአንዲት ክፉ ቀን በሠራተኝነት የተቀጠረችበት ቤት የሚኖር የዘመድ ልጅ በክፉ አይኑ ተመለከታት። በወቅቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረው ወጣት የአስራ አምስት አመቷ የገጠር ጉብል ላይ አይኑ አረፈ። ከእለታት በአንዱ ቀን ለአመታዊ ክብረ በዓል የቤቱ ሰው በሙሉ ተለቃቅሞ ለንግስ ጉዞ ሄደ። ያኔ እሷና የዘመድየው ልጅ ቤት ቀሩ። ይህች የዋህ የገጠር ልጅ እንደለመደችው ሥራዋን ሠርታ ለልጁ እራት አቅርባ ወደ መኝታዋ ሄደች። ከዚያም መአድ ቤት ውስጥ ፍራሽ አንጥፋ ጋደም ከማለቷ ነበር እንቅልፍ ይዟት ጭልጥ ያለው።
ድብን ያለ እንቅልፍ ውስጥ መግባቷን የተመለከተው ወጣትም ቀድሞ አይኑ ያረፈባትን ልጅ ተመኘ። ልጅቱ ከእንቅልፏ የነቃችው ወጣቱ እንዳትነቃነቅ አድርጎ ካሰራት በኋላ ነበር፡፡ እኩይ ተግባሩን ለመፈፀም አቅዶ የነበረው ወጣት ቀድሞ በተዘጋጀው መንገድ እጇን አስሮ አፏን በጨርቅ ጠቅጥቆ ግብረ ስጋ ግንኙነት ፈፀመባት።
ያላሰበችው ነገር የደረሰባት ወጣት ቤታቸውን አደራ ሰጥተዋት የሄዱት ሰዎች ወደ ቤታቸው ሳይመለሱ ጨርቄን ማቄን ሳትል ማልዳ ተነስታ እንደ ወፍ በራ ጠፋች። ጠፍታ እራሷን አጠናክራ ህክምና አድርጋ ወደ ሥራዋ ለመመለስ ስታስብ ነፍስ ጡር መሆኗን ሰማች።
ይህንን ስትሰማ ሰማይ ምድሩ የተደፋባት ይቺ ሴት ዘመድ ጋር ተጠግታ ልጇን ወለደቻት። ከዚያም በየሰው ቤቱ እየሠራች እስከ አምስት ዓመት እድሜዋ ድረስ ብቻዋን አሳደገቻት። ከዚያም ኑሮ እየከበዳት፤ የልጇም ፍላጎት እየጨመረ ሲሄድ ካላገባሁሽ እያለ የሚያስቸግራትን ሰው ጥያቄ ተቀበለች።
ይህ ሰው ልጇን እንደ ልጁ እየተንከባከበ ያሳድግላት ጀመር። አዲሱ ባልና ሕጻኗን አብረው ለተመለከታቸው አባትና ልጅ እንጂ እንጀራ አባትና እንጀራ ልጅ አይመስሉም ነበር።
ያልታሰበው ጥቃት
ባሏ ለልጇ መልካም አባት መሆኑ ያስደሰታት ሴት ሙሉ ትኩረቷን ወደ ሥራ አድርጋ ለእድገት ትጣጣር ነበር። ባልም በትርፍ ጊዜው በሙሉ ልጅቷን መንከባከብ ሥራው ነበር። እንደ አባት አስፈላጊውን ነገር በሙሉ እያሟላላት ያስተምራት ጀመር።
ልጅቷ የቅድመ መደበኛ ትምህርቷን አጠናቃ አንደኛ ክፍል ገባች። በእንክብካቤ በመያዟ የተነሳ ቁመቷ አድጎ ቆንጆ ልጅ ሆነች። አባዬ የምትለው አባትም የልጅቷ ቁመት ሲያደግ እድሜዋን ረስቶ በክፉ አይኑ ይመለከታት ጀመር። የሁለተኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ልጅ በትምህርቷ ጎበዝ ቀልጣፋና ታዛዥ ነበረች።
እናት የራስዋን ቁስል ዋጥ አድርጋ ልጇን ለማሳደግ አቅም የሰጣትን ባለቤቷን እጅግ ከማመኗ የተነሳ ልጇ ላይ እንኳን ጥቃት ቁንጥጫ ያሳርፍባታል ብላ አታስብም ነበር።
ታሪክ ራሱን ይደግማል ሆኖ እናቷ የቀመሰችውን ፅዋ ልጅቷም ባመነችው ሰው እንድትቀምስ ተፈረደባት። አባት ለድጋፍ ለእቅፍ እንጂ ለጉዳት ሳይታሰብ የልጅቷን ህልም አጨለመው።
አባትየው ሙአዝ ከፈለኝ ይባላል። ታህሳስ 1 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 6፡00 ሰዓት በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ቦታው ካራ ጋቢሳ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤት ውስጥ አባትና ልጅ እንደ ሁልጊዜው ተቀምጠው እየተጫወቱ ነበር።
ይህች የ8 ዓመት ዕድሜ ያላትንና በራሱ ቁጥጥር ስር የሚያሳድጋትን የእንጀራ ልጁን ከትምህርት ቤት ስትመጣ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ተቀምጦ ያገኘችውን አባቷን ስማ አጠገቡ ተዝናንታ ተቀምጣ ነበር። የእናቷን አለመኖር የተመለከተው ይህ ሰው ልጅቷን አፏን አፍኖ አስገድዶ ደፈራት።
ይህ ድርጊት እንዳይታወቅበት ልጅቷን ቢላ ይዞ “ብትናገሪ አንችንም እናትሽንም እገላችኋለሁ“ በማለት ዝም እንድትል ያደርጋታል። ልጅቷ ከዚያ ቀን አንስቶ ደስታዋ መጥፋቱን እናት ብታስተውልም የልጅ ነገር ነው በማለት ቸል ትላታለች። ሰውየው ግን የሠራው ጥፋት ሳይነቃበት በመቆየቱ ሕጻኗን እየደጋገመ ይደፍራት ጀመር።
ከእለታት አንዱ ቀን እናቷ ሥራ ውላ መጥታ እንደተለመደው ልጇን ውሃ ስጪኝ ስትላት መንቀሳቀስና ከመቀመጫዋ መነሳት አለመቻሏን ትመለከታለች። እናቷም ስትጠይቃት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ አባቴ የምትለው ሰው ያደረገባትን ነገር በዝርዝር ትነግራታለች። ሙአዝ የተባለው የሴትዮዋ ባለቤት በተደጋጋሚ እንደሚደፍራት እና ቢላ ይዞ “ብትናገሪ አንችንም እናትሽንም እገላችኋለሁ“ እያለ ያስፈራራት እንደነበር ለእናቷ ትነግራታለች።
ከሥራ ደክሟት የመጣችው እናት በራሷ የደረሰው ቁስል በልጇ መድረሱን ስትሰማ እንደ እብድ እያደረጋት ወደ ፖሊስ ጣቢያ በረረች። ፖሊሶቹን የደረሰባትን ነገር በሙሉ በእንባ በማጀብ አስረድታ ወደ ቤት ይዛቸው መጣች። ፖሊስ አድብቶ አራጁን አባት በቁጥጥር ሥር አዋለው።
ልጇን ወደ ህክምና ሳትወሰድ ማደር የተሳናት እናት በማታ ይዛት ሆስፒታል ሄደች። በድንገተኛ ክፍል ተቀብለው ያስተናገዷት ሀኪሞችም ጉዳቱ የከፋ ባይሆንም የሥነ ልቦና ጉዳቷ ከፍ ያለ መሆኑን ነግረው ክትትል እንድታደርግ መክረው ወደ ቤት ላኳት። ባመነችው የተከዳችው እናት ልጇን አቅፋ ፍትህ እስክታገኝ መጠባበቅ ጀመረች።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር ካዋለ በኋላ ምርመራውን ቀጠለ። የልጅቷን ቃል፤ የህክምና ምርመራ ወረቀትን ይዞ የእምነት ክህደት ቃሉን ለመቀበል ቁጭ አሉ። መጀመሪያ ላይ ጉዳዩን ማመን ባይፈልግም ምርመራው እየጠነከረ ማስረጃዎች እየወጡ ሲሄዱ ሰውየው ጥፋቱን አምኖ መቀበል ግድ ሆነበት።
ተጠርጣሪው ጥፋተኛ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ ቁጥር 627/1/እና 627/4/ሀ/ ሥር የተመለከተውን በመተላለፍ ለአካለ መጠን ያልደረሰችን ልጅ በተለያዩ ቀናት እና ጊዜ በተደጋጋሚ አስገድዶ በመድፈር ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ለዐቃቤ ህግ አቀረበ፡፡
የዐቃቤ ህግ ክስ ዝርዝር
የዐቃቤ ህግ ማስረጃ ከተመለከተ በኋላ አስፈላጊውን ሥርዓት ይዞ ለፍርድ የሚቀርብበትን አካሄድ ጀመረ። ዐቃቤ ህግ ያገኘውን ማስረጃ በመጠቀም በዚህ መልኩ የክስ ዝርዝሩን አቅርቧል።
ሙአዝ ከፈለኝ የተባለው ተከሳሽ ታህሳስ 12 ቀን 2016 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 5፡00 ሰዓት በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ቦታው ካራ ጋቢሳ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የ8 ዓመት ዕድሜ ያላትንና በራሱ ቁጥጥር ሥር የሚያሳድጋትን የእንጀራ ልጁን ከትምህርት ቤት ስትመጣ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ አፏን አፍኖ አስገድዶ ከደፈራት በኋላ እናቷ ከሥራ መጥታ ውሃ ስጪኝ ስትላት መንቀሳቀስና ከመቀመጫዋ መነሳት ባለመቻሏ እናቷም ስትጠይቃት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በተደጋጋሚ እንደሚደፍራት እና ቢላ ይዞ “ብትናገሪ አንችንም እናትሽንም እገላችኋለሁ“ እያለ ያስፈራራት የነበረ በመሆኑ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ ቁጥር 627/1/እና 627/4/ሀ/ ሥር የተመለከተውን በመተላለፍ ለአካለ መጠን ያልደረሰችን ልጅ በተለያዩ ቀናት እና ጊዜ በተደጋጋሚ አስገድዶ በመድፈር ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት ቀርቧል፡፡
ውሳኔ
በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ህግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ቢሰጠውም ተከሳሽ ዐቃቤ ህግ ያቀረበበትን ክስና ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ በተከሰሰበት ወንጀል የጥፋተኝነት ብይን አስተላልፎበታል፡፡
በመሆኑም የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የካ ምድብ 7ኛ ወንጀል ችሎት ተካሣሹን ያስተምራል፣ ያርማል ሌላውንም የማኅበረሰብ ክፍል ያስጠነቅቃል በማለት በ15 (አስራ አምስት) ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም