ዶክተር ፋንታዬ ይማሙ ተወልደው ያደጉት በድሮው በወለጋ ክፍለ ሀገር ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ነቀምት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤትና በአርጆ አውራጃ ቢትወደድ መኮነን ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ግንቢ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
በትምህርታቸው ታታሪና ጎበዝ ስለነበሩ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል አንደኛ በመውጣት አንዳንዶቹን ክፍል ዘለው (ደብል መተው) ለማለፍ ችለዋል። በዚህም እርሳቸው ገና በዘጠኝ ዓመታቸው አራተኛ ክፍል መድረስ የቻሉ ሲሆን፤ የዛሬ 50 ዓመት የአራተኛ ክፍል ተማሪ እያሉ «ይሄ ነበር ምኞቴ» የሚል ድርሰት ለመጻፍ ችለዋል። ድርሰቱም ሳይማር ያስተማራቸውን ድሃ ወገናቸውን ለመጥቀም ገና በለጋ ዕድሜያቸው ቁጭት እንደ አደረባቸው የሚያሳይ ነው።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ከፍተኛ ውጤት አምጥተው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1973 ዓ.ም ተቀላቀሉ። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን እግራቸው በረገጠ ማግስት ገና የከፍተኛ ትምህርታቸ ውን ሀብለው ሳይጀምሩ፤ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን(ኢሲኤ) በኩል የውጭ የትምህርት ዕድል አገኙ። ህብረቱም ከስድስት አገሮች መካከል በአንዱ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ዕድሉን ያመቻቸላቸው ሲሆን፤ ወደ ጣሊያን አገር በመሄድ ትምህርታቸወን ለመከታተል ወሰኑ።
ወደ ጣሊያን አገር በማቅናት ከአንኮናይ ዩኒቨርሲቲ በፊዚዮ ቴራፒ (alternative medicine) ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ መከታተል ችለዋል። እርሳቸውም ለ34 ዓመት በጣሊያን አገር ሲኖሩ ለአገራቸው ባላቸው የጠለቀ ፍቅር እርሳቸውም ሆኑ ልጆቻቸው ዜግነታቸውን ሳይቀይሩ እየኖሩ ይገኛሉ።
በዚህም እርሳቸውና ልጆቻቸው ዜግነታቸውን ስላልቀየሩ በጣሊያን አገር በሚገኙ የመንግሥት መስሪያቤቶችም ሆነ ሆስፒታሎች ተቀጥረው መስራት ስለማይችሉ፤ ልጆቻቸው በግል ድርጅቶች ተቀጥረው ሲሰሩ እርሳቸው የራሳቸውን የፊዚዮ ቴራፒ የሕክምና ማዕከል አቋቁመው እየሰሩ ይገኛሉ።
ዶክተሯም በሚኖሩበት ጣሊያን አገር በሕክምና ሙያቸውም አንቱታን ያተረፉ ሲሆን፤ ከዕለታት በአንድ ቀን አንድ ጣሊያናዊ ዝነኛ ሰው የተለያዩ የጤና ተቋማትና ሆስፒታሎች ተንከራቶ መዳን ሳይችል ቀርቶ ዶክተር ፋንታዬ ጎበዝ ባለሙያ መሆናቸውን ሰምቶ እርሳቸው ዘንድ በመምጣት ፈውስን በማግኘቱ «ግሩም የአበሻ እጅ ነው» ብሎ በማድነቅ በአንዴ በፍቅራቸው ተጠምዶ የጋብቻ ጥያቄ አቀረበላቸው። እርሳቸውም የትዳር ጥያቄውን ይሁንታ ሰጥተው ከዚህ ሰው ጋር ትዳር መስርተው ልጆች አፍርተዋል።
በዚህም ይህ ጣሊያናዊ ባለቤታቸው ለውለታቸው ምን እንዲያደርጉላቸው ሲጠይቋቸው፤ ዶክተሯም በአገራቸው ላይ ሳይማር ያስተማራቸውን ማህበረሰብ የሥራ ዕድል የሚፈጥርና የዳቦ ጥያቄውን የሚመልስ ፋብሪካ እንዲከፍትላቸው በመሻታቸው፤ ጣሊያናዊው ባለቤታቸው የተለያዩ ፋብሪካዎችን በኢትዮጵያ ሊከፍቱላቸው ችለዋል።
ዶክተር ፋንታዬ ይሄን አጋጣሚ በመጠቀም ሆስፒታል ብከፍት የተማረው የሰው ኃይል ነው የሥራ ዕድል የሚያገኘው። ስለዚህ ሳይማር ያስተማረኝ ድሃው ማህበረሰብ በቀየው የሥራ ዕድል እንዲያገኝ እና ለልጆቹ የዳቦ ጥያቄው መልስ እንዲሰጥ፤ እንዲሁም የገጠሩ ማህበረሰብ የሥራ ዕድል አግኝቶ ሳይቸገር ለልጁ ደብተር እና እስክርቢቶ እንዲገዛ የዛሬ 16 ዓመት በዓለም ላይ የመጀመሪያውን የጤፍ፣ፓስታና ማካሮኒ ፋብሪካ በአገራቸው መክፈት ችለው ነበር።
የፈጠራ ሥራቸውን ሀብለው የጀመሩት በዚህ ሥራ ሲሆን፤ ከጤፍ፣ ከአትክልት፣ ከጥራጥሬ፣ ከፍራፍሬ እንዲሁም በአገር ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ግብዓቶችን በመጠቀም 11 የሚደርሱ የፈጠራ ሥራዎችን በመስራት በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት በፈጠራ ባለቤትነት መብት ለማስመዝገብ በቅተዋል።
የጤፍ ፓስታና ማካሮኒ
ይህን ሥራ ከዛሬ 16 ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ቃሊቲ አካባቢ ግራኖ ዶሮ (ወርቃማው እህል) የሚል የፓስታና ማካሮኒ ፋብሪካ አቋቁመው መስራት ጀምረው ነበር። እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ገላን ከተማ ሚያ የፓስታና ማካሮኒ ፋብሪካ አቋቁመው ሲሰሩ የነበረ ሲሆን፤ በሁለቱ ፋብሪካም ለ360 ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። በዚህም ኢትዮጵያ በዓለም የመጀመሪያዋ የጤፍ፣ ፓስታና ማካሮኒ አምራች አገር በመሆን የፈጠራ ባለቤትነት መብት የምስክር ወረቀት ለማግኘት በቅታለች። ይሄም ምርት በአሜሪካን አገር የኤፍዲአይ ምስክር ወረቀት (food and rad administration certificate) ያለው ሲሆን፤ ወደ አሜሪካ ከሚገቡ ጥቂት የአፍሪካ ምርቶች መካከል አንዱ ለመሆን በቅቷል። በአሜሪካ 1ኪሎ ፓስታና ማካሮኒ በ120 ዶላር ይሸጣል።
ይሄንን የፈጠራ ሥራ ከጤፍ በተጨማሪ በጠቅላላ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ጥራጥሬዎችን በመጠቀም የሰሩ ሲሆን፤ ውሃ ሳይጨመርበት በአትክልትና በፍራፍሬ ጭማቂ የተሰራ ፓስታና ማካሮኒ ነው። ምርቱም ከተለያዩ የፍራፍሬና የአትክልት ጭማቂ በተገኘ ቀለም በማስዋብ ለዓይን ሳቢ እንዲሁም ጣፋጭ ተደርጎ የተሰራ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ባለቀለም የአትክልት ፓስታና ማካሮኒ እንዲሁም ከተለያዩ ጥራጥሬዎች የጥራጥሬ ወተት በማዘጋጀት በፈጠራ ባለቤትነት መብት ማስመዝገብ ችለዋል።
የስኳር እና የኮሊስትሮል መድኃኒት
ጤፍ በንጥረ ነገር የበለጸገ ሲሆን ስምንት ንጥረ ነገሮችን በውስጡ ይዟል። በመሆኑም ጤፍን እንደ ዋና ግብዓትነት በመጠቀም ከተለያዩ ጥራጥሬዎች፣ ፍራፍሬዎች እና አትክልቶች ጋር በመቀላቀል የሕፃናትና የአዛውንቶች ምግብ ማዘጋጀት ችለዋል። ይሄም አንድ የፈጠራ ሥራ ሥራቸው ሲሆን፤ የስኳር እና የኮሊስትሮል መድኃኒትን በተመሳሳይ ጤፍን እንደ ዋና ግብዓትነት በመጠቀም ከተለያዩ ጥራጥሬዎች፣ አትክልቶችና ፍራፍሬዎች ማዘጋጀት ችለዋል። እርሳቸውም ስለ አሠራሩ እንዳብራሩት ጤፍ፣ ጥቁር ሽንብራ፣ አጃ፣ ገብስ፣ እና ዳጉሳ ተፈጭቶ አንድ ላይ ይቀላቀላል። እንዲሁም አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ እጽዋቶችን እና ቅመማቅመሞችን ጨምሮ በማቀላቀል እንደሰሩት ጠቁመዋል። ይሄንንም አንድ ላይ በማዋሃድ የንጥረ ነገር ይዘቱ እንዳይሞት በፀሐይ ብርሃን ይበስላል። ከዚህ ውህድ ለስኳር በሽተኞችና ከፍተኛ ኮሊስትሮል መጠን ላለባቸው ሰዎች ፍቱን መድኃኒት በእንክብል መልክ ይዘጋጃል። በተጨማሪም ከዚህ ውህድ ለሕፃናትና ለአዛውንቶች ምግብ ይዘጋጃል።
የዳቦ ክሬም
ይሄንን የፈጠራ ሥራ ጠቅላላ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ እንደ ሱፍ፣ ሰሊጥ፣ የዱባ ፍሬ፣ ተልባ፣ ኑግ፣ ባቄላ፣ አጃ፣ ገብስ፣ ዝንጅብል፣ ለውዝ፣ ኮረሪማ፣ ጥቁር፣ አዝሙድ፣ እርድ ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉ ቅመማ ቅመሞችን፣ የቅባት እህሎችንና ጥራጥሬዎችን አስፈጭቶ አንድላይ በመቀላቀል እንደ ስልጆ ወይም እልበት አድርጎ በመስራት የዳቦ ክሬም መስራት ችለዋል። ክሬሙ ለተለያዩ በሽታዎች ፍቱን ሲሆን፤ ሰዎች ሲፈልጉ በጥብጠው መጠጣት ወይም በዳቦ አድርገው መመገብ ይችላሉ።
የውሻና የድመት ምግብ
ነጮች ውሻና ድመታቸውን ከልጆቻቸው ለይተው ስለማያዩና ከልጆቻቸው በላይ እንክብካቤ ስለሚያደርጉላቸው በዓለም ላይ የድመትና የውሻ ምግብ ከፍተኛ ገበያ አለው። እርሳቸው ከዚህ ገበያ አገራችን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሮ እንድታገኝ በማሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የጥራጥሬ፣ የአትክልት እና የፍራፍሬ ዓይነቶችን አንድ ላይ በመቀላቀል በእህል ወተት በማዋሀድ የውሻና የድመት ምግብ ለማዘጋጀት በቅተዋል። የምግቡ ንጥረነገር በኤሌክትሪክ ኃይል በሚበስልበት ጊዜ ንጥረ ነገሩ እንዳይሞት በፀሐይ ብርሃን ነው የሚበስለው። ይሄንንም ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለአገር የሚያስገኝ ነው።
ተፈጥሯዊ የተረፈ ምርት ማዳበሪያ
ኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነቷ ከፍ እንዳይል ከሚያደርጉ ችግሮች አንዱ የአሲዳማ አፈር መስፋፋት ነው። ገበሬው ይሄን ችግር ለመፍታት አሲዳማ አፈሩን በኖራ አፈር በማከም የግብርና ሥራውን እያከናወነ ይገኛል። በኖራ የታከመው አፈር ከሁለት ዓመት በኋላ ተመልሶ አሲድ ስለሚሆን ችግርን ከስር ከመሰረቱ መፍታት አይችልም። እንዲሁም ለኖራው ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው።
እርሳቸውም ይሄን ችግር በማገናዘብ በአገር ውስጥ የሚገኝ ማንኛውንም ተረፈ ምርት በመጠቀም ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ ለመስራት ችለዋል። ማዳበሪያውም ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ችግር ሳያስከትል ምርትና ምርታማነትን የሚጨምር ሲሆን፤ ገበሬውም ጤንነቱ የተጠበቀ ምርት እንዲያመርት ያስችለዋል። እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ ማዳበሪያዎችን በማስቀረት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት የሚያስችል ሲሆን፤ ማንኛውም ተረፈ ምርት አካባቢን ከመበከል ወደ ማዳበሪያነት ተቀይሮ ለዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ይሄንን ከተለያዩ የተረፈምርቶች የሚዘጋጅ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ በኢንስቲትዩቱ የቴክኒክ ባለሙያዎች አስገምግሞ፤ ማዳበሪያው ሙሉ በሙሉ ከተፈጥሮ ግብዓቶች የሚዘጋጅ በመሆኑ በአካባቢም ሆነ በማህበረሰቡ ጤና ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት የማያስከትል ከመሆኑም ባሻገር ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠርና የውጭ ምንዛሬ ሊያስገኝ የሚችል ስለሆነ ጥቅም ላይ መዋል እንደሚችል ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል።
የጠርሙስ የፈጠራ ሥራ
የላስቲክ ምርቶች አካባቢን በመበከል የዓለምን አየር ንብረት እያዛቡና ብዝሀ ሕይወትን እያጠፉ በመሆኑ፤ ዶክተሯም እነዚህን የላስቲክ ምርቶች ከተለያዩ የአፈር ዓይነቶች በሚሰሩ የጠርሙስ ምርቶች በመተካት ችግሩን ለማቃለል የሚያስችል የፈጠራ ሥራ ይዘው ቀርበዋል። እርሳቸውም የፈጠራ ሥራን የካኦሊን አፈር፣ ሳንድ ስቶን (ከእምቅ አሸዋ ከሚፈጠር ድንጋይ)፣ የኖራ ድንጋይ፣ ከሸክላ አፈር፣ ከሸንኮራ አገዳ ልጣጭ ወይም ተረፈምርት፣ ከእንሰት ቃጫ ስስና ጠንካራ ጠርሙስ ለማዘጋጀት ችለዋል።
እንዲሁም ጠረሙሱ የተለያየ ከለርና ጥንካሬ እንዲኖረው የተለያዩ የፍራፍሬ እና የአትክልት ተረፈ ምርቶችን እንደግብዓት በመጠቀም ለመስራት ችለዋል። በዚህም ከስፒናች ተረፈ ምርት አረንጓዴ ጠርሙስ፣ ከካሮት ተረፈምርት ቢጫ ጠርሙስ ማዘጋጀት ችለዋል።
በተጨማሪም የፈጠራ ሥራው የፕላስቲክ ውሃ መያዣን (ሀይላንድን) ወደ ጠርሙስ ውሃ መያዣ ለመቀየር የሚያስችል ሲሆን፤ ለመኖሪያ ቤት፣ ለመድኃኒት ቤት፣ ለሆቴሎችና ለምግብ ቤቶች መገልገያ የሚውሉ የጠርሙስ ምርቶችን ማምረት ያስችላል። በአጠቃላይ እ.ኤ.አ በ2021 የፕላስቲክ ምርቶችን በጠርሙስ ምርቶች በመተካት አካባቢን ከብክለት ለመከላከልና ብዝሀ ሕይወትን ለመታደግ ለሚደረገው ዘመቻ የራሱን ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት የፈጠራ ሥራ ነው።
ፌርሙዝ
በተጨማሪም ምግብንና መጠጥን ትኩስነቱን እንደያዘ እንዲቆይ የሚያደርግ የፈጠራ ሥራ የሰሩ ሲሆን፤ ፌርሙዙን ከሸክላ አፈርና ከካኦሊን አፈር ሰርተዋል። ፌርሙዙም ጥንካሬና ውበት እንዲኖረው የአትክልትና የፍራፍሬ ተረፈ ምርቶችን ከነዚህ አፈሮች ጋር በማቀላቀል ሰርተዋል። የፈጠራ ሥራው በእንቅስቃሴና በፀሐይ ብርሃን ኃይል በመሰብሰብ 24 ሰዓት ሙቀትን ጠብቆ መያዝ የሚችል ሲሆን፤ ፌርሙዙ ባለሁለት ክፍል በመሆኑ በአንዴ ምግብና መጠጥን ለመያዝ ያስችላል። በአጠቃላይ የፈጠራ ሥራውን በአገር ውስጥ የሚገኙ የአፈር ዓይነቶችን እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ተረፈ ምርቶችን በመጠቀም የሰሩ ሲሆን፤ የፈጠራ ሥራው ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ ቀላል በመሆኑ በሥራ ቦታና በመስሪያ ቤት ለመጠቀም ተመራጭ ነው።
በአጠቃላይ ዶክተሯ ከነዚህ የፈጠራ ሥራዎች በተጨማሪ ለጭንቀት፣ ለሪህ፣ ለአጥንት መሳሳት፣ ለራስ ምታት፣ ለጨጓራ፣ ለእንቅልፍ ማጣትና ለሌሎች በሽታዎች ፍቱን የሆኑ መድኃኒቶችን በአገር ውስጥ የሚገኙ እጸዋቶችን፣ ጥራጥሬዎችን፣ ፍራፍሬዎችን፣ ቅመማ ቅመሞችን እና አትክልቶችን በመጠቀም በመስራት በፈጠራ ባለቤትነት መብት ለማስመዝገብ በዝግጅት ላይ ናቸው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2011
ሶሎሞን በየነ