«ችግርን መለየት ግማሽ ሥራ ነው» የሚለውን ብሒል የሚያገናዝብ ትውልድ ከድህነት ለመውጣትና ማህበራዊ ተጠያቂነትን በማስፈን የማህበረሰቡን አንገብጋቢ ጉዳዮች በቅጡ ማጤን እንደሚገባው ይነገራል። የአንድ አገር ነዋሪዎች በማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚነት ዙሪያ የሚኖራቸውን ግንዛቤ በተጨባጭ የሚያሰፍሩባቸው ተግባራትን ማስቀመጥም ከተማረው የማኅበረሰብ ክፍል ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ የማኅበረሰቡን ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማኅበራዊ ችግሮች አንጥሮ በማውጣት መፍትሄ ለማበጀት ግብዓት መለየት፣ ቅደም ተከተልን በማስቀመጥ የትኛው ጉዳይ የበለጠ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል? በማለት ተቀዳሚውና የተለየው ችግር ላይ ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል።
በአገሪቷ ውስጥ የመሠረታዊ አገልግሎቶች ማሻሻያ ፕሮግራም አካል በሆነውና ሕዝባዊ ማህበራዊ ተጠያቂነትን አመላካች በሆነው በዚህ መርሃ ግብር ከወረዳ አመራሮች ጀምሮ፣ የማህበር አመራሮችን ጨምሮ፣ ከማህበረሰብ የተውጣጡ በርካታ ሰዎች ተሳታፊ ሆነውበታል።
የማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም በትምህ ርት፣ በጤና፣ በውሃና ፍሳሽ እንዲሁም በግብርና መሠረተ ልማቶች ላይ ያተኮሩ ናቸው። አገልግ ሎት ሰጪዎች እና አገልግሎት ተቀባዩ (ሕዝብ) ተማምነው፣ የሥራ ድርሻ ተከፋፍለው ከዚያም ከየቀበሌው ሰዎች ተመርጠው፣ የድርጊት ኮሚቴ ፈጥረው፣ በተስማሙባቸው ጉዳዮች ላይ ተግባራዊ ሥራ ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል።
ዜጎች አገልግሎት የማግኘት መብታቸው እንዲጠበቅና ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ የማህበራዊ ተጠያቂነት ሥራ ውጤት እያስገኘ ነው የሚሉት የማህበራዊ ተጠያቂነት ኮሚቴ ሰብሳቢ ሮልፍ ሁኒንግ፤ የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ከዓለም ባንክና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ በአገሪቱ ሁሉም ክልሎች በሚገኙ የተመረጡ ወረዳዎች ላይ በአገልግሎት ሰጪዎችና ተገልጋዮች መካከል በመሆን ዜጎች ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ የግንዛቤና የሥልጠና ሥራ በመስጠት ሥራውን ተደራሽ ማድረግ እንደተቻለ ይናገራሉ።
ፕሮግራሙ መሠረታዊ የአገልግሎት ማሻሻያ ስር ያለ ፕሮግራም ሆኖ ሁለቱን አካላት ማለትም አገልግሎት ሰጪና ተቀባይ በማወያየትና ግልፀ ኝነት በመፍጠር አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ በሚያ ስችል መልኩ እየተሰራ ስለመሆኑም ሮልፍ ሁኒንግ ያብራራሉ።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ በአሁኑ ወቅት ኅብረተሰቡ ጥያቄዎችን ማንሳት መጀመሩ በአገልግሎት ሰጪው በኩል ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችል እንቅስቃሴዎችን መፍጠሩ የፕሮግራሙን ስኬት የሚያሳይ ሲሆን፤ በተለይ አቅም የሌላቸው ሴቶች፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች እኩል የአገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የማህበረሰብ አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ጋር በመሆን ተጠቃሚነታቸው ላይ በመስራት ለውጥ እንዲመጣ ተደርጓል።
ሮልፍ ሁኒንግ፤ ከባለፉት ሁለት ምዕራፎች ስኬታማ ጉዞ በመነሳት አገልግሎት ሰጪዎችና አገልግሎት ተጠቃሚዎች አገልግሎቶችን ለማሻ ሻል አብሮ እንዲሰሩ የሚያስችል የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ምዕራፍ ሦስት በይፋ መጀመሩን ጠቅሰው፤ ፕሮግራሙ የአይሪሽ ኤይድ፣ አውሮፓ ህብረት፣ ኦስትሪያን ዲቨሎፕመንት ኤጀንሲ፣ ዲፓርትመንት ፎር ኢንተርናሽናል ዲቨሎፕመንት፣ ኤምባሲ ኦፍ ስዊድን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በስፋት እንደሚተገበር፤ ወደ 30 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ፈሰስ እንደ ሚደረግለት፤ ፕሮግራሙን በወረዳ ደረጃ ለሚተ ገብሩ ከ100 በላይ ለሚሆኑ አገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚከፋፈል እንደሚሆን አስታውቀዋል።
ፕሮግራሙ የመሠረታዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎች ፍላጎታቸውንና ጥያቄያቸ ውን የሚያሰሙበትና የፖሊሲ አውጪዎች የማህበራዊ አገልግሎት ተደራሽነት ብልሹነትን በማቃናት ተጠያቂ የሚያደርጉበት መሆኑንም ነው የኮሚቴው ሰብሳቢ ሮልፍ ሁኒንግ የሚናገሩት።
የተለያዩ አገልግሎቶች በፍትሃዊነት ተደራሽ እንዲሆኑና የተጠያቂነት ሥርዓት ባልተማከለ ሁኔታ በሁሉም ደረጃ እንዲሰፍን ለማድረግ እንደሚሰራ፤ ለዚህም አገልግሎቱ በዋናነት በትምህርት፣ በጤና፣ በውሃ፣ በገጠር መንገድና በግብርና ዘርፍ የሚሰራ መሆኑን አክለዋል። በዚህም እስካሁን በየአምስት ዓመቱ ሁለት ምዕራፎችን በማዘጋጀት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ223 ወረዳዎች በላይ ተጠቃሚ ተደርገዋል። በምዕራፍ ሦስት መርሃ ግብር የተጠቃሚዎቹ ወረዳዎች ቁጥር ወደ 500 እንደሚያድግም ገልጸዋል።
በ2006 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ይህ ፕሮግራም በሦስተኛው ምዕራፉ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች 500 ያህሉን ማካተቱ ከዚህ ቀደም ተጠቃሚ ያልሆኑና በርካታ ጥያቄዎች የነበራቸውን አካባቢዎች መልስ ለመስጠትና የላቀ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንደሚረዳ ሮልፍ ሁኒንግ ገልጸዋል።
ፕሮግራሙ አገልግሎቱ ባልተዳረሰባቸው ወረዳዎች ላይ በተከታይነት ለመስራት መታቀዱን የሚጠቁሙት ሮልፍ ሁኒንግ፤ በየዓመቱ አዳዲስ 100 ወረዳዎችን በማዳረስ የማህበራዊ ተጠያቂነትን ማስፋት ቀዳሚው ዓላማው መሆኑንና፤ ለዚህም በየወረዳው የሚገኙ ተቋማት በአገልግሎቱ የመሳተፍ ፍላጎት ካላቸው ማመልከት እንደሚችሉና በጋራ ለመስራት ምቹ አጋጣሚዎች መኖራቸውን አመላክተዋል።
«በዚህ ዓመት 77 አዳዲስ ወረዳዎችን አካተናል። ለዚህ የሚሆኑ ባለሙያዎች በማህበራዊ ተጠያቂነት ላይ ሥልጠና ወስደው ግንዛቤ እንዲያገኙ በቅድመ ዝግጅቱ ሰርተናል» ሲሉም በአገልግሎቱ ተደራሽነት ላይ የሚሰሩ አካላት አስቀድመው እንዲዘጋጁ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በሁለት ተከታታይ ምዕራፎች ሲተገበር በቆየው የማህበራዊ ተጠያቂነት አገልግሎት ሲሳተፉ የነበሩትም ፕሮግራሙ በአገልግሎቶች ላይ በርካታ ለውጦችን ስለማምጣቱ ይናገራሉ። በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የወረዳ ስድስት አረጋውያን ማህበር ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ሀጎስ በርሄ እንደሚሉት፤ በፊት ትምህርት ቤትም ይሁን ጤና ጣቢያ የራሱን ሥራ መስራት ሲፈልግ ከወረዳ ጀምሮ ባሉት የመንግሥት መዋቅሮች የቢሮክራሲ ችግሮች ነበሩበት። አሁን ግን የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ስንሆን፤ ይህ ችግር ተቀርፏል።
ዘመናዊ መጸዳጃ ቤት ለአካል ጉዳተኞችና ለአረጋውያን ተሰርቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በየትምህርት ቤቶች መጸዳጃ ቤቶች እንዲሰሩና ወንዶችና ሴቶች ለየብቻቸው እንዲጠቀሙ አስችሏል። ይህም ማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማህበራዊ ችግሮቹ እንዲቀረፉለት ያስቻለ ፕሮግራም ነው።
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የሴቶች ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ ጸሐይ በንቲ፤ የማህበራዊ ተጠያቂነት አገልግሎት ፕሮግራም ከየትኛውም አሠራርና አካሄድ የተለየ ነፃነትን ያጎናጸፈ እንዲሁም ሁሉንም ሴቶች ልብ የሚያነሳሳ ካለ ማወቅ ወደ ማወቅ ያሸጋገር ፕሮግራም ነው ይላሉ። የጠያቂነትና የአገልግሎት ሰጭነትን ተግባር በጉልህ ያሳየ መሆኑንም ይጠቁማሉ።
በአካባቢው በርካታ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች የነበሩ ሲሆን፤ ነገር ግን ይህ ፕሮግራም በመዘርጋቱ አሁን ላይ ችግሩ እየተቀረፈ ስለመምጣቱም ይገልጻሉ። በዚህ የማህበራዊ ተጠያቂነት መርሃ ግብር በጤና፣ በፅዳት በተለይም በትምህርት ዙሪያ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት አገልግሎት ሰጪና ተቀባይ ተገናኝተው እንዲወያዩ በማድረግ በሁለት ተከታታይ የትግበራ ምዕራፎች ላይ የተሻለ ውጤት መምጣቱን ይናገራሉ። ነገር ግን አሁንም ቢሆን በየጤና ጣቢያዎች በርካታ ችግሮች ስላሉ በቀጣይነትም ሊሰራበት ይገባል ሲሉም ወይዘሮ ጸሐይ ይናገራሉ።
የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ በበኩላቸው፤ ፕሮግ ራሙ በዓለም ላይ ካሉት ትልልቅ መርሃ ግብሮች አንዱ መሆኑንና ዓላማውም በመሠረታዊ የማ ህበራዊ አገልግሎቶች ሁሉንም ማኅበረሰብ ተደራሽ በማድረግ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጠቃ ሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሆነ ይጠቁማሉ።
አቶ አድማሱ፤ ድህነት ተኮር መርሃ ግብሩ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲስፋፉ ከማድረግ ባሻገር በአገሪቷ ፈጣን ለውጥ ለማምጣት፣ የልማትና ዴሞክራሲ አስተሳሰብን ለማስፈን አስተዋጽኦ እንዳለው በመጥቀስ ተጠያቂነትና ግልጸኝነትን በማረጋገጥ የመንግሥትን የማስፈጸም አቅም በማሳደግ አገሪቷን ከድህነት ለማውጣት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ይደግፋል ብለዋል።
የኅብረተሰቡን ማህበራዊ አገልግሎት የማግኘት መብት ለማስጠበቅም ፕሮግራሙ ቀጥተኛ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል። ፕሮግራሙ ድህነት ተኮር መርሃ ግብር በመሆኑ በድህነት ላይ ተጽእኖ የሚያሳርፉ ችግሮችን ለመቀነስ አገልግሎቱን በሰፊው ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም አስታው ቀዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2011
አዲሱ ገረመው