የኢትዮጵያ የሥነ-ሕዝብ እና የጤና ጥናት ከመጪው ወር ጀምሮ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፡አምስተኛው ዙር የኢትዮጵያ የሥነ-ሕዝብ እና ጤና ዳሰሳ በመላ ሀገሪቱ ከመጪው መጋቢት ወር ጀምሮ ሊካሄድ መሆኑ ተገለጸ፡፡ የመጀመሪያው የብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ወደ ሥራው ለመግባት የሚያስችለውን ውይይት አካሂዷል፡፡

በመድረኩ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የሥነ-ሕዝብ እና ጤና ዳሰሳ (ኢ.ዲ.ኤች.ኤስ.) እኤአ በ2000 ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ በኢትዮጵያ ፖሊሲዎችን ለማውጣት አግዟል፡፡ የእናቶች እና የሕፃናት ጤና ፕሮግራሞችና የቤተሰብ ምጣኔ ላይ በጎ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ በ2024 የሚካሄደው ጥናት በጤና እና በሥነ ሕዝብ ጉዳዮች ወቅታዊ የመረጃ ክፍተቶችን ለመፍታት ያስችላል፡፡ የዳሰሳ ጥናቱ የእናቶች እና የሕፃናት ጤናን ጨምሮ፣ የመራባት መጠን፣ አመጋገብ፣ ኤችአይቪ፣ የአካባቢ ጽዳትና ንፅህና፣ የቤት ውስጥ ጥቃት፣ የውሃ ጥራት እና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ያጠቃልላል፡፡

የዳሰሳ ጥናቱ ዓላማ ለኢትዮጵያ ጤና እና ደህንነት የተሟላ መረጃ ለመስጠት ሲሆን፤ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለማሳለፍና በፍጥነት መረጃን ለመስጠት በጥንቃቄ ታቅዶ የሚመራ ነው፡፡

ሚኒስትሯ፤ ለዘላቂ ልማት ግቦች ቁርጠኝነት፣ ኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሻሻል፣ የእናቶችና የሕፃናትን ሞት ለመቀነስ እና የሥርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማሳደግ እየሰራች መሆኗን ገልጸው፤ ከሥነ ሕዝብና ጤና ዳሰሳ ጥናት የሚገኘው መረጃ በአካባቢያዊ  ፖሊሲዎች ላይ ብቻ ሳይሆን ዓለምአቀፍ ግቦችን ለማሳካት አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063 የተሻለች አፍሪካን ለማስፈን ያለመ፣ ከ (ኢ.ዲ.ኤች.ኤስ.) የተገኙ ግንዛቤዎች በአህጉሪቱ የጤና ሥርዓት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ለማራመድ ጠቃሚ ናቸው ብለዋል፡፡

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እንደ አፍሪካ የጤና “ኦቭዘርቫቶሪ” ባሉ ውጥኖች ላይ በመሳተፍና ምርጥ ተሞክሮዎችን በማካፈል እንዲሁም አፍሪካን ጤናማና ጠንካራ ለማድረግ እየሠራች መሆኗን ገልጸዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ እንደገለጹት፤ አምስተኛው ዙር ጥናት በ11ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በጀት የሚካሄድ ሲሆን፤ ወጪው በመንሥትና አጋር አካላት በኩል የሚሸፈን ነው፡፡

ዶክተር ደረጀ እንዳሉት፤ አብዛኛው የጥናቱ የዝግጅት ምዕራፉም ተጠናቅቋል፡፡ ጥናቱ በአንድ ዓመት ውስጥ ተጠናቅቆ የሚያልቅ በመሆኑ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ወደ ዋናው ሥራ የሚገባ ይሆናል፡፡

እኤአ በ2024 የሚሠራው የኢትዮጵያ ሥነ ሕዝብና ጤና ጥናት በርካታ ጉዳዮችን ያጠቃለለ ነው ያሉት ዶክተር ደረጄ፤ በጠቅላላው ሁሉንም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮችን የሚነካ በርካታ አባወራና እማወራ ጋር የሚደርስ፤ በቤተሰብ ደረጃ መረጃ የሚሰበስብና ለሚቀጥሉት ዓመታት የመረጃ ምንጭ የሚሆን፤ ወሳኝ የሚባሉና ጤናና የሥነ ሕዝብ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉና የፖሊሲ ውሳኔ ለመስጠት ተዓማኒ መረጃ የሚገኝበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሥነ -ሕዝብና ጤና ጥናት በየአምስት ዓመቱ ሲያካሂድ የቆየ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ለአራት ጊዜ ያህል በዚሁ ዘርፍ ጥናቶች ተካሂደዋል፡፡ ይህ በጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ቀመር በ2024 የሚካሄደው ጥናት አምስተኛው ዙር ይሆናል፡፡

አዲሱ ገረመው

 

አዲስ ዘመን  የካቲት 5/2016 ዓ.ም

Recommended For You