
የአፍሪካ ኅብረት 50ኛ ዓመቱን ሲያከብር የአፍሪካውያን አንድነትና ብልጽግና መገለጫ የሆነውን አጀንዳ 2063ን ይፋ አድርጓል፡፡ አጀንዳ 2063 አፍሪካውያንን በመሠረተ ልማት የማስተሳሰር፣ የሥራ አጥ ቁጥርን የመቀነስ፣ አፍሪካውያን ተመሳሳይ መገበያያ ገንዘብ እንዲኖራቸው የማድረግ፣ የአፍሪካ ኅብረትን ማጠናከር፣ ነፃ የንግድ ቀጣናዎችን መመሥረት እና ሌሎች በርካታ ግቦችን የሰነቀ ነው፡፡
አጀንዳ 2063 ይፋ ከተደረገ ጀምሮ ምን ምን እቅዶች ተሳኩ፣ ቀሪ ሥራዎች ምንድን ናቸው፣ ከኢትዮጵያስ ምን ይጠበቃል? የፖለቲካ ሳይንስ መምህርና የፖሊሲ ጉዳዮች አማካሪ ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ(ዶ/ር) እንደሚሉት አጀንዳ 2063 ለአፍሪካውያን እድገትና ይህ ካልሆነ ግን አፍሪውያን ያለሙትን ብልጽግና እውን የማድረግ ጥረታቸውን ለማሳካት ይከብዳቸዋል፤ ሕዝቦቻቸውንም ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ብሎም ከግጭት ለማላቀቅ አይችሉም። አንድነት የሚረዱ በርካታ ግቦችን የያዘ ነው። ፕሮግራሙን ለማስፈጸም በተሠሩት ሥራዎች አመርቂ ውጤቶች ተገኝተዋል። ያም ሆኖ ግን በርካታ ያልተሳኩ ጉዳዮች አሉ።
በአጀንዳ 2063 ከተገኙ ስኬቶች መካከል አንዱ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ሥርዓት መውጣቱና ቢሮ መቋቋሙ ነው የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ ይህም የአህጉሩን ኢኮኖሚ ለማሳደግ፣ ሥራ ፈጠራን ለማሻሻል፣ ለሸቀጦች እና አገልግሎቶች አንድ የንግድ ማዕከል በመገንባት ድህነትን በመቀነስ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ያስረዳሉ።
የትራንስፖርት መሠረተ ልማት አለመሟላቱ ለግብይት ሥርዓቱ መጀመር ፈተና በመሆኑ የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ማሻሻያ ማድረግ፣ ፖለቲካዊ ቀውሶችን በመፍታት፣ ሙስናን በመዋጋት፣ ዘመናዊ አሠራሮችን በመዘርጋት እና ተመሳሳይ የመገበያያ ገንዘብ እንዲኖር በማድረግ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ማለፍ እንደሚገባም ይገልጻሉ።
አፍሪካን ሠላማዊ አህጉር ማድረግ ከአጀንዳ 2063 ግቦች መካከል ቢሆንም 31 የሚደርሱ የአፍሪካ ሀገራት ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ይገኛሉ ያሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ከሚገኙት ሀገራት መካከል አንዳንዶቹ የመንግሥት ግልበጣ ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረት ሕዝቡ እየደገፈው እንደሚገኝ ያስረዳሉ።
በዚህም ሀገራቱ ከአፍሪካ ኅብረት አባልነት እየተወገዱ ሲሆን፤ ፖለቲካዊ ቀውሱ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ የአፍሪካ ኅብረት በ2063 ሊደርስበት ካቀደው የልማት ግቦች ላይደርስ ይችላል ይላሉ። ሁሉም ባለድርሻ አካላት የአፍሪካ ሀገራትን ከፖለቲካ ቀውስ በማውጣትና የሕዝቡን ኑሮ በማሻሻል ኅብረቱ በ2063 ሊደርስበት ካቀደው የልማት ግቦች ለማድረስ በአንድነት መበልጸግ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።
የአፍሪካ መንግሥታት ከሕዝባቸው ጋር በመነጋገር ሰላምን የማምጣት፣ ቀጣናዊ ልማትንና ትስስርን የማጠናከር፣ ሙስናን የመወጋት፣ መልካም አስተዳደርን የማጎልበት፣ ከአፍሪካውያን በሕገወጥ መንገድ የሚዘረፉ ሀብቶችን ማስቆም እና ሌሎች ሥራዎችን ማከናወን ለአጀንዳ 2063 ስኬታማነት የቤት ሠራዎች መሆናቸውን ያስረዳሉ።
እያንዳንዱ ሀገር የሕዝቦችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል፣ የትምህርትና የጤና ተቋማትን ማስፋፋት እና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባም ጨምረው ያስረዳሉ። ናይጄሪያ፣ አልጀሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ሞሮኮ እና ሌሎች የአፍሪካ ትልልቅ ሀገራት ለአጀንዳ 2063 ስኬታማነት በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል ሥራ መሥራት አለባቸው ይላሉ።
የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኝ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን በበኩላቸው፤ አፍሪካ ለሕዝቧ ኢኮኖሚያዊ ልዕልና እና ነፃነት የሚረዳ የአጀንዳ 2063 እቅድ ማውጣቷ የሚደነቅ ተግባር ነው ይላሉ። አጀንዳ 2063 አፍሪካውያንን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚያስተሳሰር እና በጋራ ለማደግ መልካም አጋጣሚ በመሆኑ ለስኬታማነቱ በትኩረት መሥራት ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር ነው ይላሉ።
ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የሚለውን ሀሳብ በመገንዘብ በአህጉሪቱ የሚፈጠሩትን ችግሮችን እርስ በእርስ በመግባባት መፍታት መቻላችን እና በጉዳዩ ጠንካራ አቋም መያዙ የአጀንዳ 2063 ስኬት መሆኑን ይናገራሉ። በጋራ ተጠቃሚነት፣ አብሮ በማደግ እና በቀጣናዊ ትስስሮችን ለማጎልበት በጋራ መሥራት መጀመሩ እንዲሁም አፍሪካውያን በእራሳቸው ማንነት እና ሀብት መኩራታቸውም ሌላኛው ስኬት ነው ይላሉ።
የአፍሪካ መንግሥታት መተማመን እና መተባበር ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚገባ አስታውቀው፤ አሁን ላይ የተጀመረውን ቀጣናዊ ትስስር አመርቂ ውጤት እንዲያመጣ በትብብር መሥራት እንደሚገባ ይገልጻሉ።
አጀንዳ 2063 ስኬታማ መሆን የሚችለው በአፍሪካውያን ልሂቃን መሪነት ብቻ ሳይሆን ሕዝቡም የነቃ ተሳትፎ ሲያደርግ ነው። በተጨማሪም ዴሞክራሲና ነፃነት ለሕዝቡ መስጠት፣ ትምህርት እና ግብርና ላይ ማተኮር እንደሚጠይቅም ይገልጸሉ።
በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ሥልጣንን በኃይል ለመያዝ የሚደረጉት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች የአፍሪካን ተሰሚነት እና ተፅፅኖ ፈጣሪነት የሚቀንስ ነው። በዚህ ደግሞ አፍሪካውያን በአንድነት ሆነው ለአጀንዳው ስኬታማነት እንዳይሠሩ ምክንያት ስለሆነ ለዘላቂ ሠላም መሥራት ይገባል ይላሉ።
ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም እምብርት፣ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ተሰሚነት ያላት ሀገር በመሆኗ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሀሳቡን፣ ጉልበቱን እና እውቀቱን በማቀናጀት ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ በሚሆን ደረጃ ለአጀንዳ 2063 ስኬታማነት መሥራት ይገባቸዋል ሲሉም የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተንታኙ ገልጸዋል።
ለአጀንዳ 2063 ስኬታማነት ፖለቲካዊ ቀውሶችን መፍታት፣ ሙስናን መዋጋት፣ መሠረተ ልማትን ማስፋፋት፣ ቀጣናዊ ትስስሮችን ማጎልበት፣ የሥራ ባሕልን ማዳበር እና ሌሎች አንኳር ጉዳዮች ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ምሑራኑ አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።
ይህ ካልሆነ ግን አፍሪካውያን ያለሙትን ብልጽግና እውን የማድረግ ጥረታቸውን ለማሳካት ይከብዳቸዋል፤ ሕዝቦቻቸውንም ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ብሎም ከግጭት ለማላቀቅ አይችሉም፡፡
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን የካቲት 4 / 2016