በርሃብ አንጀቱ የታጠፈ፣ እራፊ ጨርቅ ከላዩ ላይ እንደነገሩ ጣል ያደረገ የኔ ቢጤ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ማየት የተለመደ ነው፡፡ ሆኖም ከወጣት እስከ አዋቂ፣ ከድሀ እስከ ባለፀጋ ድረስ በቅርብ ርቀት ተመልክቶ አለበለዚያም ክብ ሠርቶ በሆይ ሆይታ በጋራ ከንፈርን እየመጠጡ ከማለፍ የዘለለ ተግባር ለመፈፀም መላዕክት መሆንን የሚጠይቅ እየመሰለ መጥቷል፡፡
በወጣትነት የነፍስን አያሌ ፍላጎት አሸንፎ ለሌሎች የማድረግ ‹‹በጎነትን›› መላበስ እጅጉን መታደል ነው፡፡ መሰጠትም ጭምር ነው፡፡ የዛሬው ትኩረታችን ይሄን ማድረግ በቻሉና ለነድያውያን ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ያለስስት በሚያውሉ ወጣቶች ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው፡፡
በራሱም ይሁን በሌሎች ግፊት አብዛኛው ወጣት አልባሌ ቦታ ከመገኘት ባልተላቀቀበት፤ መጥፎ ድርጊት ከመሥራት ባለተቆጠበበት፤ ያልተገቡ ሥነ ምግባሮች ከመላበስ አልፎ መጥፎ ድርጊቶች ሲፈጽም በሚስተዋልበት በዚህ ወቅት የእናንተ በእንደዚህ አይነት አስተሳሰብ መቀረጽና በእንዲህ አይነት በጎ አገልግሎት መሰማራትን እንዴት ትገልፁታላችሁ? ወጣቱና ትውልዱስ ከእናንተ ፈለግ ምን እንዲማር ትመክሩታላችሁ? ስንል ጠይቀናቸዋል፡፡
ወጣቶቹ ከልጅነታቸው ጀምሮ በርካታ ጎስቋሎችን እያዩ ያደጉ ናቸው፡፡ ነገር ግን በተናጠል የሚያደርጉት እገዛ ሊያረካቸው አልቻለም፡፡ ተመሳሳይ ፍላጎት ያሰባሰባቸው አብሮ አደግ ወጣቶች ከየጓዳው ወጥተው አንድ አቅሙ ያልጠና ‹‹ኬብሮን›› የተሰኘ ማህበር መመስረት ችለዋል፡፡
የገቢ ምንጩም በሚያገኙት ሽርፍራፊ ሳንቲም የተቋቋመ ነው፡፡ ለነገሩ መመስረታቸውን የሚገልፁት ተሰባስበው በድርጊታቸው ሲሆን እውቅና የተሰጠው ደግሞ በነድያውያን ዘንድ እንጂ ከዚያ አለፍ ብለው እወቁልኝ ማለቱን ብዙም እንዳልፈለጉት ነግረውኛል፡፡
ወጣት ዮሐንስ ኃይሉ በአዲስ አበባ ለገሀር አካባቢ ልዩ መጠሪያው ‹‹ድንጋይ ጣቢያ›› አካባቢ ተወልዶ ያደገ ሲሆን የ‹‹ኬብሮን ማህበር›› አባል ነው፡፡ ወጣቱ እንደገለጸው፤ የተመሰረተበት አላማ ለታመሙ፣ አቅም ለከዳቸውና በየጎዳናው ጥጋጥግ ጎጆ ለቀለሱ ደካሞች ፈጥኖ ለመድረስ ነው፡፡ በተጨማሪም በሐዘንም ሆነ በደስታ ተገኝቶ ወግና ባህሉ እንዲሁም ሃይማኖታዊ ክዋኔው በሚፈቅደው መሰረት አለኝታነቱን ለመግለጽ ያለመ ነበር፡፡
እየዋለ ሲያድር የተራቡ፣ የተጠሙ፣ የታረዙና በበሽታ የተጎሳቆሉ ነድያውያንን ወደማገዝ ተሸጋገረ፡፡ በየወሩ ከአባላት መዋጮ በሚያሰባስቡት ሃምሳ ብር እና በማህበረሰቡ ድጋፍ አስታዋሽ ያጡ ደካሞችን አለሁላችሁ፣ አይዟችሁ ባይ ጠያቂ መሆን ጀመረ፡፡
ስድስት ሆነው የወጠኑት ይህ በጎ ሥራ 70 ያህል አባላትን አፈራ፤ ለቁጥር የሚያዳግቱ ነድያውያንን በቋሚነትም ባይሆን አንጀታቸው ሲታጠፍና ከልቦናቸው ርህራሄ ሲነጥፍ ይደርስላቸዋል፡፡ ለርሃባቸው ማስታገሻ እህል፣ ለብርድና ለፀሐይ መከለያ ጨርቅ ይደርብላቸዋል። ከዚያም ከታላቁ መጽሐፍ በሚመዘዙ ውዳሴዎች አዕምሮ ጭምር እንዲፋፋ ያደርጋሉ፡፡ መልካም ሥነ ምግባርንና በጎነትን በማስተማር ላይ መሆናቸውን ወጣቱ ይናገራል፡፡
የኬብሮን ማህበር አቅም የፈቀደውን ያህል እገዛና ድጋፍ የሚያደርግላቸው ነድያውያን መስፈርትም፣ ድንበርም የላቸውም፡፡ አጉራሽና አልባሽ ያጣ ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡ የየትኛውም እምነት፣ የየትኛውም ብሔር እና ሌላም ሌላም ጉዳዮች በኬብሮን እኩልና አንድ መሆናቸውን ይመለከታሉ፡፡ አያይዞም በየዓመቱ አንድ ቀን ለችግር ተጋልጠው ከየስርቻው የወዳደቁ ወገኖቻችንን በማሰባሰብ በሬ አርደው ድል ያለ ድግስ ደግሰው ያበላሉ፤ ያጠጣሉ፡፡ ይኩላሉ፤ ያለብሳሉ፤ ይሞሽራሉ፡፡
ከነአካቴው ጉልበታቸው ተሸንፎ አልጋ ላይ ለዋሉት ደግሞ እየተቋጠረ ከእያሉበት እንዲደርሳቸው በማድረጉ ተግባር ላይ የተሰማሩ ወጣቶች አሉ፡፡ የኬብሮን አባላት በዚች ዕለት እንደ እንዝርት እየሾሩ የሚፈጽሙት የሥራ ድርሻ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ነገር ግን ማንም ተግባሩን በትክክል ስለመወጣቱ ጠያቂ የለውም። ጠያቂውም፣ ከሳሹም በጎነት ብቻ መሆኑን ነግሮናል፡፡ እኛና እነሱን አገናኝታ ያስተዋወቀችን ይች የወጣቶች በጎነት የወለዳት በጎ ቀን ነበረች፡፡ እድሜዋም ስምንት ዓመታትን እንደዋዛ መድፈኑን ሰምተናል፡፡
የኬብሮን ማህበር ሊቀመንበር ወጣት ፀጋዬ ወልዴ እንደተናገረው፤ ‹‹ማህበሩ ከተመሰረተ ስምንት ዓመት ሆኖታል፡፡ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ከምንሰጣቸው አገልግሎቶች ሰፋ ባለ መንገድ ማገልገል እንድንችል አቅም የሆነን የአካባቢው ማህበረሰብ ድጋፍ ነው፡፡ ተግባራችን ፍፁም ሰናይ መሆኑን ከተገነዘቡ በኋላ የተቸገሩትን እና የተራቡትን ከየመንገዱና ከየእምነት ተቋማት (ቤተ ክርስቲያን) አካባቢ እየሰበሰብን መመገብ እንድንችል የበሰለ ምግብ (እንጀራ) ከመስጠት ጀምሮ እስከ ገንዘብ ድረስ በማዋጣት ከጎናችን አልተለዩንም፡፡ በእግዚአብሔር ስም ማመስገን እወዳለሁ›› ብሏል፡፡
አቅመ ደካማ፣ ረዳት የሌላቸው እና የጤና መታወክ ያጋጠማቸው ሰዎች በብዛት በሚገኙባቸው የፀበል ቦታዎች አልባሳት፣ የጽዳት መጠበቂያ ዕቃዎች፣ ምግብና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች በመያዝ ይጠይቃሉ፡፡ እንደ ጌርጌሲኖንና ኪዳን ምህረት መውጫው ገደላማ አካባቢ ተሰባስበው የሚገኙ ደካሞችና ህሙማን ከጎበኟቸው መካከል እንደሚገኙበት ጠቅሷል፡፡
ይህን ተግባር በመፈፀማችን የምናገኘው እርካታና ደስታ ወደር የለውም የሚለው ወጣቱ ምክንያቱም ታናናሾቻችን የሰፈር ወጣቶች ወግና ባህላቸውን ሳይለቁና በእምነት ጥላ ስር በመልካም ሥነ ምግባር ተኮትኩተው ማደግ እንዲችሉ አርአያ መሆን ችለናል፡፡ አሁን ሕጻናቱ እንዲህ አይነት በጎ አገልግሎት ለመስጠት ያላቸውን ፍላጎት ስታይ ትደሰታለህ፡፡
በአጠቃላይ የአካባቢው ወጣቶች ባህሪና ሥነ ምግባር ትሁት፣ ሰው አክባሪና ፈጣሪያቸውን ፈርተው ከመጥፎ ድርጊት መራቅ እንዲችሉ መንገድ ከፍቷል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ከእኛ የበለጠ መልካም ተግባር ይሠራሉ የሚል እምነት አለኝ ብሏል፡፡ ይሄ ትልቅ ውጤት ነው፡፡ እንዲህ አይነት ሥነ ምግባር ያላቸውና ሰናይ ተግባራትን የሚሠሩ ወጣቶች ጠቃሚነታቸው ለሰፈሩና ለአካባቢው ማህበረሰብ ብቻ አይደለም፡፡ ለሀገርም ኩራቶችና ሀብቶች መሆናቸውን ወጣት ፀጋዬ ተናግሯል፡፡
ወጣት ጽዮን ሙጅብ በበኩሏ ‹‹በራሳቸው በተሰባሰቡ የሠፈር ወጣቶች ማህበረ ኪብሮን የተመሰረተው መዋደድን፣ አንድነትን፣ መረዳዳትን፣ አለኝታነት፣ ፍቅርን እና በጥቅሉ በጎነትን በተግባር ለመግለጽ ነው፡፡ ከዚያም መሰባሰባችን የራሳችንን መዋደድና መቀራረብ አጠንክሮልናል፡፡ ሲቀጥልም ለምን ችግሮቻችንን በራሳችን መቅረፍና ማቃለል አንችልም? የሚል ተነሳሽነትን መፍጠር ችሏል፡፡ አስተሳሰቡ እያደገና እየጎለበተ ሲመጣ ለችግር የተጋለጡና አቅመ ደካሞችን ወደማገልገሉ መሸጋገራቸውን ገልፃለች።
ወጣቷ እንደምትለው ‹‹የገጠማችሁ ችግር የለም ወይ ላልከኝ፤ ውስጣዊ ፍላጎት ያሰባሰበን በመሆናችን የሚገጥሙን መሰናክሎች ከበጎ አገልግሎት አያሰናክሉንም፡፡ መንገድ ላይ ድንኳን ጥለን ነው ነድያውያንን የምናስተናግደው። የምናበስለውና ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶች የምናደርገው ደግሞ በየአባላቱ ቤት እየዞርን ነው። የቁሳቁስ እጥረቶች አሉብን፡፡ ራሱን የቻለ መሰባሰቢያ ቤትም የለንም፡፡ ግን አሳስበውንም አያውቁም ምክንያቱም በጎ ሥራ ለራስ ነው፡፡
በጎ መሥራት ለሕሊና ከሚሰጠው እርካታ በላይ በፈጣሪ ዘንድ የተወደደ በመሆኑ እሱን አስበን ነው ለወገናችን የምንሠራው ሲሉም ነግረውኛል። በእርግጥ ያሉብንን ችግሮች ቢቃለሉና ቢቀረፉ ከዚህ በላይ ሰፊ በጎ ተግባር ማከናወን እንችል ነበር፡፡ እስከ አሁን ድረስ ግን የመንግሥት አካላት፣ በበጎ ፈቃድ ዙሪያ የሚሠሩ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች እገዛ አድርገውልን አያውቁም። እኛም ጠይቀን አናውቅም፤ ለመጠየቅም አላሰብንም፡፡
አሁን አሁን የምታየውና የምትሰማው የሰው ልጅ ባህሪና ድርጊት የሚያሳዝን ነው፡፡ ቀጣዩ የዚች ሀገር ባለቤት ወጣቱና ሕጻናቱ ምን እየሆነ እንደሚመጣ ስታስብ ከባድ ነው፡፡ ፈሪሐ እግዚአብሔር አይታይበትም፡፡ የእግዚአብሔርን ሕግጋት አክብሮና ከመጥፎ አስተሳሰብ ተላቆ አቅሙ በፈቀደው ልክ ለነፍሱ የሚሠራ እየጠፋ ነው፡፡
ስለዚህ የእኛ አላማ ወጣቱና ሕጻናቱ መስመር የሳተ እንዳይሆን አርአያ መሆን ነው። በቻልነው ልክ ሃይማኖታዊና ሞራላዊ የሥነ ምግባር መመሪያዎችን ጠብቀውና አውቀው እንዲያድጉ በተግባር ለማሳየት እየሞከሩ እንደሆነም አስታውቋል፡፡
ከገንዘቡ እስከ ጉልበቱ ድረስ ለአቅም ደካማና አስተዋሽ ለሌላቸው ነድያውያን ማዋል የእሱ ልዩ የደስታ ምንጭ መሆኑን አብሮ አደግ ጓደኞቹ የሚመሰክሩለት ወጣት ታምሩ ጉታ፤ ‹‹አቅማችን ውስን ሆኖ የምንሰጠው የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም በቂ የሚባል አይደለም፡፡ አንተም እንደታዘብከው ወጣቶቹ ቅንነትና ሞራል አላቸው፡፡
በመሆኑም ቤተሰቦቻችንን፣ ጎረቤቶቻችንን እና የአካባቢውን ማህበረሰብ አስተባብረን ነድአውያንን በማብላት አብረን ተደስተናል፡፡ እኛ አስተባበርን እንጂ ከማብሰያ ቦታ ጀምሮ እያንዳንዱ ነገር ማህበረሰቡ ከራሱ ቀንሶ ለሌላቸው በቅንነት የሚያደርገው ነው፡፡ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡
ወጣቱም በእምነቱ ሥር ሆኖ በጥሩ ሥነ ምግባር ታንፆ የማህበረሰቡን ወግና ባህል በማክበር እገዛ ለሚሹ ወገኖቹ ለመድረስ በአቅሙ የሚያደርገው ጥረት የሚያስመሰግን ነው።
የሌሎች ሰዎችና ድርጅቶች በጎፈቃድና እገዛ ታክሎበት ከዚህ በበለጠ ከዕለት እገዛ አልፎ የተጎሳቆሉ ወገኖቻችን ታክመው፣ ድነውና መቋቋም ችለው በተራቸው ለሌሎች አለንላችሁ ሲሉ ማየት እንደምንችል ተስፋ አለኝ፡፡ በሌላ በኩል በየአካባቢው የሚገኙ ወጣቶች ማህበረሰባቸውን አክብረውና ተከባብረው የፈጣሪ ስጦታ በሆነው ወጣትነታቸው ወንድሞቻቸውን የሚያስተምርና ሀገርን የሚጠቅም በጎ ተግባር መሥራት ይገባቸዋል፡፡ በጎነት የክፍያ ውጤት አይደለም በማለት አስተያየቱን ሠጥቷል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2011
ሙሐመድ ሁሴን