የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ አገልግሎት ስለመተግበሩ ምን ያህል መረጃ አለዎት? በአዲስ አበባ ከተማ እና በሌሎች አራት ክልሎች አገልግሎቱ እንደሚሰጥስ ያውቃሉ? የካፒታል ዕቃዎች ኪራይ ሥርዓት እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ በተለይም የካፒታል ፋይናንስ ችግር ላለባቸው ነባርና አዲስ ሥራ የሚጀምሩ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የካፒታል ዕቃዎች በፋይናንስ ኪራይ ወይም የዱቤ ግዥ በመስጠት የምርት ጥራትና ምርታማነታቸውን በማሳደግ በኩል የማይተካ ሚና ያበረክታል፡፡
በመሆኑም በኢትዮጵያ አገልግሎቱን መስጠት እንዲችል በአዋጅ ቁጥር 103/90 በ1990 ዓ.ም አቅጣጫ ቢቀመጥም በተቀናጀ መንገድ መተግበር ከጀመረ ግን ሁለትና ሦስት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በዚህ እና ተያያዠ ጉዳዮች ዙሪያ ከካፒታል ዕቃዎች ፋይናንስ ንግድ ሥራ አክሲዮን ማህበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ መሳይ እንሴኔ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ለንባብ በቅቷል፡፡
አዲስ ዘመን፡– የካፒታል ዕቃዎች የፋይናንስ ኪራይ አገልግሎት ምንድን ነው? አጀማመሩስ ምን ይመስላል?
አቶ መሳይ፡– የካፒታል ዕቃዎች የፋይናንስ ኪራይ ወይም በዱቤ ግዥ ስምምነት መሰረት ያለምንም መያዣ በተወሰነ ጊዜ ክፍያ በመፈፀም የማምረቻ መሣሪያ ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችል በአይነት የሚደረግ የፋይናንስ አቅርቦት ማለት ነው፡፡ በመሆኑም በእኛ በኩል የሚሰጡትም 3 አገልግሎቶች ሲሆኑ የፋይናንሻል ኪራይ፣ የዱቤ ግዥ እና የምክር አገልግሎቶች ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ በ1990 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 103/90 መሰረት አገልግሎቱን በሀገሪቱ እንዲተገበር አቅጣጫ ተቀምጦ ነበር፡፡ አቅርቦቱም በልማት ባንክ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት አማካኝነት እንዲከናወን ተመላክቶ ነበር። በዘርፉም የግል ባለሀብቱ ይሰማራበታል የሚል አስተሳሰብ የነበረ ቢሆንም አፈፃፀሙ ሲገመገም በሚፈለገው ደረጃ ወደ ተግባር መምጣት አለመቻሉን መንግሥት መረዳት ቻለ፡፡
የግል ባለሀብቱም ከሦስቱ አገልግሎቶች የአጭር ጊዜ ኪራይን ብቻ (በኮንስትራክሽን ዘርፍ) በመያዝ ወደ ተግባር መግባት ችሏል፡፡ ሆኖም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን መደገፍ ያልተቻለበት ሁኔታ በመፈጠሩ ነባሩን በአዋጅ ቁጥር 807/2005 እንዲሻሻል በማድረግ ክፍተቱን መሙላት የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል።በዚህ ምክንያት ራሱን የቻለ የካፒታል ዕቃ አቅራቢ ተቋም ሊኖር እንደሚገባ እምነት ተያዘ። በአራቱ ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሳቸውን የቻሉ በንግድ ሕጉ መሰረት የሚሠሩ የካፒታል አቅራቢ ተቋማት እንዲመሰረቱ ተደርጓል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኩል ፈቃድ አግኝተው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ተችሏል፡፡
አዲስ ዘመን፡– አዲስ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ለሚታሰበው የኢኮኖሚ ሽግግር ምን አስተዋጽኦ ያበረክታል?
አቶ መሳይ፡– እንደ ሀገር ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለሚደረገው ጉዞ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ አፈፃፀም ግምገማም የካፒታል ዕቃ አቅርቦት ክፍተት እንዳለበት ተለይቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በከተማው የተያዘው ኢንዱስትሪ ልማት በተለይም የካፒታል ዕቃ አቅርቦትን በማመቻቸት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን ማሳደግ ለከተማው እድገት ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ለውጥ የሚያስገኘው ጥቅም ከፍተኛ ነው፡፡ በመሆኑም ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛና ከፍተኛ ባለሀብት የሚደረገውን ሽግግር በመደገፍና በማፋጠን የጎላ ሚና ያበረክታል፤ እያበረከተም ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡– አገልግሎት እየተሰጠባቸው ያሉት ዘርፎች ምን ምን ናቸው?
አቶ መሳይ፡– የተቋቋመበት ዓላማ ክፍተት ያለበትን ዘርፍ ለመደገፍ ያለመ ነው፡፡ በመሆኑም እንደ ሀገር ክፍተት ያለባቸውና መደገፍ የሚገባቸው ተብለው የተለዩ እድገት ተኮር ዘርፎችን በመደገፍ ለኢንዱስትሪው መርነት መሰረት መጣልን ታሳቢ አድርጎ የሚሠራ ሲሆን በዚህ ዙሪያ ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ማሽነሪዎችን በማቅረብ ችግራቸውን የሚቀርፍ ነው፡፡
አገልግሎት ከሚሰጥባቸው ዘርፎች መካከል በዋናነት የተለያዩ የጨርቃ ጨርቅ አልባሳት ማምረቻ፣ የሹራብ ሥራ፣ የቆዳ ውጤቶች፣ የደረቅ ምግብ ማቀነባበሪያ፣ የብረታ ብረት ሥራ፣ የእንጨት ሥራ፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ፣ የእደ ጥበባት ውጤቶች፣ የኮንስትራክሽን ግብዓት፣ የመልሶ መጠቀም ማምረቻ፣ የህትመት እና ሌሎች የማምረቻ ማሽነሪዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡– በሕብረተሰቡ ተመራጭ የሚያደርጉ ምን የተለዩ ጥቅሞች አሉት?
አቶ መሳይ፡– የፋይናንሻል ሊዝ አገልግሎት በውጪው ዓለም በሰፊው ጥቅሙ የተለመደ አሰራር ነው፡፡ በእኛ ሀገር ደግሞ የሚያስገኛቸው ብዙ ጥቅሞች በመኖራቸው በአጭር ጊዜ የሥራ ፈላጊው ሕብረተሰብ የፍላጎት መዳረሻ እየሆነ ነው፡፡
እውቀትና ክህሎት ኖሯቸው በካፒታል እጥረት ሥራቸውን መጀመርና ማስፋት ላልቻሉ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች አቅማቸውን በማጎልበት በዋጋና በጥራት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በማድረግ ሀብት መፍጠር እንዲችሉ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የፋይናንስ ሥርዓት የካፒታል ዕቃዎች ኪራይ አገልግሎት ሂደት ተጠቃሚ በመሆን የካፒታል ዕቃ ባለቤት መሆን የሚቻልበት መልካም አጋጣሚን መፍጠር ችሏል፡፡
ለረዥም ጊዜ ተደራጅቶም ሆነ በተናጠል ለመሥራት እንቅፋት የነበሩ የዋስትና ችግሮችን ቀርፏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እንደ ሥራ ሁኔታው አዋጭነት የመሣሪያ ኪራይ ክፍያ ማጠናቀቂያ ጊዜ በረዥም ጊዜ (ከ3 ዓመት እስከ 6 ዓመት) ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ ከተጠቀሱት በተጨማሪ በኢንተርፕራይዞች የሚቀርቡ የማምረቻ መሣሪያዎች ከቀረጥና ታክስ ነፃ መደረጋቸው፣ ተከራዩ የካፒታል ዕቃውን በኪራይ በማግኘቱ ያለውን ካፒታል ለሥራ ማስኬጃ ማዋል እንዲችል ዕድል ፈጥሯል፡፡
በመሆኑም ለካፒታል ቁጠባ ጠቀሜታ ያለው፣ የተከራዮቹን የንግድ እንቅስቃሴና የመክፈል አቅም ከፍላጎት ጋር አገናዝቦ የክፍያ መጠንና የክፍያ ጊዜ ስምምነት ማድረግ የሚያስችል መሆኑ፣ እንደ ጥሬ ገንዘብ ለሌላ ላልተፈለገ ዓላማ የማይውል በመሆኑ ተከራዩ የጥሬ ገንዘብ ፍሰቱን በዕቅድ እንዲመራ ማስቻሉ፣ ከ4 እስከ 6 ወር የሚደርስ የብድር መክፈያ የእፎይታ ጊዜ የሚሰጥ መሆኑ እና ሌሎች በርካታ ጥቅሞች በማስገኘት ለሥራ ፈላጊዎችና ሥራቸውን ለሚያስፋፉ በጣም ተመራጭ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– ዘርፉ ትኩረት የሚሰጣቸው የማሕበረሰብ ክፍሎች አሉ? ተደራሽነቱስ ምን ያህል ነው?
አቶ መሳይ፡– አዎ ይኖራሉ፡፡ በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የሚሠራ ነው፡፡ በመሆኑም በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከሙያ ተቋማት ተመርቀው ሥራ አጥ ለሆኑ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና ለልዩ ፈጠራ ሥራዎች ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል፡፡
ከተደራሽነት ጋር በተያያዘ ቂርቆስና ልደታ ክፍለ ከተሞች በዋናው መሥሪያ ቤት አገልግሎት የሚያገኙ ሲሆን በሌሎቹ ክፍለ ከተሞች ቅርንጫፍ መክፈት ተችሏል፡፡ ቢሆንም ማህበረሰቡ ዘንድ በቅርበት መገኘት፣ እውቅና እና ግንዛቤ በሰፊው በመፍጠርና ተቋሙን በማስተዋወቅ በኩል ውስንነቶች አሉብን፡፡
አዲስ ዘመን፡– የገጠሙ እንቅፋቶችና የተወሰዱት መፍትሔዎች ካሉ?
አቶ መሳይ፡– ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ፈቃድ ያገኘን ቢሆንም መመሪያዎች ተርጉሞ ለሥራ ዝግጁ ከማድረግ አኳያና ከሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ፈጥኖ ወደ ሥራ መግባት ሳይቻል ቆይቷል። ወደ ሥራ ከተገባ ሦስት ዓመት ቢሆነውም በሙሉ አቅም መሥራት የተቻለው ለሁለት ዓመት ያህል ነው፡፡
የተቋሙ የፋይናንስ አቅም ውስንነት እንደተጠበቀ ሆኖ ከማሽን ዋጋ አኳያ የዶላር የምንዛሪ ዋጋ መጨመርና እጥረት መኖር፣ለማህበረሰቡ በሰፊው ግንዛቤ መፍጠር አለመቻል፣ እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ ተደራሽ አለመሆን እና ሰፊ አመኔታን ማሳደር አለመቻል ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ ከውጭ አገር ይሠሩ የነበሩ ሥራዎች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ ተደርጓል። የተለያዩ የልብስ የስፌት ማሽነሪዎች ይጠቀሳሉ፡፡ የበጀት ውስንነቶችን ለመቅረፍ ከተለያዩ አበዳሪ እና ረጂ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት በመሥራት ችግሩን ማቃለል ተችሏል፡፡
አሁን ላይ የብድር ፍላጎቱ ከፍተኛ እየሆነ ነው። መንግሥት ለዘርፉ ከሰጠው ልዩ ትኩረት አኳያ የማበደር ጣሪያችን (የብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠው የአደጋ ምጣኔ) 13 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ሲሆን እስከ አሁን የሰጠነው ግን ከፍተኛው 3 ሚሊዮን የሚደርስ ነው፡፡ በእኛ በኩል የማሽነሪ ዕቃዎች ወስደው በተወሰነ ደረጃ ከመንገጫገጭ የዘለለ ውድቀት የገጠማቸው ኢንተርፕራይዞች የሉም፡፡ በአጠቃላይ በቀጣይ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመለወጥ በሚደረገው ዘርፈ ብዙ ርብርብ ውስጥ ከዚህ የላቀ አስተዋጽኦ ማበረከት የሚያስችል መደላድል ተፈጥሯል፡፡ በቅንጅት ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ ከልብ እናመሰግናለን፡፡
አቶ መሳይ፡– እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2011
ሙሐመድ ሁሴን