ያልታረመው ወንጀለኛ

ኤርትራ ውስጥ አስመራ ላይ የተወለደው ዳንኤል በርሔ፤ እንደልጆች ቦርቆ በእናት እና በአባት እንክብካቤ ለማደግ አልታደለም:: ከእናቱ ተኪኤን አፅበሃ ጋር በመቀሌ ከተማ ሕይወቱን ሲገፋ፤ አባቱ በርሔ ስዩም ልጅን ለማሳደግም ሆነ ሚስትን ለማስተዳደር ያለባቸውን ግዴታ አይወጡም ነበር:: እንደውም አብረዋቸው አይኖሩም:: በዚህ ምክንያት ዳንኤል ገና በልጅነት ዕድሜው ከዓቅሙ በላይ እየሠራ እናቱን እያገዘ እራሱን ማስተማር ጀመረ::

ዕቃ ከመሸከም ጀምሮ ብረታብረት እስከመስራትና ቀለም እስከመቀባት ሲደርስ፤ ሥራው አደከመኝ ብሎ ትምህርቱን አላቋረጠም:: ቀን ይሠራል፤ ማታ ይማራል:: የእናቱን እና የእራሱን ወጪ እየሸፈነ ኑሮውን ይገፋል:: የአስረኛ ክፍል ብሔራዊ የማጠቃለያ ፈተናን ከወሰደ በኋላ ግን ትምህርቱን መቀጠል አልቻለም:: እንደውም መማር ቀርቶ ሕይወቱን የበለጠ የሚያከብድበትን እና ኑሮውን የሚያወሳስብበትን ወንጀል ፈፀመ::

ዳንኤል ራሱ በሰጠው የዕምነት ክህደት ቃል ላይ እንዳሰፈረው፤ ‹‹ የ10ኛ ክፍል የማጠቃለያ ፈተና ውጤቴን ተቀብዬ ወደቤት ስመጣ እናቴን የአባቱን ስም የማላውቀው ኃይለማርያም የተባለ ሰው አስገድዶ ሊደፍራት ሲል ደረስኩበት::›› ይላል::

ያየውን ለማመን የከበደው ዳንኤል እናቱን ለማዳን አማራጭ ለማግኘት ሲያማትር ብረት የሌለው የአካፋ ወፍራም እንጨት አገኘ:: ‹‹እናቴን አስገድዶ ሊደፍር ሲል አገኘሁት፤›› ያለውን ሰው ለመምታት ሰነዘረ:: ነገር ግን ሰውዬው አምልጦ እንጨቱ የእናቱ አናት ላይ አረፈ:: ደፋሪ የተባለው ሰው ሮጦ አመለጠ:: እናት መሬት ላይ ተዘርረው ደማቸው መፍሰስ ጀመረ::

ዳንኤል እናቱ በከፍተኛ መጠን ደም እየፈሰሳቸው መሆኑን ሲያይ ሮጦ ‹‹ እናቴ ልትሞትብኝ ነው::›› ብሎ ጎረቤት ጠራ:: የሰፈሩ ሰዎች ተጯጯሁ:: እናት ሃኪም ቤት ሳይሔዱ እዛው እንደወደቁ ደማቸው እየፈሰሰ ሕይወታቸው አለፈ:: ሰዎቹ ተሰብስበው እናትህን የገደልከው አንተ ነህ ብለው ከበቡት፤ ድርጊቱን መፈፀሙን ነገር ግን አስቦት እንዳልሆነ ለማስረዳት ቢሞክርም የሚያምነው ጠፋ:: ፖሊስ ተጠራ:: ይህ የሆነው በ2004 ዓ.ም ነው::

ዓቃቤ ሕግ የገዛ እናትህን ገድለሃል ሲል ከሰሰው:: ማስረጃ እና መረጃ ተዘጋጅቶ ፍርድ ቤት ቀረበ:: ምስክር ተሰምቶ ዳንኤል 20 ዓመት ተፈረደበት:: ለዘጠኝ ዓመት ከታሠረ በኋላ በ2012 ዓ.ም ከእስር ተፈታ:: ዳንኤል መቀሌ መቆየት አልፈለገም:: በዛ ላይ በትግራይ ጦርነት የነበረበት ጊዜ በመሆኑ አዲስ አበባ ገባ:: ነገር ግን አዲስ አበባ ላይ የሚያስጠጋው ወገን አላገኘም:: ምርጫው ሳይሆን በዕጣ ፈንታ ሳሪስ አካባቢ መኖር ጀመረ:: ሊስትሮ እየጠረገ ሲሠራ ቆይቶ፤ ባገኘው ገንዘብ በልቶ መተኛ ተከራይቶ ኑሮውን መግፋት ጀመረ:: የሥራ ፍላጎት እንዳለው የተረዳች አንዲት ሴት ተባብራው እንጨት ቤት ተቀጠረ፤ ኑሮ መሻሻል ጀመረ:: ዕድሜው 27 ላይ ደርሷል:: ለነገ የተሻለ ሕይወት እያሰበ ሥራውን ቢቀጥልም፤ ነገር ግን በድጋሚ ሌላ ሕይወቱን የሚያውክ ኑሮውን የሚያመሰቃቅልበት አጋጣሚ ተፈጠረ::

የፀጉር ቤቷ ወጣት

ወጋህታ ቀሳይ ትባላለች:: እጅግ የምታምር ለግላጋ የ25 ዓመት ወጣት ናት:: የአፍንጫዋ ሰልካካነት፤ የከንፈሯ እና የዓይኖቿ ውበት ማንኛውንም ወንድ ያማልላል:: ሳሪስ አደባባይ መኪና መሻገሪያ ድልድይ አካባቢ ፍሬሕይወት ሕንፃ ላይ ፀጉርቤት ተቀጥራ ስትሠራ ብዙ ወንዶች ይከጅሏት ነበር:: ወጋህታ እንደስሟ ብርሃን ሆና ሁሉንም በፈገግታ አስደስታ እና አሳስቃ ታልፋቸዋለች::

በሌላ በኩል ሥራዋን በትጋት ከመሥራት ውጪ፤ ማንም ላማግጥሽ ብሎ ለሚጠጋት ፊት አትሰጥም:: ዳንኤል ደግሞ በልዩ ሁኔታ ወዷታል:: ለተለያዩ ሰዎች ‹‹ሳያት ደስ ትለኛለች›› እያለ ደጋግሞ ያወራል:: እርሷ ደግሞ ሌሎች እርሷ ከማትፈልጋቸው እነርሱ ግን ከሚወዷት ወንዶች ለይታ አላየችውም:: ሲያናግራት መልስ ከመስጠት ውጪ ለፍቅር ግንኙነት ፈቃደኛ አልሆነችም::

ሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡30 አካባቢ እንደለመደው ዳንኤል ወጋህታን ሊያይ ሔደ:: ነገር ግን በማየት ብቻ ማቆም አልፈለገም:: ተጠግቶ ሊያቅፋት፤ ሊስማት እና ሊገናኛት ወደደ:: ዳንኤል ወደ ፀጉር ቤት በመሔድ የሽንት ቤት ቁልፍ ጠየቀ:: ወጣት ወጋህታ ፍፁም አልጠረጠረችም፤ ቁልፉን ሠጠችው:: እርሱ ግን ቁልፉን ብቻ ሳይሆን እርሷንም እንደሚፈልጋት ነገራት:: ልቀፍሽ፤ ልሳምሽ ብሎ አስቸገራት፤ ‹‹እምቢ እንዳትነካኝ::›› አለችው::

ዳንኤል በወጋህታ ምላሽ ተበሳጨ:: ቁልፉን ጥሎ ወደ ገበያ ሔደ:: ከገበያ ተመልሶ በድጋሚ ወደ ፀጉር ቤት ሔዶ አንኳኳ፤ ወጋህታ ቃሳይን የሽንት ቤት ቁልፍ ጠየቃት:: በድጋሚ ቁልፉን ሰጠችው:: ሽንት ቤት አካባቢ ደርሶ ወዲያው ተመለሰ:: ቁልፉ እምቢ አለኝ ብሎ እርሷ እንድትከፍት ሲጠይቃት ልትከፍትለት ወደ ሽንት ቤት ሔደች::

የመጨረሻዋ ሰዓት

ወጋህታ ዳንኤል የሽንት ቤት ቁልፍ እንቢ እንዳለው ገልፆ እንድትከፍትለት ሲጠይቃት አምናው ልትከፍትለት ሔደች:: ነገር ግን ሽንት ቤት ስትደርስ ወደራሱ አስጠግቷት ሊገናኛት ሞከረ:: ሙሉ ሰውነቷን መጥፎ ስሜት ተሰማት፤ ለመግለፅ በሚከብድ መልኩ ሰውነቷን ከበዳት፤ ፈቃደኛ አለመሆኗን ብትገልፅለትም ለማስገደድ ሞከረ:: ወጋህታ እንዲለቃት ታገለችው:: ቦታው ጠባብ በመሆኑ ከግድግዳው ጋር አጣብቆ ገበያ ሔዶ በ110 ብር የገዛውን ባለጥቁር እጄታ ቢላዋ በአንገቷ ላይ ሲደግን ወጋህታ የድረሱልኝ ጥሪ አሰማች::

ጩኸቷን ተከትሎ አንገቷ ላይ የደገነውን ቢላዋ አጠበቀባት:: ወጋህታ አንገቷን ተወጋች፤ አልወደቀችም በድጋሚ ጮኸች:: በቀኝ በኩል አንገቷ ላይ ያሳረፈውን ቢላዋ አንስቶ በግራ በኩል ደረቷን ወጋት፤ የግራ ደረቷ የታችኛውን ክፍል አጥንቷን በመውጋቱ ቢላዋው ሳምባዋ ላይ ደረሰ::

የወጋህታ የጩኸት ድምፅ የጎዳና ተዳዳሪው ምስክር አማኑኤል ጋር ደረሰ:: ጩኸት ወደሰማበት አቅጣጫ ሲመለከት በእምነበረድ ከተሠራው ደረጃ ላይ ዳንኤል እየሮጠ ሲወርድ አየው:: ዳንኤል ወንጀል መፈፀሙን የተጠራጠረው አማኑኤል ወደ ወጋህታ እየሮጠ እግረ መንገዱን ሰዎች ዳንኤልን እንዲይዙት ተማጸነ:: አጠገቧ ሲደርስ ከፍተኛ ደም ሲፈሳት ተመለከተ:: ዳንኤልን ሰዎች ተሰብስበው ያዙት:: ወደ ሳሪስ ፖሊስ ጣቢያ ስልክ በመደወል ወንጀል መፈፀሙ ተጠቆመ:: ወጋህታ ሆስፒታል ተወሰደች ነገር ግን ሕይወቷን ማትረፍ አልተቻለም::

የፖሊስ ምርመራ

የዕለቱ ተረኛ ፖሊስ ሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡30 አካባቢ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ክልል ልዩ ቦታው ሳሪስ አደባባይ መኪና መሻገሪያ ድልድይ አካባቢ ፍሬሕይወት ሕንፃ ላይ የተፈፀመ ወንጀል መኖሩን ጥቆማ ደረሰው:: ፖሊስ በአካል ተገኝቶ ወንጀል መፈፀሙን አረጋገጠ:: የ27 ዓመቱ ተጠርጣሪ ዳንኤል ከገበያ ሔዶ በገዛው ቢላዋ ወጋሕታን እንደወጋት መዘገበ::

ተጠርጣሪው ሳሪስ ፖሊስ ጣቢያ ተገኝቶ በፈቃደኝነት ወዲያው ቃሉን እንዲሰጥ ተደረገ:: ተጠርጣሪ ዳንኤል በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል ላይ እንዳብራራው፤ ወንጀሉን የፈፀመው ወጣት ወጋህታ ቃሳይን የሽንት ቤት ቁልፍ እንድትከፍትለት ሲጠይቃት ልትከፍት ስትሔድ ተከትሏታል:: በኋላም የግብረስጋ ግንኙነት ለመፈፀም ሲጠይቃት ፈቃደኛ ባለመሆኗ ከገበያ ሔዶ ቢላዋ ገዝቶ በመመለስ በድጋሚ የሽንት ቤት ቁልፍ እንቢ እንዳለው ገልፆ እንድትከፍት ጠርቷታል:: ልትከፍትለት በሩ አካባቢ ስትደርስ አንገቷን እና ደረቷን በቢላዋ እንደወጋት አምኗል::

መርማሪ ፖሊስም የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የፎረንሲክ ምርመራ ውጤትን፤ በወንጀል ስፍራው የተገኘው ቢላው እንዲሁም ተጠርጣሪ ዳንኤል ወጋሕታን እንደገደለ የሚያሳይ ገላጭ የሟች የአሟሟት ሁኔታን፣ ተጠርጣሪ ስለቱን የገዛበት ፌስታል ከነማሸጊያው፣ ወንጀሉ የተፈፀመበትን ቢላዋ በኤግዚቢትነት መገኘቱን አረጋግጦ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ እንዲከስ አቀረበ::

የዓቃቤ ሕግ ክስ

ዓቃቤ ሕግ በመርማሪ ፖሊስ የቀረበውን ማስረጃ ገላጭ ፎቶ ግራፎችን እንዲሁም ተከሳሾች በወ/መ/ስ/ህ/ቁ 27(2) መሠረት ለፖሊስ የሰጠውን የእምነት ክህደት ቃል በማስረጃነት አያይዞ እና የሰባት ሰዎችን ምስክርነት አካቶ እንዲሁም ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የፎረንሲክ ምርመራ በተገኘው ደብዳቤ መሠረት ጨካኝነቱን እና አደገኝነቱን በሚያሳይ መልኩ ሟች በቀኝ በኩል አንገቷን እና በግራ በኩል ደረቷን በመውጋት በድጋሚ የግራ ደረቷ የታችኛውን ክፍል የጎድን አጥንቷ በመውጋት ሳምባዋን በመውጋት በፈፀመው ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ተጠያቂ ሊሆን ይገባል፤ ተጠርጣሪ ዳንኤል ወጣት ወጋሕታን ገድሏታል ሲል፤ ለፍርድ ቤቱ ጉዳዩን አቀረበ።

ፍርድ ቤት በነበረው ክርክርም ተከሳሽ ዳንኤል በርሔ የእምነት ክህደት ቃሉ ላይ ድርጊቱን መፈፀሙን አምኗል:: ቀድሞ ጩኸቷን የሰማው የጎዳና ተዳዳሪው ምስክር አማኑኤል ፈቃደን ጨምሮ ሌሎችም ስድስት ምስክሮች ገዳይ ሲሮጥ አይተው እንደያዙት እና በኋላም በነበረው ሁኔታ እርሱም አምኖ እጅ መስጠቱን ተናገሩ:: በመጨረሻም ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ በበቂ ሁኔታ ያስረዳ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የሚከተለውን ውሳኔ አስተላለፈ።

 ውሳኔ

 በፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ጥቅምት 27/2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ በ23 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

አዲስ ዘመን  የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You