በርካቶች ስለሰላም ያላቸው እሳቤ ትርጓሜው ኃያል ነው:: ሰላምን ያለ አንዳች ማወላወል በበጎነት ይገልጹታል:: ያለምንም ጥርጣሬ ግምቱን ያጐሉታል:: ማንም ቢሆን ከሰላም ይልቅ ጦርነትን አይመርጥም:: መቼም ቢሆን በሰላም ውሎ ማደርን፣ በቸር ወጥቶ መግባትን ይሻል::
ከጦርነት፣ ከአመጽና ሽብር የጸዳ አካባቢ አውሎ ለሚያሳድረው ሕዝብ የሚኖረው ቱርፋት የበዛ ነው:: በእንዲህ ዓይነቱ ስፍራ የሚገኝ ነዋሪ ለትውልዱ የሚተርፈው ተስፋ በገንዘብ አይተመንም:: ምንጊዜም አትራፊ ነውና ዋጋው የበዛ እሴቱ የገዘፈ ነው::
ይህ ዓይነቱ ማኅበረሰብ ሁሌም ስለነገ የሚሰንቀው ትልምና ጉዞ በየሰበቡ አይከሽፍም:: በኮሽታ አይደናቀፍም:: አስተማማኝ ሰላም ካለው የሃሳቡን ይሞላል፣ የዕለት ዕቅዱን ይከውናል:: ረጅሙን መንገድ በስኬት ተጉዞ ያጠናቅቃል::
የሰላም አስፈላጊነት ለሰው ልጆች ብቻ አይደለም:: ለምድር ፍጥረታት ሁሉ በእጅጉ ወሳኝ ነው:: ኑሯቸው በዱር ገደል የሆነ አራዊቶች ደኑና ጋራው፣ ጫካና ጥሻው ቢነካባቸው አይወዱም:: በአንዳች ምክንያት የህልውና፣ የእስትንፋሳቸው መገኛ ሰላሙ ቢናጋ፣ ቅጥሩ ቢነቃነቅ በስፍራው አይገኙም:: ቦታውን ጥለው፣ አካባቢውን ርቀው ይሰደዳሉ.:: እግራቸው ሰላም ካለበት፣ እፎይታ ከሚኖርበት ስፍራ ይገኛል::
ይህ እውነት የሰላምን ወሳኝነት ያመላክታል:: ማንም ሕይወት ያለው ፍጡር ስለመኖር ሰላምን ሊላበስ ፣ ግድ ይላልና:: ከምንም በላይ ግን የሰውልጅ ስለራሱ በሰላም መኖር፣ ያለመኖር ቁልፉን በእጆቹ ጨብጧል:: የሰላም ትርጓሜ በወጉ በገባው ጊዜ ቃሉን በተግባር ይኖረዋል::
ሰላም ይሉትን ኃያልነት የኋሊት ከርችሞ ጆሮ ዳባ ሲል ደግሞ የእጆቹ ቁልፎች ለጥፋት ይዘጋጃሉ:: የሰላም ትርጓሜው የሚጎላው በጦርነት፣ በግጭትና ሁከት መሀል በሚፈጠር እውነታ ነው:: ጦርነት ባለበት ስፍራ ሰላም በእጅጉ ይናፍቃል:: ግጭትና ሁከት ልምድ በሆነበት አካባቢም ይህ ታላቅ እሴት ብርቅ መሆኑ አይቀሬ ነው::
ጦርነት ያየው፣ ግጭት የበዛበት ዓለም ሁሌም ከሰላም ሕይወት የራቀ ነው:: በዚህ ስፍራ የሚያድግ ኢኮኖሚ፣ የሚበለጽግ የሀገር ሀብት አይታሰብም:: ተምሮ፣ መለወጥ፣ ሀገር ወገንን ማሻሻል ይሉትም ዘበት ሆኖ ይቀጥላል::
ሰላም በጠፋ፣ እፎይታ በራቀ ጊዜ፣ ጦርነት እግሩን ይሰዳል፣ ግጭት ተስፋፍቶ ወንጀል ይዳብራል:: ግለኝነት፣ ራስ ወዳድነት ሕጋዊ መልክ ይላበሳል:: ይህ ዓይነቱ ውጤት ለሰውልጆች ሕይወት አደጋው የከፋ ነው:: ሰዎች በነፃነት ፣ ወጥተው እንዳይገቡ፣ ሠርተው እንዳያድሩ ሳንካ ይሆናልና::
ብዙዎች እንደሚያምኑት ሰላም የህሊና እረፍት ነው:: ውስጠትን በእፎይታ ያሳርፋል:: ለማንነት የማይሻር ሀሴትን ያሻግራል:: ከሁከት ከሽብርና ጦርነት የራቀ ትውልድ ሲኖር ከዓላማው ይገናኛል:: ሰላም ባለበት ሁሉም አለና ያሻን ለመፈጸም፣ በነፃነት ለመራመድ መንገዱ ግልጽና ሰፊ ነው::
አንድ ሰው በውስጡ የሚያዳብረው ጤናማ ስሜት ለሌሎች ሲጋባ ሰላማዊ ግንኙነት ይዳብራል:: ይህ እውነት ከማንም ጋር በፍቅርና በአንድነት ተግባብቶ እንዲኖር ምክንያቱ ነው:: ሰላምን ይዞ በሰላም መራመዱም ትርጉሙን መልካም አድርጎ ፍሬውን ያሳ ምራል::
ሰላም ይሉት ታላቅ ጉዳይ ኃያልነቱ የሚጎላው ከችግርና ሁከት፣ ከጦርነትና ስደት በኋላ ያጣጣሙት ጊዜ ነው:: አንዳንዴ በእጅ እንደያዙት ወርቅ ሆኖ አጠገባችን ለኖረው ሰላም ዋጋ ላንሰጥ እንችላለን:: በአንዳች አጋጣሚ እፎይታችን ሲነጠቅ፣ ሰላማችን ሲነሳ ግን የዚህ ታላቅ እሴት ውድነት በእጅጉ ይገባናል::
ዛሬ የዓለማችንን መልክ ከለወጡት ምክንያቶች አንዱ እንደዋዛ ባለመግባባት የሚከሰቱ ጦርነቶችና አደገኛ ግጭቶች ናቸው:: እነዚህ እውነታዎች አስቀድመው የሰዎችን ሰላም ለመንጠቅ የመነሻ ምክንያት ይሆናሉ:: የሰላም እጦትን ተከትሎ በሚነሱ መፈናቀሎችም የሰው ልጆች ከሀገር ቀያቸው ርቀው ይሰደዳሉ::
በክፉ ቀናት ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ርቀው ለመሄድ፣ ሮጠው ለማምለጥ ይሳናቸዋልና የችግሩ ሰለባ ከመሆን አያመልጡም::
ለትውልድ መሠረት የሆኑት እነዚህ ወገኖች በውስጣቸው ከሚኖር ታሪክ ጋር ለመባከናቸው ሰበቡ ደግሞ የሰላም ርሃብና ጥም ነው::
ሁሌም ሰላምን የሚሹ የዓለም ሀገራት በጠረጴዛ ዙሪያ ለስምምነት ይቀመጣሉ፣ የሀገር መሪዎችም ድርድርን ይይዛሉ:: ምንጊዜም የሰላም ዋጋው ከፍ ያለ ነውና ጦርነትን ያሸንፋል፣ ሁከት ግጭትን ይንዳል:: ሰላም ባለበት ሁሉ አሸናፊነት ከራስ ጋር ይሆናል::
ለመላው ዓለም በነጭ ርግብ የሚመሰለው የሰላም እሴት ጨለማ የሚያላብሰውን ፣ አለመግባባት አስወግዶ ፍጹም ሰላምን ለማስፈን ጉልበቱ ኃይል አለው:: መቼም ቢሆን ሰላም ካለ የልማት መንገዱ ይሰፋል፣ የትምህርት ዕድሉ ይቃናል:: የመኖር ዋስትና ዕውን ሆኖ ለመላው ዓለም ይዳረሳል::
የሰላም ዋጋው ሲጎላ በመተሳሰብና፣ በፍቅር የተመሠረተ ማንነት ይዳብራል:: ዜጎች ወንዝ ተሻግረው፣ ባህር አቋርጠው ቢሄዱ ከልካይ የላቸውም:: ሰላም ባለ ጊዜ ጨለማው ብርሃን ነው:: ጥሻ ገደሉ አያስፈራም:: ጫካ ተራራው አያሰጋም:: በሰላም ጊዜ አላፊ አግዳሚው ወዳጅ ዘመድ ነው:: ኮሽታ አያስደነብርም፣ ጥርጣሬ፣ ውሎ አያድርም:: ሁሌም በሰላም ጎዳና ተጓዥ መንገደኛ አይመረጥም :: ማንም በእኩል ይራመዳል::
የሰላም እጦት ችግሩ የበዛ ነው:: ሀገር ያፈርሳል፣ ወገን ያራርቃል፣ የነበረን መልካምነት አስወግዶ ስምን በክፉ ይተካል:: ይህ ዓይነቱ ሀቅ በሰፋ ጊዜ ርሃብ ስደትና መከራን ሊያስከትል ግድ ነው:: እንዲህ በሆነ ጊዜ የሰው ማንነት ትርጉም የለውም:: መኖር ይሉት ወግ ይዛባል፣ ሕይወት ይባል ታሪክ ይጠፋል::
ሰላም በሌለበት እንኳን ሰው ወፍ አታድርም:: ሀገር ምድሩ በስጋት ይሞላል:: በዚህ ጊዜ ሠርግ፣ ለቅሶ፣ ደስታ ኀዘን፣ ዕድር፣ ማኅበር፣ ታሪክ ናቸው:: ነግቶ በመሸ ቁጥር እንቅልፍ ብርቅ ይሆናል:: የጎረሱትን ለመዋጥ ጊዜ ይጠፋል:: ሰላም ከሌለ ሁሉም ምንም ነው:: የዘንድሮን መሥራት፣ የከርሞን ማቀድ፣ ዘበት ነው::
ሰላም ካለ ግን መንገዱ ቀና ነው:: የተዘራው ይታጨዳል:: ሀገር ምድሩ ገበያ፣ መንደሩ ፣ ከምኞቱ ይገናኛል:: ሰላም ካለ የደረሰ ጉብል ይዳራል፣ የተዳረው ሙሽራ ወልዶ ይስማል፣ ያልተማረው ፊደል በወጉ ይቆጥራል:: በሰላም ጊዜ የቋንቋው ቀለም ደማቅ ነው:: ሁሉም በአንድ ይስማማል:: በእኩል ዓይን ይግባባል::
ሰላም ካለ በምድር፣ በባህር በሰማዩ መንገድ አለ:: ይህ ዕውን ይሆን ዘንድ ሁሉም ቢያብር ቢተባበር ደግሞ ትውልድ ያለ ዕንቅፋት፣ ሀገር ያለችግር ትሻገራለች:: የሰላም እጆች ሲጣመሩ ድህነት፣ ድንቁርና፣ ጉስቁልና ታሪክ ይሆናል:: ሁሉም የሰላም ጽዋን ቢያነሳ ለበሽታው ፈውስ ያገኛል:: ማርከሻ መድኃኒቱ በመሀል እጁ ነውና::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም