የአካባቢው ህዝቦች አንተ ትብስ፤ አንች ትብሽ ተባብለው፣ ተከባብረውና በፍቅር የሚኖሩበት ቀዬ ባለፉት ሶስት ዓመታት የስጋት ቀጣና ሆኗል። እነዚህ ሁለት ህዝቦች በጥርጣሬ ሲተያዩ ቆይተዋል። ከብቶች ተዘራርፈዋል፡፡ በባላጣነት ተያይተዋል። በዚህ የተነሳም አካባቢው የግጭት ስጋትና ቀጣና ሆኖ ለሶስት ዓመታት ዘልቋል።
ዛሬ ግን በአካባቢው ሰላም ለማስፈንና ወንድማዊና እህታዊ ግንኙታቸውን ለማደስ በጋር መድረክ እየተወያዩ ናቸው፡፡ በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ጉጂና በደቡብ ክልል የቡርጂ ልዩ ወረዳ የህብረተሰብ ክፍሎች፤
በእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በአስተ ዳደር ወሰኖቻቸው አካባቢ መቼም ቢሆን ታይቶ የማይታወቅ ግጭትና ቅራኔ ተፈ ጥሮ ቆይቷል፡፡ ይህም የአካባቢው ሰላም ከመደፍረሱ ባሻገር በሁለቱም ወገን በአካባቢው የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማህበራዊ ህይወት አመሰቃቅሎ ቆይቷል፡፡ ሰዎች ተፈናቅለዋል፤ ተማሪዎች ትምህርታቸውን መከታተል አልቻሉም፤ ተፈናቃዮች ለዕርዳታ ተዳርገዋል። ኑሮአቸው ተቃውሷል፡፡
የሰዎችን ማህበራዊ ህይወት ያመሰ ቃቀለውን አሳዛኝ ክስተት ለመለወጥና አካባ ቢውን ወደ ቀደመው ሰላም ለመመለስ የምዕራብ ጉጂ ዞንና የቡርጂ ልዩ ወረዳ የአገር ሽማግሌዎችና አመራሮች እየሰሩ ናቸው፡፡
የቡርጂ ልዩ ወረዳ የጸጥታ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ኢሳቅ ጨምዶ፤ የጉጂና የቡርጂ ማህበረሰቦች በደስታም ሆነ በሀዘን ጊዜ አብረው የሚረዳዱና ዘመናትን የዘለቀ በአብሮነት ያሳለፉ ናቸው፡፡ በአካባቢው ተጋግዘውና ተባብረው የሚኖሩ፤ አንዱ የሌላውን አብሮነት የሚፈልጉ፤ የተሳሰሩና የጋራ የህልውና ገመድ ያላቸው ናቸው፡፡
ለአብነትም ከብቶቻቸውን በአንድ የግጦሽ ስፋራ የሚያሰማሩ፤ በጋራ ገበያ የሚገበያዩ፤ በኑሯቸውም ቢሆን ማህበራዊ ትስስር የነበራቸው ህዝቦች ናቸው ይላሉ። ሆኖም ባለፉት ሶስት ዓመታት በእነዚህ ህዝቦች መካከል የቅራኔ ንፋስ መንፈሱን አውስተዋል፡፡ በአካባቢው ግጭት ተከስቶ በሁለቱ የአስተዳደር ወሰን አካባቢ ያሉ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውና በባላንጣነት መተያየት መጀመራቸውን አልሸሸጉም። የግጭቱ መንስኤ ደግሞ እንደቀድሞው በግጦሽ ሳርና ውሃ ሳይሆን የፖለቲካ ነጋዴዎች በለኮሱት እሳት መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡
ሆኖም የጉጂ ዞንና የቡርጂ ልዩ ወረዳ አመራሮችና የአገር ሽማግሌዎች የሁለቱን የህዝቦች የቀደመ የጠበቀ ትስስርና አብሮነት ለመመለስ ሁለተናዊ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ተስፋ ሰጭ ውጤቶች መገኘታቸውን አንስተዋል፡፡ ለምሳሌም፤ ለሶስት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው በጋራ መገበያየት በሁለቱ ህዝቦች መካከል ውይይት ከተጀመረ ወዲህ እንደገና ተጀምሯል። የችግሩን መንስኤና ጥፋተኞችን በሁለቱም ወገን ተለይተው ርምጃ እንዲወሰድባቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ህዝቡ አጥፊዎችን ወደ ህግ በማቅረቡ ሂደት ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ነው የገለጹት፤
የምዕራብ ጉጂ ዞን የሰላምና የጸጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ ደስታ ኤታና በበኩላቸው፤ ሁለቱም ህዝቦች በግለሰብ ከሚነሳ ግጭት በስተቀር በማህበረሰብ ደረጃ ተጋጭተው አያውቁም፡፡ ከሶሰት ዓመታት ወዲህ ግን ይህ መልካም ግንኙነት በፖለቲካ ነጋዴዎች ጥላሸት ሊቀባ ችሏል ይላሉ፡፡ የተፈጠረው ግጭትም በሁለቱ ዞንና ልዩ ወረዳ አዋሳኝ የሚኖሩ ህዝቦች ማህበራዊ ህይወታቸው እንዲመሰቃቀልና ከቀያቸውም እንዲፈናቀሉ ማድረጉን አውስተዋል፡፡ እርስ በርስ ከብቶችን መዘራረፋቸውንም ነው ያወሱት፤
በሁለቱም ወገን ያለው ህዝብ ከግጭቱ በስተጀርባ የነበሩ የፖለቲካ አመራሮችን ሆነ በድርጊቱ የተሳተፉ አካላትን ህብረተሰቡ አጋልጦ ለህግ እንዲቀርቡ ለማድረግ በጋራ ውይይት መወሰኑ በአካባቢው የሰላም አየር እንዲነፍስ አድርጓል ባይ ናቸው፡፡ ከአገራዊ ለውጡ በኋላም በእነዚህ ሁለት ህዝቦች መካከል ቀደም ሲል የነበረውን ሰላም ለማውረድ በፖለቲካ አመራሩ በኩል በሙሉ ልብ እየተሰራ እንደሚገኘ ጠቅሰዋል፡፡
“የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ” በሚለው ብሂል መሰረትም የተፈጠረውን ግጭት ለማስወገድ የአገር ሽማግሌዎች ግንባር ቀደሙን ሚና እንዲጫወቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንና ጥሩ ለውጥ መታየቱን ተናግረዋል።
ምክንያቱም ግጭት ገፅታን ጎድቷል፤ ንብረት አውድሟል፤ የሰው ህይወት አጥፍቷል፤ ሰዎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል፤ የዜጎችን ህይወት አመሰቃቅሏል። ስለዚህ መንግስትም ሆነ ህዝቡ የየራሳቸውን የቤት ስራ በአግባቡ በመስራት የአካባቢውን ሰላም መመለስ አንገብጋቢ አጀንዳቸው አድርገው እየሰሩ ናቸው ብለዋል፡፡
የቡርጂና የጉጂ ህዝቦች ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖት የሚጋሩና የተሳሰሩ ህዝቦች ናቸው። የፖለቲካ ነጋዴዎች በፈጠሩት ግጭት የሰው ህይወት እንዲጠፋና ደም በከንቱ እንዲፈስ ሆኗል፡፡ ሆኖም ችግሩ እንደተፈጠረ ቁጭ ብሎ በመነጋገር መፍታት ይቻል ነበር። ስለዚህ ካለፈው ስህተትና ጥፋት በመማር የሁለቱን ህዝቦች አብሮነትና አንድነት በልማት ለማስተሳሰር የአመራሩ ሀላፊነት ነው፡፡
ብዙ ጊዜ በኢትዮጵያ የአስተዳደር ወሰን አካባቢዎች ግጭቶች የሚከሰቱት በሁለት መንገድ ሲሆን፤ አንደኛ በሀብት ፍትሀዊ አጠቃቀም ነው። በተለይ በአርብቶ አደሮች አካባቢ የአስተዳደር ወሰኑ በትክክል ተቀምጦ እያለም እንኳን ለግጦሽ ሳርና ውሃ ፍለጋ ከአንዱ ክልል ወደ ሌለው ክልል ይንቀሳቀሳሉ። በህገ መንግስቱ ህዝቦች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ቢደነገግም አፈፃፀሙ ላይ መስተዳድሮቹ በትክክል እየሰሩበት ባለመሆኑ ግጭቶች እየተፈጠሩ መሆኑን የፖለቲካ ምሁራን ይናገራሉ።
በጉጂና በቡርጂ አወሳኝ አካባቢዎች የተከሰተው ችግር ምንጩ በሁለቱም ወገን ግለሰቦች የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር ህዝቡን በጥቃቅን ጉዳዮች እየቀሰቀሱ እርስ በራስ እንዲጋጩ ማድረጋቸው መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ። ሁል ጊዜ ችግሮች የሚፈጠሩት ጥቅማቸውን ብቻ በሚያሳድዱ ፖለቲከኞች አማካኝነት ነው፡፡ እነዚህን ግለሰቦች ከህዝቡ ነጥሎ ማውጣት አስተዳደራዊ አልያም ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ሲሉ መንግስትን ጠይቀዋል ።
በጉጂና በቡርጂ መካከል የነበረውን ግጭት ለመፍታት ህብረተሰቡን በማሳተፍ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለመጀመር ዕቅድ አውጥተን ወደ ስራ ገብተናል የሚሉት ደግሞ የጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ፤ ህብረተሰቡ ራሱ እኛ ጥልና ግጭት አንፈልግም ብሏል፡፡ ለግጭት እንደ መነሻ ምክንያት የሚጠቀሰውን ውሃና የግጦሽ ሳር በጋራ ለመጠቀምና ሰላም ለማስፈን የቡርጂና የጉጂ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ተስማምተዋል፡፡ የተፈናቀሉም ካሉ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ይደረጋል፡፡ ይህን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር ቀጣናውን የሰላም አየር እንዲነፍስበትና ልማት እንዲስፋፋበት ይሆናል ሲሉ ነግረውናል፡፡
በዚህ ረገድ የምዕራብ ጉጂ ዞንና የቡርጂ ልዩ ወረዳ የሰላምና የጸጥታ ሀላፊዎች ከህዝቡ ጋር በመተባበር ብዙ ስራ መስራት ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም ችግሩ ስር ሳይሰድና ጥፋት ሳያስከትል በውይይትና በድርድር መፍታት ይቻላል። እናም ችግሩን በመፍታት ዙሪያ ከአመራሮቹ ጎን ለጎን ህዝቡም እርስ በእርስ እንደ ችግር የሚያነሳቸው ጉዳዮች ላይ በግልፅ እንዲወያይ ማድረግ ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በሰላም አብሮ የመኖር እሴት ማጎልበትና ሳይሸራረፍ ጠብቆ ለሚቀጥለው ትወልድ ማስተላለፍ ከአገር ሽማግሌዎችና ከህብረተሰቡ ይጠበቃል፡፡
ምክንያቱም ግጭቶች የሰዎችን ማህበራዊ ህይወት እያናጉ ናቸው፡፡ በግጭቶች ምክንያት ሰዎች ቀያቸውን ትትው እንዲፈናቀሉ አድርጓል፤ የህጻናት ጤና ይቃወሳል፡፡ ለትምህርት የደረሱ ልጆችም ከትምህርታቸው ይስተጓጎላሉ፡፡ የቀጣይ ህይወታቸው ተስፋ ንም ያጨልማል፡፡ ለልመና ይዳርጋል፡፡ በጥቅሉ ለከፍ ችግር ያጋልጣል፡፡
ግጭቶቹ ደግሞ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህላዊና ማህበራዊ መገለጫ አላቸው። ሁለቱም ዞንና ልዩ ወረዳ በጋራ ዕቅድ አውጥተውና ችግሮችን ለመከላከል እየተ ናበቡ ቀጣይነት ያለው ስራ መስራት ካልቻሉ በስተቀር ችግሩ ሲፈጠር አስታርቆ መመለስ በቂ አይደለም። የችግሮቹ መንስኤ ምንድን ናቸው ተብሎ በቀጣይነት እየተጠና መፍትሄ እየተሰጠው መሄድ ይኖርበታል፡፡ በኢትዮጵያ የሽምግልና ስርዓት በህብረተሰቡ ትልቅ ተሰሚነት አለው፡፡ ስለዚህ የአገር ሽማግሌዎችን በመጠቀም በአካባቢው ባለፉት ሶስት ዓመታት የደፈረሰው ሰላም በዘላቂ መልኩ እንዲነፍስ ማድረግ ተችሏል። ምክንያቱም ውይይት የማይፈታው ነገር የለምና ፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2011
ጌትነት ምህረቴ