የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በግብርና ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ዘርፉ ለአገሪቱ ከ35 በመቶ በላይ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ 79 በመቶ የሚገመተው የህብረተሰብ ክፍልም በዚሁ ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችም ቢሆን ከ79 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው የሚሸፈነው በግብርና ምርት ነው፡፡ ይህንን በመገንዘብም መንግሥት የግብርና ዘርፉን ለማዘመን የተለያዩ ተግባራት ሲያከናውን ቆይ ቷል፡፡
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር አብርሃ አዱኛ፤ ለትግበራው ከፍተኛ ግምት የተሰጠው የመስኖ ልማት ዘርፍ በቀዳሚነት ተጠቃሽ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ከሚሠሩ ሥራዎች መካከልም የመካከለኛና ሰፋፊ የእርሻ ግድቦችን ማስፋፋት፤ ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚሆኑ ምርቶች እንዲመረቱ በማድረግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት ተክቶ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ይላሉ፡፡
ሚኒስቴሩ በአገሪቱ እየተስፋፋ ያለውን ሥራ አጥነት ለመቀነስ በአዲስ ስልት ለመተግበር ከቀየሰው ተግባር መካከልም የተማሩ ወጣቶችን በመስኖ ዘርፍ ማሰማራት ተጠቃሽ መሆኑን አመለክተው፤ የተማሩ ወጣቶችን በዘርፉ አሰማርቶ ግብርናውን በዘመነ መንገድ እንዲተገበር ማድረግ ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
ትግበራው ለወጣቶቹ ካፒታል በመፍጠር በኩል የላቀ ድርሻ ይኖረዋልም ባይ ናቸው። ከዚህ ባሻገርም በመርሐ ግብሩ የሚሳተፉ ተመራቂ ተማሪዎች ሌሎች ወጣቶችን ቀጥረው በማሠራት ሀብት እንዲያከማቹ ያስችላቸዋል፤ ሲሉ ነው ዶክተር አብርሃ የሚገልጹት፤
የመጀመሪያው የወጣቶች የመስኖ ልማት መርሐ ግብር በ2009 ዓ.ም ተተግብሮ ሲሠራበት መቆየቱንም ያስታውሱና፤ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በግድቦች የተያዘውን ውሃ መነሻ በማድረግ፤ የከርሰ ምድርን ውሃ እና ወንዞችን በመጠቀም የተሠራ እንደነበርም ይናገራሉ፡፡ ይህ ትግበራ ቀጥሎም የተማሩ ወጣቶች በዘመነ መንገድ በዘርፉ እንዲሰማሩ ለማስቻል መታቀዱንም ይጠቅሳሉ።
ሰሞኑን በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት የተማሩ ወጣቶች ተለይተው ስልጠና እየወሰዱ መሆናቸውንም ጨምረው አብራርተዋል። የተማሩ ወጣቶች በግብርና ሥራ መሰማራታቸው ለዘርፉ መዘመን ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋልም ይላሉ። ዶክተር አብርሃ፤
በግብርና ዘርፍ ለመሰማራት ስልጠናውን እየወሰዱ ከሚገኙት መካከል ወጣት እድሪስ ዓሊ አንዱ ነው፡፡ እርሱ እንደሚለው ትግበራው ዘግይቶ የተጀመረ ነው። ከዚህ በፊት ከተንዳሆ እርሻ ወስደው ሲሠሩ የነበሩ ጓደኞቻቸው ያገኙትን ውጤት በማየታቸው እነርሱም ሆነ በአብዛኛው የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ዘንድ ወደ ዘመናዊ እርሻ ለመግባት መነቃቃት ተፈጥሯል፡፡ በመሆኑም ወደ ሥራው ለመግባት ቁርጠኞች ናቸው፡፡
ዘመናዊ ግብርና በዘርፉና በተዛማጅ ሙያዎች በሰለጠኑ ወጣቶች መጀመሩ ከአፋር ክልል ማህበረሰብ የበለጠ ለአገር ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ክልሉ ሜዳማ ነው፡፡ ለረጅም ዓመታት በእንስሳት ግጦሽ ያሳለፈና አብዛኛው መሬት እርሻ ያልተሠራበት ነው። ድንግል መሬትና ምቹ የአየር ንብረት አለው፡፡ የአዋሽ ተፋሰስ ወንዝም አካባቢውን አቋርጦ የሚያልፍ በመሆኑ ለእርሻ ሥራ አመቺነት አለው። ይላል ወጣት እድሪስ፤
ክልሉ ከጂቡቲ ድንበር በአጭር ኪሎ ሜትር ርቀት እንደመገኘቱም ለውጭ ገበያ ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራል የሚለው ወጣት እድሪስ፤ በአፋር ክልል ዝናብ ተከትሎ ይሄድ የነበረውን ማህበረሰብ ወደ ከፊል አርሶ አደርነት ማምጣት ይቻላል። ለክልሉ ማህበረሰብም የሥራ ዕድል ይፈጥራል ይላል፡፡
አሁን በአፋር ክልል በተማሩ ወጣቶች የተጀመረው ዘመናዊ እርሻ በርካታ ስኬቶች ይኖሩታል የሚለው ወጣት እድሪስ፤ “ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን እጥረት ይቀርፋል። የአብዛኛውን ወጣት በአገር ውስጥ ሠርቶ የመለወጥ ዕድልም ያሰፋል” ይላል፡፡
የሌሎች አካባቢ ወጣቶች መጥተው በዘርፉ የሚሰማሩበት ዕድል የሚፈጥር በመሆኑም እየላላ ያለውን የአንድነት ብሎን ያጠብቀዋል፤ የሌሎች ክልል ወንድሞችና እህቶችም ወደ አፋር ክልል ገብተው የሚያለሙበት ዕድል ይፈጥራል በአብሮነት ላይ የሚያበረክተው ድርሻ አለው። ሲልም ያክ ላል።
ሌላው ተሳታፊ ወጣት ከድር አሊም፤ ጠንክረን ከሠራን ከእራሳችን አልፈን ለሌሎች ሥራ መፍጠር የሚያስችለን በመሆኑ አጋጣሚው መልካም ዕድል ይዟል ይላል፡፡ በአፋር ክልል በስንዴና በአቦካዶ ምርት ውጤታማ ተሞክሮ መኖሩን የሚያመለክተው ወጣት ከድር፤ ለሥራው ኃላፊነት ወስደን ጠንክረን መሥራት ይገባናል ይላል፡፡ ውጤታማ እንዲሆኑም በፌዴራልና በክልል የሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎች ድጋፍ፤ ምክርና ክትትል እንዲያደርጉላቸው ጠይቋል፡፡
ሌላው ሰልጣኝ ሀይደር መሀመድም፤ በዘመናዊ መንገድ ወደእርሻ ሥራ እንዲሰማሩ መደረጋቸው ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ይጠቅስና፤ የሥራ ዕድል እንደሚከፍት፤ የአፋር ክልልን የዘመናዊ እርሻ ማዕከል ለማድረግ የሚረዳ፤ የክልሉን ገቢ የሚያሳድግና ለግብርና ምርት ማቀነባበር ግብአት የሚሆን ምርት ለማግኘት የሚጠቅም መርሐ ግብር መሆኑን ይናገራል። ሌሎች ወጣቶችም በቀጣይ ዕድሉን እንዲያገኙ መሠራት እንዳለበትም ያመለክታል፡፡
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፤ በ2011 ዓ.ም በግብርና እና ተያያዥ ሙያዎች የተመረቁ 12 ሺህ ያህል ተማሪዎችን በመስኖ ልማት እንዲሰማሩ ዕቅድ መያዙን ይጠቅሳሉ። ለዚህ ትግበራም በአገር አቀፍ ደረጃ 50 ሺህ ሄክታር መሬት በዘመናዊ መንገድ እንዲለማ መለየቱንም ይጠቁማሉ።
ትግበራው በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ሥራ አጥነት ለመቅረፍ እና ድህነትን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ያመለክታሉ። ይህ ጅማሬ በመሬት ስፋትና በተሳታፊዎች ቁጥር በየዓመቱ እያደገ እንዲሄድ እንደሚደረግም ነው የሚያመለክቱት፤
እንደ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ማብራሪያ፤ የተማሩ ወጣቶችን በማደራጀት መሬት፣ ቴክኖሎጂ እና ፋይናንስ በማቅረብ የመስኖ ልማት እንዲስፋፋ ማድረጉ ግብርናውን እንዲዘምን ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታል፡፡
ትግበራው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች በመተካት የውጭ ምንዛሬን ያስቀራል፤ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤የወጪ ምርቶችን በዓይነትና በብዛት ለማሳደግ ያስችላል። እንዲሁም በአገር ውስጥ እየተገነቡ ላሉ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት ለማቅረብ ያግዛል፡፡
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች አገር መሆኗን የሚያነሱት ኢንጂነር ዶክተር ስለሺ፤ በአማካኝ ወደ አንድ ትሪሊዮን ኪዮብ ውሃ የዝናብ መጠን ይገኛል፤ ከዚህ ውስጥ 12 በመቶ ወደ 22 ቢሊዮን ሜትሪክ የወንዝ ውሃ ሆኖ በገጸ ምድር ይፈስሳል ይላሉ፡፡ 40 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዮብ የሚሆነው ደግሞ ወደ መሬት ዘልቆ እንደሚከማች ይጠቁማሉ፡፡
የመሬትን መጠን ሲያመለክቱም በአገር ውስጥ ሊለማ የሚችል 5 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያዩ ተፋሰሶች ውስጥ ተጠንተው የተቀመጡ መኖራቸውን ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ይጠቁማሉ፤ እንደርሳቸው ገለጻ፤ በከፍተኛ መስኖ እስከአሁን የለማው ግማሽ ሚሊዮን ሄክታር ብቻ ነው። በትናንሽ መስኖ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር ለምቷል ተብሎ ይገመታል፡፡ በጥቅሉ እስከአሁን የለማው መሬት ከ20 በመቶ ያልዘለለ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡
በተቀናጀ የመስኖ ልማት ለመሰማራት የሚሰለጥኑት ወጣቶች ትኩረት ሰጥተው በመሥራት ይህንን ታሪክ መቀየር እንዳለባቸውም ያመለክታሉ። ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ማልማት የሥራ ዕድል ለማሳደግ ድርሻው ከፍተኛ ነው፡፡
ትግበራውን ለማሳካት በተለያዩ ግድቦች ተይዞ የሚገኘውን ውሃ ጥቅም ላይ ይውላል ሲሉ የሚያብራሩት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ፤ በአቅራቢያ ለሚገኙ መሬቶች በማዳረስ፤ የከርሰ ምድር ውሃን በማልማት፤ ተፋሰሶችን ተከትሎ ባሉ መሬቶችን ወንዞችን በመጥለፍ ተጨማሪ የመስኖ መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋትን እንደሚያካትትም ይገልጻሉ። ሰልጣኞች ለስኬቱ ትኩረት ሊሰጡ እንደ ሚገባም ያሳስባሉ፡፡
ለዘንድሮው መርሐ ግብር በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች 12 ፕሮጀክቶች መለየታቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በአፋር ክልል የተንዳሆን የመስኖ ግድብ በመጠቀም ስድስት ሺህ ሄክታር ይለማል ይላሉ። ለዚህም በመጀመሪው ዙር በአፋር ክልል 300 ወጣቶች ተመልምለው የመጀመሪያ ዙር ስልጠና መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
ከአፋር ክልል በተጨማሪም፤ በተያዘው በጀት ዓመት የሚተገበር፤ ከኦሮሚያ ክልል 863፣ ከሶማሌ ክልል 750፣ ከጋምቤላ ክልል 420 ወጣቶች መመዝገባቸውን አመልክተው፤ ስልጠና ለመውሰድ በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ይገልጻሉ፡፡ በትግበራው በግብርናና ተመሳሳይ ዘርፎች የተማሩ ወጣቶች እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል፡፡
መንግሥት ዘመናዊ እርሻ እንዲስፋፋ አስፈላ ጊውን ግብዓቶች ለማሟላት ፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ጥረት ያደርጋል ያሉት ዶክተሩ፤ ወጣቶ ችም ራሳቸውንና ማህበረ ሰባቸውን ጠቅመው በአገር ልማት እና ዕድገት የበኩላቸውን ድርሻ ሊያበረክቱ እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2011
ዘላለም ግዛው