ኢትዮጵያ ከ900 ሺህ በላይ ዓለም አቀፍ ስደተኞችን ተጠልለው የሚኖሩባት ሀገር ናት:: እነዚህ በርካታ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች በሀገሪቱ ድንበር አካባቢዎች ይኖራሉ:: የሚኖሩባቸው አካባቢዎች መሠረተ ልማት ያልተሟሉባቸው በመሆናቸው ለበርካታ ችግሮች መዳረጋቸውን ይነገራል::
በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች መሠረት ስደተኞች ከተሰጧቸው መብቶች መካከል ተጠልለው በሚኖሩበት ሀገር ዲጂታል መታወቂያ የማግኘት፣ የመማር፣ ሥራ የመሥራት እና መሰል መብቶች እንዳላቸው ተመላክቷል:: እነዚህ መብቶታቸው ለመጠቀም ከዘመኑ ጋር አብሮ መራመድ የሚያስችላቸው የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው ይታመናል::
አሁን ባለው ሁኔታ ስደተኞችን የሚኖሩባቸው መጠለያዎች ከዲጂታል ዓለም ራቅ ያሉ ስለሆኑ ለመማርም ሆነ ወደ ሥራ ለመቀላቀል የሚያደርጉት ጥረት አዳጋች ያደርገዋል:: ይህ ችግር ለመቅረፍ ደግሞ ከቴክኖሎጂ በማቀራራብ ዲጂታልን ለማስፋት የሚያስችሉ ሥራዎች መሥራት የሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅ ተግባር ነው::
በቅርብም ስደተኞችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ሥራዎች በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት በዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት (ILO)፣ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽን (አይሲቲ ፓርክ)ና በሱማሌ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ መካከል ተደርጓል::
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶክተር) ወቅት እንደተናገሩት፤ ስምምነቱ ስደተኞችንና በአካባቢው ለሚኖረውን ማኅበረሰብ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ምቹ የሥልጠና እና የሥራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ነው::
እሳቸው እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ዲጂታል መር የኢኮኖሚ ልማት ለመገንባት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ሥራ በመግባቱ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው:: ስትራቴጂው አካታች በማድረግ የቴክኖሎጂ የለውጥ ኃይል በመገንባት ስደተኞችን እና ተደራሽ ያላደረጋቸው ተጋላጭ ቡድኖችን ተደራሽ በማድረግ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማስፋት ያለመ ነው::
ኢትዮጵያ ስደተኞችን በመቀበል ረጅም የሚያኮራ ታሪክ ያላት ሀገር ናት ያሉት ሚኒስትሩ በለጠ(ዶ/ር)፤ ስምምነቱ የዲጅታል መሠረተ ልማትን ለማሟላትና በሀገሪቱ ተጠልለው የሚገኙ ስደተኞች በዘርፉ ያላቸውን ክህሎት እንዲያሳድጉ የሚረዳ መሆኑን አመላክተዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የቴክኖሎጂ እድገት ፍኖተ ካርታ ብቻ ሳይሆን የዲጂታል አብዮቱ እውነተኛ አቅም የሚታይበት በመሆኑ ሁሉም ሰው የሚያሳትፍ እድል እንዳለው ጠቅሰው፤ ይህም የሚሆነው ስደተኞችን እና ሌሎች ያልተካተቱ የማኅበረሰብ ክፍሎች አካታች ሲያደርግ እንደሆነ አመላክተዋል ::
ሚኒስትሩ በለጠ (ዶ/ር)፤ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚቻለው ስደተኞችን፣ ተጋላጭ ማኅበረሰቦችንና ሁሉንም የማኅበረሰብ አካላት በማሳተፍ መሆኑን ይናገራሉ:: ስምምነቱም ስደተኞች የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ምቹ ምሕዳር የሚመቻችበት መሆኑን ያስረዳሉ::
የዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት (ILO) በኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን የዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት ቢሮ ዳይሬክተር አሌክሲዮ ሙሲንዶ በበኩላቸው፤ ድርጅታቸው አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል::
ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያና ኤርትራ የተውጣጡ ከ916 ሺህ በላይ ስደተኞችን እያስተናገደች መሆኑን አንስተው፤ ስምምነቱ በኢትዮጵያ የሚገኙ በርካታ ስደተኞች የዲጂታል ክህሎትን በማሳደግ የሚያጋጥማቸውን የመረጃ ክፍተት ለመሙላትና የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ያለመ መሆኑን ገልጸዋል:: ስምምነቱም ሴቶችን ወጣቶችን ጨምሮ ስደተኞችንና የተገለሉ ቡድኖች የበይነ መረብ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት ዘርፍ ዋና መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ስዩም መንገሻ በበኩላቸው የሦስትዮሽ ስምምነቱ ሰፊ ፋይዳ እንዳለው ይናገራሉ:: እሳቸው እንደሚሉት፤ ከዲጂታል አካታችነት እና ከዲጂታል ሊትረሲ ጋር በተያያዘ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ነው:: ይህም ስምምነትም ዲጂታል አካታችነት ስትራቴጂን (digital inclusion strategy) ለመሥራት የሚያስችል ትልቅ ግብዓት ይሆናል::
‹‹ዲጂታል ስትራቴጂው እስካሁን ባለው ሂደት የስደተኞች ካምፕ ያሉትን ስደተኞችን የሚያካትት አልነበረም›› ያሉት አቶ ሥዩም፤ አሁን ላይ አካታች የሆነ ስትራቴጂ በመንደፍ በስደተኞች እና ሌሎች ተደራሽ ያልሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን አካታች በማድረግ ተደራሽነት ለማስፋት የሚያግዝ መሆኑን ይገልጻሉ::
በስምምነቱ መሠረት ከኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ (አይሲቲ ፓርክ) ኮርፖሬሽን ጋር የሚሠራው ሥራ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሥራ የማያገኙ ተማሪዎችን የቴክኒካል ብቃት የሚያገኙበት ሁኔታ የሚያመቻችና ሥራ ለመሥራት የሚያግዝ እንደሆነ አመላክተዋል:: ከዚህም በተጨማሪ ስደተኞቹ በአይሲቲ ፓርኮች ውስጥ በሚገኙት ኢንኩቤሽን ማዕከላት ገብተው ራሳቸው አብቅተው እንደሚወጡም ለማድረግ እንደሚረዳ ያስረዳሉ::
የሱማሌ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር የተደረገ ስምምነት እንዲሁ የስደተኞች የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት የሚያሰፋ ነው:: ቢሮው በዲጂታል ኢኖቬሽን ማዕከል ያለው ቢሆንም ለማዕከል የሚያስፈልጉት ማቴሪያሎች የተሟላ ስላልሆነ የሚያስፈልገው ማቴሪያሎች ለማሟላት እና ወደሥራ እንዲገባ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት መደረጉን አብራርተዋል::
አቶ ሥዩም እንደሚሉት፤ አሁን ባለው ሂደት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕጎችን ስለምትከተል በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ስደተኞች ከዜጋው በተወሰነ መልኩ ይለዩ እንጂ ዲጂታል መታወቂያ የማግኘት፣ የመማር እና ሥራ የመቀጠር መብት አሏቸው:: እስካሁን ዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽ ስላልሆነ ተደራሽ ለማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን ለዲጂታል አካታችነቱ የሚያስፈልጉ ፕላትፎርሞች፣ ማቴሪያሎች፣ ታብሌቶች ተደራሽ እንዲሆኑ እየተደረገ ይገኛል::
ዲጂታል 2025 ስትራቴጂ በዋናነት አራት ቁልፍ ተግባራት ያሉት ሲሆን፤ በመሠረተ ልማት ተደራሽነት፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ረገድ አስቻይ ሲስተም በመገንባት፣ ዲጂታል ኢኮ ሲስትም እና ዲጂታል ፕላትፎርም ላይ ብዙ ሥራዎች ለመሥራት የሚያስችል ነው:: ዲጂታል ኢኮሲስተምን ተደራሽ በማድረግ በዲጂታል ላይ ያለውን የክህሎትና የእውቀት ክፍተት መሙላት ያስችላል:: በዚህ ዓመት አሁን እንደተጀመረ እንደሱማሌ ክልል በተወሰኑ ክልሎች ተደራሽ እንደሚያደርግ ጠቅሰው፤ በቀጣይ ተደራሽነቱን በማስፋት የስደተኞች ካምፖች ያሉባቸው ቦታዎች ተደራሽ የሚደረግ መሆኑን ነው አቶ ሥዩም የሚናገሩት::
ወይዘሮ ፋጡማ መሐመድ የሱማሌ ክልል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ናቸው:: እሳቸውም በክልሉ ያሉ የዲጂታል እንቅስቃሴን አስመልክቶ ሲገልጹ፤ በክልሉ 95 ያህል ወረዳዎች ያሉ ሲሆን፤ 50 በመቶ ያህል ለሚሆኑት የዲጂታል ተደራሽነት የተስፋፋባቸው አካባቢዎች ናቸው:: በክልሉ 11 ዞኖች ያሉት ሲሆን በክልል ያሉ መሥሪያ ቤቶችን አውቶሜት በማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ:: በተለይም ዲጂታል ቴክኖሎጂን ተደራሽ በማድረግ ረገድ ከባዮ ኢመርጂንግ እና ከስፔስ ሳይንስ ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ በመሆን የሚሠሩ ሥራዎች እንዳሉ አመላክተዋል ::
‹‹በክልሉ በርከት ያሉ ስደተኞች አሉ›› ያሉት ወይዘሮ ፋጡማ፤ እነዚህ ስደተኞች ውስጥ ብዙ ሥራ ፈት ወጣቶች ያሉ ሲሆን፤ ከዓለም የሥራ ድርጅት ጋር በመተባበር ወጣቶች በማሠልጠን አስፈላጊውን እውቀት ካገኙ በኋላ ወደ ሥራ የሚገቡበት ሁኔታ እንደሚመቻች ጠቁመዋል:: በፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ዙር ከ300 በላይ ሰዎች የሚሳተፉበት ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ ከ30 በመቶ ያህል ሴቶች ናቸው:: በክልሉ ባለው ወደ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) ማዕከል እንዲገቡ የሚደረግበት ሁኔታ መኖሩን አመላክተዋል::
ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት የሀገር ውስጥ ፕሮግራም ኦፊሰር ወጣት ማርታ ፀሐይ፤ ስምምነቱ ከሦስቱም ተቋማት ጋር የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል እንደሆነ ትናገራለች:: በስምምነቱ የስደተኞችን አካታችንን ለማምጣት፣ የእውቀት ልማት ላይ እንዲሳተፉና በተጨማሪ የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል ሥራዎች የሚሠሩ መሆኑን ጠቅሳ፤ ከኢንፎርሜሽን፣ ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) ፓርክና ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ከሱማሌ ክልል ጋር የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት የሚያስችል መሆኑን አመላክታለች::
ፕሮግራም ኦፊሰሯ እንደምትለው፤ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አገር አቀፍ ዲጂታል አካታችነት ስትራቴጂ እየቀረጸ ስለሚገኝ በዚህ ስትራቴጂ ውስጥ የዓለም አቀፍ ስደተኞች ጉዳይ እንዲካተት የማድረግ ሥራ ይሠራል:: በኢትዮጵያ 900 ሺህ የሚደርሱ ስደተኞች ያሉ ሲሆን፤ እነዚህ የቴክኖሎጂ ጋር በተገናኘ የተለያዩ ሥልጠናዎች እና የሥራ እድል ማግኘት እንዲችሉ በስትራቴጂው ተካትቶ እንዲሠራ ይፈልጋል::
ዲጂታል ስትራቴጂው መካተት ያለባቸው ሁሉ እንዲካተቱ ከማድረግ አንጻር ዲዛይን የተደረገ ፕሮግራም መሆኑን ገልጻ፤ በሀገሪቱ ያሉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በሥልጠና በትምህርት እንዲሁም በማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲካተቱ ከማድረግ አንጻር የሚሠሩ ሥራዎች መኖራቸው ትገልጻለች::
ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት በአፋርና በሱማሌ ክልል ያስጠናው ጥናት እንደሚያሳየው ከስደተኞች አንጻር ከዲጂታል ክህሎት አለመኖር፣ ከዚያ በተጨማሪ ከትምህርት ወደ ሥራ የሚደረገው ጉዞ ለስደተኞች ቀላል አይደለም:: የተመቻቹ የሥራ ፈጠራ እድሎች የሉም:: የሶሾል ኔትወርክ ስለሌላቸው በቀላሉ መረጃዎችን ለማግኘት የሚቸገሩ መሆኑን የሚያሳይ ነው ስትል ተናግራለች::
ከኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) ኮርፖሬሽን ጋር የተደረገው ስምምነት በአይሲቲ ፓርክ 16 የሚሆኑ የተለያዩ ኢንቨስተሮች ስለሚገኙ በወጣቶች የተለያዩ አገልግሎቶች እንዲያገኙ የሚደረግ መሆኑን ገልጻ፤ አገልግሎት ለስደተኞች ክፍት እንዲሆን የማስቻል ሥራ እንደሚሠራ አመላክታለች::
ከዚህ በተጨማሪ በአይሲቲ ፓርክ ውስጥ ካሉ ኢንቨስተሮች ጋር በመነጋገር የሥራ እድል ለመፍጠር እንደሚሠራ አመላክታለች:: አሁን ላይ የሚሠራው ሥራ በተሞክሮ ደረጃ የሚሰፋ ሲሆን፤ የዚህ ፕሮግራሞ ውጤት ታይቶ ቀጣዩ ፕሮጀክት የሚቀጥሉ መሆኑን ነው የምታስረዳው::,
እንደፕሮግራም ኦፊሰሯ ማብራሪያ፤ የሱማሌ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር የተደረገው ስምምነትም እንዲሁ የዓለም ሥራ ድርጅት እ.ኤ.አ 2022 ሱማሌ ክልል ላይ ያስጠናው ጥናት የሚያሳየው ስደተኞች የሥራ እድል ወይም ዲጂታል ክህሎት ለማግኘት የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥሞቸው ነው:: ይህ ፕሮግራም እነዚህ ተግዳሮቶች በመቅረፍ ከመሠረተ ልማት አቅርቦት፣ የኢንተርኔት ኔትወርክ ተደራሽነት፣ ዲጂታል ክህሎት እና የሥራ እድል ከመፍጠር ያለመ ነው::
የዓለም ሥራ ድርጅት በኩል የመሠረተ ልማት ተግዳሮቶች እና የኢንተርኔት ተደራሽነት እንዲሁም ከክህሎትና ዲጂታል እውቀት ጋር የተለያዩ ተግዳሮቶች እና የሥራ እድል ከመፍጠር አኳያ ያሉ የተለያዩ ተግዳሮቶች ለመፍታት ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ነው የምትለው ወጣት ማርታ፤ ድርጅቱ የዲጂታል ኢኖቬሽን ማዕከል በሱማሌ ክልል ስደተኞች ባሉበት በቀብሪዳሓር አካባቢ እንደሚያቋቁም ትናገራለች ::
በተጨማሪም በጂግጂጋ ሁለት ዲጂታል ኢኖቬሽን ማዕከሎች ተቋቋመው ሥራ የሚሠራ ሲሆን፤ የእነዚህ ማዕከል ዋና ዓላማ ስደተኞች መረጃን የሚያገኙበት ማዕከል ሆኖ ለብዙ ስደተኞች የኢንተርኔት ኔትወርክ ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል:: ከዚህም በተጨማሪ የሥልጠና ማዕከል ሆኖ ስለሚያገለግል የስድስት እና የሦስት ወራት ሥልጠናዎች የሚሰጡበት እንደሚሆን ታመላክታለች::
ፕሮግራም ኦፊሰሯ እንዳለችው፤ ከጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ፣ እዚያው ካሉ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት እና ከሱማሌ ክልል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በመተባበር ካሪኩለም ተቀርጾ ሥልጠና የሚሰጥ ይሆናል:: እነዚያ የሠለጠኑ ተማሪዎች ደግሞ ከሥልጠና ወደ ሥራ መሰማራት እንዲችሉ ለማድረግ የዓለም ሥራ ድርጅት የመሥሪያ አካባቢ እና ዲጂታል ኢኖቬሽን ማዕከላት በማቋቋም ሠልጠነው የተመረቁ ወጣቶችን ሥራቸውን ማከናወን እንዲችሉ ወደ አሥር የሚደርሱ የሥራ አካባቢዎች ይዘጋጃሉ:: በዚህ መሠረት ወጣቶቹ የራሳቸው ሥራ እንዲሠሩ ይደረጋል::
እነዚህ ሦስት ስምምነቶች በዓለም ሥራ ድርጅት ዲጅታል ኢኮኖሚን ለማምጣት የተቀረጹ ቆይታ ጊዜያቸውም የተለያየ እንደሆነ የምትናገረው ወጣት ማርታ፤ ከኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ዲጅታል አካታች ስትራቴጂን የመቅረጽ የተጀመሩ ሥራዎች ያሉ መሆኑን አንስታ፤ ሥራዎቹ ለሚቀጥሉት ለአራት ወራት የሚሠሩ እንደሆኑ ገልጻለች:: የአይሲቲ ኮርፖሬሽን ጋር የሚሠራው ሥራ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ሲሆን፤ የሱማሌ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮም እንዲሁ ለአስራ አንድ ወራት የሚቆይ እንደሆነ አመላክታለች::
በዚህም ፕሮግራም ዲጂታል ኢኮኖሚ ከመገንባትና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚሠሩ ሥራዎች ከ7ሺ በላይ ስደተኞችን ዒላማ ያደረጉ ናቸው የምትለው ፕሮግራም ኦፊሰሯ፤ የሚሠሩት ሥራዎች ከስደተኞች ጋር ብቻ የተያያዙ ሳይሆኑ ኢትዮጵያውያንም ያካተተ እንደሆኑ አመላክታለች:: በአይሲቲ ፓርክ በቀጥታ ተጠቃሚ የሚሆኑ 275 ወጣቶች መሆናቸውን ጠቅሳ፤ በሱማሌ ክልል 300 የሚደርሱ ወጣቶች ተጠቃሚ የሚሆኑ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 250 ተማሪዎች የክህሎት ሥልጠና ያገኛሉ:: ቀሪዎቹ 50ዎቹ የሥራ እድል የሚመቻችላቸው መሆኑን ታስረዳለች::
ለዚህ ፕሮጀክት የ11ሚሊዮን ብር የተመደበ መሆኑን ገልጻ፤ ስምምነቱም ዲጂታል ኢኮኖሚ በመገንባት ሂደት ስደተኞችና ቴክኖሎጂን ለማቀራረብ የሚያስችል ነው ብላለች::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም