ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ መጠን ታገኝባቸው ከነበሩ የወጪ ምርቶች ዋናው ቡናዋ ነበር። በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ የተለያዩ የወጪ ምርቶች ቢኖሯትም ቡና አሁንም የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በኩል ፋይዳው ከፍተኛ ነው።
የኢትዮጵያ ቡና በዓለም በጣም ይፈለጋል። ቡናው በቅመምነት እንደሚፈልግም ነው የሚገለጸው። ቡናው ልዩ በመባል የሚታወቅም ሲሆን፣ በዚህም ሀገሪቱ ተጠቃሚ ነበረች። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ሀገሪቱ ከቡና የወጪ ምርት የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ እየቀነሰ መጥቷል። ለእዚህ ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች ቢጠቀሱም ቡናዋን የጣለችው ራሷ ኢትዮጵያ ናት ሲሉ በዘርፉ ለዓመታት የሠሩት እና አሁን ደግሞ በቡና ማቀነባበር ሥራ ውስጥ የተሰማሩት አቶ ሀይሌ ግብሬ ይገልጻሉ። ከአቶ ሀይሌ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡– የቡና ዋጋ የወደቀ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።የዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው ይላሉ ?
አቶ ኃይሌ፡– በመጀመሪያ ደረጃ ቡናውን የጣልነው እኛ ነን። ቡናው ወድቆ አይደለም፤ የጣልነው እኛው ነን። እንዴት በለኝ። የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ስፔሻሊቲ ተብሎ ልዩ ማዕረግ ተሰጥቶት ነበር።በዚህም የይርጋጨፌ ቡና 25 ሳንቲም ከዓለም ቡና ገበያ ዋጋ በላይ ፣ የሲዳሞ ቡናም ከ10 እስከ 15 ሳንቲም ተሰጥቷቸው ነበር። የወለጋ ቡናም እንዲሁ ከኒዮርክ ቡና ዋጋ በላይ ጭማሪ ተሰጥቶት ነበር።
ኢትዮጵያ ይህን መብቷን ተጨማሪ መብት ይገባኛል ብላ ተከራክራ ቡናዋ ልዩ ቡናነቱን አስታውቃ ወርቅ ነው የተባለውን ቡና ዳይመንድ ነው ብላ ተከራክራ ማሸነፍ ትችል ነበር። ይህ ለምን ሆነ ብትለኝ የኢትዮጵያ ቡናን ዓለም በቅመምነት ነው የሚጠቀመው። ዓለም የኢትዮጵያ ቡናን እንደ ማናቸውም ቡና አይደለም የሚጠቀመው። ቡናችንን በሌሎች ቡናዎች ውስጥ በመጨመር በቅመምነት ነው የሚጠቀሙት።
ሀገሪቱ ቡናዬ በማናቸውም ቡና ውስጥ የምትጠቀሙት ቅመሜ ስለሆነ የእኔ ልዩ ስጦታ ስለሆነ ብላ ራሷን ከፍ ማድረግ ሲገባት የእኔ ቡና ተራ ቡና ነው ብላ ዓለም እምቢ እያላት ራሷ ተራ ቡና ነው ብላ ዲክለር አድርጋለች።
ተራ ቡና ስለሆነ ሸቀጥ/ኮሞዲቲ / ነው፤ ኮሞዲቲ ስለሆነ በምርት ገበያ/ኢሴክስ/ይሸጥ ብላ ዋጋዋን የጣለች ኢትዮጵያ ራሷ ናት፤ይህን ቆሜ እመሰክራለሁ። ጣለችው። ባለቤት የጣለውን አሞሌ ባለእዳ አያነሳውም ነው የሚባለው። ይሄ መረጃ ያለው ነው፤ ተገንዘብልኝ። ይሄ ኢትዮጵያ የተቀበለችው ነው፤ ኢትዮጵያ መልሳ የጣለችው ነው።
አዲስ ዘመን፡– የቡናዋን ልዩ ቡናነት የጣለችው ኢትዮጵያ ራሷ ናት ሲሉ ምን ለማለት ነው ?
አቶ ሀይሌ፡– የኢትዮጵያ ቡና ጣእም እየተለካ እየቀመሰ ላኪዎች በጥንቃቄ የሚልኩት ቡና ነበር። ምርት ገበያ ገብቶ ቡና ከቡና ተደበላልቆ የኢትዮጵያ ቡና የድሮ ማእረጉን አጣ። ተደበላለቀ፤ በቃ። ሲደበላለቅ የኢትዮጵያ ቡና ይሄ ነው ማለት አስቸገረ፤ ገዥዎቹ ለምሳሌ የይርጋ ጨፌ ቡናን ይርጋ ጨፌ ነው ለማለት እንዲሁም የሲዳሞን ቡና የሲዳሞ ቡና ለማለት እየከበዳቸው ነው።ስለዚህ ቡናውን አበላሹት። በዚህ የተነሳም ገበያ ፈላጊዎቹ የተበላሸውን በተባለሸ ዋጋ እንገዛለን እያሉ ዋጋውን እያወረዱ ጣሉት።
አዲስ ዘመን፡– ሌሎች ምክንያቶችስ ምንድን ናቸው ?
አቶ ሀይሌ፡– ሁለተኛው ምክንያት የዓለም ሁኔታ ነው። አሁን በዓለም ብዙ የቡና ምርት አለ። የዓለም ቡና በብዛት ገበያ መግባትም ሌላው ችግር ነው። ብዙ ምርት ስላለ አቅርቦት ሲባዛ ፍላጎት ዝቅ ይላል። ስለዚህ ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው ቡናዎች በብዛት እየተመረቱ ስለሆነ የኢትዮጵያ ቡና እንደ ቅመም ስለሚወሰድ ቅመም የሚጠቅመው በመጠኑ ነው። ቡናችን ቅመም በመሆኑ የሚፈልጉት በመጠኑ ነው፤ ገዥዎች የሚፈልጉት ዝቅተኛ ደረጃ ያለውን ቡና ነው፤ ይህ ቡና ደግሞ በርካሽ ዋጋ ይገኛል። ሦስተኛው ቡና ዛሬ የኤክስፓርት ሸቀጥ/ኮሞዲቲ/ አይደለም። ቡናው ለገቢ ሸቀጥ ማስመጫነት ‹‹ባርተር ትሬዲንግ›› / ዕቃ በዕቃ ማስመጫነት እንደ መሳሪያ እንዲያገለግል እየተደረገ ነው። ቡና በርካሽ ዋጋ ሸጠው ከዚህ በሚያገኙት የውጭ ምንዛሬ ብረትና ሌሎች ሸቀጦች ሀገር ውስጥ እያስገቡ በውድ ዋጋ በመሸጥ የኑሮ ውድነቱን እያባባሱ የሚገኙ አካላት አሉ። ኢትዮጵያ በእዚህ ድርጊት ክፉኛ እየተሰቃየች ነው።
እነዚህ ወገኖች የሚያተርፉት በሚልኩት ቡና አይደለም፤ይህም በልዩ ኦዲት ሊታይ ይችላል፣ የሚያተርፉት ከቡና የውጭ ምንዛሬ በሚያገኙት ገንዘብ ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገቡትን ሸቀጥ ለድሃው ኢትዮጵያዊ በውድ ዋጋ እየሸጡ ነው።ይህ አደጋ ነው፤በዚህ ዓይነቱ ድርጊት ኢትዮጵያ ወደፊትም መቆምም አትችልም። ይሄ አራኛው ምክንያት ነው።
አምስተኛው ደግሞ የሀገሪቱ የጸጥታ ችግር ነው። ሳንደብቅ እንነጋገር። ንግድ መተማመን ይፈልጋል፤ ገዥዎቹ ደግሞ አልቻሉም፤ ይደርስልናል አይደርስልንም ፈተና ነው። ስጋት ላይ ናቸው።
ፖለቲከኞች ሀገራቸውን ማየት አለባቸው። የእነሱን የግል ፍላጎት ስልጣን ፍላጎት አይደለም ማየት ያለባቸው። ይቺ ሀገር እንዳትወድቅ መከላከል ግዴታቸው ነው። እነሱ ተባብረው ሰላም ካልፈጠሩ ሀገሪቱ ከእዚህ በበለጠ ታዘቀዝቃለች። በሀገሪቱ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ገዥዎች ደግሞ አልቻሉም፤ይደርስልናል አይደርስልም ፈተና ነው።
አዲስ ዘመን፡– መፍትሔውስ ምን ሊሆን ይችላል ይላሉ።
አቶ ሀይሌ፡– ቀድሞ እንደነገርኩህ የሀገሪቱን ሰላም ማረጋጋጥ ቡና ብቻ ሳይሆን ሌሎች የወጪ ምርቶች በፍጥነት እንዲላኩ ያስችላል። ለዚህ አፋጣኝ መፍትሔ መሰጠት አለበት።
ስለዚህ የሰላም ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራ ይገባል። ሁሉም ፖለቲከኛ ሀገርን ማዕከል አድርጎ ስለ ሰላም ሊሠራ ይገባል። ነገ መልሶ አንዱ ቢያሽነፍ የሚያስተዳድረው ይህችኑ ሀገር ነው። ሀገር ማፍረስ ላይ መረባረብ አይገባም። በተለይ የወጪ ገቢ ንግድ፣ኢንቨስትመንት ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል። የሽምግልና ምክር ይሄ ነው።
የምርት ገበያን /ኢሴክስ/ን መዝጋት ሌላው መፍትሔ ነው። የቡና ገበያን በዱሮው መንገድ፣ ገዥዎች በሚፈልጉት ዓይነት ማስኬድ ያስፈልጋል። ገበያው እኛ በምንፈልገው መንገድ መሆን የለበትም፤ ቡና ሁሌም በገዥዎች ፍላጎት ላይ የተወሰነ ገበያ ነው፤ ይህ ሲሆን ቅመሙ የኢትዮጵያ ቡና ተፈላጊነቱም እየተሻሻለ ይመጣል። ይህ ተፈጥሯዊ መሻሻል ሲጨምር የኢትዮጵያን ቡና የተሻለ ያደርገዋል። በዚህ ላይ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠት አለበት።
ይሄ የት ይጀመራል መሰለህ። ከእርሻ አያያዛችን፣ ከቡና አሰጣጣችን ፤አደራረቃችን ይጀምራል። እስከ መጨረሻው ድረስ በጥራት ከተሠራ የኢትዮጵያ ቡና ምንጊዜም ተፈላጊ ነው። ስለዚህ ይሄ እንደድሮው ተመልሶ ተመርምሮ ተጠንቶ ትኩረት ተሰጥቶት ባለሙያ እንዲኖረው ተደርጎ ስልጠና የሚሰጥበት ሁኔታ ተመቻችቶ፣መስተካከል አለበት።
ሌላው መፍትሔ የኢትዮጵያ ቡና ማህበርን ጠንካራ ማድረግ ነው። ተወዳዳሪ ሊያደርግ ውጪ ሄዶ መወዳደር የሚያስችል አካል መሆን ይገባዋል። ማህበሩ ግን ምንም እየሠራ አይደለም፤ እንደ ሌሎች ማህበራት ጠንካራ አይደለም።
ማህበሩ ጠንካራ ሊሆን ይገባል፤ ተደራዳሪ መሆን አለበት። ጠንካራ ባለሙያ ሊኖረው ይገባል፤ የቡና ፈንድ አዘጋጅቶ በዓለም እየዞረ የእኔ ቡና ብሎ ማስተዋወቅ ይኖርበታል። ራሳችንን ብዙ መሸጥ ይኖርብናል።
የንግድ ውድድሩ በጣም ጥብቅና ሸር/ሽሩዲቲ/ የበዛበት ስለሆነ ይቅርታ አድርግልኝና እነዚህ ቡና ላይ የወጡትን ልቅ ህጎች መንግሥት ዞር ብሎ አይቶ መሰብሰብ ይኖርበታል። ምክንያቱም ንግድ ሽሩዲቲ ነው። መንግሥት በጣም ልቅ ህጎችን ነው ያወጣው። ወደፊት ለሀገሪቱ አደጋ የሚያመጡ በመሆናቸው እንደገና ታይተው ሊከለሱ ይገባል። ኢትዮጵያን ሊያጠፉ የሚችሉ ህጎችም ወጥተዋል።
ኢትዮጵያ ቡና ከውጭ አስመጥታ ቆልታ እንድትልክ የወጣው ህግ ሀገሪቱን የልዩ ቡና ባለቤትነቷን ሊያሳጣት የሚችል ልቅ ህግ ነው። ይሄ ከቢፒአር ባልተለየ መልኩ ኢትዮጵያን የሚያጠፋ ህግ ነው። እንደ ዜጋ የሚያስደነግጥ ህግ ነው።
አዲስ ዘመን፡– የቡና ግብይት ህጉን ማለትዎ ነው ?
አቶ ሀይሌ፡– አዎ። ህጎቹ እንደገና ሊታዩ ይገባል። ኢትዮጵያ በቡና ላይ ዕውቀቱ ያላቸው አንጋፋ ሰዎች አሏት፤ ቡና ላይ የተፈጠሩ ሰዎች አሉ፤ አርጅተው እቤት የተቀመጡ አሉ፤ እነዚህን በመሰብሰብና አማካሪ በማድረግ በሳል ህግ መውጣት ይኖርበታል። የሩጫ ህጎች ብዙውን ጊዜ ለአደጋ ያጋልጣሉ፤ የበሰለ ዘመን የሚሻገር ህግ ያስፈልጋል።
ህግ ሁሌም አንድ ቦታ የሚቆም አይደለም። ነገር ግን ለተወሰነ ጊዜ መቆየትን /ኮንሲስተንሲ/ ይፈልጋል። የሚቀያየር ህግ /ኢንኮንሲስተንሲ ህግ/ በአብዛኛው ያስቸግራል። ስለዚህ ነባር ሰዎችን ፈልጎ እስቲ ይህን እዩት ፤ምንድንነው ነገሩ በሚል ጠንከር ያለ ሥራ መሠራት አለበት።
አዲስ ዘመን፡– ከማስተዋወቅ አኳያስ ምን መሠራት አለበት ይላሉ ?
አቶ ሀይሌ፡– የማስተዋወቅ ሥራ በላኪዎች ማህበር እንዲሁም በመንግሥት በኩል መሠራት ይኖርበታል። ንግድ ገጽታ ነው። በዚህም የገጽታ ግንባታ መሥራት ይኖርበታል።
የቡና ፍላጎት እየበዛ ከመጣ የኛ ምርታማነት ምን መሆን አለበት? የኛን ቡና እናስፋፋ ወይስ እናጠናክር የሚለውን ለይቶ እየተናጋገሩ መሥራት ያስፈልጋል። ፍላጎት እየሞላ ከመጣ አዳዲስ ፍላጎትን መመልከት ይገባል።
በጣም አዳዲስ ፍላጎት እየመጣ ነው። ስለዚህ አሮጌ ፍላጎት እየሞላ ነው፤ አዳዲስ ደግሞ እየመጣ ነው። ክፍተቱ ምን ያህል ነው? እኛ ምን ያህሉን መሙላት እንችላለን? በሚለው ላይ የበሰለ ጥናት ማካሄድ ያስፈልጋል።
ለስምና ሰርተፍኬት ያህል ብቻ መሠራት የለበትም፤ የቡና እና ሻይ ግብይት ባለስልጣንን፣ የላኪዎች ማህበርን ጨምሮ ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ በሚያሰኝ አቋም ደረጃ መገንባት አለባቸው። አለበለዚያ የቡናው ዋጋ እየወደቀ በሄደ ቁጥር መመለስ ይከብደናል። ቡናው የወደቀው በቆሎ ነው ስለተባለ ነው።
ዓለም አቀፍ ገጽታችንን ማሳመር፣ የወጪ ምርት መተካቱ ላይ በሚገባ መስራት ያስፈልጋል። አስመጪዎች እንዴት የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ይችላሉ የሚለውም እየታየ በቡና የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ ተተንርሶ የሚሠራው የገቢ ንግድ የቡና ዋጋን እየገደለው ይሄዳል። ለአስመጪዎች የውጭ ምንዛሬ የሚያገኙበት የተሻለ አማራጭ ቢፈጠርላቸው መልካም ነው። ይህም የቡናው ዋጋ እንዲነሳ ሊያደርግ ይችላል።
አዲስ ዘመን፡– ቡና በብዛት ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ እቅዱን ማሳካት ይቻላል፤ ዋጋ ወድቋል በሚል ብዙ ቡና እጅ ውስጥ እንዲቆይ ማድረግ በጥራት ላይም ችግር ያስከትላልና ባለው ዋጋም ቢሆን መላኩ ይጠቅማል ይባላልና በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ሀይሌ፡– እርግጥ ነው ፤ቡና እጅ ላይ ሲቆይ ጣእሙ ይበላሻል። የአገሪቱን ገጽታ አንድም እያበላሸ ያለው ይሄው ነው፤ ቶሎ መላክ አለበት። ቶሎ ለማውጣት ግን ገዥዎቹ መቀበል አለባቸው። እኛ ስለፈለግን አይደለም፤ ገዥዎች መቀበል አለባቸው፤ በነፃ እሰጣለሁ ፣በአነስተኛ ዋጋ ሰጥቻለሁ ብትል እና እምቢ ቢሉ ምን ማድረግ ትችላለህ፡ ካንተ ለመውሰድ መተማመኑ የለኝም ቢሉ ምን ትላለህ?
ሁለት ነገር ነው፤ ገዥዎች የኢትዮጵያን ቡና የሚፈልጉበት ትልቁ የገበያ ወቅት ከታኅሣሥ እስከ ሚያዝያ ያለው ነው፤ይህ የኢትዮጵያ የቡና ወቅት አልፏል፤እውነቱን ለመናገር የቡና መሰብሰቢያ ጊዜያቸው አልፏል፤ ከታኅሣሥ እስከ ሚያዝያ የኢትዮጵያን ቡና በአስቸኳይ የመሰብሰቢያ ጊዜያቸው ነበር። ከታኅሣሥ እስከ ሚያዝያ ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ አላስተማመነም ብለው ከኬንያና ታንዛኒያ ከሌሎች ሀገሮች ቡና ለመተካት ሔደዋል፤ዛሬ እናንት ብታጣድፉ ከየት ከየት ይመጣል።
አዲስ ዘመን፡– እዚህ ላይ የቡና እና ሻይ ባለስልጣን ሳናግር በአገሪቱ የቡና መላክ ተሞክሮ ሲታይ አራተኛው ወር ነው ብዙ ቡና የሚላክበት ብለውኛልና ይህን እንዴት ያዩታል?
አቶ ሀይሌ፡– ይሄ እኮ መጀመሪያ በተገባው ኮንትራት መሠረት ነው የሚፈጸመው። መጀመሪያ ኮንትራቱን ወደዚህ ገፋ አድርገው ነው የሚወስዱት። የተገባ ኮንትራት ካለ ዱሮም የሚወጣው ሰኔና ሀምሌ ነው።
አንዱም የኢትዮጵያ ኮንትራት ችግር የሄ ነው። እነሱ ለረጅም ጊዜ ኮንትራት ወስደው አቆይተው መውሰድ ይፈልጋሉ። ሀገራቸው ላይ ለመጋዘን
ማውጣት አይፈልጉም። እዚህ አከማችተው ቶሎ መጫን ይፈልጋሉ። የኢትዮጵያ ህግ ሦስት ወር ኮንትራት ስለሚል ይሸሻሉ። የኢትዮጵያ ህግ ችግር አለበት የምልህ ለዚህ ነው።
ህጋችን የገዥዎቻችንን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ነው ወይ የምልህም አንዱም ኮንትራትን ይመለከታል። እነሱ ዘጠኝ ወር ኮንትራት ይፈልጋሉ፤እኛ ሦስት ወር እንላለን። እነሱ የአምስት ወር የስድስት ወር ኮንትራት ይዘው ቡናቸውን መሸጥ ይፈልጋሉ። እዚያ መጋዘን የላቸውም፤ እዚህ እንዲቆይላቸው ይፈልጋሉ።
እኛ ቶሎ ቶሎ ኮንትራት ሰጥተን በኮንትራት እንኳ አስተማማኝ ሁኔታ ፈጥረን ቡናችን እንዲወጣ ማድረግ ይኖርብናል። ይህን እንደ አንድ ስትራቴጂ መጠቀም ይኖርብናል። እነዚህ ህጎች መሻሻል አለባቸው።
አሁን ወደ መጨረሻው ይገዙናል፤ ለምን፤ የኢትዮጵያ ላኪ ጥቅምት ላይ እንወረሳለን በሚል ይሸጣል ብለው ይጠብቃሉ። ይህም የኢትዮጵያ ህግ የፈጠረው ችግር ነው። ቡና ካደረ እወርስሃለሁ ስለሚል ህግ ስላለ ገዥዎቹም ዋጋ ቀንሰው ሲሸጡ እገዛለሁ ብለው ይጠብቃሉ። ራሳችን ህጎቻችንን በደንብ መፈተሸ አለብን። ቅድም ያልኩት ይህን ነው። ችግር እንፈታለን እያልን ያጣናቸው ህጎች ራሳችን ላይ ማሰሪያ እየሆኑ ነው።
ጥቃቅን ችግሮችን እንፈታለን ብለን ያወጣናቸው ህጎች ችግር እሆኑብን ነው፤ ቡና ቶሎ እንዲላክ ብለውን ያወጣነው ህግ ለገዥው ምቹ ጊዜ ሰጠ። እንዲዚህ ዓይነት ህጎች ላይ በጣም መሥራት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– ስላደረጉልን ትብብር በጣም እናመሰግናለን።
አቶ ሀይሌ፡– እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2011
ሀይሉ ሣይለድንግል