ሰውዬው ታክሲው ውስጥ ከገባ አንስቶ የስልክ ጨዋታው አልተቋረጠም:: አንዱን ስልክ በስንብት ዘግቶ አፍታ ሳይቆይ በሌላ ወሬ ይጠመዳል:: እሱን ጨርሶ ደቂቃዎች ሳይቆጠሩ እጆቹ ሌላውን ጥሪ ለማንሳት ይፈጥናሉ::
አጋጣሚ ሆኖ ከሰውዬው ንግግር በቀር የሚሰማ አንዳች ቃል የለም:: በታክሲው ሬዲዮም ሆነ ቴፕ አልተከፈተም :: መንገደኞቹም ቢሆን እርስበርስ እያወሩ አይደለም:: የሚሰማው የመኪናው ሞተርና የሰውዬው እረፍት አልባ ንግግር ብቻ ነው::
ይህ ሰው አሁንም ያወራል:: ተሳፋሪው እሱን ያዳምጥ ይመስል በዝምታ ተደምሟል:: እኔ ከንግግሩ እንደተረዳሁት የያዘው ጉዳይ የባልና ሚስትን እርቅ ይመለከታል:: የንግግሩ ሂደት ደግሞ ልክ እንደ ተከታታይ ፊልም ከአንዱ የስልክ መልዕክት ወደ ሌላኛው የሚያልፈው ያለ አንዳች ማቋረጥ ነው::
ነጥቦቹ ሲገጣጠሙ ሙሉ ታሪኩን ለማወቅ የሚቸግር አይደለም:: ተናጋሪው ከወዲያኛው ጫፍ የሚመጣለትን ቃል መልሶ በራሱ አንደበት እየደገመ ያወራዋል:: የያዘውን ስልክ ጨርሶ ወደሚቀጥለው ሲሻገርም የሰማውን ጉዳይ እየደገመ፣ መልሶ እየተናገረ ነው ::
አስገራሚው ጉዳይ ይህ መሆኑ ብቻ አይደለም:: እሱ ብቻ የሚያውቀውን የሰዎች ምስጢር እየዘረገፈ ሲተነትን ይሉኝታን አያውቅም:: በታሪኩ መሐል አንድ ሁለት ብሎ፣ ስሞችን ይጠቅሳል:: የአንዱን ታሪክ ለሌላው እያሳጣ ያማል። ከሚያናግረው ሰው የሚሰማውን ሌላ ሐሜት እየተነተነ ለሌሎች ያብራራል::
በአጠቃላይ ሰውዬው የት እንዳለና፣ ምን እያወራ እንደሆነ ደንታ የሰጠው አይመስልም:: እንዳሻው የሰዎችን ስም እየጠራ፣ የፈለገውን የወሬ ኮሮጆ እየፈታ ነው:: አስታራቂ መስሎ፣ ማጣላቱን፣ ደግ መስሎ መክፋቱን በንግግሩ ማወቅ ለማንም አድማጭ ግልጽ ነበር::
የመንገዱ መዘጋጋትና የመኪናው ዝግታ የሰውየውን ማንነት ለማወቅ ጊዜ ሰጥቷል:: ከአንዱ ስልክ ወደ ሌላው በሚያደርገው ንግግር ‹‹ሰው ምን ይለኛል››ን እያስበውም:: ያለገደብ የሚነዛው ወሬ የሌሎችን ጆሮ ቢያግልም ለእሱ ይህ ስሜት ምንም አልነበረም::
ሰውዬው አሁንም ያለፋታ፣ ያለአንዳች ይሉኝታ ድምፁን ከፍ አድርጎ ማውራቱን ይዟል:: ያለማቋረጥ ጭርታውን እየጣሰ የሚሰማው ወሬ በአብዛኞች ዘንድ ትዝብት ላይ እንደጣለው መገመት ችያለሁ:: አብዛኛው ተሳፋሪ ፊቱን አኮሳትሮ፣ እጁን በአፉ ጭኖ በግርምታ እያዳመጠው ነው::
የሚገርመው ሰውየው የያዘው ጉዳይ ሽምግልና ቢመስልም ውጤቱ ግን ማጣላት ማጋጨት መሆኑ ነው:: በንግግሩ መሐል የሚያነሳቸው ጉዳዮች አንድም ቁም ነገር የሌላቸው፣ ምክንያታዊ ያልሆኑና የሚያበሽቁ ጭምር ናቸው:: እሱ ግን ምንም ሳይሳቀቅ ያሻውን እያነሳ ይጥላል::
ይህ ሰው ሚስትዬው ዘንድ ደውሎ አንድ ጉዳይ ያነሳና ባልየው ስልክ ላይ ተቃራኒውን ሀሳብ ጭሮ እሳት ያቀጣጥላል:: ይህን ጉዳይ በወጉ ሳይቋጭም ወደሌሎች ስልክ እጁን ያነሳል:: በሚያስገርም ፍጥነት ነገሮችን ገጣጥሞ ድንቅ ታሪክ አድርጎ ይሰፋቸዋል::
ይህ ሁሉ ጉዳይ እየሆነ ያለው በታክሲ ውስጥ በነበረው የአፍታ ጉዞ ነበር:: እውነት ለመናገር የሰውየው የነገር ቅንብር የሚያስገርም ነው:: ለዚህ ክፉ ልምዱ ዕውቅና መስጠቱ ደግሞ በእጅጉ ያሳፍራል:: እኔና ሌሎች እንዲህ ይሰማን እንጂ በእሱ ዘንድ ያስከተለው አንዳች መሳቀቅ አልነበረም:: ይህ ግለሰብ በኖረበት ልምዱ በየአፍታው የሌሎችን ምስጢር እየዘራ፣ መሄድን ተክኖበታል::
አሁን ዕድሜ ለሰውዬው ይሁንና ሳናስበውና ውስጣችን ሳይፈቅድ የሰማነውን የሰዎች ታሪክ እንደያዝን ከታክሲው መውረድ ጀምረናል:: እሱ ግን አሁንም ወሬው የተቋጨ አይመስልም:: ከታክሲው ወርዶ አስፓልቱን ተሻግሮ እስኪሄድ ስልኩ ከጆሮው አልተነሳም:: ‹‹ወይ ጉድ !›› ብሎ ከመታዘብ በቀር ሌላ ምን ይባላል::
አንዳንዴ አንዳንዶች የት እንዳሉ የሚረሱ ይመስላል:: ስልክ አንስተው የሚያወሩትን አያውቁም:: ‹‹ወሬ›› ብለው ሲጀምሩ ንግግራቸው ሌሎች ሰዎች ዘንድ ይደርሳል ብለው አይገምቱም:: እንዳሻቸው የፈለጉትን ይናገራሉ:: ማማት ያለባቸውን ሰው ስሙን እያነሱ ይዘረጥጣሉ:: ሰዎች ሚስጥር ብለው ያወጓቸውን ሁሉ የአደባባይ ጨዋታ ያደርጉታል::
ብዙ ግዜ ይህ አይነቱ ልማድ ስልክ ንግግር ላይ ብቻ የሚከሰት አይደለም:: በሰዎች መካከል በሚኖር የግል ጨዋታም በግልጽ ይስተዋላል:: ሁለት አልያም ከዛም በላይ የሆኑ ሰዎች በትራንስፖርት ጉዞና በሌሎች መሐል ሆነው የሚያወጉት ጉዳይ ሳይታስብ የጋራ የሚሆንበት አጋጣሚ ይኖራል ::
እንዲህ አይነቶቹ ወገኞች የሚነጋገሩት በተለይ ስለመሥሪያቤታቸው ከሆነ ሥራና ሠራተኛ ይሉት፣ ጉዳይ የባቄላ ወፍጮ መሆኑ አይቀሬ ነው:: ሰዎቹ ስለ አለቆቻቸው ባሕርይ፣ ስለ ሠራተኞች ምደባ፣ ስለሥራ አፈጻጸም ውጤትና ሌላም ጉዳይ እየመዘዙ ሲተነትኑ የሌሎችን በዙሪያ መኖር ልብ አይሉትም:: አልገባቸውም እንጂ እየዘረገፉት ያለው እውነት የመሥሪያ ቤታቸውን ጥብቅ ሚስጥር ነው::
እነሱ ቦታና ግዜ አልመረጡምና የሚያወሩትን በሙሉ የስፍራው አድማጭ በእኩል ይጋራዋል:: የጉዳዩን መነሳት እንጂ ‹‹ማን ምን ይለኛል? የሚሉ ባለመሆናቸውም ትናንት ያወሩትን፣ ማግስቱን ከሌሎች አፍ ይሰሙታል:: እንዲህ መሆኑ ሌሎችን ጨምሮ ስለራሳቸው ክብር የሌላቸው መሆኑን አመላካች ነው::
አሁን ባለንበት የቴክኖሎጂ ዘመን የወሬ ቅብብሎሹን ለማስፋት ይህ አይነቱ አጋጣሚ ሰፊ ድልድይ ይሆናል:: አንዳንዶች ወሬን ፈጥረው ‹‹በሬ ወለደ›› በሚሉበት ሁኔታ እንዲህ አይነቱ ወሳኝ ምንጭ ከታማኝነት በላይ ነው:: ጥቂት ጫፍ ይዞ ሀገር ያህል አሉባልታን ለሚሰፉ ቀላጤዎች አጋጣሚው በበሶ ላይ ቅቤን እንደማፍሰስ ይሆናል::
እንዲህ አይነቶቹ ወሬ አነፍናፊዎች ‹‹አሉ፤ ተባለን›› ለማናፈስ ሩቅ መሄድ አያሻቸውም:: በተለይ የሚፈልጉት ጉዳይ የመሥሪያ ቤቶች ወሳኝ ሰነድ ከሆነ የሰሙትን፣ ካልሰሙት አቀናብረው ሰፊ የነገር ስልቻን ለመዘርገፍ ያመቻቸዋል::
ሰዎች ባለመጠንቀቅ የሚያወሩት ጉዳይ የብዙዎችን መሠረት ያናጋል:: ማንነታቸውን አቅልሎም ክብራቸውን ዝቅ ያደረጋል:: ከምንም በላይ ደግሞ በወሬው መሐል ያለ በቂ መረጃ የሚነሱ ጉዳዮች መርዛምነታቸው አይሽሬ ሊሆን ይችላል::
‹‹ከአፍ ከወጣ አፋፍ›› እንዲሉ ወሬ አንዴ ከምላስ ካመለጠ መመለሻው ከባድ ነው:: ጉዳዩ ብዙ ከተባለለት በኋላ በአንድ ጀንበር ማስተባበያ ልስጥበት ቢሉ የሚቻል አይደለም:: ምንግዜም ምላስን የሚያዝ፣ የሚገዛው ታላቁ አዕምሮ ነውና ቆም ብሎ ማሰቡ ግድ ይላል::
በሆነ አጋጣሚና ከመናገራችን በፊት አንድም ከራሳችን፣ አንድም ከአካባቢያችን በአስተውሎት ብንተዋወቅ እናተርፋለን እንጂ አንከሰርም:: ‹‹ታሞ ከመማቀቅ›› አስቀድሞ መጠንቀቅ ይሉትን ብሂል ለዚህም ልማድ ብንጠቀምበት ይበጃል:: ‹‹ዝም ባለበት አፍ ዝምብ አይገባም›› እንዲሉ ነውና::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 22 ቀን 2016 ዓ.ም