‹‹ስማርት ኮርት ሲስተም›› – የፍትሕ ሥርዓቱን ለማዘመን

ዲጅታል ኢትዮጵያ እውን የማድረጉ ጉዞ ከተጀመረ ቅርብ ጊዜ ቢሆንም፣ ጉዞውን የሚያፋጥኑ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፤ ይህን ተከትሎም ለውጦች እየታዩ ናቸው። በተለይ ተቋማትን በማዘመን የአሰራር ሥርዓቶችን ወደ ዲጅታል የመቀየር ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው፤ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎቶችን ዲጅታላይዝድ ከማድረግ አኳያ ብዙ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው። በዚህም እንደ ሀገር 528 የሚሆኑ የለሙ የዲጅታል አገልግሎት መስጫዎች ተግባራዊ ተደርገዋል።

ዜጎችን ላልተገባ ወጪና እንግልት ሲዳርጉ የቆዩ አብዛኞቹን አሰራሮች የመቀየር ተግባር እየተከናወነ ሲሆን፤ በዚህ ዲጅታል አሰራር በኩል እየተከናወነ ባለው ተግባር የተቀላጠፈና የተሳለጠ አገልግሎት መስጠት እየተቻለም ይገኛል። በተለይ ብዙ ተገልጋዮች የሚስተናገዱባቸው ዜጎችን ለምሬትና ለቅሬታ የሚዳርጉ አገልግሎቶች ዲጅታል ከተደረጉ በኋላ ችግሮች በብዙ መልኩ ተፈትተው ዜጎች በቀላሉ በዲጅታል አገልግሎት ተጠቀመው ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኙ ነው።

አሁንም ዲጅታላይዜሽን በመስፋፋት ሁሉንም ተቋማት ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ተገልጋዩ አገልግሎቶችን በቀላሉ እያገኘ ካለበት ሁኔታ መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው። ወደዚህ አሠራር ሳይገቡ የቆዩ ተቋማት አሁን ወደ አገልግሎቱ እየገቡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በተለይ ዜጎች ለአላስፈላጊ ውጭ ሲዳረጉባቸው ከቆዩባቸው ምሬትና እንግልት እንዲሁም ተደጋጋሚ ቅሬታ ያቀርብባቸው ከነበሩትና የአገልግሎት አሰጣጣቸውን እንዲያዘምኑ ሲፈለጉ ከነበሩት ተቋማት መካከል የፍትሕ ተቋማት ይገኙበታል።

በተለይ ፍርድ ቤቶች ከአገልግሎት አሰጣጣቸው ጋር ተያይዞ የአገልግሎት ጥራት ጉድለት ሲስተዋልባቸው መቆየታቸው ይታወቃል። አሰራራቸውን በማዘመን ዜጎች የሚፈልጉትን አገልግሎት በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያደርግ ስርዓት መከተል ዘመኑ የሚጠይቀው ተግባር ሆኗል። የዚህ አሰራር እውን መሆን ዜጎችን ከእንግልትና ከአላስፈላጊ ውጪ በመታደግ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል።

በቅርቡም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በጋራ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማዘመን የሚያስችል “ስማርት ኮርት” የተሰኘ የቴክኖሎጂ ውጤት መተግበሪያ ይፋ አድርገዋል። ኢንስቲትዩቱ በሁሉም ዘርፎች ላይ ችግር ፈቺ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ምርቶች ተደራሽ በማድረግ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል። በዚህም ባለፉት ሦስት ዓመታት የጤና፣ የትራንስፖርት፣ የፋይናንስና ሌሎች የአገልግሎት ዘርፎችን ለማዘመን የሚረዱ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አበልፅጓል።

ይህንን ሥራ በማስቀጠል የፍትሕ ሥርዓቱን ለማዘመን የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማበልፀግ ችሏል። ተቋሙ ለሀገር እድገት እንቅፋት የሆነውን የፍትሕ መጎደል ለማስቀረት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ውጤቶት ሰርቶ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስረክቧል።

ኢንስቲትዩት ያበለጸገው ‹‹ስማርት ኮርት››የተሰኘው መተግበሪያ የፍርድ ሂደቱን ሊያዘገዩ የሚችሉ ሁኔታዎችን በማስቀረትና ጊዜን በመቆጠብ በችሎት ወቅት አሁናዊና ታአማኒነት ያላቸው መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ለመያዝ እንዲሁም አስፈላጊ ሲሆን መረጃን ማቅረብ የሚችል የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤት ነው።

ይህ ቴክኖሎጂ ‹‹በቨርችዋል ኮርት›› በመጠቀም ዳኞችና ጠበቆች በአካል መገኘት የማይችሉባቸው ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ በያሉበት ሆነው በቪዲዮ ኮንፍረንስ አማካኝነት በርቀት እንዲገናኙ ማድረግ የሚያስችል ነው። ከዚህ በተጨማሪ የርቀት ምስክርነት መቀበል ወይም ምስክሮች ቨርችዋል በሆነ መልኩ ቃላቸውን የሚሰጡበት ሥርዓት፣ ዲጅታል የሰነድ ማስተዳደሪያ ሥርዓት፣ በችሎት ወቅት ደረጃቸውን የጠበቁ ምስሎችና ድምጽ መያዝ የሚያስችሉ፣ በችሎት ክርክር ወቅት የተቀረጹ ድምጾችን ወደ ጽሁፍ መቀየርና ሰነዶችን ማዘጋጀት የሚያስችሉ መተግበሪያዎችንም የያዘ ነው።

በዚህ መተግበሪያም ስድስት ሺ 44 ሰዓት የሚፈጅ የድምጽ ቅጂ፣ ሶስት ሺ 590ሰዓት የሚፈጅ የድምጽና የጸሑፍ ቅጂ፣ እንዲሁም ስድስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ዓረፍተ ነገሮችን ለግብዓትነት አገልግሎት ማዋል ያስችላል።

‹‹ስማርት ኮርት›› በፍርድ አሰጣጥ ሂደት ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን በማስፈን በጊዜና በሁኔታ ያልተገደበ ዘመናዊ የፍርድ ሥርዓትን ለዜጎች ለመስጠት ይጠቅማል። ዘመናዊ የችሎት ክፍል/ስማርት ኮርት ሩም/ ያለው ሲሆን፣ ከዚህ በፊት በወረቀት ይቀርቡ የነበሩትን ፋይሎች ዲጅታይዝድ በማድረግ የፍርድ ሂደቱ ዘመኑ በደረሰበት የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ እንዲመራ ማድረግ የሚያስችል ነው።

ዘመናዊ የችሎት ክፍል ያለው ቴክኖሎጂ፣ የተለያዩ የዲጅታል መተግበሪያ ቁሶችም ተካተውበታል። በእነዚህ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች የክስ ፋይሎችን መሰነድ የሚያስችል አገልግሎት ይሰጣል። ይህ የዲጅታል መረጃ አያያዝ በፍርድ ቤቶች በተለምዶ የሚያዝ (በማንዋል በሚጠቀሙበት ወቅት) የሚከሰተውን የፋይል መጥፋትና የመረጃ መዛባት ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረትም ይጠቅማል።

እነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የፍትሕ አሰጣጥ ሂደቱ ግልጽና ዘመኑን የዋጀ ይሆን ዘንድ በኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች በጥንቃቄ የተሰሩ ናቸው። የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ ካሜራዎች፣ ትላልቅ ስክሪኖች እና የድምጽ ቅጂን ማስቀረት የሚችሉ ኦዲዮ ሪከርደሮች ታዳሚዎችን የሚያሳትፍ ግልጽ ችሎት ለማድረግ ፋይል መያዝ የሚችልም ነው። በችሎት ወቅት የፍርድ ውሳኔንና የተከራካሪን ድምጽ ቀድቶ ወደ ጽሑፍ መቀየር የሚያስችል መተግበሪያ ያለው መሆኑን የኢንስቲትዩት መረጃ ያመላክታል።

ቴክኖሎጂው ይፋ መደረጉን አስመልክቶ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና፤ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የቴክኖሎጂ አብዮት ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ ቁልፍ ምዕራፍ የሚፈጸምበት በዓለማችን ታሪክ አዲስ ገጽታ ጭምር መሆኑን አስታውቀዋል፡

ለፍትሕ ሥርዓቱም ተደራሽ መሆን ካለባቸው ታላላቅ ዘርፎች ይህ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ አሁን ያበለጸገው ‹‹ስማርት ኮርት ሲስተም›› የፍትሐ ሥርዓቱን ወደ ሽግግራዊ ለውጥ እንደሚመራም ያመለክታሉ። ‹‹ቴክኖሎጂዎች የዳኝነት ሥርዓቱን ወደ ሽግግራዊ ለውጥ የሚመሩና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የታገዘ ቀልጣፋ የዳኝነት ሂደትን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ናቸው›› ሲሉ ይገልፃሉ።

ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ ወደ ሥራ ከገቡት መተግበሪያዎች በተለይ ንግግር ወደ ጽሁፍ የሚቀየር መሳሪያ የዳኝነት ሥርዓቱን ቀልጣፋ በማድረግና ሥራን በማቃለል ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። ይህ ሥርዓት በችሎት ሂደት የሚቀርቡ የቃል ክርክሮች ምስክሮችን ጨምሮ አጠቃላይ የችሎት ሂደቱን ወዲያውኑ ወደ ጽሁፍ በመቀየር ግልባጭ ለዳኞች ማቅረብ የሚያስችል ነው።

ሌላኛው ዘመናዊ መልዕክት መለዋወጫ (ስማርት ቻትፖት) ለተገልጋዮች በቀላሉ በዘመናዊ ስልካቸው ወይም በኮምፒዩተር አማካኝነት ያለ ገደብ መረጃ የሚያቀርብ ከሰዎች ንክኪ ነጻ የሆነ ቴክኖሎጂ ነው። ይህም ተገልጋዮች መደበኛ የቢሮ ሰዓት ሳይገድባቸው የትኛውም የሕግ ትርጉምን የተመለከቱ መረጃዎችን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮች ለመያዝ የሚያስችል አማራጭ እንደሚፈጥር የሚገልጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የመልዕክት መለዋወጫ አገልግሎቱ መረጃን ከማድረስ ባሻገር የተገልጋዮችን ቅሬታ የሚያስተናግድበት ሥርዓት የተበጀለት መሆኑንም ነው ያመላከቱት።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በበኩላቸው፤ ዘመኑን የዋጀውን ይህንን ‹‹የስማርት ኮርት›› ቴክኖሎጂ ተግባራዊ በማድረግ ከፍትህ እጦት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት እንደሚቻልም ይገልጻሉ።

እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ሲስተሙ የፍትህ ሥርዓቱን እጅግ ዘመናዊ፣ የዳኝነት ሥርዓቱን ቀልጣፋና ተደራሽ ማድረግ ያስችላል። ለተቋሙ የለሙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ ንግግር ወደ ጽሁፍ የሚቀይር ሥርዓት (እስፒች ትራንስክራይብ ሲስተም)፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ችሎት/ስማርት ኮርት ትሩ/እና ዘመናዊ የውይይት መለዋወጫ ሮቦትና ኢንፎርሜሽን ዲስክ መረጃ መስጫ/ስማርት ቻት ፖት/ ናቸው። እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ወደ ሥራ ሲገቡ በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ ጥራት ያለውና የተቀላጠፈ የፍትሕ ሥርዓት ካለማግኘት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎችን በእጅጉ ይቀንሳል።

መተግበሪያው ዘመናዊ ዳኝነት ሥርዓት እንዲኖር የሚያስችል ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ አቶ ቴዎድሮስ፤ የለማው ሥርዓት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሽግግራዊ ለውጦችን ለማምጣት እንደሚያግዝ ያመላክታሉ።

ይህ ‹‹ስማርት ኮርት›› መተግበሪያ የመንግሥትና የተገልጋዩ ሀብትና ጊዜ ሳይባክን ተገልጋዩ ለአላስፈላጊ እንግልትና ወጪ ሳይዳረግ ጥራት ባለው መልኩ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፤ በሁሉም ፍርድ ቤቶች አገልግሎት ላይ እንዲውል እንደሚደረግ አመላክተዋል። መተግበሪያው አገልግሎት ላይ እንዲውል ሲደረግ የዳኞችን ሸክም እንዲያቀል ያደርጋል ሲሉ ያስረዳሉ።

የዳኝነት አገልግሎቱን ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢና ተደራሽ የሚያደርገው ከመሆኑም በላይ አስተዳደራዊ ችግር መፍቻዎች በመረጃ ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ ያስችላል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ዘመኑ የደረሰባቸው ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ ማዋላቸው ፍትሕ የሰፈነባት፣ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚደረገውን ጉዞ ያግዛል ሲሉ ይናገራሉ።

በሥራ ላይ መዋል የጀመሩት ቴክኖሎጂዎች ዳኞችንና የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች የስራ ጫናና የፍርድ ቤቱን ወጪ በመቀነስ ሥራን የማቀላጠፍ ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸው፤ ቀሪዎቹን ቴክኖሎጂዎች የማልማትና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ስራዎችን በማጠናቀቅ ፍርድ ቤቶችን ወረቀት አልባ ለማድረግና አገልግሎቶችን ለባለጉዳዮች ምቾት እንዲሰጡ የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያስረዳሉ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤ መንግሥት የአገልግሎት አሰጣጡን ጨምሮ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ በቴክኖሎጂ የታገዙ ቀልጣፋ አሰራሮች እየተዘረጉ ናቸው። በ‹‹ስማትር ኮርት›› የተደገፈ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት መጀመሩ እንደ ሀገር ተስፋ ሰጪ ምእራፍ ላይ መሆናችንን ያመለክታል ሲሉም ጠቅሰው፣ በተለይ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ሙሉ በሙሉ ስኬታማ እንደሚሆን እርግጠኛ የሚያደርግ ነው ይላሉ።

የዳኝነት አገልግሎት አንድ ሀገር ውስጥ የሕግ የበላይነት እንዲከበር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ሥር እንዲሰድና የአገር ልማትና ብልጽግና እንዲሳካ ወሳኝ ስለመሆኑ የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይደለም ያሉት አቶ ታገሰ፤ ፍርድ ቤቶች የሚሰጧቸው አገልግሎቶች ለዜጎች ዋስትና መሆናቸውንና ጥንቃቄ እንደሚያስፈልጋቸው ያመለክታሉ። ይህ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው የዳኞች አገልግሎት ቀልጣፋ፣ ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ፣ ግልጽ፣ ጥራት ያለው፣ ተገማችና ተዓማኒነት ያለው ሲሆን ብቻ መሆኑንም ያስገነዝባሉ።

የዳኝነት አገልግሎትን ለማሳለጥ የለሙት ሥርዓቶች በራስ በጀትና የባለሙያዎች አቅም የለሙ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህም ሀገራችን ብዙ ተስፋ ሰጪ እምቅ አቅም እንዳላት እንደሚያመለክት ነው አቶ ታገሰ የገለፁት።

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You