
መምህርት ማኅደር ሰለሞን ትባላለች። የተጣራ የፕሮሶፒስ ባዮቻር ምርት የሚያመርት ኢነርጀቲክ ኢኮ ቻር ማኑፋክቸሪንግ ፒ ኤል ሲ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ናት። የዩኒቨርሲቲ መምህርት ስትሆን፤ ሁለተኛ ዲግሪዋን በተማረችበት ወቅት ያሳተመችው የምርምር ሥራ የመደርደሪያ ሲሳይ ሆኖ እንዳይቀር ጥረት በማድረጓ ተግባር ላይ ማዋል ችላለች። ይህንን የምርምር ሥራ ለሌሎች መምህራን እና ተማሪዎች አርአያ ለመሆን አስባ የጀመረችው እንደሆነ የምትናገረው መምህርት ማኅደር፤ ያሰበችው ተሳክቶላት ውጤት ማግኘቷን ትገልጻለች።
ድሬዳዋና አፋር በሄደችበት አጋጣሚ ‹‹ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ›› /መስኪት/ የተባለውን መጤ አረም ጎጂነት በመረዳት የሁለተኛ ዲግሪ ጥናታዊ ጹሁፍ ለመሥራት በማሰቧ ተጨማሪ ምርምርና ጥናት በማድረግ ጥናታዊ ጽሁፍ ማሳተም ቻለች። ጥናቱን ማሳተሟ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ስለገባት ወደ ተግባር ተለውጦ ጥቅም ላይ ውሎ ሕብረተሰቡ ሊጠቀምበት እንደሚገባ አምና ሥራ ላይ ለማዋል በቁርጠኝነት ተነሳች።
ከአራት ዓመታት ድካምና ልፋት በኋላ ሀሳቧ ተሳክቶ፤ ‹‹ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ››/መስኪት/ የተባለውን ባዮማስ ለአፈር ተስማሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮች በማካተት ወደ ባዮቻር ምርት /የተፈጨ ከሰል መሰል ምርት/ በመለወጥ ለአፈር ለምነት ተስማሚ የሆነ ግኝት ማውጣት ችላለች።
ሀገሪቱ አብዛኛው ሕዝብ አርሶ አደር እንደመሆኑ፤ ይህ ‹‹ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ››/መስኪት/ የተሰኘ ዛፍ ያለውን ጉዳት በመመልከት ለአራት ዓመታት ምርምር በማድረግና የላብራቶሪ ትንታኔ በመሥራት ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል ውጤት ማግኘቷን ትገልጻለች።
መምህርት ማኅደር አሁን ላይ ኢነርጀቲክ ኢኮ ቻር ማኑፋክቸሪንግ ፒኤ ልሲ የተሰኘ ድርጅት በመመሥረት እየሠራች ትገኛለች። ድርጅቱ የተጣራ የፕሮሶፒስ ባዮቻር ምርት ያመርታል። ለአራት ሰዎች የሥራ እድል ፈጥራለች። የባለቤትነት መብት ለማግኘት በሂደት ላይ ትገኛለች።
የምርምር ሥራዋ ለአራት ዓመታት ጥናት የተደረገበት ሲሆን፤ ከዚህ በፊት በፕሮቶታይፕ ደረጃ ተሰርቶ አርሶ አደሩ ማሳ ላይ ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑን የምትናገረው መምህርት ማኅደር፤ የባዮቻር ምርት ቅም ላይ ከመዋሉ በፊት አፈሩ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? የሚለው ለማወቅ መጀመሪያ የነበረው አፈሩ ያለበት ደረጃ ይለካል። ቀጥሎ ባዮቻሩን ከተጠቀሙ በኋላ ያለው ውጤት ይታያል። በዚህ ረገድ ባዮቻሩ ከተጠቀሙ በኋላ መጀመሪያ አሲዳማ ከነበረው አፈር ተሻሽሎ ንጹህ እየሆነ መጥቷል።
ባዮቻር ተፈጥሮአዊ ስለሆነ አፈር ለምነት፣ በአፈር ውስጥ ያሉትን ባክቴሪያዎች የተሻለ እንዲሆን አድርጓል። አፈሩ ውሃ የመያዝ አቅሙም የተሻሻለ ሆኗል የምትለዋ መምህርት ማኅደር፤ ባዮቻር የአፈር ለምነት በማስጠበቅ የግብርናው ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችል ነው ብላለች።
በሀገሪቱ የሚገኘው ከ14 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ምክንያት በመሸርሸር አደጋ ያጋጥመዋል። ይህንን የምርምር ግኝቱ ወይም ባዮቻር ምርቱ ጥቅም ላይ ውሎ አፈር ላይ በሚደረግበት ጊዜ በመሸርሸር የተጎዳው መሬት አሲዳማነቱ ይቀንሳል። የአፈር ለምነት ተጠብቆ ግብርናውን ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻልም ታመለክታለች።
አፈር ላይ ብዙ ስላልተሠራ አፈርን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመርመር አርሶ አደሩን በሚጠቅም ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር የአፈር ለምነትና የግብር ምርታማነት ለማስጠበቅ እየሠራች መሆኑን ትናገራለች።
መምህርት ማኅደር እንዳብራራችው፤ በተለይ በአፋር ክልል ያለው ‹‹ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ›› /መስኪት/ ተክል በ1950 ወደ ኢትዮጵያ የገባ ሲሆን፤ ዛፉ ረጅም ስር ስላለው ሌሎች በአካባቢው ላይ የሚበቅሉ ተክሎች ውሃ በመምጠጥ እንዲደርቁ ያደርጋል። የግጦሽ መሬትን ይወራል። የእርሻ ሰብልን ይወራል። አካባቢው ለመኖሪያነት ምቹ እንዳይሆን ያደርጋል። እንዲወገድና እንዲጠፋ ይፈለጋል። ይሁንና ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ይሸፍናል። ይህ በየዓመቱ ብዙ ሺ ሄክታር መሬት በላይ እየሸፈነ ያለ አረም መሰል መጤ ዛፍ በአካባቢው፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።
‹‹ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ›› /መስኪት/ ከአፋርና ከድሬዳዋ በተጨማሪ በአንዳንድ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎችም በብዛት ተስፋፋቶ ይገኛል። ይህንን ተክል አሁን ባለው ደረጃ ብቻ እንኳ ወደ ምርት ቢቀየር ከ50 ዓመታት በላይ መጠቀም የሚያስችል ነው። ዛፉ ጎጂ ቢሆንም ጥቅም ላይ የማዋል እድሉ በጣም ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ዛፉን በተመለከተ የተለያዩ ኬሚካልና ፊዚካል ትንታኔዎችን በመሥራት በተለያዩ ጊዜያትና የሙቀት መጠን ወደ ጠቃሚ ባዮቻር የመለወጥ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ትላለች።
‹‹አሁን ላይ ወደ ሥራ ገብተን የምርቱን ፕሮቶታይፕ በማውጣት ለአርሶ አደሩ እየተጠቀምንበት እንገኛለን›› የምትለው ማኅደር፤ በዚህም አመርቂ ውጤቱ ማግኘት መቻሏን ትገጻለች። ይህንን ሥራ ለመሥራት የሚያስፈልጉት ማሽኖች በተለያዩ በዩኒቨርሲቲዎች እና በሌሎች በአነስተኛ ደረጃ የሚሠሩ አምራቾች የሚጠቀሙባቸውን ማሽኖች እየተገለገሉ እየሠሩ መሆኑን ገልጻ፤ በቀጣይ የመሥሪያ ቦታዎችን በማመቻቸት ማሽኑን በመግዛት ውጤታማ ሥራ ለመሥራት አቅደው እየተንሳቀሳቀሱ መሆኑን አስታውቃለች።
ወደ ገበያ ለመውጣት የሚያስፈልገው ማሽኑን መግዛት እንደነበር ጠቅሳ፤ በአዩቴ አፍሪካ ቻሌንጅ 2025 ውድድር ሦስተኛ በመውጣት 7ሺ 500 ዶላር ሽልማት በማግኘታቸው ይህንን ኃላፊነት በመውሰድ ማሽን በመግዛት ሥራውን ለማስፋፋት እንዳቀደች ትናገራለች። እስካሁን በአነስተኛ ደረጃ በቤት ውስጥ እየሠሩ መሆኑን ጠቅሳ፤ ይሄንን በማሳደግ ከፍ ወደአለ ደረጃ ለመድረስ ማሽን እንደሚያስፈልጋቸው ትገልጻለች። ‹‹ ለዚህ የሚሆን ፈንድ ደግሞ አግኝተናል። ማሽኑን ከገዛን በኋላ ምርቶቻችንን በማምረት ለአርሶ አደሩ እና በከተሞች የጓሮ አትክልት ለሚያመርቱ የማኅበረሰብ ክፍሎችም ተደራሽ እናደርጋለን›› ትላለች።
መምህርት ማኅደር እንዳብራራችው፤ ባዮቻር ለማምረት ‹‹ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ››/መስኪት/የተሰኘው ዛፍ ይቆራረጣል። በመቀጠል በላብራቶሪ የኬሚካል ፍተሻ በማድረግ ትንታኔ ይሠራለታል። እንዲደርቅ ከተደረገ በኋላ የሚፈለገው ሰዓትና የሙቀት መጠን በመጠቀም፤ በማቃጠል የተለያዩ ተፈጥሮአዊ ኬሚካሎች ወደ ከሰልነት እንዲቀየሩ ይሠራል። ከሰሉ ከተፈጨ በኋላ በላብራቶሪ የጥራት ደረጃውን በመፈተሸ በተለያየ መጠን በኪሎ እየተለካ ተደራሽ ይደረጋል። ከአንድ ኪሎግራም ጀምሮ እስከ 25 ኪሎግራም ያህል በተለያዩ መጠን በማሸግ ዝግጁ የሆነውን አንድ ኪሎ ግራም በሃያ አምስት ብር ብቻ እየተሸጠ ተደራሽ እየተደረገ ይገኛል።
የባዮቻር/የተፈጨ ከሰል/ ምርቱ ለተፈጥሮ መሬት እንዲስማማ ተደርጎ የተዘጋጀ በመሆኑ፤ አጠቃቀሙ ዘር ከተዘራ በኋላ ባዮቻሩ በማሳው ላይ ይደረጋል። ይህም መሬቱ በውሃ እንዳይወሰድና እንዳይሸረሸር ያደርገዋል። አፈሩ አሲዳማ ከሆነ ደግሞ ተክሉን ለማደግ የሚያቀጭጨው በመሆኑ አሲዱ እንዲጠፋ ያደርገዋል። ይህ አሲዳማነት ይቀንሳል፤ ውሃ የመያዝ አቅሙ እንዲጨምር ያደርገዋል። አፈሩ ለም እንዲሆን፤ በቀላሉ በውሃ እንዳይወሰድና በአፈር ውስጥ ያሉ ጠቃሚ ባክቴሪያዎች ለረጅም ጊዜ እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል።
በተጨማሪ ከኢንዱስትሪዎች የሚወጡ ኬሚካሎች ካሉ ባዮቻሩ በውስጡ ይዞ እጸዋቱ እንዳይጎዱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል። በአየር ላይ ያለውን ካርባንዳይኦክሳይድ በመምጠጥ በአፈር ውስጥ ለረጅም ዓመታት ይዞ ማቆየት ይቻላል። ይህ ደግሞ አየር ንብረት ያማከለ የግብርና ምርት እንዲኖርና ኮርቦንዳይኦክሳይድ እንዲቀንስ የራሱ አስተዋጽኦ አለው። ከዚህ ባሻገር ዘርፈ ብዙ ተግባራት አሉት ትላለች።
የባዮቻር ምርቱ ተሞክሮ ውጤታማ ሆኗል የምትለው መምህርት ማኅደር፤ አዲስ አበባና አርሲ አንዳንድ አካባቢዎች በሰላጣ፣ በቆላ ላይ ተሞክሮ ውጤታማ ሆኗል። መጀመሪያ የባዮቻር ምርት ከመዘጋጀቱ በፊት አፈር በመውሰድ ምርመራ የተደረገበት ሲሆን፤ ምርቱ ከተደረገባቸው በኋላ ደግሞ ያለውን ለውጥ በመርመር የተሻለ ምርት ለማግኘት አስችሏል።
የተለያዩ የአፈር አይነቶች አሉ። እነዚህም ሸክላማ፣ ለም እና ሌሎችም የመሬት ዓይነቶች ያሉ ሲሆን፤ ባዮቻሩ በተፈጥሮ የተሠራ ምንም አይነት የሚጨመርበት ሰው ሰራሽ ነገርና ኬሚካል ስለሌለው ተፈጥሮአዊ ስለሆነ ለሁሉም አፈር አይነት ተስማሚ ነው። በተለይ ለሸክላማ አፈር ጥቅም ላይ እንዲውል ቢደረግ ይመከራል። ምክንያቱም ሸክላማ አፈር ውሃ አይዝም እንዲሁም የለምነት ችግርም አለበት። ግኝታቸው ለሸክላማ አፈር እና ለተጎዳ መሬት ጥቅም ላይ ቢውል የተሻለ አቅም እንዲኖር ይረዳዋል ስትል አስረድታለች።
መምህርት ማኅደር እንደምትለው፤ ድርጅቱ አሁን ላይ መቶ በመቶ ከፕሮሶፒስ የተሠራ ባዮቻር እያመረተ ይገኛ እየተሠራበት ያለው ተፈጥሯዊ በሆነ መልኩ ባዮቻር ላይ ብቻ ነው። በቀጣይ 80 በመቶ ከ‹‹ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ›› 20 በመቶ ከኮምፖስት (ከተለያዩ የእጽዋት ብስባሽ) ጋር ለመቀላቀል ጥናት እየተደረገ ነው። በተጨማሪ በጠጣርና በፈሳሽ መልኩ ተሰርቶ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆንና የምርቶቹ አቅም ለመጨመር የተለያዩ ጥናቶችን እያደረጉ ናቸው። እንዲሁም በሌሎች ነጥረ ነገሮች ላይ የተለያዩ ምርምሮች እየሠሩ ሲሆን፤ ከቡና ተረፈ ምርትና ከሌሎች ነገሮች ባዮቻር ለማምረት የሚያስችል ጥናት ተደርጎ ተጠናቋል።
በሌላ በኩል ድርጅቱ በፍቃደኛነት የአፈር ጥበቃና የአካባቢ አጠቃቀምን በተመለከተ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ ለሁለተኛ ደረጃና ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት በማኅበረሰቡ ውስጥ ግንዛቤው እንዲስፋፋና እንዲዳበር እንዲሁም እንዲሰርጽ እያደረጉ ይገኛሉ። አርሶ አደሮችም እንዲሁ ስልጠናዎች እንዲያገኙ እያደረጉ ነው።
አሁን ላይ አርሶ አደሩ ለማዳበሪያነት እየተጠቀመ ያለው ዩሪያና ዳፕ ነው የምትለዋ መምህርት ማኅደር፤ ይሁንና ዩሪያና ዳፕ ተፈጥሯዊ አይደሉም። በሌላ በኩል አፈሩን እየጎዱት ይገኛሉ። እየተሸጡ ያሉበት ዋጋም ቢሆን በኪሎ ከ60 እስከ 80 ብር የሚገመት ነው። የማዳበሪያ ዋጋ በቅርቡ ደግሞ ከ170 ፐርሰንት በላይ ጭማሪ አሳይቷል። አዲሱ ተፈጥሯዊ ምርት ግን በዋጋም ቢሆን የተሻለ የአርሶ አደሩን የመግዛት አቅም ባገናዘበ መልኩ ማቅረብ የሚችል ነው ትላለች።
‹‹ አሁን ላይ እያመርትን ያለነው በአነስተኛ ደረጃ ባሉ ማሽኖችና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባሉ ላብራቶሪዎች በመጠቀም ነው። በዚህ ሳቢያ ተደራሽነታችን ውስን ነው›› የምትለው መምህርት ማኅደር፤ በአዩቴ አፍሪካ ቻሌንጅ ውድድር በማሸነፋቸው የተሰጣቸው የገንዘብ ሽልማት ከሰሉን የሚፈጩበትን ማሽን ለማስመጣት መታቀዱን ትገልጻለች። በቀጣይ ድርጅቱ በሰፊው ማምረት ሲጀምር ከመንግሥትና ከክልል የግብርና ቢሮዎች ጋር አብረው ግንዛቤ በመስጠት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችሉ ሥራዎች ይሠራሉ ስትል አብራርታለች።
ድርጅቱ ምርቱን ለተጠቃሚ አርሶ አደሮች ከመስጠት በፊት አፈሩ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ጥናት ካደረጉ በኋላ ግንዛቤው እንዲኖራቸው ስልጠና እንደሚሰጥ ትገልጻለች። ከዚያ በኋላ ምርቱን በቋሚነት ለማቅረብ የሚያስችሉ የገበያ ትስስሮች ለመፍጠር የሚሠራ መሆኑን ጠቁማ፤ እንደ ሀገር ሲታሰብ ግብርና በጣም ሰፊ ዘርፍ በመሆኑ አንድ ድርጅት ብቻ የሚሠራው ሳይሆን የእሷ ድርጅትም የራሱን አስተዋጽኦ ከማበርከት አንጻር እየሠራ መሆኑን አመላክታለች።
‹‹ድርጅቱ ‘ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ’ ዛፉን ከአፋር እያመጣ እየሠራ ነው። ከዚህ በኋላ ማስመጣት የሚቻለው ለሙከራ ያህል የሚሆነውን ብቻ ነው። ጥሬ ግብዓቱ ያለበት ቦታ ማሽኑን በመትከል እየተጎዳ ያለውን መሬት በማከም መሥራት አቅደናል።›› የምትለው ማኅደር፤ በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ከተለያዩ ተረፈ ምርቶች እንደሚሠሩ ገልጻለች።
አብዛኛው ሕዝብ በግብርና የሚተዳደር በመሆኑ ባለው ፍላጎት ልክ ተደራሽ ለማድረግ አስቸጋሪ ቢሆንም አፈር ላይ ችግር የሚፈጥሩ ነገሮች መፍትሔ ለመስጠት ይሠራል። ለዚህም ጥቅም ላይ የሚውሉትን ጥሬ ግብዓቶች በማስፋት ምርቱ ተደራሽ ለማድረግ ይሠራል። ነጻ ስልጠናዎች መስጠት የሚያስፈልግ በመሆኑ ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ የሚሠሩ መሆኑን ትናገራለች። የሀገር ውስጥ ፍላጎት መሸፈን ከተቻለ ወደ አፍሪካ ሀገራት ለመላክ ድርጅታቸው ማቀዱን አብራርታለች።
‹‹ይህንን ምርት ለመፈተሽ የሞከርነው በሚያምኑን ሰዎች መሬት ላይ ነው። የተሻለ ውጤት መጥቷል። አርሶ አደሩ የኬሚካል ምርቶች ዋጋ መጨመርን መቋቋም ባለመቻሉ አማራጮች በመፈለግ ላይ መሆኑን ገልፃ፤ ምርቱ የተሻለ ውጤት የሚያመጣና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብ ስለሆነ አጠቃቀሙን በተመለከተ ስልጠና የሚሰጥ በመሆኑ ሰዎች ግኝቱን የማይጠቀሙበት ምንም አይነት ምክንያት አይኖራቸውም›› የምትለው ማኅደር፤ መሬቱን የማይጎዳ ተፈጥሮዊ የሆነ ምርት በቅናሽ ዋጋ የቀረበ በመሆኑ አንዱ ሌላውን እያየ የማይጠቀምበት ዕድል ሰፊ እንደሚሆን አስገንዘባለች።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም