በክልሉ የመማሪያ መጽሐፍትን ለእያንዳንዱ ተማሪ ለማዳረስ ሁለት ዓመት ይፈጃል

– እስካሁን 20 ሚሊዮን የመማሪያ መጽሐፍት ለተማሪዎች ተሰራጭቷል

አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል የመማሪያ መጽሐፍትን ለእያንዳንዱ ተማሪ ለማዳረስ ሁለት ዓመት ሊፈጅ እንደሚችል የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። እስካሁን 20 ሚሊዮን የመማሪያ መጽሐፍት ለተማሪዎች መሰራጨቱ ተጠቁሟል።

የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት ፤የመማሪያ መጽሐፍትን ለሁሉም ተማሪዎች ማዳረስ አለመቻሉ በትምህርታቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ይገኛል። በክልሉ የመማሪያ መጽሐፍትን ለእያንዳንዱ ተማሪ ለማዳረስ ሁለት ዓመት ሊፈጅ ይችላል።

በኦሮሚያ ክልል በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አምስት ሚሊዮን፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አንድ ሚሊዮን 54 ሺህ ፣በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ደግሞ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ተማሪዎች ይገኛሉ ያሉት ኃላፊው፤በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ተማሪዎች መጽሐፍትን የሚያቀርበው የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሲሆን ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ መጽሐፍትን የማቅረብ ኃላፊነቱ የትምህርት ሚኒስቴር መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ትምህርት ሚኒስቴር በክልሉ ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ላሉ ተማሪዎች 14 ሚሊዮን መጽሐፍትን ማቅረብ የሚኖርበት ቢሆንም እስካሁን ድረስ ለክልሉ ማድረስ የቻለው 5 ሚሊዮን (35 ነጥብ 7 በመቶ) መጽሐፍትን ብቻ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር የተቀረውን መጽሐፍትን ደረጃ በደረጃ እያተመ ለማቅረብ ቃል መግባቱን የገለጹት ኃላፊው፤ ሚኒስቴሩ ያቀረበውን መጽሐፍት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለተማሪዎቹ ማሰራጨቱን ተናግረዋል። ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎች በተሻለ ሁኔታ መጽሐፍት ማዳረስ ቢቻልም ሌሎቹ ክፍሎች ላይ ግን ከፍተኛ ችግር አለ ብለዋል።

የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መጽሐፍትን አትሞ የሚያሰራጨው የክልሉ ትምህርት ቢሮ መሆኑን ገልጸው፤ ለእነዚህ ትምህርት ቤቶች 36 ሚሊዮን መጽሐፍት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ቢሮው እስካሁን ድረስ አትሞ ማሰራጨት የቻለው 15 ሚሊዮን መጽሐፍትን መሆኑን ጠቅሰዋል።

በክልሉ መጽሐፍትን ለእያንዳንዱ ተማሪ ለማድረስ ከዚህ በኋላ ሁለት ዓመት እንደሚፈጅ በክልሉ የትምህርት ትራንስፎርሜሽን መተንበዩን የገለጹት ኃላፊው፤ በዚህ ዓመት ግን አንድ መጽሐፍ ለሁለት ተማሪ ለማድረስ እቅድ መያዙን አብራርተዋል።

በአሁኑ ጊዜም ኢንተርኔት ማግኘት የሚችሉ ተማሪዎች መጽሐፉን ከቢሮው ድረ ገጽ አውርደው እንደሚጠቀሙና ይህንን ማግኘት የማይችሉ ተማሪዎች ደግሞ በመምህራኖቻቸው በኩል የሚያገኙበት እንዲሁም አቅም ያላቸው ትምህርት ቤቶች የተወሰኑ መጽሐፍቶችን እያተሙ ለተማሪዎቻቸው የሚያደርሱበት ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል።

ኃላፊው ‹‹መጽሐፍ በተማሪዎች እጅ ላይ አለመገኘቱ በትምህርታቸው ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ከባድ መሆኑን ብንረዳም ማተሚያ ግብአቶች ከውጭ ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ እጥረት በመኖሩ ከአቅም በላይ ሆኖብናል›› ሲሉ የችግሩን መንስኤ አብራርተዋል።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ጥር 16/2016

Recommended For You