ከህሊና ጋር ትንቅንቅ

ባለፈው ሐሙስ ነው፡፡ በአዲስ አበባ፣ 02 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የፒያሳና አራት ኪሎ ታክሲ መያዣው ጋ (የረር ሕንጻ አጠገብ) ቆሜ ሰው እየጠበቅኩ ነው፡፡ ከሕንጻው ሥር ብዙ ጫማ የሚያጸዱ (ሊስትሮ) ልጆች አሉ። አንደኛው ሰውዬ ጫማ ለማስጠረግ ከጎን ተቀምጦ ወረፋ እየጠበቀ ነው፡፡ በዚህ መሐል አንዲት ሁለት ልጆች የያዘች እናት መጣች፡፡ አንደኛውን በጀርባዋ ያዘለችው ሲሆን ሁለተኛው በእግሩ ከፊት ከፊቷ የሚሄድ ነው። በልመና ላይ ነች።

ወረፋ ከሚጠብቀው ሰውየ ጋ ስትደርስ ሰውየው ወደ ኪሱ ገባ፡፡ ከኪሱ ካወጣው ብር ውስጥ ዝቅተኛው 50 ብር ነው፡፡ ያወጣውን ብር በአንደኛው እጁ ይዞ ወደ ሌላኛው ኪሱ ገባ፡፡ በዚህን ጊዜ ሕጻኑ ልጅ እጁን ወደ ሰውየው ዘረጋ። ይሄኔ እናትየዋ የልጁን እጅ መታ እያደረገች ‹‹እረፍ›› አይነት ቁጣ ተናገረችው፡፡ ሰውየው የፈቀደውን ይስጥ እንጂ ግዴታ በሚመስል መንገድ መሆን የለበትም በሚል ከህሊናዋ ጋር እየታገለች መሆኑ ነው፡፡ ሰውዬው ከሌላኛው ኪሱ ሲገባ ዝርዝር ብር አጣ፡፡ ወደ ኪሱ መግባቱ ደግሞ ሴትዮዋ እና ልጆቹ እንዲጓጉ አድርጓል። እሱም ከህሊናው ጋር እየታገለ ነው፡፡ 50 ብሩን ነጥሎ በማውጣት ሰጣት፡፡ አመስግና ሄደች። እኔም በውስጤ ደስ የሚል ነገር ተሰማኝ። ምንም እንኳን ያላሰበውን ቢሆንም የሰጠው ቢያንስ ከእርሷ እሱ ይሻላልና ለእርሱም የህሊና ደስታ ነው፡፡

እንዲህ አይነት ከህሊና ጋር ትንቅንቅ የሚገጠምባቸው ሁኔታዎች የሚያጋጥሙኝ ልጅ ይዘው በሚለምኑ እናቶች ላይ ነው። አዲስ አበባ ውስጥ በየካፌውና ምግብ ቤቱ ውስጥ ሰውነታቸው የጠወለገ ሕጻናት ይዘው የሚመጡ እናቶች ብዙ ናቸው፡፡ ከምግብ ቤቶች ባለቤቶች ጋር አትገቡም የሚል ሌላ ትንቅንቅም አለ፡፡ እነዚህን እናቶችና ሕጻናት ማየት ልብን ይሠብራል። የሞቀ ቤትና ንብረት የነበራቸው ሰዎች ናቸው። ሕጻናት ይዛ የምትለምን አንዲት እናት ሳይ የዚያች እናት ነገር ብቻ አይደለም የሚያሳስበኝ፤ እሷን የመሰሉ በከተማዋ ጎዳናዎች ዳር ሁሉ አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ሕጻናት ይዘው የሚለምኑ እናቶች ሳይ ‹‹የሚሰጣቸው ይኖር ይሆን?›› በሚል ስጋት ጭምር ነው እጃቸውን የዘረጉበትን ሁሉ የማየው፡፡ በእርግጥ ችግሩ ለእነዚህ እናቶች 5 ብር እና 10 ብር በመስጠት የሚቀረፍ አይደለም!

ከችግሩ በላይ የሚያሳዝነው ከህሊና ጋር ያለው ትንቅንቅ ነው፡፡ ያቺ ሴትዮ የምትለምነው ተቸግራ ነው። ልጇ ወደ ሰውየው እጁን ሲዘረጋ የከለከለችው ግን በሰጪው ሰውዬ መልካም ፈቃድ ብቻ መሆን አለበት እያለ አዕምሮዋ ስለሚታገላት ነው፡፡ ያ ሰውዬ የያዘውን ብር ሁሉ ቢሰጣት ደስታዋ ነው። ያ ግን መሆን ያለበት በሰውዬው መልካም ፈቃድ ብቻ ነው፡፡ ወዲህ ደግሞ ልጇ እጁን መዘርጋቱ ሰውየው እንዲታዘበኝ ያደርገኛል ብላ ከህሊናዋ ጋር እየታገለች ነው፡፡ በዚህ ሕይወት ውስጥ ሆና እንኳን ‹‹ልጇን በጨዋነት አታሳድገውም እንዴ?›› ይሉኛል የሚል ይሉኝታ ይዟታል፡፡ አሳሳቢው ነገር ይህ ችግር እየከፋ ሲሄድ፣ ተጨማሪ ተፈናቃይ ሲበዛ እና ሰጪ ሲጠፋ አሁን ያለው ይሉኝታ እና ከህሊና ጋር የሚደረግ ትንቅንቅ ያልቃል፡፡ አሁን እየኖሩ ያሉት ከዚህ በፊት በነበራቸው የምቾት ጊዜ ባዳበሩት ይሉኝታና ህሊና ነው፡፡

ሰጪው ሰውዬም ህሊናው እምቢ ብሎት ነው 50 ብር የሰጠው፡፡ መጀመሪያ ላይ ዝርዝሮች ሲፈልግ ነበር። ያቺ ልጆች የያዘች እናት ከፊቱ ቆማ ግን ዝርዝር አጣሁ ብሎ መተው አልቻለም፤ ሊያደርገውም አይችልም፡፡ ምክንያቱም እጁን ከኪሱ አስገብቶ ሲያወጣ ከታየ በኋላ መተው ለማንም ሰው ይከብዳል፡፡

ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ ግን እነዚህ ይሉኝታዎች እንዳይሟጠጡ ያስፈራል፡፡ ለልመና የሚሰማሩ ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ብቻ ይታይ የነበረው አሁን በየምግብ ቤቱና በየካፌው በር ላይ ሆኗል። በየትኛውም ቦታ ላይ ሕጻናት ይዘው የሚለምኑ እናቶችን ማየት የተለመደ ነው። ይህ ቁጥር እየጨመረ ከሄደ የሚሰጠው ዜጋ ቁጥር ይቀንሳል፡፡ ከዚህ በፊት የሚለምን ሰው ሲያይ አንጀቱ ይላወስ የነበረ ሰው የዕለት ከዕለት ክስተት ሲሆንበት እየተላመደው ይሄዳል፡፡ ከዚህ በፊት አንድ የተቸገረ ሰው ሲታይ ‹‹ለወገን ደራሹ ወገን ነው›› በሚለው ተረባርቦ ማዳን ተችሎ ነበር፡፡ አሁን ግን የተቸገረውና የሚለምነው ቁጥር ከበዛ የሰጪ ሰዎች አዕምሮ የተቸገረ ሰው ማየትን ይላመደዋል፡፡

ለጊዜው በተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች፣ ችግረኞችን ማየት መላመዳቸው በልመና ላይ የተሰማሩት የሚበሉት እንዲያጡ ያደርጋል። የሚበሉት አጡ ማለት ደግሞ ነገርየው በልመና ብቻ እንዲገደብ አያደርገውም። ቁጥሩ እየጨመረና እየከፋ ከሄደ ዝርፊያ እና መቀማት ሁሉ ሊጀመር ይችላል። አዲስ አበባ አሁን ከሚታየው በላይ ተፈናቃይ ዜጎች ይኖሯታል። ያኔ ችግሩ ለሁሉም ይተርፋል ማለት ነው፡፡ አሁን በጥሩ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉትንም ይነካል ማለት ነው፡፡ በ“አደገኛ አጥር እና በ“አደገኛ ውሻ ሊከላከሉት የሚችሉት ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው፡፡”ሲቀጥል የውጭው ሁኔታ የተረበሸ ከሆነ በቤት ውስጥ ሰላም ሊኖር አይችልም፡፡ ከውጭ ዳቦ ገዝቶ መግባት የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡

እነዚህ ነገሮች ዛሬ ላይ ሆነን ስናያቸው ምናልባትም ‹‹ሟርት›› ሊመስል ይችላል፡፡ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች የሚታዩ በልመና ላይ የተሰማሩ ዜጎች ቁጥር ግን እንዲህ በቀላሉ የሚታይ መሆን የለበትም። የመንገደኛ ልብስ ላይ ተጣብቀው የሚከታተሉ ሕጻናት በየጎዳናው ላይ አሉ። እንቅስቃሴው ሁሉ በመኪና የሆነ ሰው ይህን ችግር አይረዳው ይሆናል፤ ለጊዜውም እሱን አያገኘው ይሆናል፡፡ ችግሩ እየከፋ ከሄደ ግን እንኳን በመኪና በአየር የሚሄድም አያመልጥም። ምክንያቱም የከተማዋ የውጭ ሁኔታ ሲበላሽ የውስጡንም ያበላሸዋል፡፡ ዛሬ ላይ የተደላደለ ኑሮ ላይ ያሉ ሰዎች ነገ ወጣ ብለው የሚዝናኑበት ሁኔታ ላይኖር ይችላል፡፡

ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ምን ሆነው ነው ለልመና የተሰማሩት? የሚለውን ሁሉም ሰው ሊጠይቅ ይገባል፡፡ እነዚህ ሰዎች የሞቀ ቤት የነበራቸው ናቸው። ሀገርን መቀለብ የሚችል ምርት ያመርቱ የነበሩ ናቸው፡፡ ለተቸገረ ያጎርሱ የነበሩ ናቸው። ልመናን ከማንም በላይ ይፀየፉ የነበሩ ናቸው። እንኳን ለምኖ ገዝቶ መብላትን እንደ ነውር የሚያዩ ነበሩ፡፡ ግን በየአካባቢያቸው ያለው የሰላም እጦት ለዚህ ችግር ዳረጋቸው፡፡

ስለዚህ ችግሩ አሁን ካለበት ከመባባሱ በፊት መንግሥትም ሕዝብም ጉዳዩን ‹‹በቃ›› ሊለው ይገባል!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You