ባሳለፍነው ሳምንት በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ የሀዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ሰባተኛውን አገር አቀፍ አውደ ጥናት አካሂዷል። አውደ ጥናቱ «የጋራ ባህላዊ እሴት ለጠንካራ አገራዊ አንድነት»የሚል መርህ ነበረው። በወቅቱም የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው በርካታ ሀሳቦች ተንሸራሽረዋል። አንኳር የሚባሉ ነጥቦች ተነስተውም በአከራካሪ ነጥቦች ታጅበዋል።
በደብረብርሃን መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የስነ- ህይወት መምህሩ ገብረሀና ዘለቀ በዩኒቨርስቲው በተካሄደው የጥበብ ጉባኤ ላይ «ፍቅር እሰከመቃብር» የተሰኘውን የረጅም ልቦለድ መድብል ላይ ጥልቅ ዳሰሳ አቅርበዋል። መምህር ገብረሀና በጥናታቸው ለማሳየት የሞከሩት የደራሲውን የሀዲስ አለማየሁን ሀሳብ እና ለማለት ፈልገዋል ያሉትን ትንቢት ጭምር ነው።
ጥናቱ ታሪካዊ የምርምር ዘዴን የያዘ ነው። የመጀመሪያው ደረጃ ፍንጭ በደራሲው የተጻፈው ፍቅር እሰከመቃብር ሲሆን ሁለተኛው ደረጃ የመረጃ ምንጭ ደግሞ የተለያዩ አብያተ መጽሐፍት ናቸው። እንደ መምህር ገብረሀና ዳሰሳም በፍቅር እስከመቃብር የረጅም ልቦለድ መጽሐፍ ውስጥ የተካተቱትን ምሳሌዎችና ህልሞች፣ የልደትና የሞት ክዋኔዎች፣ የተለያዩ ተምሳሌቶችና መልክዓምድር ገለጻዎችን በጥልቀት ለመመርመር ተችሏል።
የመምህሩ ዳሰሳዊ መነሻ መሰረት ያደረገው በፍቅር እስከመቃብር ታሪክ ከተጠቀሱት መሀል አራት ዋና ዋና ገጸባህርያት ላይ ነው። እነሱም ፊታውራሪ መሸሻ፣ ጉዱ ካሳ ዳምጤ፣ በዛብህ ቦጋለና ሰብለወንጌል መሸሻ ናቸው።
ፊታውራሪ መሸሻ
ፊታውራሪ ከኖሩበት አራትና አምስት መቶ ዓመታት በፊት በአጼ ዘርአይ ያዕቆብና በአጼ ልብነድንግል ዘመነ መንግሥት አስተሳሰብ እንደ ወራሽ ልጅ የሚንገበገቡና የሚቆጩ ናቸው። ይህ ጥንታዊና ኦሪታዊ አስተሳሰባቸውም እሳቸው ከሚኖሩበት ዘመን ጋር የተቃረነ እና የተጣላ ሆኖ ተገልጿል። ፊታውራሪ መሸሻ አቻ የማይገኝላቸው የመከራ ምንጭ ከመሆናችም በላይ በድርጊቱ የረቀቀና ስጋ የለበሰ ሰይጣን ያህል ተስለው ይታያሉ። እንደፍየል መንታ የክፋት ቀንድ ያላቸው፣ ግፍ ማድረግና መመኘትን የፅድቅ ዋጋ አድርገው የሚቆጥሩና ለክፋታቸው ምሳሌ የሌላቸው ተደርገው የሚታሰቡ ናቸው።
እሳቸው ሁሌም ለሰብለወንጌልና ለዘራቸው ክብር ሲሉ ይቆማሉ። በደል ሁሉ በደም እንጂ ይቅር በመባባል አይጸዳም ብለውም ያምናሉ። ሰብለወንጌል የፊታውራሪ መሸሻ የፍቅርና የፀብ ምንጫቸው ናት። አቻቸውን ሲያማርጡ ተጎሳቁላለች፣ ለጋብቻ በሚጠይቋት ሁሉ የሚያፍሩና ራሳቸውን ከፍ የሚያደርጉ በመሆናቸውም ልዩ ከሚሉት የዘር ሀረጋቸው ጋር በማያያዝ «ተደፈርን» ብለው የሚያምኑ ናቸው። ከዚህ ባህሪያቸው በመነሳትም ፊታውራሪ መሸሻ በደራሲው ምናብ ዘውዳዊውን ስርአት ወካይ ሆነው ተቀርጸዋል።
ጉዱ ካሳ
ሀዲስ አለማየሁ ካሳን በራሳቸው ማንነት ይወክሉታል። ጉዱ ካሳ አብዮተኛ ነው። ለለውጥ የቆመ በመሆኑ ለውጥን ከራሱና ከቤቱ ጀምሯል። የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን የወረሯትን ሽፍቶች፣ አመፀኞች፣ አሰናካዮችና ፈሪሳዊያንን ሁሉ በጽኑ ይቃወማል። ከሚገኝበት ስርዓት ሹመትን፣ ሽልማትን ይጸየፋል፣ ከማህበረሰቡ ራሱን ያገለለ በመሆኑ ማህበረሰቡም አግልሎታል። የፊታውራሪ ዳምጤ ብቸኛ ልጅ ሆኖ በአያቶቹ ያደገና በልማዱ፣ በወጉና በስርዓቱ ላይ የሸፈተ ሲሆን ቤተክርስቲያንም በወጉ ያስተማረችው ሊቅ መሆኑ ተጽፎለታል። እንደ ደራሲውም ያለ አባት አድጓል። ነቢይነት፣ መገሰፅንና መገለል ስላለበት የመጥምቁ ዮሐንስን ባህሪና ጥሪ አላብሶታል።
እንደ ደራሲው ትንቢታዊ አሳሳል ጉዱ ካሳ ከባላባት ወገን ወጥተው ለለውጥ የሚነሱ፣ የሚታገሉትንና ከታችኛው ማህበረሰብ ጋር የሚሰለፉትን ወገኖች ማንነት የሚያሳይ ነው። ጉዱ ካሳ ለለውጥ ሲሉ ጥቅም፣ ክብርና ስልጣናቸውን የማይፈልጉትንና ከራሳቸውና ከዘራቸው ይልቅ ህዝባቸውንና ሀገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያንን በግልጽ ይወክላል።
በዛብህ ቦጋለ
በነቢዩ ኤርምያስ አምሳል የተቀረፀ ሲሆን የውድነሽ በጣሙና የአቶ ቦጋለ መብራቱ ብቸኛ ልጅ ነው። በዛብህ የስዕለት ልጅ በመሆኑ ለታቦቶች ተሰጥቷል። ህልም አላሚ፣ ትንቢት ተናጋሪና፣ አብዮተኛም ነው። ከሰብለወንጌል በስተቀር ሚስት የማያገባ ድንግል ሲሆን ከንጉስ ግብር ተገኝቶ ያልቀመሰና፣ መግቢያውን እንጂ መውጫውን የማያውቅ ስለመሆኑ ተገልጿል፣ የስርአቱን ጥቅምም ሆነ ማእረግ የማይፈልግና የተፀየፈ ነው። ሩፋኤል የቅኔ መምህር ሲሆን ችኩል፣ ተስፋ ቆርጦ የወደቀ፣ ምኞቱ የጨነገፈበት፣ ሰቆቃው የበረታና በወንበዴ ተደብድቦ ከሰብለወንጌል ክንድ ላይ ያረፈ ወጣት ነው።
መምህር ገብረሀና በጥናታቸው እንዳስቀመጡትና እንደደራሲው ሀዲስ አለማየሁ ትንቢታዊ አቀራረጽም በዛብህ ማለት ኢትዮጵያን የሚወዱ፣ የሚያፈቅሩ፣ ያለእርሷ ህይወትም፣ ደስታም፣ ተስፋም የሌላቸውን፤ በፍፁም ልባቸው፣ በፍፁም ነፍሳቸው፣ በፍፁም አካላቸው ለክብርዋና ለብልፅግናዋ የሚባዝኑትንና መስዋዕትነት የከፈሉትን ወይም የሚከፍሉትን ልጆቿን ይወክላል።
ሰብለወንጌል መሸሻ
የፊታውራሪ መሸሻና የወይዘሮ ጥሩአይነት ብቸኛ ልጅ ናት። በፍቅር እስከመቃብር መጽሐፍ ላይም ንጽህትና ድንግል ስለመሆኗ ተገልጿል። እንደ ደራሲው የባህርይ አቀራረጽ ደግሞ ሰብለ ማለት የእቴጌ ሰብለወንጌልና የእቴጌ ምንትዋብ ምሳሌና ባለራዕይ ናት። ውሳኔዋ ፅኑና ያለ ወንድ ግንኙነት ፍቅርን ያረገዘች ልጃገረድ በመባልም ተጠቅሳለች።
ሌቱ በድቅድቅ ጨለማ፣ ሰማይ በከዋክብትና ጨረቃ ሲደምቅ ሰብለ ከሙሽራ ቤቷ ወጣች። የአባ ተክለሀይማኖትን የምንኩስና ልብስን ተጎናጽፋም ከመንደሯ ርቃ ጠፋች። «አባ አለም ለምኔ» ስትልም ራሷን ሰየመች። እንደደራሲው ትንቢት ሰብለወንጌል አብዮተኛ ናት። ታስራና ተጠምቃ የተፈታች ቆራጥና ጠንካራ ሴት።
ሰብለ «ከምወደው ውጪ አልዳርም» በማለቷ ውሳኔዋ የጸና ነበር። ይህን በማድረጓም የበዛብህን መቃብር ጠባቂ ሆና ዘልቃለች። በመጨረሻም እውነተኛ ፍቅሯን በጽናቷ አውጃ እሷም ላትነቃ ከጎኑ አሸልባለች።
ሰብለወንጌል ማለት የወንጌል ሰብል፣ የወንጌል ፍሬ ማለት ነው። ደራሲውም በትንቢታቸው ሀገር ሁል ጊዜም በድንግልና የተባረከች በመሆኗ በሰብለወንጌል ውክልና እንድትገለጥ ስለዋታል።
የፍቅር እስከመቃብር ትንቢት በፊታውራሪ መሸሻ ዕድሜ
ጥናት አቅራቢው መምህር ገብረሀና እንደሚሉት የፍቅር እስከ መቃብር ዋና ዋና ገፀ-ባህርያትን የእድሜ አወካከል ለማወቅ መጽሐፉ ከታተመበት ዘመን 1958 ዓ.ም ላይ በመጽሐፉ ውስጥ የተገለፀውን እድሜያቸውን በመቀነስ የሚታሰብ ነው። የገጸባህርያቱ የዕድሜ ልኬታና ዘመኑ የሚወክለው ትንቢትም እንዲህ ይገለጻል።
በመጽሐፉ ገጽ 143 ላይ እንደተገለጸው የፊታውራሪ መሸሻ በርይሁን ዕድሜ 70 ዓመት ይሆናል። ከ1958 ላይ 70 ሲቀነስ ደግሞ ፊታውራሪ በ1888 ዓ.ም የተወለዱ መሆናቸውን እንገነዘባለን። ይህም የአድዋ ጦርነት የድል ዓመት ነው። ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦች ነፃነት ምልክትና ተምሳሌት ነች። ይህ ጊዜም የሀገር አንድነት በደም የተዋሀደበት፣ የአዲሲቷ /የዘመናዊቷ/ ኢትዮጵያ ህዝቦች ህብረትና የአዲሱ ትውልድ መነሳት በተለየ አይበገሬነት የለመለመበት ዘመን ነው። ፊታውራሪ መሸሻም ዘመኑን ለማሰብ ፅናትንና ለዓላማ መቆምን ለማሳየት በሚል መሞትን ወደዋል።
የጉዱ ካሳ ዕድሜና የሀዲስ ትንቢት
ጉዱ ካሳ በሰብለወንጌልና ፊታውራሪ መሸሻ ዕድሜ መካከለኛ ዘመን ላይ 40 ዓመቱ እንደሆነ ይታወቃል። መጽሐፉ ከታተመበት 1958 ዓ.ም ላይ 40 ሲቀነስም ስሌቱ 1918 ዓ.ም. ላይ ያደርሰናል። ይህ ጊዜም ካሳ የተወለደበት ዓመት ሆኖ እናገኘዋለን። ዘመኑ ደግሞ የንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ አስተዳደር እየተዳከመና አብዮተኛው አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን እየገነኑ የታዩበት ጊዜ ነው። ስለሆነም ካሳ የለውጥ አቀንቃኝ ሆኖ እንዲሳል ተደርጓል።
የሰብለወንጌል ዕድሜና የሀዲስ ትንቢት
ሰብለወንጌል ሃያ አምስት ዓመቷ ነው። ከ1958 ላይ 25 ሲቀነስ ዘመኑን 1933 ዓ.ም ላይ ያደርሰዋል። ይህ ጊዜ ሰብለ ወንጌል የተወለደችበት ዓመት ነው። ይህ ዓመት ደግሞ ኢትዮጵያ በልጆቿ ተጋድሎ ከኢጣሊያ አምስት ዓመት ወረራ በኋላ ነፃ የወጣችበት ወቅት ነው።
ከሰብለወንጌል ጋር የተያያዙ ህልምና ምሳሌዎች
ሰብለወንጌል እስከ ስድስት ዓመቷ ድረስ ከሰፈሩና ከአካባቢው ልጆች ጋር ትጫወት ነበር። አንድ ቀን ግን ጭቃ ላይ ወድቃ ወደ ቤቷ እያለቀሰች ስትመጣ ፊታውራሪ በማየታቸው ተናደዱ። አጋጣሚውንም እንደመደፈር ቆጠሩት። ከዚህ በኋላም ሁኔታዎች በድንገት ተለዋወጡ። እሷም ከእኩያ ጓደኞቿ ተለይታ የክብር እስረኛ ልትሆን ተገደደች።
በ1933 ዓ.ም ላይ 5 ዓመታትን ስንደምር 1938 ዓ.ም ላይ ያደርሰናል። ከዚህ በኋላ ያለው የአንድ ዓመት ጊዜም የነጻነት ማግስት ሆኖ ተመዝግቧል። በዚህ ወቅት ደግሞ የአርበኞች የድል ብስራት አልተረሳም። ለውለታቸው የተለየ ክብርና ሞገስ ነበራቸው። ከቆይታ በኋላ ግን ባንዳዎችና ስደተኞች የበላይነቱን በመያዛቸው አርበኞች በተለያዩ ሰበቦች ወህኒ መውረድ ጀመሩ። እንደእነ በላይ ዘለቀና ሌሎችም ለስቅላት ተዳረጉ።
ይህኔ በሰብለወንጌል የተሰየመችው ሀገር የልጆቿ መሆኗ ተረት ሆኖ የባንዳዎች መናሃሪያ ሆና ታየች። ልክ እንደሰብለወንጌል ሀገሪቱ የቁም እስረኛ ልትሆን ተገደደች። ደራሲው ሀዲስም በመጽሐፋቸው ላይ ይህን ቁጭታቸውን በሰብለወንጌል በህፃንነት የክብር እስረኛነት አስታከው ስርዓቱን እንዳሻቸው ይሸነቁጡታል።
ሀዲስ በመጽሐፋቸው ሰብለወንጌልን ለፊታውራሪ ታፈረ ድንበሩ ለመዳር ለበአለ ገና ጊዜ ተቆርጦላት እንደነበር ይጠቅሳሉ። በዚሁ የታህሳስ ወር ላይም በጠና ታማ ላትሞት መትረፏን ያወሳሉ። ይህ ጊዜ ደግሞ በገሀዱ እውነታ ሲቃኝ የ1953 ዓ.ም. የታህሳስ ግርግርን ያመላክታል። እነ ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ ኢትዮጵያን ለልጆቿ ለማድረግ መፈንቅለ መንግሥት በመሞከራቸው ስርዓቱ ለጥቂት የተረፈበት እንደሆነም ያስታውሳል። ይህንን ሁኔታ ለአንባቢያን ለማመላከት ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ቁጭታቸውንና የተስፋቸውን መምከን በእልህና በሲቃ አያስቃኙ ሰብለወንጌል «ታማ ትሞታለች» ተብሎ ሲጠበቅ በህይወት ስለመትረፏ ይነግሩናል።
የሰብለወንጌል ህልም
ሰብለወንጌል በህልሟ ከገደል ወገብ ላይ ሆና ለመውጣት ስትታገልና በመጨረሻ ከአፋፉ ላይ የበቀለ ሳር ነገር ይዛ ስታመልጥ ማየቷን ለበዛብህ ትነግረዋለች። ገደል ዘመንን፣ ዕድሜን ይገልጻል። ሳር እርጥበትን፣ ተስፋን የመከራ ዘመን ማብቂያን ያመላክታል። ሰብለወንጌል አብዛኛውን የገደሉን ክፍል ወጥታዋለች። ሆኖም ግን ወደ ኋላ እየተንሸራተተች ትመለስና እንደገና ከገደሉ ጫፍ ላይ የበቀለ ሳር ይዛ ለመውጣት ስትሞክር ትነቃለች።
ሰብለ አብዛኛውን ገደል መውጣቷና ሳር መጨበጧ ካለፈው የመከራ ዘመን ርዝመት አንፃር ሲመዛዘን የነፃነት ዘመን ቅርብ መሆኑን ሀዲስ ይነግሩናል። የገደሉ ርዝማኔ ምንያህል አስፈሪና እልህ አስጨራሽ እንደሆነም በሰብለወንጌል የህልም ጭንቀት አሳበው ይጠቅሱታል።
የሰብለ ወንጌል ነፍሰጡርነት
ሰብለ «በዛብህ አልደፈረኝም ነፍሰጡርም አይደለሁም ቢፈልጉ በባልቴት ያሳዩኝ፣ እኔ ግን እሱን እወደዋለሁ’’ ስትል መልስ ሰጥታለች። ሰብለወንጌል የኢትዮጵያ ተምሳሌት እንደመሆኗ ደራሲው ሀገር በልጆቿ ለውጥ ማርገዟን፤ ይህም በእትብት፣ በደምና አጥንት ጥልቅ ፍቅር የታሰረ መሆኑን ለማመላከት « እኔ እወደዋለሁ» ስትል በበዛብህ በኩል በግልፅ ማረጋገጧን ያመላክታሉ።
የደራሲ ሀዲስ አለማየሁን የፍቅር እስከመቃብር ትንቢት አስመልክቶ ጥናት አቅራቢው መምህር ገብረሀና ዘለቀ ያደረጉት ዳሰሳ በዚህ አያበቃም። በሚቀጥለው ሳምንት በመጽሐፉ ላይ የተካተቱ ቀሪ ሀሳቦችን ይዘን እንመለሳለን።
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 24/2011