የማረሚያ ቤት የተሀድሶ ልማት ሥራዎች ውጤት እያስገኙ ነው

አዲስ አበባ፡- በማረሚያ ቤት እየተከናወኑ የሚገኙ የተሃድሶ ልማት ዘርፍ ሥራዎች ውጤት እያስገኙ መሆናቸውን የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገረመው አያሌው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፣ ኮሚሽኑ በስሩ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች በተሃድሶ ልማት ዘርፍ እያከናወናቸው በሚገኙ የትምህርትና ሥልጠና ሥራዎች የታራሚዎችን አመለካከት መቀየርና የሙያ ባለቤት ማድረግ ችለዋል፡፡

ታራሚዎች የቀለም ትምህርትን መሠረት ባደረገ መልኩ እያገኙ ባለው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና የእንጨት፣ የብረታ ብረት፣ የሽመና፣ የኤሌክትሪክ፣ የቧንቧ፣ የጨርቃ ጨርቅና የሌዘር ሙያን እየተካኑ እንደሚገኙ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ሥልጠናው ታራሚዎች ሰርቼ መለወጥ እችላለው የሚለውን አመለካከት እንዲላበሱ ከማስቻሉም ባለፈ ከማረሚያ ቤት በሚወጡበት ጊዜ በሠለጠኑበት ሙያ ተሠማርተው ራሳቸውን በኢኮኖሚ እንዲችሉና፣ ቤተሰባቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ያስችላቸዋል ያሉት አቶ ገረመው፤ ለውጡ በተግባርም እየታየ ይገኛል ብለዋል፡፡

ሁሉም ታራሚዎች የቴክኒክና ሙያ ፍላጎት ላይኖራቸው እንደሚችል ያነሱት የቴክኒክና ሙያ ፍላጎቱ ለሌላቸውና ከአርሶና አርብቶ አደር አካባቢ ለመጡ ታራሚዎችም በእንስሳት እርባታ በከተማ ግብርና፣ በአነስተኛ መሬት ጓሮ አትክልትን እንዴት ማልማት እንደሚቻልና በሰብል ልማት ላይ በተግባር የታገዘ ሥልጠና እየተሰጣቸው እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

በቴክኒክ ሙያና በግብርና ሙያ ዘርፍ የታራሚዎች የሥራ ውጤቶች በማረሚያ ቤቶች አካባቢ ያለው ማኅበረሰብ እንዲጠቀም በመሸጫ ሱቆች አማካኝነት ለሽያጭ እንደሚቀርብና ታራሚዎቹም ተጠቃሚ እንደሆኑ የጠቆሙት አቶ ገረመው፤ ታራሚዎች በማኅበራት ተደራጅተው ከሚያገኙት ገቢ 80 መቶ እንዲቆጥቡ እንደሚደረግም አመልክተዋል፡፡

ቀሪውን 20 መቶ ደግሞ የማረሚያ ቤቱን አሠራር ተከትለው ለራሳቸው እንዲጠቀሙና ቤተሰባቸውንም በማረሚያ ቤት ሆነው ማገዝ የሚችሉበት ሁኔታ እንደተመቻቸላቸውም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ታራሚዎች የንባብ ባህላቸውን እንዲያሳድጉና በመጻሕፍትም እንዲታረሙ ለማስቻል ቤተ መጻሕፍትን በአግባቡ የማደራጀት ሥራዎች እተሠሩ እንዳሉ የጠቆሙት አቶ ገረመው፤ ከፍተኛ የትምርት ተቋማትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ሥራውን በመደገፍ ረገድ ከኮሚሽኑ ጋር በትብብር እየሠሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ኮሚሽኑ ከሁሉም ማረሚያ ቤቶች 47 ተማሪዎችን ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ማስቀመጡን ያስታወሱት አቶ ገረመው፣ ከአንዳንድ ትምህርት ቤቶች በተሻለ ሁኔታ ብዙም የተመቻቸ ሁኔታ በሌለበት ኮሚሽኑ ካስፈተናቸው ተማሪዎች መካከል 4ቱን ወደ ዩኒቨርሲቲ ማሳለፍ መቻሉንና ብዙዎቹ ማካካሻ ትምህርትና ድጋሚ ፈተና እንዲወስዱ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡

ይህም አንዱ የተሃድሶ ልማት ዘርፍ የትምህርትና ሥልጠናው ውጤታማነት ማሳያ ነውም ብለዋል፡፡ አያይዘውም፣ ኮሚሽኑ በዘርፉ ከተለያዩ አካላት በጎ ግብረ ምላሽ እየተሰጠው እንደሚገኝም ኃላፊው አንስተዋል፡፡

ኮሚሽኑ በስሩ በሚገኙ የድሬዳዋ ማረሚያና ማረፊያ ማዕከል፣ ሸዋሮቢት ማረሚያ ማዕከል፣ ዝዋይ ማረሚያ ማዕከል፣ ቃሊቲ ማረሚያ ማዕከልና ቃሊቲ የሴቶች ማረሚያና ማረፊያ ማዕከላት ታራሚዎች የእርም ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸውና፣ ለሀገራቸው ጠቃሚ ዜጋ መሆን የሚያስችላቸውን የተሃድሶ ልማት ሥራዎችን አጠናክሮ እንደደሚቀጥል ኃላፊው አመልክተዋል፡፡

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

አዲስ ዘመን  ጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You