በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙና ከኢትዮዸያ ጋር በመልካ ምድራዊ አቀማመጥና በረጂም ጊዜ ታሪክ የተሳሰሩ ጎረቤት አገሮች ማለትም ኬንያ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ኤርትራ ለአገሪቱ ሰላም፣ ዲሞክራሲና ዘላቂ ልማት መረጋገጥ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳላቸው የማይካድ እውነታ ነው፡፡ኢትዮጵያ ከነዚህ አገራት ጋር ተመሳሳይ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክና የተፈጥሮ ሀብት የሚጋሩ ህዝቦች ያሏት መሆኑ ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ ቀጥተኛ የሆነ ትስስር እንዲኖራት አድርጓል፡፡
በመሆኑም በኢትዮጵያ በጠረፍ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ከመሀል አገር ከሚኖረው ማህበረሰብ ይልቅ በባህል፣ በእምነት፣ በቋንቋ እና በተፈጥሮ ሀብት የተሳሰሩ በመሆኑ፤ ከፍተኛ የንግድ ግንኙነት ያካሂዳሉ። መንግስትም ይሄን ታሳቢ በማድረግ ከነዚህ ጎረቤት አገሮች ጋር የድንበር ንግድ ስምምነት በማድረግ እየሰራ ቢሆንም የንግድ ስምምነቱ ተፈጻሚ ባለመሆኑ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር በመምከር ስምምነቱን ለማደስ እየሰራች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ ከአጎራባች አገሮች ጋር በአዲስ መልክ ግንኙነቷን ማጠናከሯ በቀጣናው የበለጠ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል ሚና እንዳለው በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ ገልጸው፤ ከአጎራባች አገሮች ጋር የጠረፍ ንግድን አጠናክሮ ለመቀጠል ያስፈለገበት ምክንያት በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦች የሚያስፈ ልጋቸውን የእለት ተዕለት የምግብ አቅርቦት፣ ሸቀጥ እንዲሁም ሌሎች እቃዎችንና አገልግሎቶችን በአቅራቢያቸው ማግኝት እንዲችሉ ነው ብለዋል።
ከመሀል አገር ወደ ጠረፍ የተለያዩ ምርቶችን ለማቅረብ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅና መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት የሚከብድ በመሆኑ ምርቶችን ወደ ድንበር አካባቢ ለሚገኙ ህዝቦች በበቂ ሁኔታና በታሰበው ጊዜ ለማድረስ አዳጋች መሆኑን አቶ ወንድሙ ይናገራሉ። በመሆኑም አካባቢን መሰረት ያደረገ መሰረታዊ ችግሩን የሚፈታ የጠረፍ ንግድ ስምምነት በአገሮች መካከል መፍጠር አስፈላጊ ነው፤ የንግድ ስምምነቱ አንድ አገር በጠረፍ አካባቢ የሚገኙ ዜጎቿን የግብይትና የምርት አቅርቦት ችግር ለመፍታት ከሌሎች አጎራባች አገሮች ጋር የስምምነት ፊርማ የሚያደርግ እንደሆነ ገልጸዋል።
በዚህም በጠረፍ አካባቢ የሚኖሩ የሁለቱም አገር ህዝቦች በተወሰነ ኪሎ ሜትር ድንበር ተሻግሮ ወደ ጎረቤት አገር በመግባት ምርትና አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ ይፈጥራል፤ በድንበር አካባቢ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት የማይገኝበት ሁኔታ ሲመቻች ደግሞ ሀብረተሰቡ በሁለቱም አገራት ገንዘቦች መገበያየት የሚችልበት ሁኔታም ይፈጠራል እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ።
ስለዚህ ኢትዮጵያ በጠረፍ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎቿን ተጠቃሚ ለማድረግ ከሱማሊያ ሪፐብሊክ፣ ከሱዳን፣ ከኬኒያ፣ ከኤርትራ፣ ከጂቡቲ በአጠቃላይ ከሚያዋስኗት አገሮች ጋራ የድንበር ንግድ ስምምነት አድርጋለች፤ በተለይ ከሱማሊያ ሪፐብሊክ፣ ከሱዳን፣ ከኬኒያና ከጂቡቲ ጋር የነበራት የጠረፍ ንግድ ግንኙነት በስምምነት የታሰረ በመሆኑ በአካባቢዎቹ ላይ ምን አይነት የምርት እጥረት አለ፤ የሚፈለገው ምርትና አገልግሎት ምንድን ነው፤ ምርቶቹና አገልግሎቶቹ በማን መሟላት አለባቸው የሚሉት ነገሮች ተወስኖ በዛ አካባቢ ምርትና አገልግሎት እንዲያቀርቡ ተፈቅዶላቸው የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች መኖራቸውን ይናገራሉ።
በስምምነቱ መሰረት የግብይት መጠኑ የሚወሰን ሲሆን፤ በጠረፍ አካባቢ የሚንቀሳቀስ የገንዘብ መጠን ተወስኖ ግብይት ይፈጸማል። ነገር ግን ከላይ በተጠቀሱ ጎረቤት አገሮች በኩል ላልተወሰነ ጊዜ ያደረጉትን ስምምነት ተፈጻሚ ባለማድረጋቸው ወደ ተፈጻሚነት እንዲመጣ፣ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረው እና ስምምነቱ እንደገና እንዲሻሻል የማድረግ ስራዎች ተጀምረዋል ብለዋል።
እንደ አቶ ወንድሙ ገለጻ ስምምነቱን ለማደስ ከነዚህ አገራት የተውጣጡ የድንበር የልማት ኮሚሽን እንዳለ ጠቁመው፤ ኮሚሽኑ በየስድስት ወሩ እየተገናኘ የድንበር ንግዱን አፈጻጸም ይገመግማል፣ ችግሮቹን ለይቶ እርምጃ እንዲወሰድና ውሎች እንዲሻሻሉ ያደርጋል ብለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የጋራ የድንበር ኮሚሽን ኮሚቴ እንዳለ አቶ ወንድሙ ገልጸው፤ ኮሚቴው ከሁለቱም አገሮች ከቀበሌ፣ ከወረዳ ከዞን እና ከክልል የተውጣጣ መሆኑንና በድንበር አካባቢ የሚገኘውን ማህበረሰብ የሚያገለግሉ የመንግስት አካላት የድንበር ንግዱን የሂደት ሪፖርት እንደሚገመግሙና የአፈጻጸም ሪፖርት ለዋናው የልማት ድንበር ኮሚሽን ያቀርባሉ፤ ኮሚሽኑ ይህን ሪፖርት መሰረት በማድረግ በየጊዜው መሻሻል ያለባቸው ጉዳይ ካሉ እንዲሻሻሉ ያደርጋል። እንዲሁም ፍላጎትን መሰረት በማድረግ መጨመር ያለባቸው ምርቶች ወይም ሌላ ነገሮች ካለ እንዲጨመር ይደረጋል ብለዋል አቶ ወንድሙ።
በተጨማሪም በጠረፍ አካባቢ አንድ ነጋዴ ሸቀጥ ለማመላለስ የሚፈቀድለት የካፒታል መጠን የተወሰነ ሲሆን፤ ከህዝብ ቁጥሩ አኳያ የተወሰነው ገንዘብ ያነሰ ከሆነ ኮሚሽኑ እንዲጨመር ይደረጋል። እንዲሁም ከቀረጥ ነጻ የሚገቡ ምርቶችን ኮሚሽኑ ከውጭ ያለቀረጥ እንዲገቡ ለነጋዴዎችና ለባለሀብቶች የውጭ ምንዛሬ በማመቻቸት እነዚህን ምርቶች ከውጭ አገር እያመጡ ለጠረፍ አካባቢ ህዝቦች እንዲያደርሱ በማድረግ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚደረግበት አሰራር አለ ብለዋል።
እርሳቸውም አሁን ላይ እነዚህ ጎረቤት አገሮች ስምምነቱን ተፈጻሚ ያላደረጉበትን ምክንያት ሲገልጹ፤ የጎረቤት አገሮች የጠረፍ አካባቢ ማህበረሰብ ፍላጎት ከኛ ማህበረሰብ ፍላጎት ጋር ላይጣጣም ይችላል። ስለዚህ የነዚህ አገሮች ማህበረሰብ የራሳቸውን ፍላጎት ካሟሉ ስምምነቱን አንጠቀምም ካሉ ማቆም ይችላሉ።
እንዲሁም እነዚህ አገሮች በድንበር አካባቢ ላሉ ህዝባቸው በኢትዮጵያ በኩል የሚያገኙትን ሸቀጥና አገልግሎት በአንድም በሌላ መንገድ ካገኙና “ፍላጎታችንን አሟልተናል በኢትዮጵያ በኩል የምንፈልገው የምርት አቅርቦትና አገልግሎት የለም” ካሉ ስምምነቱ ለእነርሱ ምንም ስለሆነ፣ በፍላጎት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ስምምነቱን ማቆም ይችላሉ። ሊገደዱም አይችሉም። ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ የጠረፍ ንግዱ የአንድ ወገን ስምምነት ይሆናል ማለት ነው።
አቶ ወንድሙ ኢትዮጵያ በድንበር አካባቢ የሚኖሩ የዜጓቿን ጥቅም ታሳቢ በማድረግ ስምምነቱን ለማደስ ፍላጎት ማሳየት ስላለባት በኛ በኩል ገፍተን ሄደን የጎረቤት አገሮችን ፍላጎት እንደገና በማጥናት መለየት አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም በጠረፍ አካባቢ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመግታት፣ ህገወጥ ንግድ እንዳይኖር ለማድረግ፣ ምርቶቻችን ያለአግባብ በጠረፍ አካባቢ እንዳይወጡ በመከላከል ህጋዊ የንግድ ሂደት እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል።
ስለዚህ አሁን ላይ የድንበር ልማት ኮሚሽኑ በተናጠል ከእያንዳንዱ ጎረቤት አገራት ጋር ምክክር ማድረግ መጀመሩን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ በኩል የድንበር ንግድ ስምምነቱን ለማደስና ተፈጻሚ ለማድረግ ለጎረቤት አገሮች ጥያቄ አቅርባለች። የጎረቤት አገሮችን ምላሽ መሰረት በማድረግ ስምምነቱን ህጋዊ የማድረግ ስራ ይሰራል ብለዋል ዳይሬክተሩ።
አቶ ወንድሙ ኮሚሽኑም በውይይቱ ስምምነቱን የመከለስ፣ ዳግም ወደ ስራ የማስገባት፣ በእነርሱ በኩል ስምምነቱ የተቀዛቀዘበትን ምክንያት መጠየቅ፣ አሁን ላይ ፍላጎታቸው ምን እንደሆን የመለየት ስራ እንደሚሰራ ጠቁመው፤ በድንበር አካባቢ አንዳንድ ሸቀጦች በፍላጎት መሞላት ምክንያት፣ በሌላ ሸቀጥ በመተካት እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ውል ውስጥ የነበሩ ከውል የሚወጡበትና በሌላ አዳዲስ ሸቀጦች የሚተኩበት ሁኔታ እንደሚኖር ጠቁመዋል።
እንዲሁም ጠረፍ አካባቢ የማህበረሰቡ የምርትና የአገልግሎት ፍላጎት በጣም ከጨመረ ነጋዴ ሊጨምር ይችላል። በዚህ አካባቢ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴው እንዳይስፋፋ በነጋዴው የሚንቀሳቀስ የገንዘብ መጠን ጥናት በማድረግ እንደ አስፈላጊነቱ ከፍና ዝቅ ሊል እንደሚችል ተናግረዋል።
የጉምሩክ ኮሚሽኑ ስራ ህገወጥ የሸቀጥ ዝውውር እንዳይኖር ቁጥጥር የሚያደርግና ህጋዊ የንግድ ዝውውር እንዲኖር ለማበረታታት መሟላት ያለባቸውን መሰረታዊ ነገሮችን የሚያመቻች ሲሆን፤ እነዚህ ሁለት ተግባራቶች ለጉምሩክ ኮሚሽኑ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው ያሉት በጉምሩክ ኮሚሽን የጉምሩክ ህግ ተገዥነት ዘርፍ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ ባሳ፤ በጎረቤት አገራትና በአገራችን መካከል ያለው የንግድ እንቅስቃሴ የተሳለጠ እንዲሆን የተለያዩ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ አሸናፊ ኮሚሽኑ የጠረፍ ንግዱ የተሳለጠ እንዲሆን እቃዎች ሲወጡና ሲገቡ እንዳይንገላቱና መንገድ ላይ እንዳይቆዩ በማድረግ ለተጨማሪ ወጪ፣ ለጊዜ ብክነት፣ እና ለምርት ጥራት መጓደል እንዳይጋለጡ ኮሚሽኑ አሰራሩን ዘመናዊ እያደረገ ይገኛል ብለዋል። ለአብነትም የባለፈው አመት የአገሪቱን የቢዝነስ አመቺነት የአፈጻጸም ሪፖርትን ብንመለከት ከ159 አገሮች 159ኛ ደረጃ ላይ በመሆን ይሄን ለማሻሻል ኮሚሽኑ በርካታ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል ብለዋል።
አቶ አሸናፊ ኮሚሽኑ ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል የጉምሩክ ስነስርዓትን ለመፈጸም አላስፈላጊነታቸው የጎላ ሰነዶችን ቁጥር መቀነስ እና በስጋት አስተዳደር (በሪስክ ማኔጅመንት) አሰራር ላይ ያሉ የስጋት አጣጣል መስፈርቶች እንዲቀንሱ ተደርጓል ብለዋል። እንዲሁም በሙከራ ላይ ያለውና በሚቀጥለው አመት ይተገበራል ተብሎ የሚታሰበው ለባለ ድርሻ አካላት ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ቦታ ለመስጠት የሚያስችል ሲንግል ዊንዶው የሚባለውን ፕሮጀክት ለመተግበር በሂደት ላይ ነው። በአጠቃላይ ረጅም ሰንሰለትና አላስፈላጊ ቢሮክራሲዎችን የማሳጠርና የማስወገድ ተግባራት እየተከናወነ ሲሆን፤ ይሄም ወጪና ገቢ እቃዎች በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ለማድረግ ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
እርሳቸውም እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ በድንበር ንግድ ላይ ህገወጥ የሆኑ እንቅስቃሴዎች እንዳይኖር አስፈላጊውን ቁጥጥር የሚያደርግ ሲሆን፤ በአጠቃላይ የጉምሩክ ስነ ስርዓትን ሳያሟሉ የሚገቡና የሚወጡ እቃዎች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር በማድረግ በጠረፍ አካባቢ የሚካሄዱ ንግዶች ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ተግቶ እየሰራ ነው ብለዋል።
እንዲሁም የጋራ የድንበር አስተዳደር ኮሚሽን የሚያደርጓቸውን የውይይት ሰነዶች ለጉምሩክ ኮሚሽኑ የሚላክ መሆኑን አቶ አሸናፊ ገልጸው፤ ሰነዱ በተጨባጭ መሬት ላይ ያለው ነገር ምንድን ነው የሚለውን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ፤ በጋራ ኮሚሽኑ ምን አይነት ውሳኔዎች እንደተላለፉ የሚገልጽ እና ምን ምን ክፍተቶችና ጠንካራ ጎኖች እንዳሉ የሚያሳይ በመሆኑ፤ ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ጥረት በማድረግ የታዩትን ክፍተቶች በማሟላት ሰላማዊና ደህንነቱ የተጠበቀ የጠረፍ ንግድ እንዲኖር የሚያደርግ አሰራር መኖሩን ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ የኮንትሮባንድ ንግድ በአንድ አገር ላይ በዋናነት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያው ችግርን ከማስከተል ባሻገር የስራ አጥ ቁጥርን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል። ምክንያቱም መንግስት ማግኘት ያለበትን የግብር መጠን ማግኘት ስለማይችል የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ አቅም አይኖረውም። እንዲሁም ደህንነታቸው ያልተረጋገጡ ምርቶች በህገወጥ መንገድ በጠረፍ በኩል ስለሚገቡ የማህበረሰቡን ለጤና ችግር የሚዳርግ ከመሆኑ ባሻገር የኮንትሮባንድ ንግድ በአንድ አገር የተረጋጋ የንግድ ሂደት እንዳይኖር በማድረግ የፖለቲካ አለመረጋጋት ይፈጥራል ብለዋል አቶ አሸናፊ።
አቶ አሸናፊ በጠረፍ በኩል ሸቀጦች፣ መድሀኒቶች፣ የመዋቢያ ቁሳቁሶች፣ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችና የጦር መሳሪያ እንደሚገቡ ጠቁመው፤ እነዚህ በህገወጥ የሚገቡ ምርቶችና መሳሪያዎች በአንድም በሌላ መልኩ በማህበረሰቡ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳላቸው አሳስበዋል። ስለዚህ ኮሚሽኑ የኮንትሮባንድ እቃዎች ወደ አገር እንዳይገቡ ጠንክሮ እየሰራ እንደሆነ ኃላፊው ገልጸው፤ ማህበረሰቡ ከኮሚሽኑ ጎን በመሆን ይህን ህገወጥ ተግባር በመላ አገሪቱ በመታገል የተረጋጋ ሰላምና ቀጣይነት እድገት ያላት አገር መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2011
ሶሎሞን በየነ