‹‹ሞኝና ወረቀት የያዘውን አይለቅም!››

ሰሞኑን ከትምህርት ማስረጃዎች ጋር በተያያዘ ምክንያት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እና ትራንስክሪፕት አስፈልጎኝ የቆዩ ሰነዶቼን እያገላበጥኩ ነበር፡፡ በዚያው እግረ መንገድ የሁለተኛ ደረጃ እና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሰነዶቼን እያየሁ ነበር። በትዝታ ወደ ኋላ ብዙ ሄድኩ፡፡ የትዝታ ጥሩ ነገሩ ግን በትዝታው መመሰጥ ብቻ ሳይሆን በሆነ ወቅት ላይ ምን ይደረግ እንደነበር ማሳየቱ ነው፡፡

በተለይም በአንደኛ ደረጃ የትምህርት ማስረጃዎቼ ብዙ ነገር አየሁ፡፡ በግሌ ከትንሽ ወረቀት ጀምሮ መረጃዎችን የማስቀመጥ ልማድ አለኝ፡፡ ይህ የጠቀመኝ ነገር ‹‹ያኔ እንዲህ ነበር?›› እያልኩ እንደ ታሪክ መጥቀሙ ነው፡፡ እንደ ስነ ዜጋና ስነ ምግባር (ሲቪክስ) አይነት ትምህርቶች ላይ ወቅታዊ ጉዳዮችን እንጠየቅ ነበር። ለምሳሌ ‹‹የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማን ይባላል?›› የሚለው ጥያቄ ላይ ‹‹ስዩም መስፍን ብዬ መልሼ›› ያገኘሁትን ‹‹ራይት›› እንደ አዲስ ነው የኮራሁበት። ለአንድ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ የሀገሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማወቅ ብርቅ ሆኖ ሳይሆን ቢያንስ ግን በዚያን ጊዜ ‹‹እንዲህ እንጠየቅ ነበር?›› የሚለውን የፈተና ሁኔታ እንድገመግም አድርጎኛል፡፡ በእንዲህ አይነት ሁኔታዎች ከዓመታት በፊት የነበሩ የሥርዓተ ትምህርት ሁኔታዎችን፣ የትምህርትና የፈተና አሰጣጥ ሁኔታዎችን፣ የወቅቱን አጀንዳዎች እናይበታለን ማለት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የመማሪያ መጻሕፍቱ ተቀምጠው ቢሆን ኖሮ የበለጠ ጥሩ ነበር ማለት ነው፡፡

ዋናው የትዝብቴ ጉዳይ ግን እነዚህ ሰነዶች በወረቀት ስለሆኑ ነው ያገኘኋቸውና በዲጂታል ቢሆን ምን ይሆን ነበር? የሚለው ነው፡፡

የብዙዎቻችሁ መልስ የሚሆነው ዲጂታል ከወረቀት በላይ ቀልጣፋና አስተማማኝ መሆኑን ነው፡፡ ለረጅም ዘመን የመቆየት ዕድል ያለው፣ ለአያያዝም ሆነ ከአንድ አማራጭ ወደ ሌላ አማራጭ ለማስተላለፍ ምቹ መሆኑን ነው፡፡ ከወረቀት አንፃር ሲተያይ፤ ወረቀት ኋላቀር፣ ዲጂታል ደግሞ ዘመናዊ ናቸው፡፡

አሁን ግን ሳስበው ‹‹ሞኝና ወረቀት የያዘውን አይለቅም›› የተባለው ለአበው ዘመን ብቻ አይደለም፤ ለዚህኛው ለዲጂታሉ ዘመንም የሚሆን ይመስለኛል። ምክንያቱም ከዲጂታል መረጃዎቼ በላይ የወረቀት መረጃዎቼን በብዛት ስላገኘኋቸው ነው፡፡

የእጅ ስልኬ ላይ ብዙ መረጃዎችን አስቀምጣለሁ። በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ብዙ ነገሮችን አያለሁ። በማይበት ጊዜ የሚያስቁ ነገሮች ሳገኝ፣ ታሪካዊነት ያላቸው መረጃዎች ሳገኝ፣ የሆነ ጊዜ ላይ ያስፈልጉኛል ብዬ የማስባቸውን ማብራሪያዎች ሳገኝ ‹‹ሴቭ›› አደርጋለሁ፡፡ በተንቀሳቀስኩባቸው አጋጣሚዎች አስገራሚ ነገሮችን ሳስተውል፣ የሚያምር ተፈጥሮ ሳገኝ ፎቶ አነሳለሁ፡፡ በአጠቃላይ በእጅ ስልኬ ላይ ዘመናዊ በሆነ መንገድ ብዙ መረጃዎችን አስቀምጣለሁ፡፡

ችግሩ ታዲያ የሆነ ወቅት በሆነ አጋጣሚ አንዳንዶቹን አጠፋቸዋለሁ፡፡ ለምሳሌ የሆነ ፋይል ስፈልግ ‹‹ስክሮል›› እያደረኩ ቶሎ ላላገኘው እችላለሁ። በዚህን ጊዜ ‹‹የማያስፈልገውን ሁሉ ሰብስቤ ሰብስቤ ነው የሚያስቸግረኝ›› የሚል ሀሳብ ይመጣብኝና አያስፈልጉም ያልኳቸውን አጠፋቸዋለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እየነካካሁ ባለሁበት ‹‹ለምን ቦታ ይይዛል?›› በሚል አሁንም አያስፈልጉም ያልኳቸውን አጠፋቸዋለሁ፡፡ ግን የሆነ ጊዜ ላይ ያስፈልጉኛል፡፡

ከወረቀቶቹ ጋር ግን ዕለት በዕለት አልገናኝም። ቦታቸውን ይዘው ይቀመጣሉ፡፡ ከብዙ ጊዜ በኋላ ቢያስፈልገኝ ነው፡፡ ያኔ ደግሞ እንደ ትዝታ ጭምር ይሆኑብኛና በስስት ነው የማያቸው፡፡

ይህንን ስል ግን ወረቀትን ከዲጂታል እያስበለጥኩ አይደለም፡፡ መረጃ አያያዝ እንደ ብልህነታችንና ጉብዝናችን ነው የሚወሰነው፡፡ በወረቀትም ቢሆን ፋይል ስናገላብጥ፣ ወረቀት ሲከመርብን ‹‹የማያስፈልገውን ሁሉ ሰብስቤ ሰብስቤ›› የሚል ሀሳብ ይመጣብንና እየመረጥን መጣል እንጀምራለን። የተጣለው ወረቀት የእሳት እራት ይሆንና ጭራሹንም አመድ ሆኖ ይቀራል፡፡ ሲቀጥል ለአደጋ የመጋለጥ ዕድሉም ሰፊ ነው፤ በቀላሉ ለውሃ እና ለእሳት ተጋላጭ ነው፡፡ ሰፊ ቦታ የመያዝ ዕድሉም የሚታወቅ ነው። የዲጂታል መረጃዎች የእጅ ስልክ ላይ ወይም ‹‹ላፕቶፕ›› ላይ በዝተው ቢያስቸግሩን በ‹‹ሀርድ ዲስክ›› አድርጎ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ ዘመናዊነቱና ቀልጣፋነቱም ይሄው ነው፡፡

ዋናው ጉዳይ ግን ዲጂታል ይሻላል ወይስ ወረቀት? የሚል ክርክር አይደለም፡፡ በሁለቱም በኩል 100% አስተማማኝ አለመሆኑ ነው፡፡ አስተማማኝነቱ ቢያንስ 90 ቢበዛ 99 በመቶ ቢሆን ነው፡፡ ልብ ብላችሁ ከሆነ ባለፈው ዓመት ‹‹ጉግል›› አንድ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር፡፡ ይሄውም የቆዩ እና እየተንቀሳቀሱ ያልሆኑ አካውንቶች ላይ ያሉ የኢሜል መረጃዎች ሊጠፉ ስለሚችሉ ጥንቃቄ አድርጉ የሚል ነበር፡፡ በአጋጣሚ ሳይጠቀምበት የቆየ ሰው ያጠራቀማቸው መረጃዎች ሁሉ ይጠፋሉ ማለት ነው፡፡

አሁንም ባለፈው ዓመት የሜታ ካምፓኒ ፌስቡክ ላይ ችግር ተፈጥሮ ስለነበር እንደዚሁ ይቅርታ ጠይቋል። ስለዚህ የበይነ መረቡ ዓለምም ችግር ሊያጋጥመው ይችላል ማለት ነው፡፡ ልክ በሰዎች ሕይወት ላይ እንደ ኮቪድ-19 አይነት ወረርሽኝ እንደሚከሰተው ሁሉ ሰው ሰራሽ የሆነው የበይነ መረቡ ዓለም ላይ ችግር አይፈጠርም ማለት አይቻልም፡፡

አንዳንድ ወገኖች በአጉል ሰለጠንን አይነት እሳቤ ‹‹በዚህ ዘመን ወረቀት?›› እያሉ ይገረማሉ፡፡ ወረቀት እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባለ ገና ብዙ በሚቀረው ሀገር የዲጂታሉን ዓለም በፈጠሩት ሀገራትም አልቀረም፡፡ የትልልቅ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዜና አንባቢዎች ዛሬም እስኪርቢቶ ይዘው ይታያሉ፡፡ ምናልባት የእስኪርቢቶ ዘመን ትውስታ ስላልወጣላቸው ይሆን?

በነገራችን ላይ የአሁኑ የቴሌግራም ዘመን ትውልድ ቀደም ባለው ዘመን ቴሌግራም የሚባል የመልዕክት መላላኪያ መኖሩን አያውቅ ይሆናል እኮ! በድሮው ጊዜ (ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ) ሰዎች መልዕክት የሚለዋወጡት በቴሌግራም ነበር፡፡ ይህ የድሮው ቴሌግራም ኤሌክትሪካል በሆነ መንገድ የምሥጢር ቁጥር ምልክት በመጠቀም የሚለዋወጡበት ነበር፡፡ እነሆ ከ170 ዓመታት በኋላ በአውሮፓውያኑ 2013 ደግሞ አሁን የምንጠቀምበት ዘመናዊው ቴሌግራም ተጀመረ ማለት ነው፡፡

ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ የድሮ የሆኑ ነገሮች፤ መነሻ ናቸውና ለማስታወስ ዘመናዊ ነገሮች በስማቸው ይሰየሙላቸዋል፡፡ እግረ መንገዳቸውንም ውለታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በሌላ በኩል አሰራሩ ፈጣን እና ምቹ ይሁን እንጂ የሚሰጡት አገልግሎትም ይመሳሰላል። በድሮው ጊዜ የነበረው ቴሌግራም መልዕክት መለዋወጫ ነበር፤ የአሁኑ ቴሌግራምም መልዕክት መለዋወጫ ነው፡፡ ጥራትና መጠኑ እየሰፋ ይሄዳል፡፡

‹‹ሞኝና ወረቀት የያዘውን አይለቅም›› ይባላልና ወረቀትን ጊዜ ያለፈበት ኋላቀር አሰራር አድርጎ ማየት ስህተት ነው፡፡ ለአገልግሎት ምቹነት ድሮ በወረቀት የነበሩ ነገሮችን ወደ ዲጂታላይዝድ አገልግሎት ሲለወጡ ወረቀቱ ባይጣል ጥሩ ነው፡፡ ለእነዚያ ወረቀቶች የሚሆን ቦታ አይጠፋም፡፡ የኢንተርኔቱ ዓለም ችግር ቢያጋጥመው እንኳን እነዚያ ወረቀቶች ምስክር ይሆናሉ፡፡

በአጠቃላይ፤ ብዙ መሥሪያ ቤቶች የዲጂታል አገልግሎት በሚል ስም ወረቀቶችን አውጥተው እየጣሉ ነውና ይህ ነገር ቢታሰብበት!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You