
አቶ መለስ ዜናዊ የፓርላማ አባላቱን ያሳቀ አንድ የተናገሩት ተረት ትዝ አለኝ። አንድ ድሃ ገበሬ ነበር፤ ገበሬው ድሃ ብቻ ሳይሆን ሰነፍ ነበር። ቤቱም ዝናብ ታፈሳለች። የሚያፈሰውን ጣሪያ ከመጠገን ይልቅ በማታፈሰው በኩል ይተኛል።
አንድ ሀብታም ገበሬ ደግሞ ዝናብ እየጣለ በዝናቡ ውስጥ ከብቶችን ያስገባል። አንዱን ሲያስገባው አንዱ ይወጣል። ሀብታሙ ገበሬ በዝናብ እየበሰበሰ ሲሯሯጥ ቤቱ ዝናብ የምታፈሰው ያ ድሃ ገበሬ በከፊል የምታፈሰው ቤቱ ውስጥ ሆኖ በቀዳዳ በኩል ሀብታሙን ገበሬ ያያል። የዚያን ታታሪ ገበሬ በዝናብ መመታት ሲመለከት ‹‹እንኳንም ድሃ ሆንኩ›› ብሎ ስንፍናውንና ድህነቱን በፀጋ ተቀበለ።
ይህን ያስታወሰኝ ሰሞኑን ያስተዋልኳቸው ሁለት ነገሮች ናቸው። ባለፈው ሐሙስ አንድ ጓደኛዬ ከቤት ግዥ ጋር በተያያዘ ምስክር ልሆነው ወደ አንድ የሰነዶች ማረጋገጫ ቢሮ ገባን። ብዙ አይነት ጉዳይ ስላለ ወከባውና ግርግሩ ብዙ ነው። በተለይ የቤት ጉዳይ ደግሞ ጣጣው ብዙ ነው። እዚያ ለመድረስ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፏል። እኔ ግን ለእነዚያ ሰዓታት እንኳን ሰለቸኝ። ስለአሰልችነቱ ስናገር ‹‹ይሄማ በጣም ቀላሉ ነው እኮ! ዋናው ጣጣ አልቋል›› ብሎ ያሳለፋቸውን ውጣ ውረዶች ነገረኝ። እኔም እንደ ቀልድ ‹‹ከዚህ ሁሉ ግን ያለቤት ቢኖሩ ምን ችግር አለው?›› ስል ዙሪያዬን ያሉት ሁሉ ሳቁብኝ።
እንግዲህ አስቡት እሱ ብዙ ውጣ ውረድ አልፎ ቤት የመግዛት ደረጃ ላይ ሲደርስ፤ እኔ ለሰዓታት መታገስ ሰነፍኩ ማለት ነው። ምንም እንኳን በሰዓቱ እንደ ቀልድ ብናገረውም ያንን ሁሉ ትዕግስትና ትጋት ነበረኝ ወይ የሚለው ግን የምሬን ነበር ራሴን እንድጠይቅ ያደረገኝ።
ሌላኛው የታዘብኩት፤ ሰሞኑን በማኅበራዊ ገፆች አንድ የቢዝነስ ዕቅድ ዘመቻ ሲካሄድ ነበር። አንድ ባለሀብት ጥሩ የቢዝነስ ዕቅድ ላላቸው ሰዎች አወዳድሮ የ100 ሺህ ብር ሽልማት እንደሚሰጥ አሳወቀ። ውድድሩ የቢዝነስ ዝርዝር ሀሳባቸው ታይቶ ብዙ ‹‹ላይክ›› ያገኘውን መሸለም ነው። በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች ‹‹ላይክ›› አድርጉልን በማለት የጓደኞቻቸውን ስሞች በአስተያየት መስጫ ሳጥኑ ውስጥ ሲዘረዝሩ (በፌስቡክ ቋንቋ ሜንሽንድ ይባላል) ነበር።
ከዚያ ዘመቻ ውስጥ ያስተዋልኩት ነገር ብዙ ወጣቶች የፋይናንስ ድጋፍ ቢያገኙ የቢዝነስ ሀሳብ ያላቸው መሆኑን ነው። በዚሁ ጉዳይ ላይም ብዙ ሰዎች ሀሳባቸውን ሲሰጡ ነበር። ለካ ብዙ ሰዎች ብዙ ሀሳብ ማመንጨት የሚችሉ ናቸው። ለዚያውም እነዚያ ሀሳቦች ለረጅም ጊዜ ታስቦባቸው፣ ብዙ ጥናትና ምርምር ተደርጎባቸው የታሰቡ አይደሉም። ድንገት ዕድሉ ሲገኝ የውድድሩ ተሳታፊ ለመሆን የጻፏቸው ናቸው። በእርግጥ አንዳንዶቹ ምናልባት ዕድል በተገኘ ጊዜ በሚል ጽፈው ያስቀመጧቸው ሊሆኑም ይችላሉ። ወይም ጀምረዋቸው በአቅም ማጣት ምክንያት የተቋረጡ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ‹‹በአቅም ማጣት የተቋረጠብኝ ነው›› ብለው የገለጹም አሉ።
እዚህ ላይ ታዲያ በትልቁ የታዘብኩት ነገር ቢኖር ብዙ ስንፍናውን የተላመደ ሰው አለ። ስንፍናውን እንደ ምቾት በመቁጠር የሚያሾፍ ብዙ ሰው አለ። ለስንፍናው መሸፈኛ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ እንደ መሰናክል ያስቀምጣል። ጎበዝ የሆኑ ሰዎች አበርቱን ብለው ለጀመሩት ነገር ተስፋ አስቆራጭ የሆኑ አስተያየቶችን ይሰጣል። ‹‹በ100 ሺህ ብር ምንም የሚሠራ ሥራ የለም አርፋችሁ ተቀመጡ!›› አይነት ሀሳብ የሚሰጡ አሉ። ‹‹ዶሮ ሸጬ፣ ከሁለት ብር ተነስቼ…›› እያሉ መነሻቸውን የሚናገሩ ብዙ ባለሀብቶች ሰምተናል። ምንም እንኳን ያኔ የነበረው እና ዛሬ ብዙ ልዩነት እንዳለው ቢታወቅም፤ ቢያንስ ግን 100 ሺህ ብር ከድሮው 2 ብር ያንሳል? ንግድ ሲባል የግድ ከትልቅ ነገር መጀመር አለበት? ብዙዎቻችን የምንሸወደው በዚህ አመለካከት ውስጥ መሆናችን ነው።
እኔ ከዚያ ዘመቻ ውስጥ የተረዳሁት ነገር የብዙዎቻችን ችግር የገንዘብ ብቻ ሳይሆን የቢዝነስ ሀሳብ መሆኑን ነው። ራሴን የታዘብኩበት ነው። ለካ ገንዘቡ ቢገኝም ጥሩ የቢዝነስ ሀሳብ ከሌለ ዋጋ የለውም! ብዙዎች የሚከስሩትም በዚህ ምክንያት መሆን አለበት። ይህን ያህል ብር ባገኝ ምንድነው የማደርግበት? የሚለውን ማሰብ ብልህነት ነው። የብዙዎቻችን ችግር ግን ከገንዘቡ በላይ ሀሳቡ ነው። ዛሬ ዓለምን እያሽከረከሩ ያሉ ትልልቅ ካምፓኒዎችና የቴክኖሎጂ ውጤቶች መጀመሪያ በሀሳብ የተጀመሩ ናቸው።
የድህነት አደገኛው ምክንያት ስንፍናን እንደ ምቾት ማየት ነው። ልክ እንደ ሰነፉ ገበሬ ዝናብ ከሚመታኝ ቢርበኝ ይሻለኛል እንደማለት ነው። ለራሱም፣ ለቤተሰብም፣ ለሀገርም ሸክም ይሆናል ማለት ነው። ልክ እንደ ግዑዝ አካል እሱ ሳይንቀሳቀስ መኖርና መብላት ነው የሚፈልግ፤ ይሄ ደግሞ ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ውጭ ሆነ ማለት ነው። ስንፍና በሃይማኖትም፣ በሳይንስም፣ በማኅበራዊ ሕይወትም የተወገዘ ነው። ብዙዎቻችን ግን ይህን ሁሉ ጥሰን ሰነፎች ነን። የአንዳንዶች ደግሞ ይባስ ብሎ ሰነፍ መሆን ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ሰነፍ ለማድረግ ተግተው የሚሠሩ መሆናቸው ነው።
በእርግጥ አንድን ነገር ለመከወን በሀገራችን አሠራር ውስጥ ብዙ አሰልቺ ውጣ ውረድ አለ። ችግሩ ግን ያ አሰልቺ ውጣ ውረድ የመጣው ከስንፍናችን መሆኑ ነው። ሁላችንም ንቁ፣ ታታሪና ኃላፊነት የሚሰማን ቢሆን ልክ እንደ ሠለጠኑ ሀገራት ቀልጣፋ አሠራር ይኖረን ነበር። ነገሮችን በፍጥነት ለመሥራት የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት (ሲስተም) ይኖረን ነበር። ሰነፎች ስለሆንን ግን ያንን መዘርጋት አልቻልንም፤ በዚህ አያያዝ ለልጆቻችን የምናወርሳቸው እንደዚሁ ውስብስብ አሠራር ያለበት አገርና ሥርዓት ይሆናል ማለት ነው።
ስንፍናን እንደ ምቾት መላመድ ምቾት ሊመስል ቢችልም ውስጡ ግን በሽታ አለበት። አንድ ሰው ታታሪ ሆኖ ሲለፋ ቢውል ምናልባት አካሉ ቢደክም ነው፤ የስንፍና ችግሩ ግን አካልን ሳይሆን አዕምሮን ነው የሚያደክም፤ ድብርት የሚባለው መጥፎ ነገር የሚመጣው ምንም ካለመሥራት ነው። እርግጥ ነው ከፍተኛ የሥራ ጫና ውጥረት እንደሚፈጥር ይታወቃል፤ ዝም ብሎ እንደመቀመጥ ግን አደገኛ ነገር አይኖርም።
አንድ ቀላል ምሳሌ ላንሳ። ለምሳሌ ይህ ገጽ የኔ ነው። ይህ ጽሑፍ ለሰኞ ታኅሣሥ 8 ቀን እንደሚወጣ ረቡዕ ወይም ሐሙስ ተነገረኝ እንበል። እሁድ እሠራዋለሁ ብዬ ብቀመጥ ዓርብ እና ቅዳሜ ነፃ መሆን አልችልም። አለብኝ የሚለውን እያሰብኩ ነው የምቆየው። ወዲያውኑ ጨርሼ ባስረክብ ግን ነፃ ሆንኩ ማለት ነው። ስለዚህ ሥራ ሳይሆን ስንፍና ነው ማለት ነው ለጭንቀት የሚዳርግ።
ቢቻል ሁላችንም ታታሪ ብንሆን፤ ያ ባይሆን እንኳን ቢያንስ ግን ሌሎችን ባናሳንፍ!
ዋለልኝ አየለ አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 8 ቀን 2016 ዓ.ም