ተቀጥሮ ይምጣ፤ ኃይል አሰባስቦ ታጥቆ በጉልበት ይምጣ ልክ ማስገባት የኛ ሥራ ነው”- ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም

 በትናንት እትማችን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ሰሞኑን አጠቃላይ በሆነው የሀገር ሰላም እና ደህንነት ለጋዜጠኞች የሰጡትን መግለጫ የመጀመሪያ ክፍል አቅርበናል። በዚሁ እትማችን በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ሸኔ ጋር የተደረገውን ድርድር ጨምሮ በአማራ ክልል ስለተፈጠረው ግጭት የሰጡትን አስተያየት አቅርበናል።በዛሬው የመጨረሻ እትማችን ፊልድ ማርሻሉ በአማራ ክልል ስላለው እውነታና ሌሎች የጸጥታና የደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ የሰጡትን መግለጫ የመጨረሻ ክፍል ይዘን ቀርበናል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ – እኛ መጀመሪያም ያ ግጭት/በአማራክልል የተፈጠረው ግጭት / እንዲፈጠር አልፈለግንም። በጣም ነው ያባበልነው። ያባበልንበት ምክንያትም፤ ፋኖ የሚል ሽፋን ስላለው ነው። መከላከያ ሠራዊትን መምታት ሲጀምር ፋኖ የሚለው ሽፋኑ ተገፈፈ። ፋኖ የሚለው ጭንብል ወለቀ። መከላከያ ሠራዊትን የሚመታ ጸረ ሰላም ኃይል ነው፤ ጽንፈኛ ነው። ከፋኖነት ጋር የሚገናኝ አይደለም የሚለው ነገር ተረጋገጠ።

ከዚያ ሕግን በተከተለ መንገድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ርምጃ ተወስዷል። አሁን ከባድ ኪሳራ ደርሶባቸዋል። እንደዜጋ ሊደርስባቸው የማይገባ የነበረ፤ ግን ተገደን የገባንበት ኪሳራ ደርሶባቸዋል። አሁን ዋና ኃይሉ ተራግፏል። አሁን ይህን ያቀነባበሩ ለረዥም ጊዜ የሚታወቁ ሽፍቶች እና ከእስር ቤት ያመለጡ ወንጀለኞች ናቸው ። እነዚህ ሽፍቶች ናቸው የእከሌ አካባቢ ፋኖ መሪ ነን የሚሉት።

የሚታወቁ ሽፍቶች የነበሩ ናቸው። ለብዙ ጊዜ። እነሱናቸው አሁን የቡድን መሪ፣ የፋኖ መሪ፣ የጎጃም፣ የምዕራብ ጎጃም፣ ምናምን እያሉ የሚወጡ ያሉት። አንዳንዶቹ ደግሞ ሰው ገለው የታሰሩ፤ በሌላ ወንጀል የታሰሩ፤ ዘርፈው የታሰሩ፤ ከእስር ቤት የወጡ፤ ያመለጡ ናቸው። አንዳንዶቹም ከጸጥታ ኃይል ተወናብደው እዛ የገቡ ናቸው።

አሁን ሠራዊታችን በጣም ጥሩ ሥራ ሠርቷል። በፊት ዞኖች፣ ትላልቅ ከተሞች ስጋት ላይ ወድቀው ነበር። መዋቅሩ ”ፓራላይዝድ” ሆኖ ነበር። አሁን መዋቅሩ በሚገባ ተደራጅቷል፣ ተዋቅሯል። የሚታገል መዋቅር መጥቷል። እንደ መዋቅር ማለት ነው። እንደ ግለሰብ እዛም፣ እዚህም እያስመሰለ የሚኖር የለም ማለት አይደለም። ግን እንደ መዋቅር ሙሉ መዋቅሩ ተስተካክሏል።

ከተሞች ሰላም ናቸው። ገጠሮች በአብዛኛው ሰላም ናቸው። አሁን ወደ ሸለቆ፣ ወደ ቆላ ወርዷል። የወረደው ለምንድ ነው? አንደኛ ያለ አቅሙ ነው የገጠመው። ሁለተኛ የገጠመበት ምክንያት የተሳሳተ ነው። ሶስተኛ የራሱን ሀገር ሠራዊት ነው የገጠመው። ይሄ በመሆኑ ምክንያት፤ ሕዝቡም አየ፤ ሕዝቡም ይሄ ኃይል ወደ አደጋ እየወሰደን ነው አለ። የነበረው ልፍስፍስ መዋቅር ተቀየረ።

ለዚህ ያበቃቸው በመዋቅሩ ውስጥ የነበረ በሽታ ነበር። ከባድ፣ መጥፎ ሥራ የሠሩ አሉ “እዳው ገብስ ነው”። አሁን ይሄ አካሄድ የአማራን ሕዝብ ፤በአጠቃላይም ኢትዮጵያንም እንደሚጎዳ ያመኑ የተቀበሉ ሰዎች ወደ ኃላፊነት መጥተው፤ አዲስ መዋቅር አደራጅተው፣ ገምግመው፣ አጥርተው፣ መድበው እየሠሩ ነው። የመከላከያ ሠራዊት ደግሞ ለነሱ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በጣም ትልቅ፣ ሰፊ የሚመሰገን ሥራ ሠርቷል።

ጠላት ደግሞ በእጅጉ ተዳክሟል። የቀሩት ምህረት ሊሰጡኝ አይችሉም የሚሉ ናቸው ፤ ምክንያቱም የኋላ ታሪካቸው ከባድ ወንጀል አለው። ተጨማሪ አሁን ወንጀል ፈጸሙ። “እኔ ምህረት ሊሰጠኝ የሚገባኝ ሰው አይደለሁም” ብለው ያመኑ ሰዎች ናቸው የቀሩት። ወንጀልህ ትልቅ ይሁን ትንሽ ምህረት መንግሥት ካደረገ፣ ምህረት ነው።ምህረት ምህረት ነው። ለእነሱም ምህረት አይደረግም የሚል ነገር የለኝም።

የሄዱበት መንገድ ግን ምንም ለአማራ ሕዝብ ጠብታ የሚጨምርለት የለውም። ያከስረዋል። እስካሁን ባለውም አክስሮታል። ብዙ ሰው ንብረት አጥቷል። የሕዝቡን መኪና ቀምተውታል፤ ብር አምጣ ብለው ቀምተውታል፤ መንገድ ዘግተውበታል፤ እንዳይነግድ አድርገውታል፤ እንዳይገናኝ አድርገውታል፤ ቱሪስት እንዳይገባ አድርገውታል፤ እና የአማራ ሕዝብ አሁን ተጠቀመ? ትክክል አይደለም።

በጣም የሚያሳፍረው ነገር መከላከያ ሠራዊቱን ምንድን ነው ያሉት “እስላም መጣ፣ እስላም መጣብህ፣ ሃይማኖትህን እንትን ሊያደርግ ነው፤ ና ማዳበሪያ ውሰድ፣ መንግሥት የከለከለህን ማዳበሪያ ውሰድ፤ መንገድ ዝጋ፤ ከኛ ጋር ሁን፤ ሴቶች ይደፍርብሃል፤ “ሸኔ ነው” እያሉ ነው የመከላከያ ሠራዊትን ስም ሲያጥላሉና ሲበክሉ የነበሩት።

መከላከያ ሠራዊት ግን በዲሲፕሊን የታነጸ፣ ሕዝባዊ ወገንተኝነት ያለው፣ እሴት ያለው ስለሆነ ወደ አማራ ክልል ገብቶ፤ ለአማራ ክልል ሕዝብ ማንነቱን አሳይቶ፤ ሕዝቡ እንደዚህ አላላቹህም እንዴ? “ዋሽታችሁናል፣ አታላችሁናል፣ አታላቹህ ወደ አልሆነ አዘቅት ውስጥ አስገብታችሁናል” ብሎ አፋጦ ይዟቸዋል። እና ነፃ አውጪ ማለት ይሄ ነው?።

ነፃ አውጪ እኮ ማን ከማን ነጻ እንደሚወጣ አስቀምጦ፣ በትጥቅ ትግል የሚፈታ የፖለቲካ አላማ አስቀምጦ፣እስትራተጂ ነድፎ፣ ጥበብ ነድፎ፣ ማንን እንደሚያቅፍ አስቀምጦ፣ማንን በጠላትነት ፈርጆ እንደሚወጋ አስቀምጦ እንጂ ዝምብለህ አደበላልቀህ ሕዝቦችን ሰድበህ ፤ሌላውን አዋርደህ፤ ሌላውን ከፍ አድርገህ እንደዚህ አይነት ትግል ዓለም ላይ የለም። ስለዚህ አማራ ክልል የተደረገው ነውጥ ለአማራ ክልል በጣም አደገኛ፤ ለአማራ ማኅበረሰብ አደገኛ፤ ለኢትዮጵያም የሚጎዳ፤ ታይቶ የማይታወቅ ነገር ነው።

ይሄን የግድ ማስተካከል ስላለብን እያስተካከልን ነው። በከፍተኛ ደረጃ አስተካክለናል፤ ከፍተኛ የሆነ ሰላማዊ ሁኔታ እየተረጋገጠ ይገኛል፤ የቀረ አለ ፤ይሠራል። እስከአሁን የቆየበት ምክንያት መታወቅ አለበት። እነዚህ ሰዎች እንደዚህ አይነት ጽንፈኞች ግንባር ይዘው አይዋጉም፤ ግንባር ይዘው አይገጥሙም፤ ሕዝቡ ውስጥ ነው የሚደበቁት፤ ከሕዝብ ጋር አትመታቸውም። ከሕዝብ ነጥለህ ነው የምትመታቸው። ከሕዝብ ነጥለህ ለመምታት ጊዜ ይጠይቃል፤ ልፋት ይጠይቃል፤ ይሄ ስለሆነ ነው የቆየው። እራሱ ግንባር ፈጥሮ፣ ምሽግ ይዞ ከመከላከያ ጋር ለመግጠም የሚያስችል አቅም የለውም። ለአቅመ አዳም አልደረሰም።

ስለዚህ ሕዝቡ ውስጥ ነው የሚደበቀው። ቤተክርስቲያን ነው የሚገባው። ቤተክርስቲያን ሲገባ ቤተክርስቲያን አትመታም። እንደዚያ ቢሆን ኖሮ የአማራ ክልል ቤተክርስቲያኖች አልቀው ነበር። ቤተክርስቲያን ይገባል፤ ቄስ ስር ይገባል፤ ይሄን ለይተህ ምን እርምጃ ለመውሰድ በጣም ከባድ ነው። ገበሬ ጋር ይገባል፤ ገበሬ እና እሱን ለመለየት በጣም ያስቸግራል፤ ጊዜ ይጠይቃል። ሕዝብን እንደከለላና ምሽግ ተጠቅመህ እየተዋጋሁ ነው ብለህ መፎከር አግባብ አይደለም። አሁንም ጊዜ ይጠይቃል።

ምክንያቱም ሕዝብና ጽንፈኛው ተለይቶ ነው እርምጃ መወሰድ ያለበት። ሕዝባችን በእነሱ ምክንያት መጠቃት የለበትም። ከባድ ነው፤ ከሕዝብ ውስጥ እንደዚህ አይነት ሰርጎ ገብ፣ ጽንፈኛ ነጥለህ መደምሰስ ከባድ ነው። መደበኛ ጦርነት አይደለም፤ ጊዜ ይወስዳል። አሁን ግን  ሕዝቡ እያወቀ ነው፤ ከሕዝቡ እየተነጠሉ ነው፤ ሕዝቡም አላስጠጋ እያለ ነው፤መዋቅሩም እየተጠናከረ ነው። ከባድ ኪሳራ ደርሶበታል፤ አቅሙ ተዳክሟል፤ የሚቀር ሥራ ግን አለ። እሱ ላይ ነው የእኛ ሥራ የሚሆነው።

ጥያቄ- ከድሮን ጥቃት ጋር በተያያዘ ሠራዊቱ ሕዝቡ መሀል የድሮን ጥቃት ፈጽሟል የሚሉ የተለያዩ ውዥንብሮች እየወጡ ነው፤ ይሄን በተመለከተ ምን የሚሉት አለ?

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ – ድሮን እኮ የተሰራው ለጦርነት ነው። ለውጊያ ነው። የገዛነው ልንዋጋበት ነው፤ እንጂ ድሮን አለን እያልን በሚዲያ ልንገልጸው አይደለም። የጦር መሳሪያ ነው፤ ልክ እንደክላሽ። ክላሽ የአቅሙን ይሰራል፤ ሌላውም የአቅሙን ይሰራል፤ ድሮንም የራሱን ሥራ ይሰራል። ድሮን እኛ የምንጠቀመው ለስብስብ ኢላማ ነው። በወታደራዊ አባባል ስብብስ ኢላማ የሚባል ነገር አለ፤ ስብስብ ኢላማ ማለት የጠላት ጠንካራ ቋጠሮ ማለት ነው።

የጽንፈኛውን ስብስብ ስናገኝ በድሮን እንመታለን። ገጥሟል እኮ፤ እኔ መሳሪያ ልመርጥለት ነው። አይ ድሮን ተውና ክላሽ ለክላሽ እንግጠም እያለ ነው ያለው?! ይሄ በመሆኑ ምክንያት ሕዝብ ላይ ድሮን አንጠቀምም ፤ አይተኮስም። መንደር ላይም አይተኮስም። የጠላት ስብስብ ሲገኝ ግን ይተኮሳል። ደግሞም ድሮን ይሄንን ያህል ተጠቅመናል ብዬ ልወስድ አልችልም። ባለን አቅም ልክ አልተጠቀምንም፤ የተለየ ምርጥ ኢላማ ሲገኝ ግን እንተኩሳለን። እሱንም ለሕዝቡ ጥንቃቄ አድርገን ማለት ነው።

ለሕዝቡ የማሳስበው ነገር አለ። ከጽንፈኛ ጋር አትደባለቁ፣ ልጆቻችሁ የሚፎክር የሚሸልል ጽንፈኛ አይተው እሱ ጋር እንዳይሄዱ፤ ልጆቻችሁን ያዙ። ሰባ፣ ሰማንያ ጽንፈኛ ተሰብስቦ ከተገኘ ወይ ሊያጠቃ፣ወይም ሊማከር ወይም ሲመገብ ካገኘነው እንመታለን። ይሄ ይቀጥላል። ድሮን የጦር መሳሪያ እንጂ የተለየ ነገር አይደለም። የሚተኮስበት ባለቤት አለው፤ ከሕዝብ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለውም። እንደውም አንዳንዱ ኢላማ ሕዝቡ ውስጥ በመሆኑ ቤተክርስቲያን በመሆኑ የተውነው አለ፤ እያወቅን ፤እያየን። ይሄ ከሕዝባዊ ባህሪያችን የሚመነጭ ነው።

ከዚህ ባለፈም እኛ የምንገዛበት ሕግ አለን። ዝም ብለን በዘፈቀደ የምንሰራ ሽፍቶች አይደለንም። እነሱ ናቸው በዘፈቀደ የሚሰሩ ሽፍቶች። አሮጊት የሚገሉ፣ ሽማግሌ የሚገሉ። ለምን እኔን አልደገፍክም፤ ለምን እከሌ የሚባል ፓርቲ ትደግፋለህ ብለው ሰው የሚገሉ እነሱ ናቸው። እኛ የእከሌን ፓርቲ ለምን አትደግፍም፣ ለምን የእከሌን ፓርቲ ደገፍክ ብለን ሰው አንገድልም። እኛ ጦርነት የገጠመንን ነው የምንገጥመው። ከገጠምክ በኋላ ደግሞ ቻለው፤ ቻለው ነው። ስለዚህ ኢላማው ከተገኘ ይሄንን በየትኛውም ፀረ ሰላም ኃይል ላይ እንጠቀማለን። ሕዝቡ ግን እንዳይጎዳ እንጠነቀቃለን።

ጥያቄ፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እዚህ እዛም የሚነሱ የሰላም እጦቶች መካከል በእሳቤያቸው በጣም ጽንፈኛ በሚባሉ አካላት ሠራዊቱን ኢላማ የማድረግ አዝማሚዎች ተደጋግመው ታይተዋል ። የዚህ መነሻ ምክንያቱ ምንድን ነው ?ከሰሞኑ እየሰማን እንዳለነው ደግሞ ሠራዊቱ ተበትኗል፤አለመግባባት ውስጥ ነው ያለው። የሚሉና ሠራዊቱ ወደ ካምፕ ይመለስ የሚሉ የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪዎች እየቀረቡ ነው።ይህንን እንዴት ያዩታል?

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ – ሠራዊቱ ላይ ዘመቻ የከፈቱ ሰዎች ግማሹ ቅጥረኛ ባንዳ ነው። ምንም ጥያቄ የሌለው። ሠራዊቱ እንደ ኢትዮጵያ ሠራዊት በመሆኑ ምክንያት ሀገሪቷ የመከላከል አቅሟ እንዲዳከም እንዲሸረሸር በማድረግ ለጥቃት የተጋለጠች እንድትሆን የሚሰሩ ኃይሎች አሉ። ዘመቻ የከፈቱት ሰዎች ተልእኮ ተቀብለው ነው።

የኢትዮጵያ ሠራዊት አሁን ያለው ጠንካራ ሠራዊት ነው። ጠንካራ ሠራዊት እንደሆነ ጠላቶቻችንም ያውቃሉ። ስለሚያውቁ ይህ ሠራዊት እንዲዳከም ይፈልጋሉ።ይህንን ለማሳካት መአት ቅጥረኛ ገዝተዋል ፤ደመወዝ ይከፍላሉ፤ ሚዲያ ይሰጣሉ፤ሠራዊቱ ላይም ዘመቻ እንዲከፈት ያደርጋሉ። አንዱ ይሄ ነው።

ሁለተኛው ሀገር ቤት የኛ የሚሏቸው ታጣቂዎችን ልክ በማስገባት ፍላጎታቸው እንዳይሳካ በማድረግ በደንብ የሠራው መከላከያ ነው። እነሱ የሚፈልጉትን በትጥቅ ትግልም ፤በሰላማዊ ሰልፍም፤ በሌላም አድርገው ሀገር ለማፍረስ ለማበጣበጥ የእርስ በእርስ ጦርነት ለመፍጠር የሚያደርጉትን ነገር የመከተው መከላከያ ነው።

ምንም ማድረግ አቃታቸው። ያልሞከሩት እኮ የለም። በመፈንቅለ መንግሥት ሞክረዋል፤ ሰላማዊ ሰልፍ አስመስለው ሞክረዋል፤ ፎክረዋል አደራጅተዋል፤ አስታጥቀዋል መከላከያ ላይ ጥቃት እንዲደረግ አድርገዋል። ሁሉንም መከላከያ ሥርዓት አስይዟል። ምንድነው የኛ ፍላጎት እንዳይሳካ ያደረገው ብለው ጠንካራ ጎን ሲፈልጉ ጠንካራ ጎኑ መከላከያ ነው። ስለዚህ ጠንካራ ጎኑን ፣ጠንካራው ቋጠሮ መመታት አለበት ነው እሳቢያቸው ።

ይሄን ሀገር ያቆመው ፤ይሄን ሀገር በየጊዜው የሚፈጠሩ አጀንዳ እያከሸፈ ለውጡ እንዲቀጥል ያደረገው ማነው ሲባል ጠንካራው ቋጠሮ መከላከያ ነው። ስለዚህ መከላከያ ካልተመታ የፈለግነው ሀሳብ ሥራ ላይ እየዋለ አይደለም በሚል ነው የሚዘመትበት።

እኛ ደግሞ ተልእኮ አለን። ተልእኮው ከውጭም ይምጣ ከውስጥም ይምጣ በኃይል የሀገሪቷን ሥርዓተ መንግሥት ፤የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት ገርስሶ ፤እኔ ነኝ ጉልበተኛ ብሎ በግድ በጠመንጃ ሊጭን የመጣ ኃይል ሁሉ እንዋጋለን። ይሄ የኛ ተልእኮ ነው። ማንም ይሁን ማን ከውጪ በወረራ መልክ ይምጣ ፤ተቀጥሮ ይምጣ፤ ኃይል አሰባስቦ ታጥቆ በጉልበት ይምጣ ልክ ማስገባት የኛ ሥራ ነው።

ልክ እያስገባ ስላስቸገረ የዚህ ሀገር ጠንካራ ቋጠሮ ማነው ሲባል መከላከያ ነው የተገኘው። ስለዚህ ይሄን ማፍረስ ነው ስራቸው። ለዚህ ነው መከላከያ ላይ ዘመቻ የበዛው። ‹ተበትኗል እንደዚህ ሆኗል፤ በጄነራል ተጣልተዋል፤ ጄነራል እከሌ ተቆጥቷል፤ የቁም እስረኛ ሆኗል› የሚለው ምኞት አይከለከል ፣ ምን እናድርግ።

መከላከያ በጠንካራ አለት ላይ የተገነባ ነው። እንደዚህ ፍርክስክስ የሚል አጀንዳ በመጣ ቁጥር የሚጭበረበር ፤ የሚርበተበት ተቋም አይደለም። ጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ በራሱ ዶከተሪን የተገነባ፤ በራሱ ዲስፕሊን የተገነባ፤ አላማውን የሚያውቅ፤ ለምን እንደሚዋጋ የሚያውቅ፤ ማንን እንደሚዋጋ የሚያውቅ፤ መንደርተኝነት የሌለው፤ ኢትዮጵያዊነት የተላበሰ እና ኢትዮጵያን የመጠበቅ ተልእኮ የወሰደ ስለሆነ ወደነፈሰበት የሚነፍስ ተቋም ግለሰብ የለውም።

ይሄ ምኞት ነው። ምኞቱ ምኞት ሆኖ ነው የሚቀረው። ስለ በመከላከያ የተወራው መአት ወሬ አለ፤ አንድም እውነትነት የለውም። መከላከያ ሠራዊት እኮ ነው የአማራን ክልል ሥርዓት እንዲይዝ ያደረገው። መከላከያ ሠራዊት እኮ ነው የሸኔን መፈንጨት ሥርዓት እንዲይዝ ያደረገው። የተጣላ ጄነራል፤ የተበተነ፣ ያኮረፈ ፣እርስ በራሱ የሚባላ ኃይል ይሄንን ሊሰራ አይችልም። ኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ ተቋም ማነው ብትል መከላከያ ነው ፣ ከመከላከያ የተሻለ የለም። እንደዛ ነው መታየት ያለበት። ወደ ካምፕ ይግባ የሚል ሰሞኑን የወጣው አስቂኝ ነገር ነው።

ወደ ካምፕ ይግባ የሚል ብቻ ሳይሆን ፣ሌላው የሰማሁት ነገር፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዳር ድንበር መጠበቅ ነው እንጂ በውስጥ ግጭት መግባት ስለሌለበት የውስጥ ግጭት ይቀጥል የሚል ነው። የመከላከያ ሠራዊት ተልኮ የሀገሪቷን ሉአላዊነት መጠበቅ ነው። የሚጠብቀው ደግሞ ጠረፍ አጥሮ አይደለም። ጠረፍ አጥሮ ምሽግ ሰርቶ ሰልፍ ሰርቶ እንደዛ አይደለም። መከላከያ ሠራዊት ሀገሪቷን የሚጠብቀው ራሱን እየገነባ ነው። መከላከያ ሠራዊት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የሚጠብቀው እራሱን እየገነባ ነው። እየሰለጠነ ነው እየታጠቀ ነው አቅም እያበዛ ነው። እየተደራጀ ነው።

ሁለተኛው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከፖሊስ አቅም በላይ የሆነ እና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ የመጣ ማንኛውም የታጠቀ የሀገር ውስጥ ኃይል መቆጣጠር እንዳለበት ተልዕኮ ተሰጥቶታል። የአማራ ፅንፈኛ ትግል ከፖሊስ በላይ አይደለም ብቻ እንዳትለኝ ወይም የሸኔ ትግል ከፖሊስ በላይ አይደለም እንዳትለኝ። ፖሊስ ወንጀል ነው የሚቆጣጠረው። የፖሊስ ሥራ ወንጀል መቆጣጠር፤ወንጀለኛን መያዝ ፤ወንጀለኛን ለፍርድ ማቅረብ ነው።

የተደራጀ የታጠቀ እና ፍላጎቱን በኃይል ለማስፈፀም ታጥቆ የመጣ የሀገር ውስጥ ኃይል ፀረ ሕገመንግሥት ነው። ፀረ መንግሥት ነው። ሀገር አፍራሽ ነው። ሕገመንግሥቱ በሚለው መሰረት መከላከያ ሠራዊት ይመክተዋል፤ ያስታግሰዋል። ይህንን ተረድተው አይደለም የተናገሩት እነዛ ሰልፍ አዘጋጅ ነን ያሉ ሰዎች። የመከላከያ ተልዕኮ ካለማወቅ የመዘበራረቅ ነገር አይቼባቸዋለሁ አንድ እሱ ነው።

ሁለተኛ ከመቼ ወዲህ ነው ፖለቲከኛ ወይም በሰላማዊ መንገድ እታገላለሁ የሚል ቡድን ግለሰብ ፓርቲ ለመከላከያ ሠራዊት ትዕዛዝ የሚሰጠው። ካምፕ ግባ ፤ከካምፕ ውጣ ፤ይሄን ቦታ ያዝ ፤ይሄን ቦታ ልቀቅ የሚለው። የገባኝ ይሄ ኃይል የፅንፈኛው የከተማ አንጃ ነው። የፅንፈኛው የከተማ አንጃ ነው። ፅንፈኛው አከርካሪው ሲመታ ተስፋ ላለመቁረጥ በከተማ ግርግር ሊመጣ የፈለገ ኃይል ነው።

ስለዚህ እኛ ወደ ካምፕ አንገባም። ፀረ ሰላም ኃይሎችን እናስተካክላለን ፤ካስተካከልን በኋላ ወደራሳችን ሥራ እንመለሳለን ብለን ነው የምናስበው እና ትክክል አይደለም። እኔ ሰልፍ አልቃወምም። የሆነ አጀንዳ ፈጥረህ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ መብት ነው። የሰሞኑ ሰላማዊ ሰልፍ ግን ነውጠኛ የጦርነት አዋጅ እንጂ ሰላማዊ ሰልፍ አይደለም።

መከላከያ ሠራዊትን ወደ ካምፕ የሚያስገባ፤ ጫካ ያለውን ፅንፈኛ የታጠቀ ኃይል ደግሞ ወደ አደባባይ የሚያወጣ ፤ወደ ከተማ የሚያስገባ ፤በሰላማዊ ሰልፍ የተደገፈ ፤ ሀገር የሚያፈርስ ነው። ስለዚህ መንግሥት መከልከሉ ትክክል ነው ብዬ አስባለሁ፤ ይሄ ሰልፍ ተከለከለ ማለት ነገ ሰልፍ አይደረግም ማለት አይደለም። ሕዝብ የሚገዛውን አጀንዳ ፈጥረህ ሰልፍ ማድረግ ትችላለህ ማለት ነው።

ለወሮበላ አምስት አምስት ሺህ ብር እየከፈልክ ከተማ ለማስበጥበጥ ሰልፍ መጥራት አይቻልም። ብሩ ደግሞ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ነው የሚመጣው። ይህንን የማያገናዝብ እና ሥራ ፍለጋ አዲስ አበባ ለመጣ ወጣት ብር እየከፈሉ አዲስ አበባን ለማቃጠል መሞከር ትክክል አይደለም።

ሠራዊቱን ወደ ካምፕ አስገብቶ ፍላጎቱን በኃይል ለመጫን የሚመጣውን ፅንፈኛ ሁሉንም እንዲቆጣጠር ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚጠራ ሰልፍ ትክክል አይደለም። ስለዚህ ካምፕም አንገባም ፤ማንም አያገባውም። የእኛን ተልዕኮ እኛ እናውቃለን። የእኛ ተልዕኮ መሰረቱ ሕገመንግሥት ነው።

ማንኛውም የታጠቀ ኃይል በአማራ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል፣ በሶማሌ ክልል፣ በአፋር ክልል በሌላውም ክልል እንደፈለገ ይፈንጭ የሚልና መከላከያ የውጭ ጠላት ካልመጣ በስተቀር ከካምፕ መውጣት የለበትም የሚል ሕገመንግሥቱን ቀይሮ እንደዛ ሊደርግ ይችላል። እስከዛ ግን እኛ ተልዕኳችንን ነው እየፈፀምን ያለነው።

ጥያቄ:- ክቡር ፊልድ ማርሻል የኢትዮጵያ ሰላም አሁን በምን ደረጃ ይገኛል? እንደ ሀገር የመከላከያ ሠራዊቱስ የሀገርን ደህንነት በመጠበቅ ረገድ አሁን የሚገኝበት የዝግጁነት ደረጃ ምን ይመስላል?

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ:- ያው እንደሚታወቀው ቀደም ሲል ሰሜን ዕዝ ከተመታ በኋላ ጦርነት ውስጥ ነበርን፤ ያጦርነት ቀላል ጦርነት አይደለም፤ ከባድ ጦርነት ነው። ሁለቱ ዓመታት ሀገሪቷ ከባድ የፀጥታ ችግር የገጠማት ጊዜ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ሸኔ በዚህ ግርግር ለመጠቀም ከፍተኛ ርብርብ አድርጓል። ሰሜኑ የአፋር፣ የአማራ ክልል በከፊል ትግራይ ሙሉ በሙሉ፣ ምዕራብ ኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ ሰፋ ያለ የጸጥታ ችግር ነበር።ቤንሻንጉል ላይ ህዳሴ ግድብ ለመስራት አስቸጋሪ እስከሚሆን ድረስ የደረሰ የፀጥታ ችግር ነበር፣ የትግራይ ያው እንደሚታወቀው ነው። አሁን ግን በከፍተኛ ደረጃ የኢትዮጵያ የፀጥታ ሁኔታ ተሻሽሏል።

በትግራይ ጦርነቱ ተካሂዶ ጦርነት እንደማያዋጣ ሲታወቅ ወደ ድርድር መጥቶ በሰላም ተፈትቷል፤ አሁን ትግራይን መልሶ የማቋቋምና የቀረው (የDDR )ፕሮግራም ሥራ ላይ እንዲውል የመስራት ሥራ ነው። ሁለተኛ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ፀጥታ መቶ በመቶ ተስተካክሏል። እዛ ያለው ጠላት በከፍተኛ ደረጃ ተመትቶ የተረፈው ኃይል በሰላም እንዲገባ ተደርጓል። ቤኔን የሚባል ኃይል ቤንሻንጉል ላይ ነበር እሱም በሰላም እንዲገባ ተደርጓል።

ከብዙ መንገራገጭ በኋላ ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ ሞክረው ሲያቅታቸው ነው ወደ ሰላም የተመለሱት። የጋምቤላ ነፃ አውጪ የሚባለውም በተመሳሳይ በሰላም እታገላለሁ ብሎ ምህረት ተደርጎለት ገብቷል። የአማራ ጽንፈኛ ደብረማርቆስ፤ ጎንደር ፤ደሴ ፤ኮምቦልቻ ለመቆጣጠር ከመፈለግ አልፎ ባህርዳርን የመቆጣጠር ፍላጎት ነበረው። በዚህም ጠቅላላ የአማራ ክልልን መዋቅር “ፓላራይዝ” ለማድረግ ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር የሽፍታ ክልል ማድረግ እና አልፎም ወደፌዴራል አፈሙዝ ማዞር የሚል የጅል እቅድ አውጥቶ ነበር ።

እሱ አሁን አከርካሪው ተመትቷል። ወደመደበቅ፤ ወደሸጥ ፤ወደዋሻ፤ ወደአባይ ለመደበቅ ወርዷል። በአሁኑ ወቅትም ሰው ወደማይኖርባቸው፤መሰረተ ልማት ወዳልገባባቸው ቦታዎች ወርዷል። አብዛኛው ቦታ ላይ የሰላሙ ሁኔታ እየተረጋገጠ ይገኛል። ሕዝቡም ሥራ ጀምሯል። በመሆኑም አማራ ክልል በከፍተኛ ሁኔታ ተቀይሯል።

ኦሮሚያ ክልል ልክ እንደ አማራ ክልሉ ተመሳሳይ ነው። ሸኔ የታንዛኒያ ድርድር ላይ እያለ ድርድሩን መንግሥት ተገዶ እንዲቀበል ያለ የሌለ ኃይላችንን አውጥተን መንግሥትን እናስጨንቀው የሚል የሞኝ ፖለቲካዊ ስትራቴጂ ነድፎ ሠራዊቱን በሙሉ አውጥቶ ከመከላከያ ጋር አጋጨውና ብዙ ዓመት የደከመበት ኃይሉ እንዲመታ ሆኗል። በማሰልጠን፤ በማዘጋጀትና በማለማመድ ብዙ ኃይል ተመትቷል። አሁን ምዕራብም ቢሆን በተነጻጻሪ ጥሩ እንቅስቃሴ ያለበት ነው።

ወታደራዊ ጥበብ እኮ መጀመሪያ እራስህን ትገመግማለህ ፤ከዚያ ጠላትህን ትገመግማለህ። በዚህም የውጊያ ጥንካሬውን ፤ትጥቁን ብዛቱን፤ አደረጃጀቱን ችሎታውን ደካማ ጎኑ ይገመገማል ።ከዚያ በኋላ የውጊያ እቅድ ይወጣል እንጂ ጠመንጃ ስለተያዘ ብቻ እቅድ አይወጣም። የፊልም ተዋናዮችን አለባበስ ለብሶ ስለተንጎራደደ ጦርነት አይከፈትም፤ ውጊያም አይደረግም። ቢያንስ እቅምን ገንብቶና ስትራቴጂ ነድፎ መዘጋጀት ያስፈልጋል። ከዛም አቅም ፈጥሬያለሁ፤ መገዳደር እችላለሁ የሚለው አቋም ላይ ሲደረስ ነው ጦርነት የሚገጠመው።

አሁን ላይ ግማሹ ቆመህ ጠብቀኝ የያዘ ሌላው ክላሽንኮፍና ብሬን የያዘ በጣም አልፎ አልፎ ድሽቃ የያዘ መንግሥትን አስገድጄ የሰላም ድርድሩን እንዲቀበል አደርጋለሁ ብሎ ዘመቻ ይከፈታል? ይህ ሁኔታ ደግሞ በህይወቱ ተመቶ በማያቀው ልክ በመመታቱ ለማንሰራራት ብዙ ጊዜ እንዲወስድ አስገድዶታል። አሁን ተስፋ ስለቆረጡ ከተሞች ላይ ቦምብ ወደመጣል፤ ግለሰቦችን ወደመግደል ተሸጋግረዋል።በነገራችን ላይ አማራ ክልል ያለውም ይኸው ነው።

 እኛ እንደ ፖለቲከኛ ቀን በቀን እየወጣን ለሕዝቡ ስለማንናገር ነው እንጂ መከላከያ ሠራዊት የሀገሩን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር በጣም እየሰራና እየለፋ ነው። ኢትዮጵያ ጥሩ ”አክቲቪስቶች” አሏት ፤ጥሩ ዜጎችም አሏት፤ ምናልባትም አብዛኛው ኃይል በዚህ ነው የሚገለጸው። ኢትዮጵያ መሰሪ አደገኛ የሆኑ ተኝተው የማያድሩ ከስልጣን በስተቀር ሌላ ሥራና አላማ የሌላቸው ማንም የሚቀጥራቸው ኤሊቶችና አክቲቪስቶችም አሏት። ሕዝቡን እግዚአብሔር ከእነዚህ ሰዎች ይሰውረው።

የአማራ የኦሮሞ የትግራይ የሶማሌ ጽንፈኛ ሁሉም ተፈለፈለ ከዚያም ተዋጋ ።ቀጥሎም መንግሥት ፈረሰ እንበል፤ ከዛስ ምን ሊያደርጉ ነው? ይህ የማያቋርጥ ሊድን የማይችል የእርስ በእርስ እልቂት አይፈጥርም? ሽምግልና የማያስተካክለው ቁርሾ አይሆንም ? ስለዚህ የየጎጡን ጽንፈኛ በማጀገን መንግሥትን ለመጣል ብቻ እንጂ ከዛስ የሚለውን ነገር ግን አልታሰበም።

ብዙ ተምሬያለሁ የሚል ነገር ግን የማያስብ ሀገሪቱን ወደጨለማ የሚነዳ ኤሊት ፖለቲከኛና አክቲቪስት ነው ያለው። እውነት ለመናገር ብዙ ፖለቲከኞች ፖለቲከኞች ናቸው ወይ ? የሚል ጥያቄ እንድታነሳ ያስገድዳሉ። እየሆነ ያለው ምንድን ነው አላማው? ምንድን ነው የሚፈልገው? እንዴት ነው የፈለገውን ማሳካት የሚፈልገው ?የሚለውን ለማወቅ አያስችልም። ይህ ደግሞ ስሜታዊ ለቀን ለቀኑ ብቻ የሚያስብ ፤ በጉርሻ የሚሰራ ፤ ሲያጎርሱት በደንብ የሚያጣላ ፤ጉርሻ ሲያጣ ዝም የሚል እየበዛ ነው።

እኛ በመረጃ የምናውቃቸው ደመወዝ ተከፍሏቸው ፀረ ኢትዮጵያ የሚሰሩ ምሁራን አሉ።ደመወዝ የሚከፍላቸው ኃይል አላማ አለው። እሱ ግን ደመወዙን ነው የሚያየው።ከዚያ በል የተባለውን ነው የሚለው። ፃፍ የተባለውን ነው የሚጽፈው። አንዳንዱ ነገር አሳፋሪ ነው፤ ወደ ሚዲያ አውጥቶ ለመናገር። እንዲህ ያለውን ኃይል መቼ ነው የፈጠርነው ፤እንዴት ነው የፈጠርነው። የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ምንድነው የሆነው። ምንድነው የገጠመው ብዬ እንዳስብ ያደርገኛል።

የሌላ ሀገር ዲያስፖራ ቴክኖሎጂ እየቀዳ ወደ ሀገሩ ይልካል።ዶላር ወደ ሀገሩ ይልካል።የራሱን ሕዝብና መንግሥት በየሄደበትና በየደረሰበት አያብጠለጥልም።ከተርኪና ከቻይና በላይ ስደተኛ ዲያስፖራ ያለው የለም። ቱርኮች ሀገራቸውን ገናና ያደረጉት ዲያስፖራዎች ናቸው። ከውጭ የሚያገኙትን ገንዘብ ሆን ብለው ሰብስበው አጠራቅመው ይልካሉ።በየሁለት ወሩ ስቴትስ ዲፓርትመንት በር ላይ አይታዩም።

የኛው ዲያስፖራ ግን ሀገሩን ለማጥፋት የተሰለፈ ይመስላል። እዚህ ውስጥ የሌሉ ሬሚታንስ፣ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር የሚልኩ ብር አጠራቅመው ኢትጵያ የተቸገረችበትን ነገር የሚከፍቱ፤የሚሰሩ አሉ። እነዚህ ሰዎች ሥርዓት ያላቸው፣በሥርዓት ያደጉ፣ሥራ የሚሰሩ፣ጩኸት ቦታ የማይውሉ፣ገንዘብ በደንብ የሚያገኙ ትምህርት እዛ የተማሩ፣እውቀት ያካበቱ ናቸው።

በኢንዱስትሪ የሚሰሩ መአት ናቸው።ትላልቅ ፎቅ የሚሰሩ፣ህክምና የሚያመጡም አሉ።ለመከላከያ የሚረዱ አሉ።ግብርና የገቡ አሉ።ለሀገራችን ኢኮኖሚ ህይወት የዘሩ አሉ። ስቴት ዲፓርትመነት በር ላይ አታገኛቸውም። እነዚህ ምርጥ የኢትዮጵያ ዜጎች ናቸው።

ፀረ ኢትዮጵያ ሆነው የሚሰሩ ምሁራን አሉ። የወሬ ገበያ/ ማርኬት ተፈጥሯል። ይሄ የወሬ ማርኬት ኢትዮጵያን እያፈረሳት ነው። ኢትዮጵያን እየጎዳት ነው። የሕዝብ ትስስርን እያላላ ነው። የሕዝብ መተማመንን እየሸረሸረ ነው። ምክር ፣ተስፋ ኤክስፒሪያንስ ነው እንጂ መስጠት የሚገባው ተባላ፣ተጋደል እከሌን አጥፋ ፣አራት ኪሎ ግባ፣የአባትህ ቤተመንግሥት እንዲዚህ አይባልም።እነዚህ ኢትዮጵያን እየጎዱ ነው።

እኛ ግን ማንም እንደዚያ ያድርግ ፣ማንም ይሞክር እስትንፋሳችን እስካለ ድረስ እንታገላለን።ኢትዮጵያ ትሻገራለች ብዬ አስባለሁ። ጥሩ እየሄድን ነው። እብደቱም እየቀነሰ ነው።ሀገሪቱ ምክክርም ይኖራታል ብዬ አስባለሁ እና ትሻገራለች። ሀብት አላት፣ሀብቱን አውጥተን መክበር አቅቶን 60 ዓመት ሙሉ ስለተኩስ ነው እያወራን የኖርነው። ለመተኮስ፣በጉልበት ስለመቆጣጠር፣ሌላውን ስለማፈን ስናስብ ነው የኖርነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሄን በደንብ መረዳት አለበት ብዬ አስባለሁ።

ጥያቄ -አልሻባብ የመከላከያ ሠራዊት ግዳጅ ውስጥ ነው ብሎ ባሰበበት ወቅት የተለያዩ ጥፋቶችን ለመስራት ይሞክራል፤በዚህ ላይ ምን ይላሉ ?

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ፦ አልሸባብ እንደምታስቡት አይደለም።አቅም የለውም። አንደኛ እኛ በሙሉ አቅም አይደለም የገባነው። ወደ አማራ ክልል ኦሮሚያ ክልል ያለውን ኃይል ለመቆጣጠር የገባነው በውስን ኃይል ነው። እኛ እዚህ ተጠምደን፣ኃይል አንሶን አልሸባብ እኛን የሚሞክርበት አጋጣሚ/ ፖሲቢሊቲ የለውም። አንደኛው ይሄ ነው ። ሁለተኛው ደግሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሌላው ጋር ይከበራል።

የእኛው ስድአደግ ጋር ነው እንጂ የሚብጠለጠለው ሌላው ግን ክብር አለው። ወጣ ብለንም እንዴት ነው የሚያዩን ብለን እንትን እንሰራለን እኮ ፣ታንዛኒያ ነበርኩ። ለእኛ ሠራዊት ያላቸው ክብር፣ምን አለበት እንዲዚህ አይነት ሠራዊት ቢኖረን የሚሉ ናቸው።ሁሉም ያውቃል። አውሮፓ አሜሪካንም ስለእኛ ሠራዊት ያውቃል። ባለፈው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አማራ ክልል ስንገባ፣የአማራ ሕዝብ ሠራዊታችንን እንዴት እንደተቀበለውና እንዳስተናገደው እናውቃለን። ሕዝቡ ነፍስ አድን እንደመጣለት ነው ያሰበው።

እዚህ ላይ ማንሳት የምፈልገው /ባይዘዌይ/ እዛ አካባቢ የተሰራው የፀጥታ ሥራ የሕዝቡም ሚና ነው። ሁሉ ቦታ እንደዚያ ነው ይምጣልኝ ነው የሚለው። በአማራ ክልል ውስጥ የእኛ ሠራዊት ያለበትና የሌለበት ቦታ አለ። የሌለበት ቦታ ያሉት ጽንፈኛው እንዳይቆጣቸው ተደራጅተው ሌሊት መጥተው እረባካችሁ ለእኛም ሠራዊት መድቡልን ይላሉ። ማን የእነሱን ደህንነትና ፀጥታ ጠብቆ እዚህ እንዳደረሰው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቃል።

ሠራዊቱን እንደ ዋስትና ነው የሚያየው።የኢትዮጵያን ሠራዊት እንደዋስትና የማያዩ ኢትዮጵያውያን ካሉ ንቅል ናቸው፤ ስድአደግ ናቸው፤ እንደገና ደግሞ ቅጥረኛ ናቸው። የእኛ ሠራዊት የተከበረ ነው። ለእኛም ሠራዊት መድቡልን ይላሉ። ማን የእርሱን ደህንነትና ጸጥታውን ጠብቆ እዚህ እንዳደረሰው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቃል።

የትም ስፍራ ብትሔድ የተከበረ ነው። ዩናይትድ ኔሽን ቢኬድ የተከበረ ነው። አሜሪካ ብትሔድ የተከበረ ነው፤ አረብ ሀገር ብትሔድ የተከበረ ነው። በአፍሪካ በሙሉ ብትሔድ የተከበረ ነው።

እንዴት ነው የምትገነቡት? ብለውም እየጠየቁን ነው። ይህ ተቋምም ሆነ ወታደር ብርቅዬ የኢትዮጵያ ሀብት ነው። እናም እኛ ሀገር በዚህ አራትና አምስት ዓመት ያጋጠመን አይነት ውጥንቅጥ፣ ችግር፣ እርስ በእርስ መገፋፋት፣ እርስ በእርስ መናናቅ፣ ኹከት፣ ግርግር፣ በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ ምክንያት ተደርጎ የተፈጠሩ ግጭቶች በሙሉ እያንዳንዱን እንደየአመጣጡ አምክኖ እዚህ ያደረሰው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ነው።

እንደዚህ የምለው እኔ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አዛዥ ስለሆንኩ አይደለም። መሬት ላይ ያለው ሐቅ እሱ ነው፤ እሱን መቀበል ነው። ተወው፤ ስለእኛ ምንም አይንገረን። ተበተኑ፤ ተጣሉ ለሚለው ነገር ጆሮ አንሰጥም። ይልቁኑ እኛ የሚመጣው ዘመን የቴክኖሎጂ ነው፤ ሀገራችን ያድጋል፤ ሕዝባችን ይበዛል። ጠላት ሊበዛ ይችላል። ስለዚህ የዛሬ 15 እና 20 ዓመት ማድረግ ያለብን ምንድን ነው በሚለው ላይ ነው ራሳችንን ያስጨነቅነው ፣ ማንም መንገደኛ የሚያወራው ወሬ ስሜት አይሰጠንም። ልካችንን፣ ቦታችንና ችሎታችንን እናውቃለን።

እንደ ኢትዮጵያ አይነት ሠራዊት አሁን ዓለም ላይ አለ ብዬ አላምንም። ብዙ ሚሳዔል፣ ብዙ ጄት፣ ብዙ ትጥቅ፣ ብዙ ደመወዝ የሚከፈለው ወታደር ሊኖር ይችላል። የኢትዮጵያ አይነት ግን ተልዕኮውን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መፈጸም የሚችል ፤ ችግር ተቋቁሞ፣ ሀገሩን አስቀድሞ፣ ራሱን አርክሶ የሚሰራ የለም። እኛ ሠራዊታችንን የምንገመግመውና የምንለካው እንደዚህ ነው። እንደገና ደግሞ ሁልጊዜ ስለ ሠራዊታችን ውስጣዊ ሁኔታ እያየን፣ እያስተካከልን፣ እየገነባን፣ እያጠናከርን ስለምንሔድ እነዚህ ሰዎች ሲያምራችሁ ይቅር መባል አለባቸው።

አልሸባብ የኢትዮጵያ ስጋት አይደለም። እንደገና እኛ በጣም ተወጥረን ፣ በጣም ተለጥጠን፣ እንዲያው አቅም አንሶን፣ እዚህ ተጠምደን ሌላው የሚገባብን ሀገር አይደለም። መስጋት አይገባም።

ጥያቄ ፦ እርስዎን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የወታደራዊ ዲፕሎማሲ ጉዞ ላይ ነበራችሁ። የእነዚያ ጉዞዎች ዓላማ ምንድን ነው? የተገኘውስ ውጤት ምን ይመስላል?

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ፡- ምን መሰለህ? ቅድም እንዳልኩህ ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በዓለም ላይ በጣም ተፈላጊ ሆኗል። ሰው እኛ ዘንድ ወታደር ማሰልጠን ይፈልጋል። ኦፊሰር ማሰልጠን ይፈልጋል፤ ፓይለት ማሰልጠን ይፈልጋል፤ ከባድ መሳሪያ ምድብተኛ ማሰልጠን ይፈልጋል። የእኛ ሠራዊት የግንባታ እሴት ይፈልጋል።

ከዚህ የተነሳ እኛን ይጋብዙናል ፤ባላቸው ይደግፉናል።

የአንተን ወዳጅነት ፈልጎ፣ ከግማሽ በላይ ሔዶ ሲጠራህ አቤት የማትል ከሆነ ራስህ አትሸጥም ማለት ነው። እኔ በአሁኑ ወቅት እኛ ዘንድ ና፣ እኛም ዘንድ ና፣ ከእኛም ጋር እንነጋገር፣ ከእኛም ጋር እንደራደር፣ ከእኛም ጋር እንፈራረም የሚል ጥሪ በዝቶብኝ ተቸግሬያለሁ። ቁጥር ስፍር የለውም።

ለምንድን ነው? ቢባል ኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር ያለ ነገር ወደእነርሱ እንዲተላለፍ ይፈልጋሉ። ስለዚህ ይጋብዙናል። የታንዛኒያ ጥሪ የተደረገልኝ መስከረም ወር ላይ ነው። አልችልም እያልኩና እያራዘምኩ ሁለቴ ደብዳቤ ጽፈን አራዝመናል። ስናራዝም ቆይተን ባለፈው ጊዜ ሲመቸን ሔደናል። ሔደንም ጥሩ ስምምነት አድርገናል።

ጥሩ የመተባበር፣ ልምድ የመቀሳሰም እና የመቀያየር፣ የስልጠና ፣ የጥገና ስምምነት አድርገናል። ይበልጥ እነርሱ ከእኛ ይፈልጋሉ። ታንዛኒያ ደግሞ ለኢትዮጵያ በጣም ክብር ያላት ፣ ኢትዮጵያን የምትወድ ሀገር ናት ። ሕዝቡም አመራሩም። ታሪካዊ ነገርም አለው። አቀባበላቸውም ግሩም ነበር። እንደዛ የሚቀበሉት ቺፍ ኦፍ ስታፍ የለም።

እኛ በአሁኑ ጊዜ በጣም ተፈላጊ ነን። መካከለኛው ምሥራቅ ያሉ ሀገሮች ድሮ ከእነርሱ የሚወሰድ ነገር ይኖራል የሚል አተያይ የላቸውም። በአሁኑ ወቅት ግን በወረፋ ማስተናገድ ነው ያቃተን። ሚሊታሪ ዲፕሎማሲው እኛ ከተዘጋጀንበት በላይ ሆነ። ሚሊታሪ ዲፕሎማሲው የሀገር ገጽታ ለመገንባት ያግዛል።

ታሪካችንን ለማሳወቅ፣ ወዳጅ ለማብዛት፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ከኛ ጋር እንዲቆሙ ለማድረግ ያግዛል። የማትተዋወቅ ከሆነ ዓለም አቀፍ መድረክም ስትሄድ ወዳንተ ጫና ቢመጣ የት ያውቅሀል። ለሚያውቀው ነው እጅ የሚያነሳው። እንዲያውም ብዙ አልሰራንም። እኛ በምንፈልገው ልክ ገና አልሰራንም።

የታንዛኒያ ጉብኝት በጣም ፍሬያማ ነበር። ጥሩ ሥራ ሠርተን ተመልሰናል። እንዲያውም እነርሱ እዚያ እንድንቆይ የፈለጉት ለአስር ቀናት ነበር። እኛ ለአራት ቀናት እንዲያደርጉልን ጠይቀን ነው የመጣነው። ሀገሪቱ እያደገች ፣ ተስፋ ያላት ሀገር እየሆነች ነው። ከእንደዚህ አይነት ተስፋ ካለው ሀገር ጋር መተሳሰር ጥሩ ነው።

ተስፋ ከሌለው ሀገር ጋር መተሳሰር ሊጎዳህ ይችላል። ተስፋ ካለው፣ አንተን ከሚፈልግህ፣ ካንተ የሆነ ነገር አገኛለሁ ብሎ ከሚያስብ፣ ለአንተ እውቅና ሰጥቶ ከሚያስብ ሀገር ጋር የሚሊታሪ ዲፕሎማሲ ማድረግ በጣም ያስፈልጋል፤ ይሄ ደግሞ ለሚሊታሪው ብቻ አይደለም ፤ ለሀገሪቱ በሙሉ የሚጠቅም ነገር ያስገኛል።

አሁን እኛ የገባን ምንድነው፤ አንደኛ ራሳችንን እናውቃለን ፤ ሁለተኛ ብዙ ሀገሮች የኛ ወዳጅ መሆን ፣ ከኛ መማር እንደሚፈ.ልጉ ፣ እነርሱ ጋ እኛ ያላወቅነው የሆነ ነገር እንዳለ ተረድተናል።

ጥያቄ ፡- ይህን ቃለ ምልልስ እያደረግን ያለነው የኢትዮጶያን የአየር ክልል በሚያስጠብቀው በኢፌዲሪ አየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ግቢ ውስጥ ነው። እርስዎ እዚህ ግቢ የተገኙበትን አጋጣሚ ምንድን ነው ?

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፡- ባለፈው የ116 ኛውን የመከላከያ ሠራዊት በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ አክብረናል። የኢትዮጵያ ሠራዊት በዚህን ቀን ነው የተመሰረተው፣ የሠራዊቱ እድሜ አሁን 116 ዓመት ደርሷል። ኢትዮጵያ አሁን ተጠፍጥፋ የተሰራች ወይም ኢህአዴግ ጠፍጥፎ የሰራት ሀገር አይደለችም፤ ታሪክ ያላት ሀገር ናት። ሠራዊቱም የተመሰረተበት፣ የጀመረበት ታሪክ አለው።

ሠራዊቱ ከትውልድ እየተወራረሰ የመጣ እሴት ፣ አርበኝነት ያለው ነው ፣ በዚህን ጊዜ የተመሰረተ፣ እየቀጠለ የመጣ፣ ሀገርን እየተከላከለ እዚህ ያደረሰ፣ አባቶቻችን ዋጋ የከፈሉበት ሠራዊት ነው ።ይህን አስተሳሰብ ይዘን፣ ሪፎርም ሰርተን 116ተኛ ዓመቱን ለመጀመሪያ ጊዜ አክብረናል።

በኢህአዴግ ዘመን አዲስ ሕገመንግሥት መጣ። የሠራዊቱም ቀን ሕገመንግሥቱ ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ ነው መከበር ያለበት ተብሎ ሰባት ዓመት በተከታታይነት በተለያየ መንገድ ሲከበር ነበር። እሱ ልክ አይደለም፤ እሱ ሀገር አይወክልም። የኢትዮጵያ ሠራዊት በ1987 ዓ.ም አይደለም የመጣው።

ከዚያ በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ሠራዊት ድክመት ሊኖረው ይችላል። ግን ደግሞ ጥንካሬም አለው፤ ሀገር ጠብቋል፤ ሀገር አቆይቷል፤ እኔ ጋ አድርሷል። አባቴ እኮ ነው እዛ ያለው። አባቴ አያቴ … ነው እዛ ያለው። ይሄ መታየት አለበት። ይሄ ሀገር ነው፤ ታሪክ አለው፣ ሠራዊት አለው።

የእኛ ሠራዊት ሲፈጠር ዓለም በቅኝ ግዛት ስር ነበር። ያን ጊዜ ከቅኝ ግዛት ነጻ የነበሩ ሀገሮች ናቸው እንጂ ሠራዊት የገነቡት፤ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ ሀገሮች ሠራዊት አልነበረባቸውም። በጣም የተወሰኑ ሀገሮች ናቸው ሠራዊት የነበራቸው። ከዚያ ከተወሰኑ ሀገሮች መሀል አንዷ ኢትዮጵያ ናት። ስለዚህ ይሄ የሠራዊት ግንባታ ሪፎርም ነው።

የአንተ አባት አርበኛ ነው። ኢትዮጵያውያን አርበኞች ናቸው። አንተ የአርበኛ ልጅ ነህ። ሀገርህን ጠብቅ ፣በአርበኝነት ለልጅህ አስረክብ ልለው ከሆነ ታሪክ መኖር አለበት። ታሪኩ ደግሞ አለ። ታሪኩን ኢግኖር አድርጌ /አላየሁም አልሰማሁም ብዬ/ መሄድ የለብኝም። የመጣ ሁሉ የተገነባውን የሚያፈርስ ከሆነ ልክ አይደለም። ስለዚህ ያከበርነው በዛ ምክንያት ነው። እሱን እንቀጥልበታለን።

መከላከያ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ብዙ ሰው አይረዳውም። መከላከያ አራት ኃይሎች አሉት። አንዱ አየር ኃይል ነው። አንዱም ምድር ኃይል ነው። አንዱ ባህር ኃይል ነው ፤ አንዱ የሳይበር ኃይል ነው። ምናልባት ምድር ኃይሉ ደግሞ የተለያየ ነው። ሜካናይዝ ነው፤ ስፔሻል ፎርስ/ ልዩ ኃይል/ ነው፤ ኮማንዶ ነው። እግረኛ ነው፤ ወዘተ.። ኃይሎቹ እንደዛ ናቸው።

አየር ኃይል የመከላከያ አንድ ኃይል ነው። ስለዚህ አየር ኃይልም ታሪክ አለው። ምድር ኃይልም ታሪክ አለው። ባህር ኃይልም ታሪክ አለው። ስለዚህ የመከላከያ ቀንን ካከበርን በኋላ ቶሎ የምስረታ ቀኑ የደረሰው አየር ኃይል ነው። አየር ኃይል ከተመሰረተ ዘንድሮ 88ኛ ዓመቱ ነው። ይህ 88 ዓመት ተከብሮ አያውቅም። ድሮ በንጉሱ ጊዜ ኤይር ፎርስ ዴይ /የአየር ኃይል ቀን / ተብሎ ስለመከበሩ አላውቅም ፤ በዚህ ላይ ብዙ ሰነድ አላገኘንም። ነገር ግን አየር ኃይል የተመሰረተበት ጊዜ ይታወቃል። ታሪክ ፤ሰነድ አለ።

በዚህ መሰረት ለመጀመሪያ ጊዜ በደማቅ ሁኔታ አየር ኃይል የልደት በዓሉን የአየር ኃይል ቀን የሚያከብርበት ቀን ስለደረሰ ለዛ በዓል እየተዘጋጀን ነው። የበዓሉ ዝግጅት የት ደረሰ? በሚለው ላይ ከአየር ኃይል አመራሮች ጋር ለመነጋገርና ዝግጅቱንም ለማየት ነው በአጋጣሚ እዚህ የመጣሁት። ቅዳሜ ነው በዓሉ፤ እናንተም ተገኙ።

ጥያቄ፡-ለአንባቢዎቻችን የሚያስተላልፉት ተጨማሪ መልእክት ካለ

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ፡- ኢትዮጵያ ብዙ ጠላቶች አሏት። ኢትዮጵያ እንዳታድግ የሚፈልጉ አሉ። ኢትዮጵያ ደግሞ የማደግ ዕድሏ በጣም ከፍተኛ ነው። አሁን ትምህርት እየተስፋፋ ነው። የወጣት ሀገር ናት። ብዙ ሀብት ያላት ሀገር ናት። ከመሬት ያልወጣ ሀብት አላት፤ ይህ ሀብት ሁለገብ /ብዙ አይነት/ ነው፤ አንዳንድ ሀገሮች በማዕድን ብቻ፣ ወይ በእርሻ ብቻ፣ ወይ በኢንዱስትሪ ብቻ፣ ወይ በቱሪዝም ብቻ ሀብት የሚኖሩበት ሁኔታ አለ። እንደዛ አይነት ሀገራት አሉ።

የእኛ ሀገር ግን ሁሉም አላት። በቱሪዝም ብትለው ተመራጭ ናት። ግብርና ብትለው የሚገርም ነው። የውሃ ማማ ናት። የመሬት ጥበት የለባትም። ማዕድንን እግዚአብሔር ሰብስቦ ያስቀመጠባት ትመስላለች።

ይህ ሁኔታ ባለበት ሁሉም ብድግ ብሎ ስልጣን ላይ ጉብ ማለት ይፈልጋል። ከዛ መዝረፍ፤ ሀገር ለማልማት እኮ አይደለም ለመዝረፍ ነው። ኢህአዴግ ያን ሁሉ የጦርነት መከራ አልፎ መጣና ስልጣን ያዘ። በኋላ ምን አደረገ? ሀገሪቱን መዝረፍ ብቻ ሳይሆን አጠባት። ደርግም መጣ፤ እሱስ ምን አደረገ? ከአንዱ ቀውስ ወደ አንዱ ቀውስ ሆነ፤

ፈረንጆች እኮ ታዝበውናል። ይሄ ሕዝብ በቃ የራሱን መንግሥት ከመቃወም ውጪ ሌላ ሙያ የለውም እንዴ ተብለናል፤ ፈረንጆቹኮ ሲያገኙን እንደዛ ነው የሚሉን። ሁል ጊዜ፤ መች ነው ይህን አቁመን ዓለም የደረሰበት የምንደርሰው?

እኛ 60 ዓመት ስንዋጋ፣ 60 ዓመት የሚበላው የሌለው ሀገር ዛሬ የት እንደደረሰ አይተናል። የዛሬ 60 ዓመት ኢምሬት የምትባለዋን ሀገር ታሪክ ሰምታችሁ ከሆነ ኢትዮጵያ እርዳታ ትሰጣት ነበር። አሁን ዓለም የሚራኮትበት ሀገር ሆናለች። ይህን 50/ 60 ዓመት እነርሱ እየተጣሉ አይደለም ያሳለፉት፤ እያለሙ፤አዳዲስ ነገር እየፈጠሩ፣ ራሳቸው ብቻ ሳይሆን የዓለም ሕዝብ እንዲያከብራቸው እንዲነግድባቸው ነው ያደረጉት። ግጭት አልነበረም፤ ይሄው አመለጡ።

ቻይና ምንድነው የነበረችው? አሁን ወደዬት ነው እየተንደረደረች ያለችው? እነ ሲንጋፖር፣ እነ ቬትናም ምንድነው የነበሩት? አንዳንዴ የእኛ ሕዝብ ስለምንድነው የሚያስበው ስል አስባለሁ፤ ብቻዬን የሆኑ ሰዎችን አመለካከት ጠባይ እና የመሳሳሉትን አይና ምንድነው እኛን የነካን የሚል ነገር ይሰማኛል።

ምንድነው ይሄ የግጭት አስተሳሰብ የወረረው ማህበረሰብ ? ስለብልጽግና የማያስብ፣ ስለፈጠራ የማያስብ፣ ከሌላው ወደ ኋላ በመቅረቱ የማይናደድና የማይጸጽተው፣ ጫማ የሌላቸውን ዘመዶቹን ገጠር አስቀምጦ እሱኑ እንደገና ወደ ግጭት ለማስገባት የሚሰራው የሚል ነገር ይሰማኛል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ማሰብ መጀመር አለበት። ቆይ እሺ፤ ኃይለስላሴ መጥፎ ሆኑ፤ ቀየርናቸው፤ ደርግ መጣ፤ ፋታ አልሰጠነውም ፤ቀየርነው። ኢህአዴግ መጣ ፤ፋታ አልሰጠነውም፤ ቀየርነው። አሁን ሌላ አዲስ መንግሥት መጣ፤ እንዲያውም ሦስት ዓመት ሳይሰራ ገና በመጀመሪያው ዓመት ለመቀየር ሠራን፤ ይሄው አሁንም እንዋጋለን።

ይህንንም ከቀየርን በኋላ እርግጠኛ ነኝ እንዋጋለን። ተሳክቶ ይህንን መንግሥት ከቀየርነው ሌላም ቢመጣ እንዋጋለን፤ አትጠራጠር። ይሄ ባህሪያችን ሆኗል። የሦስት ሺ ዓመት ታሪክ አለን እንላለን። የሦስት ሺ ዓመት ቀርቶ የ50 ዓመት ታሪክ ያለንም አንመስልም፤ በ50 ዓመት እኮ ነው የተባበሩት ኢሜሬት የተከበረ፣ የበለጸገ የለም ሀገር የሆነችው። ዓመት መቁጠር ምን ይጠቅመናል? እንደ እድሜያችን እኛ እኮ የዓለም መሪ ነው መሆን የነበረብን።

መቀየር ነው በቃ። ቴዎድሮስ መጣ፤ ያልዘመተበት የለም። ዘመነ መሳፍንት ብለን ስንት መቶ ዓመት በጨለማ ስንዋጋ ኖርን። ሁልጊዜ ጦርነት ነው። ኧረ ይብቃ።

እኔ ወታደር ነኝ ፤የሠራዊት አዛዥ ነኝ። በፍጹም ጦርነት አልፈልግም። ምክንያቱም ጦርነት ውስጥ እኔ የማዛቸው ወታደሮቼ ይቆስላሉ፤ ይሞታሉ፤ ይህ ይሰማኛል።

ሀገሬ ሰላም እንድትሆን ሁሉም ሰርቶ እንዲኖር እፈልጋለሁ። ከመጣ ግን የግድ ነው። ሀገር እስኪፈርስ እኔ ቁጭ ብዬ ማየት አልችልም። ግን መቆም አለበት። የደም ነጋዴዎችን የኢትዮጵያ ሕዝብ መቀበል የለበትም፤ መነዳት የለበትም፤ መንጋ መሆን የለበትም። እነሱን አያደፋፈረ ያለው እሱ ነው። ተከታይ ቢያጡ አለቀላቸው። ጀግና ጀግና የሚል፤ የሚያዳንቅለት፣ የሚደጉም ስለበዛ ነው። እና ይሄ ቢበቃው ጥሩ ነው።

ካሁን በኋላ በዚህ ሀገር እንደድሮው እያጋጨሁ የበላይነቴን ይዤ እቀጥላለሁ የሚል እሳቤ አይሰራም። አሁን አወቃቀሩ መጥፎ ነው። አሁን እንደ ድሮው አንዱ ግራዝማች አንዱን ገፍቶ ወደ ሥልጣን መጥቶ ጉብ ሊል አይችልም። እንደዛ ሊሆን አይችልም።ይህ አስተሳሰብ ሀገር ያፈርሳል።

ምክንያቱም እያንዳንዱ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን ሥልጣን እና መብት አግኝቷል። ክልሉን ቀጣናውን ያውቃል። ሁሉም ጠመንጃ አለው፤ እናም ፈራሽ ነው። ካሁን በኋላ በጠመንጃ መጫወት ኢትዮጵያን ብትንትኗን ያወጣታል። ይሄ እንዳይሆን ይበቃል መባል አለበት እላለሁ። ይሄ ኔጌቲቭ ቲንከሩ /አሉታዊ አስተሳሰብ/ አራማጁ ኤሊት በቃህ ሊባል ይገባል። ፖዘቲቭ ቲንክሩ /አዎንታዊ አስተሳሰብ አራማጁ/ ኤሊት ደግሞ ሊደገፍ፣ ሊበረታታ ይገባል የሚል ሃሳብ አለኝ።

እኔ ሰዎችን በራሴ አራት ቦታ እከፍላቸዋለሁ። አንደኛው የዋህ፣ ደግና ጀግና ነው። ይሄ ሰው የዋህ ነው፤ ደግ ነው፤ ጀግና ነው ፤ ሀገሩን ይወዳል፤ ለሀገሩ ይሞታል። እንደዚህ አይነት ሰዎች አሉ። ሁለተኛው ደግነት በመጠኑ፤ ከፋትም ያለው ሰው ነው፤ ወደነፈሰበት እየነፈሰ የሚኖር ሰው ነው። ሶስተኛው ክፉ ሰው አለ። ክፉ፤ ለምንም የማይሆን፤ ነጌቲቭ ቲንከር / አሉታዊ አስተሳሰብ ያለው/ አለ ብዬ እወስዳለሁ። አራተኛ ብልህ ሰው አለ፤ /ቅደም ተከተሉን ልትገለብጠው ትችላለህ።/ ብልህ ሰው፣ ሀገሩን የሚወድ ሰው፤ ለሀገሩ ማንኛውንም ነገር ያደረገ፤ ታሪክ ሰርቶ ያለፈ አለ። እንደነዚህ አይነት ሰዎች እዚህ ሀገር ላይ እንዳሉ ይታየኛል።

ከሁለተኛው ይሁን፤ ከሶስተኛው አይነት ሰው ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ መጠበቅ አለበት። ነጌቲቭ ቲንከር/ አሉታዊ አመላካከት ያለው/ የሆነ ሰው ሁልጊዜ ክፋት ይሰራል፤ ይጠራጠራል፣ ያዋጋል፣ ያጣላል፤ አይሞትም፣ ያስገድላል፣ ይበላል፣ ይኖራል፣ ይሞታል። እንደዚህ አይነት ሰዎች አሉ።

መልዕክቴ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይበቃናል የሚል ነገር መጀመር አለበት። ይሄ መነዳት መቆም አለበት። ከሞላጫ፣ ከአጭበርባሪ፣ ከማይሞት፣ ከሚያስገድል፣ ከምላሰኛ፣ ምንም ከማይችል ራስን መጠበቅ ይገባል። ከየዋሆቹ፣ ከጀግኖቹ በተለይ መጀመሪያ ላይ ያስቀመጥኳቸው ሰዎች ከራሳቸው በላይ አንተ ስትጎዳ ካዩ ልባቸው ይሰበራል። ለሰው፣ ለሀገር የሚኖሩ ናቸው። እንደነዚህ አይነት ሰዎች አሉ። እንደነዚህ አይነቶቹን ያብዛልን መባል አለበት።

ሁለተኛው አይነት ሰው አይጎዳም። በከፊል ነጌቲቨ ቲንከር፣ በከፊል ፖዘቲቭ ቲንከር ስለሆነ ነው። እሱ ደግሞ ነገሮችን ባላንስ አድርገን እንድናይ ይረዳናል። ሶስተኛው አይነት ሰው አደገኛ ነው። እሱ ነው የህብረተሰቡ ዝቃጭ ክፍል የምንለው፤ እሱ ነው፤ ለሀገሩም፣ ለእህቱም፣ ለወንድሙም፣ ለአባቱም፣ ለእናቱም ጠብ የሚል ነገር የማያበረክት። እንዳውም የሚያባላ እሱ ነው። ከእንደዚህ አይነቱ እንጠንቀቅ ። አራተኛው አይነት ሰው ላይ ትኩረት እናድርግ ፤እንደግፈው ፤ ሀገራችን ይበቃታል፤ ከዚህ የጥፋት አዙሪት እንውጣ የሚል መልዕክት አለኝ።

ክቡር ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹምና ወደር የሌለው የጥቁር አንበሳ ጀግና ሜዳይ ተሸላሚ ካለቦት ከፍተኛ ኃላፊነት አንጻር ለኛ ብለው ጊዜዎትን ሰውተው ከኛ ጋር ቆይታ ስላደረጉ ከልብ እናመሰግናለን።

ፊልድ ማርሻል ብርሁኑ ጁላ ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You