የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሰሞኑን አጠቃላይ በሆነው የሀገር ሰላም እና ደህንነት ዙሪያ ለጋዜጠኞች የሰጡትን መግለጫ የመጀመሪያ ክፍል በዛሬው እትማችን ይዘን ቀርበናል።
ጥያቄ፡- በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሸኔ የተለያዩ አካላት የተለያየ ስያሜ ይሰጡታል፤ ይሄ በሠራዊቱ መካከል እንዴት ይታያል ?
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ፡– እኛ ለስያሜ ብዙ ትኩረትና ዋጋ አንሰጥም። በስያሜው ላይ ከመጨቃጨቅ ይልቅ ተግባር ላይ ምን አይነት ኃይል ነው፣ ምን አይነት ሥራ እየሠራ ነው፣ ምን እያደረገ ነው፣ የሚለው ላይ ነው ትኩረት የምንሰጠው። ቡድኑን ግማሹ ኦላ ይላል፣ ግማሹ ኦነግ ሸኔ ይላል፣ ግማሹ ሸኔ ይላል፤ ይሄ ምንም ዓይነት ጥቅም የለውም። የፈለገ ይሁን ስሙ እያንዳንዱ ሰው መጠርያውን ሲያወጣ የራሱ የስም መነሻ አለው።
ኦላም የራሱ መነሻ አለው፣ ኦነግ ሸኔም የራሱ መነሻ አለው። ሁላቸውም መነሻ አላቸው። ቡድኑ አሁን ላይ ትልቁ የሀገሪቱ የጸጥታ ችግር ፈጣሪ ነው ፤ ስሙ እንደዚህ ነው፤ ስሙ እንደዚህ ነው በሚለው ላይ ጊዜ ማጥፋት የለብንም። በፈለገው ይጠራ የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ።
ድርድሩን በተመለከተ ድርድር የኢትዮጵያ ሕዝብም መንግሥትም ይፈልጋል። በነሱ በኩል ይፈልጉታል አይፈልጉትም በደንብ ሊታይ ይችላል። የመጀመሪያው ድርድድር ሕዝቡ፤ የፖለቲካ ኤሊቱ እና መንግሥት ስለፈለገው ነው የተደረገው። ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ኤሊቱ፤ መንግሥት የሚፈልግ ከሆነ ለምን አንነጋገርም በሚል ታስቦበት የተሠራ ነው።
በተለይ ከቲፒ ኤልኤፍ ድርድር ጋር በተያያዘ ያኛውንም በሰላማዊ መንገድ ከፈታን ይሄንንም ከተቻለ ለምን አንፈታውም የሚል ሙሉ ፍቃደኝነት ነው የነበረው። በዚያ ምክንያት የመጀመሪያ ንግግር እንዲደረግ ተደርጓል። የመጀመሪያው ንግግር ጥሩ ርቀት ሄዶ ነበር፣
ጥሩ ርቀት በመሄዱም ብዙ መካሰስ ቀርቶ ፤ ለሚቀጥለው ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ቀጣይ ሁለተኛ ዙር እናመቻች በሚል ነው ተደራዳሪዎቹ የተለያዩት። ሁለተኛ ድርድር ላይ መጀመሪያ የሆነ አግባቢ ቡድን፤ ከሁለቱም ወገኖች በመጀመሪያው ዙር የተሳተፉ እና ሌሎችም ተጨምረው ነው የሄዱት።
ድርድሩ ከሳምንት በላይ ነው የፈጀው። አዝማሚያው ጥሩ ነበር። በመጨረሻ ላይ የማያግባቡ ነጥቦች መጡ፣ የማያግባቡ ነጥቦች ሲመጡ እንደገና የማያግባቡ ነጥቦችን ለመፍታት ትንሽ የተሻለ አቅም ያለው ሰው ይምጣ ተባለና ከነሱም የተሻለ የተባለው ሰው መጣ። ከኢትዮጵያም መንግሥትን የሚወክሉ ሰዎች ሄዱ፣ ሂደቱ ጥሩ ሄዶ ነበር።
መጨረሻ ለሕዝብ ይፋ የሚሆንበት ደረጃ ላይ (ወደ ሰነድ) ከደረሰ በኋላ ያልተጠበቁ ጥያቄዎች ተነሱ። ያልተጠበቁ ጥያቄዎች ማለት/ ለመደራደር የሀገሪቱን ሕገመንግሥት የግድ መቀበል ይጠይቃል፣ የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት ሳትቀበል ድርድር የሚባል ነገር የለም። እሱን ተቀብለህ በእሱ ጥላ ስር ግን መነጋገር መደራደር መወያየት ይቻላል የሚል መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር ።
ሆኖም በመጨረሻም መጀመሪያ የተግባቡበት ነጥብ የሚያፈርሱ ጥያቄዎች መጡ። ትግል እናደርጋለን እየተባለ ያለው ለኦሮሞ ሕዝብ መብት ነው፣ የኦሮሞ ሕዝብ መብት ከዚህ በፊት ልክ ነው ተገፍቶ ነበር፣ የኦሮሞ ሕዝብ የመሬት ጥያቄ ነበረው፣ የመሬት ጥያቄ የኢኮኖሚ ጥያቄ ነው፣ ይሄንን ጥያቄ ደርግ መልሶታል፣ ሁለተኛ ብሔራዊ ጥያቄ ነበረው ኢሕአዴግ ሲመጣ መልሶታል። ማንነት አለኝ የሚለውን ማህበረሰብ የራሱ ክላላዊ መንግሥት እንዲያቋቁም ተደርጓል። ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ተደርጓል፣ ራሱን በራሱ እንዲመራ ተደርጓል።
በኢሕአዴግ ጊዜ የነበረው የመቆጣጠር ችግር ነው። የመቆጣጠር ማለት ጣልቃ የመግባት፣ የክልሎችን አመራሮች በራሱ በማዕከላዊ መንግሥት መቀየር ማለት ነው፣ በዚህ ውጣ በዚህ ግባ የማለት አይነት ችግሮች ነበሩ። የኦሮሞ ሕዝብም ሆነ ሌላውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ለውጥ ጥያቄና ትግል እንዲያመራ ያደረገው እሱ ነው።
እሱ ደግሞ ከለውጥ በኋላ እውነት ለመናገር መቶ በመቶ ተመልሶ ያደረ ጉዳይ ነው፣ በዚህ ውጣ በዚህ ግባ የሚል ተቆጣጣሪ የለም፣ ክልሎች ራሳቸውን ችለው የራሳቸውን የውስጥ ጉዳይ ራሳቸው እየጨረሱ ነው፣ እያስተዳደሩ ነው፣ እየመሩ ነው። ማዕከል ላይ ሆኖ ፌዴራል ስቴቶቹን የሚቆጣጠር ኃይል የለም።
ኦሮሚያ ክልል ጨፌ አለው፣ ካቢኔ አለው፣ ፕሬዚዳንት አለው፣ መዋቅር አለው፣ በጀት አለው፣ ገቢ ይሰበስባል፣ ከፌዴራል የሚደጎም ከጋራ የሚሰበሰብ ገቢ ይካፈላል፣ ማንኛውንም እቅድ ራሱ እያወጣ ይሠራል፣ በዚህ ግባ በዚህ ውጣ የሚለው የለም። የክልሎች ፕላን እንደየክልሎቹ ፍላጎት ነው እንጂ የተማከለ አይደለም።
አንዱ ኢኮኖሚውን በዚህ መልኩ ብሰራው ጥሩ ነው አድጋለሁ ይላል፣ አንዱ በዚህ መንገድ ብሰራው ቶሎ አድጋለሁ ይላል ፣ ስለዚህ ነፃነት አለ ማለት ነው፣ የክልል መንግሥታት ነፃነት አለ። አንዱ በለውጡ የታረመው ኢሕአዴግ የሚያደርገው የነበረ የክልሎች ጣልቃ ገብነት እንዲቆምና ለውጡ እንዲመጣ ያደረገው ይህ ጥያቄ ስለነበር ይሄ እንዲቆም ተደርጓል።
ክልሎቹ በራሳቸው ቋንቋ ይጠቀማሉ። ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድራሉ። የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ማለት ይሄ ነው። ይሄ ተረጋግጧል። እዚህ ላይ ጥያቄ የለም። በሸኔ በኩል እዚህ ላይ ‹‹ይሄ ጎደለ›› የሚለው ነገር የለውም። ስለዚህ የብሔራዊ ማንነት ጥያቄ አልተገሰሰም። ከልሎች፣ ብሔሮች ሙሉ መብት አላቸው። እራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ማለት ነው። እንግዲህ ይሄ ተመልሶ ያደረ ነው። ኢህአዴግ በከፊል መለሰው፣ በአወቃቀር፣ በአደረጃጀት በሕገመንግሥት መለሰው፣ ግን ጣልቃ እየገባ ክልሎቹን ጠቅላይ ግዛት አደረጋቸው። እና እሱ ነው አመጽ የፈጠረው።
ከለውጡ በኋላ ደግሞ ይሄ የጠቅላይነት አስተሳሰብ ቀርቷል። ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚባል ደረጃ ተግባራዊ እየሆነ ነው። ስለዚህ የመሬትን ጥያቄ ደርግ መልሶታል። የብሔር ጥያቄን ኢህአዴግ በከፊል መልሶታል። የለውጥ መንግሥት ደግሞ ኢሕአዴግ ያጎደለውን ሞልቶ መልሶታል።
ስለዚህ ምንድነው ጥያቄው ነው። በድርድሩ ላይም እዚህ ላይ የተነሳ ነገር አልነበረም። ስለዚህ ወደ ትጥቅ ትግል የሚወስድ ጭቆና አለ ተብሎ አይወሰድም። የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ የታገለለት የመሬት ጥያቄ ተመልሷል። የብሔሮች ብሔረሰቦች መብቶች ጥያቄን ኢሕአዴግ በከፊል መልሶታል። የጎደለውን የለውጡ መንግሥት ሞልቶታል።
ስለዚህ ወደ ትጥቅ ትጥቅ ትግል የሚያስገባ መሠረታዊ የማይታረቅ ቅራኔ የለም። ከዛ በመለስ ግን ይሄ ጎደለ፣ ይሄ ጎደለ የሚል ጥያቄ ሊቀርብ ይችላል። ከዛ በመለስ ‹‹ይሄ ጎደለ›› የሚባለው ጥያቄ በትጥቅ ትግል ሳይሆን በንግግር ሊፈታ የሚችል ነው። ስለዚህ ድርድሩ ላይ እንደዚህ አይነት የብሔር ጭቆና የሚገልጥ በኢኮኖሚ፣ በማንነት፣ ራስን በራስ ማስተዳደር የሚገለጽ ጥያቄ አላየንም።
ከዛ በመለስ የቀረቡ ጥያቁዎች አሉ። የቋንቋ ጥያቄ ቀርቧል። የቋንቋን ጥያቄ ይቅርና መንግሥት ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ፣ የኢትዮጵያ ፓርቲዎች ኦሮምኛ የሥራ ቋንቋ መሆን አለበት በሚል መግባባት አለ። ይቅርና ለኦሮሞ ሕዝብ እንታገላለን የሚሉ የኦሮሞ ሕዝብ መብት ሳይሆን በሌላ መንገድ የሚታገሉት ራሳቸው የሚቀበሉት ነው። መሠረታዊ መብት ስለሆነ የሚቀበሉት ነው። ሌሎች ፓርቲዎችም ይቀበሉታል።
ይሄ በጣም የሚያጣላ፣ ጠመንጃ የሚያስነሳ፣ ወደ ጫካ የሚያስገባ ነገር አይደለም። መንግሥት ደግሞ ጀምሮታል። ኦሮምኛ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ሰፋ ሰፋ ያለ ሕዝብ ያላቸው ቋንቋዎች መነገር አለባቸው ተብሎ በፓርቲ ደረጃ የተጀመረ መሰለኝ።
ይህን ማድረግ የምትችለው ሕገመንግሥቱን አሻሽለህ ነው። ሕገመንግሥት ሳታሻሽል ሕግ ጥሰህ ኦሮምኛ ቋንቋን አመጣለሁ ማለት ትክክል አይደለም። ሕጋዊም አይደለም። ጉልበተኝነት ነው። ይሄ ግን በሂደት በጋራ ትግል የሚመለስ ነው የነበረው። በሰላማዊ መንገድ ቢታገሉ ሊያስመልሱት የሚችሉት ጥያቄ ነው።
እኔ እንዲያውም ትርጉም ያለው ጥያቄ ያቀረቡት ይሄን ነው ያየሁት። እሱም ቢሆን በጣም ቀላል ጥያቄ መሆኑን ነው የማውቀው ፤ እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የምኖረው፤ የኢትዮጵያን ፖለቲካ እከታተላለሁ፣ የኢትዮጵያን ደህንነት እከታተላለሁ። ስለዚህ ይሄ ጥያቄ ትክክለኛ ጥያቄ ነው፤ ተገቢ ጥያቄ ነው፤ ግን ደግሞ በፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ውስጥ ሊመለስ የሚችል ጥያቄ ነው። ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች የተቀበሉት ፓርቲ ነው፤ ምንድነው እያጋጨ ያለው? ቋንቋ በግድ ማስመለስ ነው እያጋጨ ያለው? ቋንቋ ወደ ትጥቅ ትግል የሚወስድ አይደለም።
ትጥቅ ትግል የምትገባው፤ በጣም ወሳኝ የሆነ የኢኮኖሚ ጭቆና ሲኖር፣ የማንነት ጭቆና ሲኖር፣ እና ያንን በሰላማዊ መንገድ ማሳካት ሳትችል ስትቀር ነው። እኛ የምናውቀው፤ ድሮ ወደ ትጥቅ ትግል የገቡ ኃይሎች እንደዚያ ነው የገቡት። አሁን መነጋገር በሚቻልበት ዘመን፣ የኢኮኖሚ ጥያቄም፣ የማንነት ጥያቄም ተመልሶ ባለበት ሁኔታ ወደ ትጥቅ ትግል የሚወስድ ነገር አለ ብዬ አላምንም።
ጥያቄ ካለ ደግሞ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ሀገር ነው፤ በፓርቲ ተደራጅቶ፣ ሕዝቡን አሳምኖ፣ ተመርጦ፣ ሥልጣን ይዞ የጎደለ ጥያቄ ማሟላት ይቻላል በዚህ በኩል። ሥልጣን ላይ ያለው ኃይል ጎደለ የሚሉትን ነገር እንዲያሟላ መታገል፣ ግፊት ማድረግ ሕዝቡ በእዚያ ዙሪያ ከእነርሱ ጋር እንዲሰለፍ ማድረግ እና መንግሥት እነዚያን ጥያቄዎች እንዲመልስ ማድረግ ነው። ከዚያ ውጭ በመለስተኛ ጥያቄዎች ጫካ አትገባም።
አሁን ብዙ ጊዜ የሚባል ነገር አለ፤ ኦሮሚያ በሀብቷ መጠቀም አለባት የሚል ነገር አለ። ታዲያ ማነው እየተጠቀመ ያለው? እየተጠቀመ ያለው የኦሮሞ ሕዝብ ነው። እንደ ድሮው መሬቱ አልተነጠቀም፤ ጭሰኛ አልተደረገም። እራሱን በራሱ መወሰን አለበት፣ ዕድሉን እኮ በራሱ እየወሰነ ነው! ራስ በራስ ማስተዳደር ማለት መገንጠል ማለት ነው? ራስን በራስ መወሰን ማለት እኮ ራስን መምራት፣ የፈለከውን ማቀድ፣ ተግባራዊ ማድረግ፣ ባህልህን ቋንቋህን ማሳደግ፣ ማህበረሰብህን ኢኮኖሚህን መገንባት ነው። ይሄ ደግሞ እየተደረገ ነው።
ምንድነው ወደ ጫካ ያስገባን የሚለው ራሱ ጥያቄ አለው። ጥያቄ እንዳለ ያረጋገጥነው አሁን በተደረገው ንግግር በዚህ ደረጃ የቀረበ ነገር የለም። የቀረበ ነገር ሥልጣን አካፍሉኝ ነው፤ ጠመንጃ ያለው፣ ጫካ የሚገባው ሥልጣን ለማግኘት ከሆነ ለሀገሪቷ ሰላም አይሰጥም። እንዲህ ጫካ እየገባህ፣ ችግር እየፈጠርክ፣ ሕዝቡን ያልተገባ ዋጋ እያስከፈልክ ፣ እንነጋገር እያልክ፣ እሺ ና እንነጋገር ስትባል ደግሞ ሥልጣን አካፍሉኝ እያልክ ከሄድክ ይሄ ሥርዓት አይደለም። ሀገር የተረጋጋ አያደርግም፤ ሀገር ይጎዳል፣ የውስጥ የእርስበርስ መተማመን ያጠፋል፣ ትክክል አይደለም።
ለምሳሌ፤ አማራ ክልል ታጥቆ ያለ ኃይል አለ፤ እንደራደር ይላል፤ እንደራደር እሺ ሲባል ፤ ሥልጣን አካፍለኝ ካለ፣ ቤንሻንጉል ያለው የጉሙዝ ነፃ አውጭ እንደራደር ብሎ እሺ ሲባል ፤ ሥልጣን አካፍለኝ ካለ፣ የጋምቤላም እንዲሁ ካደረገ ለስንት የታጠቁ ኃይሎች ሥልጣን በመከፋፈል ይኖራል ፤ ይሄ ኢትዮጵያን በጣም የሚጎዳ ወደ ኋላ የሚያስቀር ነገር ነው፤ እንደዚህ አይነት ጥያቄ ነው የቀረበው።
ንግግሩ ብዙ ቀናት ፈጅቷል። ብዙ ቀናት የፈጀውም ከፍተኛ የሆነ ያለመረዳት “የሚስ አንደርስታንዲንግ” ችግር ስለነበረ ነው ። በሕገ መንግሥቱ ፤አሁን ባለው የሥርዓት አወቃቀር ፣ በሀገር ውስጥ ሕጎች ፣ በዓለም አቀፍ/ ኢንተርናሽናል ሕግ እና በግጭት አፈታት መርሆች ዙሪያ የአረዳድ ክፍተት ነበር ።
አብዛኛው ጊዜ ይሄንን በመማማር ላይ ነው ያለፈው። ወደ ዋናው ነጥብ/ ፖይንት/ ሲመጣ ግን በሕገ መንግሥት ጥላ ሥር ሆኖ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ አንድነት መቀበል ላይ፣ የኢትዮጵያን ሀገረ መንግሥት በምርጫ የመጣ ሕጋዊነት / ሌጅትመሲ ያለው መንግሥት መሆኑ ላይ መግባባት ላይ ተደርሷል። ከዛ በኋላ የመጣው እነዚህን መግባባቶች የሚሸረሽር ነገር ነው የመጣው።
እነዚህን መግባባቶች ከመሸርሸር አንፃር አንዱ ሥልጣን አካፍለኝ የሚል ነው። መንግሥት ሥልጣን ሊያካፍል ቢልም ማካፈል አይችልም። ሥልጣንን የማካፈል መብት የለውም ። ማድረግ የሚችለው ማሳተፍ ነው። ማሳተፍ ይችላል ማካፈል ግን አይችልም። ለምን መጀመሪያውኑ ወደ ምርጫ ሄደ? በጉልበት ራሱ የያዘው ሥልጣን ቢሆን ብትጠይቅ ያስኬዳል። በምርጫ ወደ ሥልጣን የመጣ መንግሥት ሥልጣን ማካፈል አይችልም። ሌሎችን ግን ማሳተፍ ይችላል፣ ሸኔንም ማሳተፍ ይችላል።
ከተፈጠረው መሠረታዊ ልዩነት አንዱ ይሄ ነው ። ሥልጣን አካፍለኝ ፤ ሥልጣን አካፍለኝ ሲባል ደግሞ ራስህ ፕሮፖዛል አስቀምጠህ ማለት ነው። ፕሮፖዛል አስቀምጠህ እዚህ ፕሮፖዛል ላይ ሥልጣን ስጡኝ የሚል ነገር ትክክል አይደለም። ሕገ መንግሥታዊ አይደለም። የኢትዮጵያ መንግሥትም አይችልም። ይሄ ሕገ መንግሥት ማፍረስ ነው ሲባል ቆይቷል። በደንብ እነሱም እስኪረዳቸው ድረስ እንዲቆይ ተደርጓል።
ሁለተኛው ወደ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ለመመለስ በሠላም ለመታገል ፓርቲ አቋቁሞ ለመታገል ወደ ሕዝብ ምርጫ ለመቅረብ የገጠር ትጥቅ ትግል ትቶ በሠላማዊ መንገድ ወደ ሕዝብ መመለስ ነው። ይሄ ልትደራደር ከሆነ ተግባራዊ ማድረግ አለብህ። ይሄን ተቀብለህ ነው ከዛ በኋላ ጥያቄ የምታነሳው። ይሄን ካልተቀበልክ ሊሆን አይችልም።
በእንግሊዝኛ “ዲስ አርም ” ይባላል ትጥቅ መፍታት። ትጥቅ መፍታት ፤ ታጣቂዎችን በተለያዩ አማራጮች ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀል “ዲሞብላይዝድ” ማድግ አለብህ። “ኢንተግሬት ” መሆን አለብህ። ይሄ ዓለም የሚሠራበት ነው። የዓለም ልምድ/ ኤክስፒሪያንስ ነው። ማንኛውም ግጭት የተፈታው በዚህ መንገድ ነው። ይሄንን ለመቀበል የመቸገር ነገር ተከስቷል።
እና ትጥቅ ሳይፈታ እንዴት ትደራደራለህ? ትጥቅ ሳትፈታ እንዴት “ዲሞቢላይዝ ” ትሆናለህ? ትጥቅ ሳትፈታ እንዴት ወደ ኅብረተሰቡ ትቀላቀላለህ? መንግሥት እዚህ ላይ በግልጽ አስቀምጧል። ዲዲአር ፕሮግራም ውስጥ መግባት አለብህ። ከዛ ትጥቅ መውረድ አለበት። ምክንያቱም በአንድ ሀገር ሁለት የታጠቀ ኃይለሥላሤ። ስለማይኖር። በቃ ትጥቅ የመያዝ ሥልጣን ያለው መንግሥት ብቻ ነው። እና ሌላው የመያዝ መብት የለውም ።
እንደ ግል ዜጋ ጠብመንጃ ሊታጠቅ ይችላል። ተደራጅቶ ግን ሠራዊት ፈጥሮ ከመንግሥት ሠራዊት ጎን ለጎን ትከሻ እያሳየ የሚሄድ ኃይል መኖር የለበትም። ይሄ መቀበል ነበረባቸው። ይህ አይነት ነገር በዓለም የለም ፤ በቃ እንደዚህ አይነት ግጭት ይፈታ ሲባል ስምምነት ከተደረሰ ወደ ዲዲአር ነው የሚገባው። ሌላው ዲሞቢላይዜሽን ነው። ዲሞቢላይዜሽን ደግሞ ትጥቅ የፈታው ኃይል ዲሞቢላይዝ መደረግ አለበት። ወደ ሕዝቡ መቀላቀል አለበት።
ወደ ሕዝቡ ከተቀላቀለ በኋላ ደግሞ ከሕዝቡ ጋር መዋሃድ አለበት ከሕዝቡ ጋር ሲዋሃድ ጫካ የቆየ ኃይል እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ መፈናቀል እና ከህብረተሰቡ አስተሳሰብ የመነቀል እና ኢኮኖሚካሊ የመጎዳት ችግር ይኖራል። ይሄን መንግሥት ይሸከመዋል። እንደየሙያው እንደየ ችሎታው መንግሥት ኢንተግሬት የማድረግ ነገር ይሠራል ማለት ነው። ይሄን ካልተቀበልክ ድርድር ብሎ ነገር የለም። ይሄንን ያለ መቀበል ችግር አለ። በዚህ ምክንያት ጥሩ ሄዶ ሄዶ በመጨረሻው / ፋይናል ፖይንቱ በነዚህ ሁለት ምክንያቶች ቆመ።
ሶስተኛ እድል ይኖራል ወይ ለሚለው የሚኖር ይመስለኛል። ትንሽ ትምህርት መማማርም ፤ ትግልም ስለ ተደረገ የሚኖር ይመስለኛል። እነዚህ ሁለቱ ፖይንቶች ደግሞ በተሳሳተ መንገድ እንዲወስዱ በማድረግ ሌሎች ኃይሎች እጅ አላቸው። አሁን እነሱ በሚጠሩት ስማቸው ልጥራቸውና ኦላ ጋ ጫካ ላይ የተሰበሰበው ኃይል የሚቆስለው የሚሞተው ሌላውንም የሚገለው አካባቢውን ከልማት ውጪ የሚያደርገው ትምህርት እንዳይኖር የሚያደርገው መሠረተ ልማት እንዳይሠራ የሚያደርገው ይሄ ኃይል ነው።
ሀገሩንም እየጎዳ ያለ እራሱም እየተጎዳ ያለ ይሄ ኃይል ነው። ይሄ ኃይል ነው ወሳኝ መሆን የነበረበት። ግን ይሄ ኃይል አይደለም እየወሰነ ያለው፣ እዚ ኃይል ላይ ታዝሎ የሚሄዱ ኃይሎች አሉ። በዚህ ኃይል ታዝሎ በዚህ ኃይል ተሸካሚነት የሚሄዱ ኃይሎች አሉ። ሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪም ባዕዳንም ዜጎችም እነዚህ ኃይሎች ነገሮችን በሰከነ መንገድ አይቶ ይሄንን ስምምነት እንዳይቀበል አድርገውታል። ፍርፋሪ ይወረውሩለት ይሆናል፣ እንደሱ ግን አይሞቱለትም ሊሞቱለት አይችሉም ሌላ መስማት አልነበረባቸውም። በቃ ችግር ውስጥ ያሉት እነሱ ናቸው እራሳቸው መወሰን ነበረባቸው።
ሌላው ኃይል ጣልቃ ስለገባ በዓለም ኤክስፒሪያንስ ታይቶ የማይታወቅ ቅድመ ሁኔታ በማቅረብ መንግሽትን አስቸግረዋል። ይሄ ነው ያለው ሶስተኛ ዕድል ይኖራል ወይ ለሚለው ሊኖር ይችላል፤ ምናልባት ሰከን ብለው አስበው “ፋይናል ፔፐር” እኮ ተዘጋጅቷል “ኢቭን ” እነዚህ አደራዳሪዎችም የሚያምኑበት ፤ወደዛ ደረጃ እሱን ወደ መቀበል ደረጃ ከተደረሰ ሶስተኛ ውይይትም ሊኖር ይችላል፣ ምናልባት ሶስተኛ ውይይት እንደ ሁለተኛ ውይይት ሰፊ ላይሆን ይችላል።
እስከ አሁን የተደከመበት ውይይትና ሰነድ አለ፣ እሱን መቀበል ላይ ከተደረሰ ሶስተኛ ውይይት ሊኖር ይችላል፣ ሶስተኛ ውይይት የመጨረሻ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ። የመጨረሻ ይሆናል ወደ ሰላም ለመምጣት ወይም እስከ መጨረሻው ሁለተኛም ላለመነጋገር የመጨረሻ ሊሆን ይችላል።
ጥያቄ፡- በአማራ ክልል ያለ የጽንፈኛ ኃይል የአማራ ሕዝብን ጥያቄ በትጥቅ እመልሳለሁ በማለት በተናጠል በነበሩ የመከላከያ ሠራዊቱ የሻለቃ ኃይሎች ላይ ጥቃት መፈጸሙ ይታወቃል። በክልሉ ያለውን ሁኔታ ደግሞ ሰላም ለማስፈን ሲባል በመንግሥት ደረጃ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ መዋቅሩን ወደ ቦታው የመመለስ፣ ሰላምንም የማስፈን ሥራ እየተሠራ ነው። ይሄ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፡- ከትጥቅ ትግል አንጻር የአማራ ክልልም ኦሮሚያ ክልል ላይ ያነሳሁትን ነገር ነው የማመጣው። የአማራ ክልል ሰዎችም ወደ ትጥቅ ትግል የሚያስገባ ጥያቄ ምንድን ነው?። አማራ ራሱን በራሱ አያስተዳድርም?። ራሱን በራሱ ያስተዳድራል። ፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ይገባል ? አይገባም። ከማህበረሰቡ የተገኙ የራሱ መሪዎች አሉት፤ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር ክልል ነው። ለክልል በተሰጠው ሥልጣንና በክልል ሕገ መንግሥት መሠረት ራሱን የሚመራ ክልል ነው። ስለዚህ የራስን እድል በራስ ከመወሰን አንጻር በአማራ ክልልም የሚነሳ ነገር አለ ብዬ አላምንም።
ሁለተኛው፣ ቅድም እንዳልኩት የመሬት ጥያቄም የለም፤ አማራ ክልል። የመሬት ጥያቄ የለም፤ የብሄር ጭቆና የለም፤ ወደ ትጥቅ ትግል ሊያስገቡ የሚገቡ ደግሞ እነዚህ ናቸው። ለዛውም እነዚህን የሚመለስ መንግሥት ከሌለ ማለት ነው። ልክ እንደ ቀደምቶቹ መንግሥታት፤ እንደ ንጉሡ ዘመን፣ ወይም እንደ ደርግ ዘመን። የአማራ አካባቢ ወደ ትጥቅ ትግል የሚያስገባ ቤዚክ (መሠረታዊ) የሆነ፣ የማይታረቅ፣ በውይይት የማይፈታ፣ ጥያቄ አለ ብዬ አላምንም። ስለዚህ ይሄ በሌለበት ወደ ትጥቅ ትግል የገባው ኃይል ከፍተኛ ስህተት ፈጽሟል ብዬ አስባለሁ።
አንዳንድ ጊዜ እንደ ጥያቄ የሚነሱ ነገሮች ደግሞ እሰማለሁ። ለምሳሌ፣ ሕገ መንግሥት ይሻሻል የሚል። ሕገ መንግሥት ይሻሻል የሚል ጥያቄ ጥሩ ጥያቄ ነው። ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ብለህ ግን ጠመንጃ አንስተህ ጫካ ሆነህ መንግሥት አትሆንም። ሕገ መንግሥት ደግሞ የአንድ ክልል ሕገ መንግሥት አይደለም። የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በሙሉ ተነጋግረውና ተስማምተው፤ ሕገ መንግሥቱ ይሄ ጉድለት አለው መሻሻል አለበት ብለው ማሻሻል የሚችሉት ነው። ክልሎች እና ሕዝቦች ጥያቄውን አንስተው ማሻሻል ይችላሉ።
አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት አይሻሻልም አላለም። ሕገ መንግሥት መሻሻል አለበት ብሎ ያምናል። ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ደግሞ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን አቋቁሟል። እዛ ላይ ውይይት ይደረግና፤ እዛ ላይ ያለው የሕዝቡም ፍላጎት ይታወቅና ሕገ መንግሥት ለማሻሻል የሚያስገድድ ነገር ካለ ሕገ መንግሥት ወደ ማሻሻል እንገባለን ብሎ እየሠራ ነው።
አንደኛ፣ አሁን ያለው ሕገ መንግሥት ሀገራዊ ነው እንጂ የአንድ ክልል አይደለም። አንድ ክልል ብድግ ብሎ ሕገ መንግሥት አሻሽሉ ብሎ ጠመንጃ ማንሳት አይችልም። ሕገ መንግሥት መሻሻል አለበት ይላል፤ ሃሳብ ያቀርባል፤ ሌሎቹንም ይቀሰቅሳል፤ ያሳትፋል፤ ሀገራዊ ያደርጋል፤ ሕገ መንግሥት ያሻሽላል። ይሄ መሆን ነበረበት እንጂ፣ ሕገ መንግሥት ካልተሻሻለ ብለህ ወደ ጫካ አትገባም። ምክንያቱም፣ ይሄ የለውጥ መንግሥት ሕገ መንግሥት አላሻሻለም የሚል አይነት ጥያቄ እንደ ቅስቀሳ ፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ስለሚቀርብ ማለት ነው። ሕገ መንግሥት ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ደብዳቤ አይቀየርም። ወይም በአንድ ርዕሰ ብሔር ወይም በሆነ ቡድን ወይም በሆነ ፓርቲ አይቀየርም። ብልጽግናም ሕገ መንግሥት ሊቀይር አይችልም።
ብልጽግና ጥያቄ ካለ ተቀብሎ ሌሎች ፓርቲዎችም፤ ሌሎች ሕዝቦችም በተሳተፉበት ሰፋ ያለ ሁኔታ ፈጥሮ ነው የሚቀይረው። አንዳንድ ምሁራን ተብዬ ሰዎች እንደሚናገሩት በጠቅላይ ሚኒስትር ደብዳቤ ሕገ መንግሥት አይቀየርም። ሕገ መንግሥት የሕጎች ሁሉ የበላይ ነው። መከላከያ ሠራዊት ሕገ መንግሥት እንዲያስከብር ተልእኮ የተሰጠው በዚህ ሕገ መንግሥት ነው። ይሄ ሕገ መንግሥት ችግርም ቢኖረው ሁላችንም አንድ ላይ ሆነን እንድንኖር ያግዛል፤ ይመራል።
ሕግ የሌለው ሀገር ይፈርሳል። ሕግ የሌለው ሀገር በርካታ ሕገወጥ የሆኑ ኃይሎችን ይፈጥራል። ችግር ሊኖረው ይችላል። ችግር ካለው ችግሩን ነቅሶ አውጥቶ መቀየር ይቻላል። ለመቀየር ሁሉንም ማሳመን ፤ማስተባበር ይቻላል፤ መወያየት ይቻላል፤ ዝግ የተደረገ ነገር የለም። ሕገ መንግሥት ለመቀየር ተብሎ ወደ ጫካ ተገብቶ ከሆነ በጣም ስህተት ነው የተሠራው። አንዱ ይሄንን ነው የምሰማው።
ሁለተኛ የምሰማው የወሰን ጥያቄ ነው። የወሰን ጥያቄ የአማራ ክልል ብቻ ጥያቄ አይደለም። ትግራይ ክልል የወሰን ጥያቄ አለው። ኦሮሚያም አለው። አፋር አለው፤ ሱማሌ አለው። ስለዚህ የወሰን ጥያቄ ማለት የሆነ ባዕድ ከውጭ ሀገር መጥቶ መሬት የያዘበት ክልል የለም። የውጭ ወራሪ መጥቶ መሬቱን ይዞበት መሬቴ ተይዞብኛል የሚያሰኝ ነገር አይደለም።
የወሰን ጥያቄ በአንድ ሀገር ውስጥ ያለ ለማስተዳደር እንዲመች የተካለለ ነገር ነው። እና ይሄ በየትኛውም ዓለም በውይይት ነው የሚፈታው። ምክንያቱም የአንድ ሀገር ሕዝቦች አብረው የሚኖሩ ሰዎች ኩታ ገጠም የሆኑ ሕዝቦች፤ ወሰን ያላቸው ሕዝቦች ስለሆኑ ማለት ነው። ስለዚህ ይሄም ለትጥቅ ትግል ምክንያት ሊሆን አይችልም። ለፖለቲካ ትግል፤ ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ለትጥቅ ትግል ምክንያት ሊሆን አይችልም። በዚህ ከሆነ እየተገዳደልን ያለነው በከፍተኛ ደረጃ ሀገራችንን እያፈረስን ነው ያለነው የሚል አመለካከት ነው ያለኝ ።
ወሰንም ደግሞ በሆነ በባለሥልጣን ደብዳቤ አይካለልም። ‹‹ይሄ የእከሌ ነው፤ አንተ ውሰድ ፤ ያ የእከሌ ነው አንተ ውሰድ›› ብሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ወይም ካቢኔ ሊወስነው አይችልም። በፍጹም እንደዛ የሚወሰን አይደለም። የሚወሰነው በሕዝቦች ተሳትፎ እዛ ቦታ ላይ ባሉ ሕዝቦች ውሳኔ ነው። መንግሥት የሚያደርገው እዛ ያለውን ሕዝብ ምን ይፈልጋል፣ ምን ይወስናል የሚለውን ሥርዓት ማስተካከል ነው። በትጥቅ ትግል ወሰን ማስመለስ የሚባል ነገር ከሆነ መላው ኢትዮጵያ እሳት በእሳት ሆኖ ይቀጣጠላል።
መነገር ያለበት እየተስተዋለ ነው። አንዱ የምሰማው እና እዛ አካባቢ ያለውን የትጥቅ ትግል የሚደግፉት ሰዎች የሚያነሱት አንደኛው የሕገ መንግሥት ይቀየር ጥያቄ ነው። ሁለተኛ ነጥብ የወሰን ጥያቄ ነው። ሶስተኛ የምሰማው እየተገደልን ነው፣ እየተፈናቀልን ነው የሚል ነው። ላለመገደል መጀመሪያ አለመግደል ነው። ገድለህ መጮህ ትክክል አይደለም። ማነው መጀመሪያ ግድያ የጀመረው? በደንብ መታየት አለበት። ከገደልክ በኋላ ስትገደል መቀበል ነው።
መፈናቀልን በተመለከተ ብዙ ቦታ ነው ያለው። የአማራ ተፈናቃይ ብቻ አይደለም። የኦሮሞ ተፈናቃይ አለ፤ የጌዴኦ ተፈናቃይ አለ። መፈናቀልን ያስከተሉ ምክንያቶች ብዙ ናቸው። ይሄ የሚፈታው በንግግር ነው። የተፈናቀለው ወደ ቦታው በመመለስ፣ በመነጋገር ነው የሚፈታው። ተፈናቀልኩ ብለህ የትጥቅ ትግል አይደረግም። በነገራችን ላይ የትጥቅ ትግል ማለት ወደ ጦር መሣሪያ ያደገ የፖለቲካ ትግል የመጨረሻ ጫፍ ማለት ነው። የመጨረሻ ምንም ተስፋ፣ ፋይዳ የለውም፤ በመነጋገር ሊፈታ አይችልም፤ በሰላማዊ ሰልፍ ሊፈታ አይችልም፤ የማይሰማ አምባገነን መንግሥት ነው ያለው የሚል ነገር ላይ ከተደረሰ በኋላ ነው።
የተፈናቀለ እንመልስ የሚሉ ክልሎች ባሉበት፣ መንግሥት ተፈናቃዮች ይመለሱ በሚልበት ሁኔታ እከሌ ተፈናቀለ ተብሎ የሚደረግ የትጥቅ ትግል ፖለቲካል አይደለም። ጥሩ ወታደራዊ ጠበብቶችም ቢሆኑ የሚያዋጣ የትግል አካሄድ እንዳልሆነ ይናገራሉ ። ስለዚህ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ አይደለም። ሕገመንግሥት ይሻሻል የሚለው አማራ ብቻ መሆን የለበትም። ሌላውም እያለ ነው። ምክንያቱም ሌላውም ከራሱ አቅጣጫ የሚፈልገው ነገር አለ።
አማራውም ከራሱ አቅጣጫ የሚፈልገው ነገር አለ። ስለዚህ የሚሻሻለው በስምምነት ነው። በትጥቅ ትግል ልታሻሽለው አትችልም። ሀገርህን ታበሳብሳት ይሆናል፤ ሕዝብህን ታዳክመው ይሆናል፤ ኢትዮጵያን ወደኋላ እንድትቀር ታደርግ ይሆናል እንጂ ነፍጥ አንስተህ የሚሻሻል ነገር አይደለም። ማንም አያሻሽልማ፤ የሚሻሻለው በኢትዮጵያ ሕዝቦች መግባባት ነው።
ወሰንም እዛ ወሰን ላይ በሚኖሩ ሕዝቦች ፍላጎት እና ውሳኔ መሠረት ነው የሚፈታው እንጂ የተቋቋመ ፤ ውሳኔ እየሰጠ ወሰን የሚያካልል ካቢኔ የለም። አይችልም። ቢያደርገውም እሳት ነው የሚለኩሰው። ስለዚህ ይሄ መታየት አለበት። የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሁሉ ጥያቄ አላቸው። ጥያቄውን አንድ ላይ ሰብስበው ተወያይተው፤ መንግሥት ደግሞ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ ነው መፈታት ያለበት። ወደ ማይታረቅ የህልውና ጥያቄ እና የጦር መሣሪያ ፍትጊያ የሚያስገባ ነገር አይደለም ያለው። የአማራ ክልልንም እንደዛ ነው የማየው።
አሁን ወደ ግጭት የገቡ ሰዎች ወንጀል ነው የሠሩት። የሠሩት ወንጀል ምንድነው፤ ልክ እንደትግራይ ሰሜን እዝን እንደመታው ብዙ ሠራዊት አልነበረም እንጂ የመከላከያ ሠራዊት ሬንጅመንቶችን ከበው ነው የመቱት። ከትግራይም ትምህርት አልወሰዱም፤ እንዴት ሰው መጥፎ ተሞክሮ ይወስዳል። የሰው ልጅ አዕምሮ የተፈጠረለት ለማሰብ ነው። ሲያስብ ደግሞ ልምድ ከሌሎች ይቀስማል፤ ልምድ ሲቀስም ደግሞ ጥሩ ልምድ ነው እንጂ የሚቀስመው መጥፎ ልምድ እንዴት ይቀስማል። ሰሜን እዝ ተመታ ተብሎ ሀገር ምድሩ ነቅሎ የወጣው መከላከያ ስለተመታ ነው። መከላከያ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የመጨረሻ ምሽግ ስለሆነ ነው። መከላከያን የሚመታ ኃይል የኢትዮጵያን ሕዝቦች የናቀ ነው። ሕግና ሥርዓት የማያውቅ፤ ሠራዊቱ ለምን እንደተደራጀ የማያውቅ ብቻ ነው።
መከላከለያ ሠራዊት በራሱ ዜጎች አይመታም። ለመጀመሪያ ጊዜ ያየነው ሰሜን እዝ ላይ የተደረገውን ነው። በጣም ከባድ ስህተት ነው እዛ የተሠራው፤ እሱ ዋጋ አስከፍሎናል። መንግሥት ከመከላከል ውጪ አማራጭ አልነበረውም። ተመሳሳይ ነገር አምጥተህ እዚህ ተግባራዊ ታደርጋለህ? ሬንጅመንቶች ነበሩ በጎጃም፣ በጎንደር፣ በወሎ፤ ተመሳሳይ በሰሜን እዝ ላይ የተደረገ ነገር ለማድረግ ነው የተሞከረው። በጣም አሳዛኝ ነገር ነው የተሠራው። ደግነቱ ሬጅመንቶቹ ጥቂት ስለሆኑ እዝ ስላልሆነ እንደሰሜን እዝ ስላልሆነ ጉዳት አለው ግን ጉዳቱ ይሄን ያህል መከላከያን የሚጎዳ አልነበረም እንጂ ተመሳሳይ ሥራ ነው የተሠራው።
በጣም ወንጀል ነው የተሠራው፤ ትክክል አይደለም። እንደገና ደግሞ ልምድ አለ፤ የትግራይ ልምድ አለ። የትግራይ ልምድ ለውድቀት ነው አይደል የዳረገን? ኢትዮጵያም ተጎድታለች ፤መንግሥትም ተጎድቷል። ይበልጥ ደግሞ ትግራይ ተጎድቷል። የትግራይ ውድቀትም የኛ ውድቀት ነው። በአጠቃላይ እንደሀገር ነው የተጎዳነው። ይሄንን እያወክ እሱኑ ልምድ አምጥተህ ተግባራዊ ማድረግ አልነበረባቸውም።
ፋኖ የሚባል ነገር ተነስቷል። ፋኖ ጋር እኛ ፀብ የለምን ብያለው ከዚህ በፊት በሰጠሁት መግለጫ። ፋኖ ማለትኮ ሀገሩን የሚከላከል አርበኛ ማለት ነው። መከላከያ ሠራዊት የሚመታ ፋኖ እኔ አይቼ አላውቅም። ሰምቼም አላውቅም፤ በታሪክም አልተፃፈም። ምን ማለት ነው ፤ለዓድዋ ጦርነት የተመመ ሠራዊትን የሚመታ ኃይል ማለት አሁን የተፈጠረው። ይሄ ፋኖ አይደለም። የሆነ ኃይል ነው እዚያ የተፈጠረው ፤ ቅድም እንዳልኩት ገድለህ ተገደልኩ አትበል ያልኩት ለዚህ ነው። ከዚያ በፊት በነበሩ ግጭቶችም ተገደልኩ የሚል የመጣው እራሱ እየገደለ አማራን ለማነሳሳት ሲል ነው ተገደልኩ እያለ ያለው። መጀመሪያም እንደዚያው ነበር ፤ ይባስ ብሎ ወደ መከላከያ ሠራዊት መጣ።
ስለዚህ ከተገደልህ መቀበል ነው ፤ እንጂ ተገደልኩ ብለህ መንጫጫት የለብህም፤ ወደህ የገባህበት ነው፤ ጠመንጃ እጅህ ላይ ሲገባ ሀገር የገዛህ መስሎህ የገባህበት ነው፤ ስለዚህ ቻለው መባል አለበት። ይህ የአማራ ጥያቄን የሚመልስ ኃይል አይደለም፤ ይሄ ቅጥረኛ ኃይል ነው፤ እነዚህ አካላት በፈጠሩት ቀውስ የአማራ ሕዝብ አሁን ጉዳት ላይ ነው፤ በጣም ተጎድቷል። የአማራን ሕዝብ ወደ ጉዳት አስገባው እንጂ ያመጣው ነገር የለም። ወደፊትም አያመጣም።
ሸኔ የወለጋንና የጉጂን ሕዝብ ፤ ከትምህርት ውጪ አደረገው እንጂ ያመጣው ነገር የለም። ወለጋ ከለውጥ በፊት ፤ ሌላው ቀርቶ በኢህአዴግ ጊዜ፣ በደርግ ጊዜም ይሁን በንጉሡ ጊዜ ከኢትዮጵያ ቀጣናዎች ወይም በድሮው አሰያየም ክፍለ ሀገሮች በትምህርት ሽፋን ፣ በምሁራን ብዛት አንደኛ ነበር። በርካታ የኢትዮጵያ ቢሮክራሲ ከዚያ ነው የሚመጣው፤ ያኔ ከሁሉም ጠቅላይ ግዛቶች መጨረሻ የትምህርት ሽፋን የነበረው ቦረና ነው። አሁን መጨረሻ ያለው ወለጋ ነው። ማነው ይህን ያደረገው ከተባለ ሸኔ ነው።
አሁን አማራ ክልል ጽንፈኞች የጀመሩት ነገር አማራ ክልል ላይ የሚያመጣው ይህንኑ ነው፤ ትምህርት ቤት መዘጋት ተጀምሯል። ተማሪዎች እየሄዱ አይደለም። ይህ ድርጊት የአማራን ሕዝብ በብዙ ዓመታት ወደኋላ የሚያስቀር ነው የሚሆነው። የአማራን ሕዝብ መንገድ ዘግተህበት፣ እርስ በእርሱ እንዳይገናኝ አድርገህ፣ ወላድ ወደ ሆስፒታል እንዳትሄድ አድርገህ፣ ነግዶ የሚኖር ሰው ሸቀጥ እንዳያመላለስ አድርገህ፣ በስንት መከራ ጥሮ ግሮ ያፈራውን መሠረተ ልማት አውድመህ፣ ፋብሪካ ላይ ጥቃት አድርሰህ፣ ለአማራ ሕዝብ ታገልኩ ትላለህ። ከባድ ወንጀል ነው። እውነት ለመናገር ይህን ተግባር የሚያደፋፍር ኤሊት የኢትዮጵያ ጠላቶች ናቸው ፤ ኢትዮጵያን አይወዷትም፤ የአማራ ሕዝብንም አይወድም። አማራ ክልል እየሆነ ያለው ይሄ ነው ።
ክፍል ሁለት በነገው እትማችን ይቀጥላል
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 4 ቀን 2016 ዓ.ም